በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ድርጅቱን የሚመራው እንዴት ነው?

ይሖዋ ድርጅቱን የሚመራው እንዴት ነው?

ምዕራፍ አሥራ አራት

ይሖዋ ድርጅቱን የሚመራው እንዴት ነው?

1. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ድርጅት ምን መረጃ ይሰጠናል? ይህስ ለእኛ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

አምላክ ድርጅት አለው? በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች እንዳለው ይገልጻሉ። ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት የዚህን ድርጅት አስደናቂ ሰማያዊ ክፍል በተመለከተ የተወሰነ ፍንጭ ሰጥቶናል። (ሕዝቅኤል 1:1, 4-14፤ ዳንኤል 7:9, 10, 13, 14) ይህ ሰማያዊ ክፍል በዓይናችን ልናየው ባንችልም እንኳ በዛሬው ጊዜ ላሉት እውነተኛ አምላኪዎች ትልቅ ትርጉም አለው። (2 ነገሥት 6:15-17) በተጨማሪም የይሖዋ ድርጅት በምድር ላይ የሚታይ ክፍል አለው። መጽሐፍ ቅዱስ የዚህን የሚታየውን የድርጅቱን ክፍል ምንነትና ይሖዋ እንዴት እንደሚመራው እንድንገነዘብ ይረዳናል።

የሚታየውን የድርጅቱን ክፍል ለይቶ ማወቅ

2. አምላክ ያቋቋመው አዲስ ጉባኤ የትኛው ነው?

2 የእስራኤል ሕዝብ ለ1,545 ዓመታት የአምላክ ጉባኤ ሆኖ ቆይቶ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 7:38) ሆኖም እስራኤላውያን የአምላክን ሕግጋት ሳይጠብቁ የቀሩ ከመሆናቸውም በላይ ልጁን ለመቀበል ፈቃደኞች አልሆኑም። በዚህም ሳቢያ ይሖዋ ይህን ጉባኤ እርግፍ አድርጎ ተወው። ኢየሱስ አይሁዳውያንን “እነሆ፤ ቤታችሁ ወና ሆኖ ይቀርላችኋል!” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 23:38) ከዚያ በኋላ አምላክ አዲስ ጉባኤ ያቋቋመ ሲሆን ከዚህ ጉባኤ ጋር አዲስ ቃል ኪዳን ገብቷል። ይህ ጉባኤ ከልጁ ጋር በሰማይ እንዲሆኑ በአምላክ የተመረጡ 144,000 ግለሰቦችን ያቀፈ ነው።—ራእይ 14:1-4

3. በ33 በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ይሖዋ በአዲስ ጉባኤ እንደሚጠቀም በግልጽ የሚያሳይ ምን ሁኔታ ተከናውኗል?

3 የዚህ ጉባኤ የመጀመሪያ አባላት በ33 በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ተቀብተዋል። ይህን አስደናቂ ክንውን በተመለከተ የሚከተለውን ዘገባ እናገኛለን:- “የበዓለ ኀምሳ ቀን በደረሰ ጊዜ ሁሉም በአንድነት፣ በአንድ ስፍራ ተሰብስበው ነበር፤ ድንገትም እንደ ብርቱ ዐውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ ከሰማይ መጥቶ ተቀምጠው የነበሩበትን ቤት እንዳለ ሞላው። የእሳት ምላሶች የሚመስሉም ታዩአቸው፤ ተከፋፍለውም በእያንዳንዳቸው ላይ ዐረፉ። ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ።” (የሐዋርያት ሥራ 2:1-4) በዚህ መንገድ የአምላክ መንፈስ አምላክ በሰማይ ባለው በኢየሱስ ክርስቶስ አመራር ዓላማውን ለመፈጸም የሚጠቀምበት የሰዎች ቡድን ይህ መሆኑን በግልጽ አመልክቷል።

4. የሚታየው የይሖዋ ድርጅት የተዋቀረው በእነማን ነው?

4 በአሁኑ ጊዜ ከ144,000ዎቹ መካከል በምድር ላይ ያሉት የተወሰኑ ቀሪዎች ብቻ ናቸው። ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ከቅቡዓን ቀሪዎች ጋር ተባብረዋል። መልካሙ እረኛ ኢየሱስ በአንድ እረኛ ሥር ያለ አንድ መንጋ ይሆኑ ዘንድ ሌሎች በጎችን ከቅቡዓን ቀሪዎች ጋር ቀላቅሏቸዋል። (ራእይ 7:9፤ ዮሐንስ 10:11, 16) እነዚህ አንድ ላይ ተጠቃልለው ኅብረት ያለው አንድ ጉባኤ ማለትም የሚታየው የይሖዋ ድርጅት ሆነዋል።

ቲኦክራሲያዊ መዋቅር ያለው

5. የአምላክን ድርጅት የሚመራው ማን ነው? እንዴትስ?

5 “የሕያው አምላክ ጉባኤ” የሚለው ቅዱስ ጽሑፋዊ አነጋገር ድርጅቱን የሚመራው ማን እንደሆነ ግልጽ ያደርግልናል። ድርጅቱ ቲኦክራሲያዊ ወይም በአምላክ የሚመራ ነው። ይሖዋ በዓይን የማይታይ የጉባኤው ራስ አድርጎ በሾመው በኢየሱስና በመንፈስ ባስጻፈው ቃሉ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ለሕዝቡ መመሪያ ይሰጣል።1 ጢሞቴዎስ 3:14, 15 NW፤ ኤፌሶን 1:22, 23፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

6. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው ጉባኤ ከሰማይ አመራር ያገኝ እንደነበረ የታየው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ አሁንም የጉባኤው ራስ እንደሆነ የሚያሳየው ምንድን ነው?

6 ይህ አመራር በጰንጠቆስጤ ዕለት በግልጽ ታይቷል። (የሐዋርያት ሥራ 2:14-18, 32, 33) የይሖዋ መልአክ ምሥራቹ ወደ አፍሪካ እንዲስፋፋ ባደረገበት ጊዜ እንዲሁም ከጠርሴሱ ሳውል ወደ ክርስትና መለወጥ ጋር በተያያዘ የኢየሱስ ድምፅ መመሪያ በሰጠበት ጊዜና ጴጥሮስ ለአሕዛብ መስበክ በጀመረበት ጊዜ የይሖዋ አመራር በማያሻማ ሁኔታ ታይቷል። (የሐዋርያት ሥራ 8:26, 27፤ 9:3-7፤ 10:9-16, 19-22) ከጊዜ በኋላ ግን ከሰማይ ድምፅ መሰማቱ፣ መላእክት ለሰዎች መታየታቸውና ተአምራዊ የመንፈስ ስጦታዎች መሰጠታቸው ቆመ። ሆኖም ኢየሱስ “እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” ሲል ቃል ገብቷል። (ማቴዎስ 28:20፤ 1 ቆሮንቶስ 13:8) በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የኢየሱስን አመራር ይቀበላሉ። ያለ እርሱ እርዳታ ይህ ሁሉ ተቃውሞ እያለ የመንግሥቱን መልእክት መስበክ አይቻልም ነበር።

7. (ሀ) “ታማኝና ልባም ባሪያ” ማን ነው? እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ይህ “ባሪያ” ምን ተልእኮ ተሰጥቶታል?

7 ኢየሱስ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ፣ ጌታ እንደመሆኑ መጠን ልዩ ኃላፊነት ስለሚሰጠው “ታማኝና ልባም ባሪያ” ለደቀ መዛሙርቱ ተናግሯል። ይህ “ባሪያ” ጌታው ወደ ሰማይ ከሄደበት ጊዜ አንስቶ ክርስቶስ በማይታይ ሁኔታ መንግሥታዊ ሥልጣኑን በሚይዝበት ጊዜ ሁሉ በትጋት እንደሚያገለግል ተገልጿል። ይህ መግለጫ አንድን ግለሰብ ሊያመለክት እንደማይችል የታወቀ ነው፤ ከዚህ ይልቅ የክርስቶስን የቅቡዓን ጉባኤ በትክክል ያመለክታል። ኢየሱስ በገዛ ራሱ ደም ስለዋጃቸው “ባሪያ” ብሎ ጠርቷቸዋል። ኢየሱስ የባሪያው ክፍል አባላት፣ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉና መንፈሳዊ “ምግባቸውን በጊዜው” በማቅረብ ያለማቋረጥ እንዲመግቧቸው አዟል።—ማቴዎስ 24:45-47 የ1954 ትርጉም፤ 28:19፤ ኢሳይያስ 43:10፤ ሉቃስ 12:42፤ 1 ጴጥሮስ 4:10

8. (ሀ) የባሪያው ክፍል በአሁኑ ጊዜ ምን ኃላፊነቶች አሉት? (ለ) አምላክ በዚህ መገናኛ መስመር በኩል ለሚያስተላልፈው መመሪያ ምላሽ መስጠታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

8 የባሪያው ክፍል ጌታው በ1914 በማይታይ ሁኔታ በተመለሰበት ጊዜ የተሰጠውን ሥራ በታማኝነት ሲያከናውን ስለተገኘ በ1919 ተጨማሪ ኃላፊነቶች እንደተሰጡት የሚያሳዩ ማስረጃዎች አሉ። ከዚያ በኋላ ያሉት ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለ አምላክ መንግሥት ምሥክርነት የሚሰጥባቸውና ከታላቁ መከራ የመዳን አጋጣሚ ያላቸውን ይሖዋን የሚያመልኩ እጅግ ብዙ ሕዝብ የሚሰበሰቡባቸው ጊዜያት ናቸው። (ማቴዎስ 24:14, 21, 22፤ ራእይ 7:9, 10) እነዚህ ሰዎችም መንፈሳዊ ምግብ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን እነሱንም የሚመግበው የባሪያው ክፍል ነው። ይሖዋን ለማስደሰት ከፈለግን እርሱ በዚህ መገናኛ መስመር በኩል የሚሰጠንን መመሪያ መቀበልና ሙሉ በሙሉ መፈጸም ያስፈልገናል።

9, 10. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከመሠረተ ትምህርት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ለመመለስና ለምሥራቹ ስብከት ሥራ አመራር ለመስጠት የሚያስችል ምን ዝግጅት ነበር? (ለ) በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ሕዝቦች ሥራ ለማስተባበር የሚያገለግል ምን ዝግጅት አለ?

9 አልፎ አልፎ መሠረተ ትምህርትንና የአሠራር ሥርዓትን የሚመለከቱ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ ምን ይደረጋል? የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 15 ወደ ክርስትና እምነት ከተለወጡ አሕዛብ ጋር በተያያዘ የተነሳው ክርክር እንዴት መፍትሔ እንዳገኘ ይነግረናል። ጉዳዩን ማዕከላዊ የበላይ አካል ሆነው የሚያገለግሉት በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች እንዲያዩት ተደረገ። እነዚህ ሽማግሌዎች ፈጽሞ የማይሳሳቱ ሰዎች አልነበሩም፤ ቢሆንም አምላክ ተጠቅሞባቸዋል። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች በጉዳዩ ላይ የሚሰጡትን ሐሳብና የአምላክ መንፈስ ለአሕዛብ ምሥክርነት እንዲሰጥ በማድረግ ረገድ የተጫወተውን ሚና የሚያሳየውን ማስረጃ ከመረመሩ በኋላ ውሳኔ አስተላለፉ። አምላክ ይህን ዝግጅት ባርኮታል። (የሐዋርያት ሥራ 15:1-29፤ 16:4, 5) ይህ ማዕከላዊ አካል የመንግሥቱ ስብከት ሥራ እንዲስፋፋ የሚያግዙ ሰዎችንም እየሾመ ይልክ ነበር።

10 በዘመናችን ያለው የሚታየው የይሖዋ ድርጅት የበላይ አካል ከልዩ ልዩ አገሮች ከመጡ በመንፈስ የተቀቡ ወንድሞች የተውጣጣ ሲሆን መቀመጫውም በይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ነው። የበላይ አካሉ በኢየሱስ ክርስቶስ የራስነት ሥልጣን ሥር ሆኖ የይሖዋ ምሥክሮች በአሥር ሺዎች በሚቆጠሩ ጉባኤዎቻቸው የሚያከናውኑትን የስብከት ሥራ በማስተባበር ንጹሕ አምልኮን በመላው ምድር ያስፋፋል። በበላይ አካሉ ውስጥ ያሉት ወንድሞች የሐዋርያው ጳውሎስ ዓይነት አመለካከት አላቸው፤ ጳውሎስ “ጸንታችሁ የምትቆሙት በእምነት ስለ ሆነ፣ ደስ እንዲላችሁ ከእናንተ ጋር እንሠራለን እንጂ በእምነታችሁ ላይ ለመሠልጠን አይደለም” በማለት ለክርስቲያን ወንድሞቹ ጽፎ ነበር።—2 ቆሮንቶስ 1:24

11. (ሀ) ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች የሚሾሙት እንዴት ነው? (ለ) ከተሾሙት ወንድሞች ጋር መተባበር ያለብን ለምንድን ነው?

11 የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል ብቃት ያላቸውን የተወሰኑ ወንድሞች መርጦ ኃላፊነት የሚሰጥ ሲሆን እነዚህ ኃላፊነት የተሰጣቸው ወንድሞች ደግሞ ጉባኤዎችን የሚያገለግሉ ሽማግሌዎችንና የጉባኤ አገልጋዮችን ይሾማሉ። ለሹመት የሚታጩት ሊያሟሏቸው የሚገቡት ብቃቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹ ከመሆኑም በላይ እነዚህ ሰዎች ፍጹማን እንዳልሆኑና ስህተት ሊሠሩ እንደሚችሉ ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። እነዚህ ወንድሞች እንዲሾሙ የድጋፍ ሐሳብ የሚያቀርቡት ሽማግሌዎችም ሆኑ ሹመቱን የሚያጸድቁት ወንድሞች በአምላክ ፊት ከባድ ኃላፊነት አለባቸው። (1 ጢሞቴዎስ 3:1-10, 12, 13፤ ቲቶ 1:5-9) በመሆኑም የአምላክ መንፈስ እንዲረዳቸው ይጸልያሉ፤ እንዲሁም በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፈው ቃሉ መመሪያ ለማግኘት ይጥራሉ። (የሐዋርያት ሥራ 6:2-4, 6፤ 14:23) ሁላችንም ወደ ‘እምነት አንድነት’ እንድንደርስ ለሚረዱን ለእነዚህ “ስጦታ” የሆኑ ወንዶች ያለንን አድናቆት እናሳይ።—ኤፌሶን 4:8, 11-16

12. ይሖዋ ሴቶችን በቲኦክራሲያዊው ዝግጅት ውስጥ የሚጠቀምባቸው እንዴት ነው?

12 ቅዱሳን ጽሑፎች በጉባኤ ውስጥ በበላይ ተመልካችነት ማገልገል ያለባቸው ወንዶች እንደሆኑ ይገልጻሉ። ይህ ሴቶችን ዝቅ የሚያደርግ አይደለም፤ ምክንያቱም አንዳንዶቹ የሰማያዊው መንግሥት ወራሾች ከመሆናቸውም በላይ አብዛኛውን የስብከት ሥራ የሚያከናውኑት ሴቶች ናቸው። (መዝሙር 68:11) በተጨማሪም ሴቶች የቤተሰብ ኃላፊነቶቻቸውን በሚገባ በመወጣት ለጉባኤው መልካም ስም አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። (ቲቶ 2:3-5) ሆኖም በጉባኤ ውስጥ የማስተማር ኃላፊነት የተሰጣቸው የተሾሙ ወንዶች ናቸው።—1 ጢሞቴዎስ 2:12, 13

13. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ሽማግሌዎች ኃላፊነታቸውን በተመለከተ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው እንደሚገባ ይመክራል? (ለ) ሁላችንም በየትኛው መብት መካፈል እንችላለን?

13 በዓለም ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ ያለ ሰው ከፍ ተደርጎ ይታያል። በአምላክ ድርጅት ውስጥ ያለው ሥርዓት ግን የሚከተለው ነው:- “ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ከሁሉ ይበልጣል።” (ሉቃስ 9:46-48፤ 22:24-26) ስለዚህ ሽማግሌዎች የአምላክ ውርሻ በሆኑት ላይ ከመሠልጠን ይልቅ ለመንጋው ምሳሌ እንዲሆኑ ቅዱሳን ጽሑፎች ይመክራሉ። (1 ጴጥሮስ 5:2, 3) የጽንፈ ዓለሙን የበላይ ገዥ በመወከል በትሕትና በይሖዋ ስም የመናገሩና በየትም ሥፍራ ለሚገኙ ሰዎች ስለ መንግሥቱ የመስበኩ መብት ግን ወንድ ሴት ሳይባል ለሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች የተሰጠ እንጂ ለጥቂት ምርጦች የተወሰነ አይደለም።

14. የተጠቀሱትን ጥቅሶች በመጠቀም በአንቀጹ መጨረሻ በቀረቡት ጥያቄዎች ላይ ሐሳብ ስጥ።

14 ‘ይሖዋ የሚታየውን ድርጅቱን እንዴት እየመራ እንዳለ በእርግጥ ተረድቻለሁ? ዝንባሌዬ፣ ንግግሬና አድራጐቴ ይህን ያንጸባርቃል?’ እያልን ራሳችንን ብንጠይቅ ጥሩ ነው። እያንዳንዳችን የሚከተሉትን ነጥቦች ብናሰላስልባቸው ራሳችንን በዚህ መንገድ መመርመር እንችላለን።

ክርስቶስ የጉባኤው ራስ መሆኑን አምኜ በመቀበል ከልብ የምገዛለት ከሆነ የሚከተሉት ጥቅሶች በሚያመለክቱት መሠረት ምን እያደረግኩ መሆን ይኖርብኛል? (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20፤ ዮሐንስ 13:34, 35)

በባሪያው ክፍልና በበላይ አካሉ በኩል የሚቀርቡልኝን መንፈሳዊ ስጦታዎች በአድናቆት ስቀበል ለማን አክብሮት እያሳየሁ ነው? (ሉቃስ 10:16)

በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሁሉ በተለይ ደግሞ ሽማግሌዎች አንዳቸው ለሌላው ምን ዓይነት ባሕርይ ሊያሳዩ ይገባል? (ሮሜ 12:10)

15. (ሀ) ለሚታየው የይሖዋ ድርጅት ያለን አመለካከት ምን ያሳያል? (ለ) ዲያብሎስ ውሸታም መሆኑን ለማጋለጥና የይሖዋን ልብ ለማስደሰት የሚያስችሉ ምን አጋጣሚዎች አሉን?

15 ይሖዋ ዛሬ የሚመራን በክርስቶስ ሥር ባለው በሚታየው ድርጅቱ አማካኝነት ነው። ስለዚህ ለዚህ ዝግጅት ያለን አመለካከት በአምላክ ሉዓላዊነት ላይ ለተነሳው ጥያቄ ምን ምላሽ እንደምንሰጥ በግልጽ ያሳያል። (ዕብራውያን 13:17) ሰይጣን በዋነኝነት የሚያሳስበን የግል ጥቅማችን እንደሆነ አድርጎ ይከራከራል። ሆኖም አስፈላጊ በሆነው በማንኛውም መንገድ ለማገልገል ራሳችንን የምናቀርብና የሰውን ትኩረት ወደ ራሳችን ከመሳብ የምንቆጠብ ከሆነ ዲያብሎስ ውሸታም መሆኑን እናጋልጣለን። ለግል ‘ጥቅማችን ስንል ሌሎችን ከመካብ’ በመቆጠብ የሚመሩንን ወንድሞች የምንወድና የምናከብር ከሆነ ይሖዋን እናስደስታለን። (ይሁዳ 16፤ ዕብራውያን 13:7) ለይሖዋ ድርጅት ታማኝ በመሆን አምላካችን ይሖዋ እንደሆነና በእርሱ አምልኮ አንድ እንደሆንን እናስመሠክራለን።—1 ቆሮንቶስ 15:58

የክለሳ ውይይት

• በዛሬው ጊዜ የሚታየው የይሖዋ ድርጅት የተገነባው በእነማን ነው? ዓላማውስ ምንድን ነው?

• የጉባኤ ራስ ሆኖ የተሾመው ማን ነው? ፍቅራዊ አመራር የሚሰጠንስ በየትኞቹ የሚታዩ ዝግጅቶች አማካኝነት ነው?

• በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ላሉት ምን ዓይነት ጤናማ አመለካከት ማዳበር ይኖርብናል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 133 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ይሖዋ በክርስቶስ ሥር ባለው በሚታየው ድርጅቱ አማካኝነት ይመራናል