ሆሴዕ 2:1-23

  • ከዳተኛዋ እስራኤል ተቀጣች (1-13)

  • ወደ ይሖዋ ይመለሳሉ (14-23)

    • “ባሌ ብለሽ ትጠሪኛለሽ” (16)

2  “ወንድሞቻችሁን ‘ሕዝቤ!’*+ እህቶቻችሁን ደግሞ ‘ምሕረት የተደረገልሽ ሴት!’* በሏቸው።+   እናታችሁን ክሰሷት፤ እሷ ሚስቴ ስላልሆነች፣+እኔም ባሏ ስላልሆንኩ ክሰሷት። ከእሷ ዘንድ ዘማዊነቷን፣*ከጡቶቿም መካከል ምንዝሯን ታስወግድ፤   አለዚያ ራቁቷን አስቀራታለሁ፤ በተወለደችበት ቀን እንደነበረችውም አደርጋታለሁ፤እንደ ምድረ በዳ፣ውኃ እንደሌለበትም ምድር አደርጋታለሁ፤በውኃ ጥምም እገድላታለሁ።   ወንዶች ልጆቿ የምንዝር* ልጆች ስለሆኑምሕረት አላደርግላቸውም።   እናታቸው አመንዝራለችና።*+ እነሱን የፀነሰችው ሴት አሳፋሪ ድርጊት ፈጽማለች፤+‘አጥብቀው የሚወዱኝን፣ደግሞም ምግቤንና ውኃዬን፣የሱፍ ልብሴንና በፍታዬን እንዲሁም ዘይቴንና መጠጤን የሚሰጡኝን ተከትዬ እሄዳለሁ’ ብላለችና።+   ስለዚህ መንገዷን በእሾህ አጥር እዘጋለሁ፤መውጫ መንገድ እንዳታገኝምዙሪያዋን በድንጋይ አጥራለሁ።   አጥብቀው የሚወዷትን ተከትላ ትሄዳለች፤ ሆኖም አትደርስባቸውም፤+ትፈልጋቸዋለች፤ ሆኖም አታገኛቸውም። ከዚያም ‘ተመልሼ ወደ መጀመሪያው ባሌ እሄዳለሁ፤+ከአሁኑ ኑሮዬ ይልቅ የበፊቱ ይሻለኛልና’ ትላለች።+   እህሉን፣ አዲሱን የወይን ጠጅና ዘይቱን የሰጠኋትእንዲሁም ለባአል አምልኮ የተጠቀሙበትን ብርና ወርቅ+በብዛት እንድታገኝ ያደረግኩት እኔ እንደሆንኩ አልተገነዘበችም።+   ‘ስለዚህ ሐሳቤን ቀይሬ፣ እህሌን በጊዜው፣አዲሱን የወይን ጠጄንም በወቅቱ እወስዳለሁ፤+እርቃኗን የምትሸፍንበትንም የሱፍ ልብሴንና በፍታዬን እነጥቃታለሁ። 10  አሁንም ኀፍረተ ሥጋዋን አጥብቀው በሚወዷት ፊት እገልጣለሁ፤ከእጄም የሚያስጥላት ሰው አይኖርም።+ 11  ደስታዋን፣ በዓሏን፣ የወር መባቻዋንና ሰንበቷን ሁሉእንዲሁም የተወሰኑትን የበዓል ወቅቶቿን ሁሉ አስቀራለሁ።+ 12  “አጥብቀው የሚወዱኝ ውሽሞቼ ለእኔ የሰጡኝ ደሞዜ ናቸው” የምትላቸውን የወይን ተክሏንና የበለስ ዛፏን አወድማለሁ፤ጫካም አደርጋቸዋለሁ፤የዱር አራዊትም ይበሏቸዋል። 13  ለባአል ምስሎች መሥዋዕት ባቀረበችባቸው፣+ በጉትቻዋና በጌጦቿ በተንቆጠቆጠችባቸውእንዲሁም አጥብቀው የሚወዷትን በተከተለችባቸው ቀናት የተነሳ ተጠያቂ አደርጋታለሁ፤እኔንም ረስታኝ ነበር’+ ይላል ይሖዋ። 14  ‘ስለዚህ አግባብቼ አሳምናታለሁ፤ወደ ምድረ በዳ እመራታለሁ፤ልቧን በሚማርክ መንገድ አናግራታለሁ። 15  ከዚያን ጊዜ አንስቶ የወይን እርሻዎቿን መልሼ እሰጣታለሁ፤+የአኮርም ሸለቆ*+ የተስፋ በር እንዲሆናት አደርጋለሁ፤በዚያም እንደ ልጅነቷ ጊዜናከግብፅ ምድር እንደወጣችበት ቀን መልስ ትሰጠኛለች።+ 16  በዚያም ቀን’ ይላል ይሖዋ፣‘ባሌ ብለሽ ትጠሪኛለሽ፤ ከእንግዲህ ጌታዬ* ብለሽ አትጠሪኝም።’ 17  ‘የባአልን ምስሎች ስሞች ከአንደበቷ አስወግዳለሁ፤+ስማቸውም ከእንግዲህ አይታወስም።+ 18  በዚያም ቀን ለእነሱ ጥቅም ስል ከዱር አራዊት፣+ከሰማይ ወፎችና መሬት ለመሬት ከሚሳቡ ፍጥረታት ጋር ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤+ቀስትን፣ ሰይፍንና ጦርነትን ከምድሪቱ አስወግዳለሁ፤+ያለስጋት እንዲያርፉም* አደርጋለሁ።+ 19  ለዘላለም አጭሻለሁ፤በጽድቅ፣ በፍትሕ፣ በታማኝ ፍቅርናበምሕረት አጭሻለሁ።+ 20  በታማኝነት አጭሻለሁ፤አንቺም በእርግጥ ይሖዋን ታውቂያለሽ።’+ 21  ‘በዚያም ቀን መልስ እሰጣለሁ’ ይላል ይሖዋ፤‘ለሰማያት መልስ እሰጣለሁ፤እነሱ ደግሞ ለምድር መልስ ይሰጣሉ፤+ 22  ምድር ደግሞ ለእህሉ፣ ለአዲሱ የወይን ጠጅና ለዘይቱ መልስ ትሰጣለች፤እነሱም ለኢይዝራኤል* መልስ ይሰጣሉ።+ 23  በምድር ላይ ለራሴ እንደ ዘር እዘራታለሁ፤+ደግሞም ምሕረት ላልተደረገላት* ለእሷ ምሕረት አደርግላታለሁ፤ሕዝቤ ያልሆኑትን* “እናንተ ሕዝቤ ናችሁ” እላቸዋለሁ፤+ እነሱ ደግሞ “አንተ አምላኬ ነህ” ይላሉ።’”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ሆሴዕ 1:9 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
ሆሴዕ 1:6 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
ወይም “ነውረኝነቷን፤ ሴሰኝነቷን።”
ወይም “የነውር፤ የሴሰኝነት።”
ወይም “ነውር ፈጽማለችና (ሴስናለችና)።”
ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
ወይም “የእኔ ባአል።”
ወይም “እንዲኖሩም።”
“አምላክ ዘር ይዘራል” የሚል ትርጉም አለው።
ሆሴዕ 1:6 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
ሆሴዕ 1:9 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።