መዝሙር 68:1-35

  • ‘የአምላክ ጠላቶች ይበታተኑ’

    • ‘አባት ለሌላቸው ልጆች አባት ነው’ (5)

    • አምላክ ብቸኛ ለሆነ ሰው ቤት ይሰጠዋል (6)

    • ምሥራቹን የሚያውጁ ሴቶች (11)

    • ሰዎችን እንደ ስጦታ አድርገህ ወሰድክ (18)

    • ‘ይሖዋ ሸክማችንን በየዕለቱ ይሸከማል’ (19)

ለሙዚቀኞች ቡድን መሪ። የዳዊት መዝሙር። ማህሌት። 68  አምላክ ይነሳ፤ ጠላቶቹ ይበታተኑ፤የሚጠሉትም ከፊቱ ይሽሹ።+   ጭስ በኖ እንደሚጠፋ ሁሉ እነሱንም አጥፋቸው፤ሰም በእሳት ፊት እንደሚቀልጥ፣ክፉዎችም ከአምላክ ፊት ይጥፉ።+   ጻድቃን ግን ደስ ይበላቸው፤+በአምላክ ፊት ሐሴት ያድርጉ፤በደስታም ይፈንጥዙ።   ለአምላክ ዘምሩ፤ ለስሙም የውዳሴ መዝሙር ዘምሩ።+ በበረሃማ ሜዳዎች* እየጋለበ ለሚያቋርጠው ለእሱ ዘምሩ። ስሙ ያህ* ነው!+ በፊቱ እጅግ ደስ ይበላችሁ!   በተቀደሰ መኖሪያው ያለው አምላክ+አባት ለሌላቸው ልጆች አባት፣ ለመበለቶች ደግሞ ጠባቂ* ነው።+   አምላክ ብቸኛ ለሆኑ ሰዎች መኖሪያ ቤት ይሰጣቸዋል፤+እስረኞችን ነፃ አውጥቶ ብልጽግና ያጎናጽፋቸዋል።+ ግትር የሆኑ ሰዎች* ግን ውኃ በተጠማ ምድር ይኖራሉ።+   አምላክ ሆይ፣ ሕዝብህን በመራህ ጊዜ፣*+በረሃውንም አቋርጠህ በተጓዝክ ጊዜ (ሴላ)   ምድር ተናወጠች፤+በአምላክ ፊት ሰማይ ዝናብ አወረደ፤*ይህ የሲና ተራራ በአምላክ ይኸውም በእስራኤል አምላክ ፊት ተናወጠ።+   አምላክ ሆይ፣ ብዙ ዝናብ እንዲዘንብ አደረግክ፤ለዛለው ሕዝብህ* ብርታት ሰጠኸው። 10  ድንኳኖችህ በተተከሉበት ሰፈር ሕዝብህ ተቀመጠ፤+አምላክ ሆይ፣ በጥሩነትህ ለድሃው የሚያስፈልገውን ሰጠኸው። 11  ይሖዋ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ምሥራቹን የሚያውጁ ሴቶች ታላቅ ሠራዊት ናቸው።+ 12  የብዙ ሠራዊት ነገሥታት እግሬ አውጭኝ ብለው ይሸሻሉ!+ በቤት የምትቀር ሴትም ምርኮ ትካፈላለች።+ 13  እናንተ በሰፈሩ ውስጥ በሚነድ እሳት* መካከል ብትተኙ እንኳ፣በብር የተለበጡ ክንፎችናበጠራ* ወርቅ የተለበጡ ላባዎች ያሏት ርግብ ትኖራለች። 14  ሁሉን ቻይ የሆነው ነገሥታቷን በበታተነ ጊዜ፣+በጻልሞን በረዶ ወረደ።* 15  በባሳን የሚገኘው ተራራ+ የአምላክ ተራራ ነው፤*በባሳን የሚገኘው ተራራ ባለ ብዙ ጫፍ ተራራ ነው። 16  እናንተ ባለ ብዙ ጫፍ ተራሮች ሆይ፣አምላክ መኖሪያው አድርጎ የመረጠውን ተራራ+ በምቀኝነት ዓይን የምታዩት ለምንድን ነው? አዎ፣ ይሖዋ በዚያ ለዘላለም ይኖራል።+ 17  የአምላክ የጦር ሠረገሎች እልፍ አእላፋት፣ ሺህ ጊዜ ሺህ ናቸው።+ ይሖዋ ከሲና ወደ ቅዱሱ ስፍራ መጥቷል።+ 18  ወደ ላይ ወጣህ፤+ምርኮኞችን ወሰድክ፤አምላካችን ያህ ሆይ፣ በመካከላቸው ትኖር ዘንድሰዎችን፣ አዎ እልኸኛ የሆኑትን ጭምር+ እንደ ስጦታ አድርገህ ወሰድክ።+ 19  ሸክማችንን በየዕለቱ የሚሸከምልን፣+የሚያድነን እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ይወደስ። (ሴላ) 20  እውነተኛው አምላክ፣ አዳኝ አምላካችን ነው፤+ደግሞም ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ከሞት ይታደጋል።+ 21  አዎ፣ አምላክ የጠላቶቹን ራስ፣ኃጢአት መሥራታቸውን የማይተዉ ሰዎችንም ፀጉራም አናት ይፈረካክሳል።+ 22  ይሖዋ እንዲህ ብሏል፦ “ከባሳን+ መልሼ አመጣቸዋለሁ፤ከጥልቅ ባሕር አውጥቼ አመጣቸዋለሁ፤ 23  ይህም እግርህ በደም እንዲታጠብ፣+ውሾችህም የጠላቶችህን ደም እንዲልሱ ነው።” 24  አምላክ ሆይ፣ እነሱ የድል ሰልፍህን ያያሉ፤ይህም አምላኬና ንጉሤ ወደ ቅዱሱ ስፍራ የሚያደርገው የድል ጉዞ ነው።+ 25  ዘማሪዎቹ ከፊት ሆነው ሲጓዙ በባለ አውታር መሣሪያዎች የሚጫወቱት ሙዚቀኞች ደግሞ ከኋላ ይከተሏቸው ነበር፤+አታሞ የሚመቱ ወጣት ሴቶችም በመካከላቸው ነበሩ።+ 26  ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት* አምላክን አወድሱ፤እናንተ ከእስራኤል ምንጭ የተገኛችሁ ሰዎች፣ ይሖዋን አወድሱ።+ 27  የሁሉም ታናሽ የሆነው ቢንያም+ በዚያ ሰዎችን ይገዛል፤የይሁዳ መኳንንትም ከሚንጫጩ ጭፍሮቻቸው ጋር፣እንዲሁም የዛብሎን መኳንንትና የንፍታሌም መኳንንት በዚያ አሉ። 28  አምላካችሁ ብርቱዎች እንድትሆኑ አዟል። ለእኛ ስትል እርምጃ የወሰድከው አምላክ ሆይ፣ ብርታትህን አሳይ።+ 29  በኢየሩሳሌም ካለው ቤተ መቅደስህ+ የተነሳ፣ነገሥታት ለአንተ ስጦታ ያመጣሉ።+ 30  ሕዝቦቹ ከብር የተሠሩ ነገሮችን አምጥተው እስኪሰግዱ* ድረስበሸምበቆዎች መካከል የሚኖሩትን አራዊት፣የኮርማዎችን ጉባኤና+ ጥጆቻቸውን ገሥጽ። ይሁንና ጦርነት የሚያስደስታቸውን ሕዝቦች ይበታትናል። 31  ከነሐስ የተሠሩ ዕቃዎች* ከግብፅ ይመጣሉ፤+ኢትዮጵያ* ለአምላክ ስጦታ ለመስጠት ትጣደፋለች። 32  እናንተ የምድር መንግሥታት ሆይ፣ ለአምላክ ዘምሩ፤+ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ዘምሩ፤ (ሴላ) 33  ከጥንት ጀምሮ በነበሩት ሰማየ ሰማያት ላይ ለሚጋልበው ዘምሩ።+ እነሆ፣ እሱ በኃያል ድምፁ ያስገመግማል። 34  ለአምላክ ብርታት እውቅና ስጡ።+ ግርማዊነቱ በእስራኤል ላይ ነው፤ብርታቱም በሰማያት* ውስጥ ነው። 35  አምላክ ከታላቅ መቅደሱ ሲወጣ፣* ፍርሃት* ያሳድራል።+ እሱ ለሕዝቡ ብርታትና ኃይል የሚሰጥየእስራኤል አምላክ ነው።+ አምላክ ይወደስ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

“በደመናት ላይ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“ያህ” የይሖዋ ስም አጭር መጠሪያ ነው።
ቃል በቃል “ፈራጅ።”
ወይም “ዓመፀኞች።”
ቃል በቃል “በሕዝብህ ፊት በወጣህ ጊዜ።”
ቃል በቃል “አንጠባጠበ።”
ቃል በቃል “ለርስትህ።”
“በበጎች ጉረኖ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ቢጫማ አረንጓዴ ቀለም ባለው።”
ወይም “በጻልሞን በረዶ የወረደ ያህል ነበር።”
ወይም “ግርማ የተላበሰ ተራራ ነው።”
ቃል በቃል “በጉባኤዎች።”
“እስኪረጋግጡ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“አምባሳደሮች” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ኩሽ።”
ቃል በቃል “በደመናት።”
ቃል በቃል “መቅደስህ (ስትወጣ . . . ታሳድራለህ)።”
ወይም “አክብሮታዊ ፍርሃት።”