በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሚጠፉት ወገን ነህ ወይስ ከሚተርፉት?

ከሚጠፉት ወገን ነህ ወይስ ከሚተርፉት?

ምዕራፍ 12

ከሚጠፉት ወገን ነህ ወይስ ከሚተርፉት?

1. ይህ ምዕራፍ የትኞቹን ጥያቄዎች እንድናስብባቸው ያበረታታናል?

ዛሬ ያለው ሃይማኖታዊ ሁኔታ በልባችን ውስጥ በእርግጥ ምን እንዳለ እንድናሳይ የሚያስገድድ ነው። ይሖዋንና መንገዶቹን በእርግጥ እንወዳለንን? “ጽድቅን ወደድህ ዓመፅንም ጠላህ” እንደተባለለት እንደ ልጁ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ነንን? (ዕብራውያን 1:9) ሌሎች ሰዎች ከየትኛው ወገን እንደሆንን ያውቁ ዘንድ ይህን አቋማችንን በግልጽ ለማሳየት ፈቃደኞች ነንን? ስለ ኢዩና ኢዮናዳብ ስለተባለ የሬካብ ልጅ የሚተርከው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ አቋማችንን ለመመርመር ይረዳናል።

2. ኢዩና ኢዮናዳብ እነማን ነበሩ?

2 ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት በአሥረኛው መቶ ዘመን ኢዩ ሰማርያን መዲናው ያደረገው የአሥሩ የእስራኤል ነገድ መንግሥት ንጉሥ እንዲሆን ተቀብቶ ነበር። ኢዩ የክፉውን ንጉሥ የአክዓብን ቤት ሁሉ የመደምሰስ ተልዕኮ ተሰጠው። ከሚደመሰሱት መካከል የበኣልን አምልኮ ለማስፋፋትና የይሖዋን አምልኮ ለማጥፋት ትጥር የነበረችው ንግሥት ኤልዛቤል አንዷ ናት። ቄንያዊው (ስለዚህም እስራኤላዊ አልነበረም ማለት ነው) ኢዮናዳብ ኢዩን ሊገናኘው በወጣ ጊዜ የመደምሰስ ፕሮግራሙን አውቆ እንደነበረ ጥርጥር የለውም። ታዲያ ኢዮናዳብ ለይሖዋ የነበረው ፍቅር ምን ያህል ጠንካራ ነበር? መመለክ ያለበት እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ብቻ ነው ከሚሉት ጋር እንደሚሰለፍ በግልጽ ያሳይ ይሆንን?

“ልብህ ከልቤ ጋር በቅንነት ነውን?”

3. ኢዮናዳብ ለይሖዋ አምልኮ የነበረውን አቋም በይፋ ያሳወቀው እንዴት ነው?

3 ሁለቱ ሰዎች ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ኢዮናዳብ አቋሙን ግልጽ እንዲያደርግ ኢዩ ጠየቀው። “ልቤ ከልብህ ጋር እንደ ሆነ ያህል ልብህ ከልቤ ጋር በቅንነት ነውን?” ሲል ጠየቀው። ኢዮናዳብም ምንም ሳያመነታ “እንዲሁ ነው” አለው። ኢዩም “እንዲሁ እንደ ሆነስ እጅህን ስጠኝ” አለው። ከዚያም ኢዮናዳብን ወደ ሰረገላው አወጣውና “ከእኔ ጋር ና፣ ለእግዚአብሔርም መቅናቴን እይ” አለው። ኢዮናዳብ ፈርቶ ወደኋላ አላለም። — 2 ነገሥት 10:15, 16፤ ዘዳግም 6:13–15⁠ን ተመልከት።

4, 5. (ሀ) ኢዩ የበኣል አምላኪዎች ማንነታቸውን እንዲያሳዩ ያደረገው በምን ዘዴ ነበር? (ለ) ኢዩ ከዚያ በኋላ ምን እርምጃ ወሰደ? ኢዮናዳብስ የት ነበር? (ሐ) በእነዚያ የበኣል አምላኪዎች ላይ የተወሰደውን እርምጃ ስትመለከት ምን ይሰማሃል?

4 ሰማሪያ ከደረሱ በኋላ ኢዩ የበኣል አምላኪዎች ሁሉ የማን ወገን መሆናቸውን እንዲያሳዩ የሚጋብዝ እርምጃ ወሰደ። ነቢያቱ፣ ካህናቱና የበኣል አምላኪዎች ሁሉ በበኣል ቤት ለሚቀርበው ታላቅ መሥዋዕት ተጠሩ። ያልመጣ ማንኛውም ሰው በሕይወቱ ይቁረጥ የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጠ። የበኣል አምላኪዎች ከሌሎች ይለዩ ዘንድ ልዩ ልብስ እንዲሰጣቸው ኢዩ አዘዘ። ይሖዋን እናመልካለን የሚሉትም በእርግጥ ማንን እንደሚያገለግሉ በዚሁ መንገድ ሚናቸውን እንዲለዩ ተደረጉ። በኣልና እርሱ የሚወክለው የሐሰት አምላክ ሰይጣን ዲያብሎስ ታላቅ ክብር የሚላበሱበት ሰዓት የመጣ መስሎ ታየ።

5 ይህ ቦታ እውነተኞቹ የይሖዋ አምላኪዎች የሚገኙበት ስፍራ አልነበረም። በቦታው የተገኙት የበኣል አምላኪዎች ብቻ እንደሆኑ ለማረጋገጥ ፍተሻ ተካሄደ። ከዚያ በኋላ የበዓሉ ሥነ ሥርዓት ጀመረ። በውጭ በኩል ደግሞ የኢዩ ሰዎች ተዘጋጅተው ይጠብቁ ነበር። ምልክት እንደተሰጣቸውም እርምጃ መውሰድ ጀመሩ። “ግደሉአቸው፤ አንድም አይውጣ” በማለት ኢዩ አዘዛቸው። ሁሉም የበኣል አምላኪ ተደመሰሰ፤ የበኣልም ቤት ተገነደሰ። “እንዲሁም ኢዩ በኣልን ከእስራኤል አጠፋ።” የዚህን ክንውን ለማየት ኢዮናዳብ ከኢዩ ጎን ቆሞ ነበር። (2 ነገሥት 10:18–28) ስለተፈጸመው ነገር አንተ በግልህ ምን ይሰማሃል? ማንኛችንም ብንሆን በሌሎች ሰዎች ሞት፣ በክፉዎችም ሞት ጭምር የምንደሰት ባንሆንም እርምጃው ለምን አስፈላጊ እንደነበረና ዛሬ እኛ እንድናነበው ታስቦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለምን ተመዝግቦ እንደቆየልን ይገባናልን? — ከሕዝቅኤል 33:11 ጋር አወዳድር።

6. (ሀ) ታላቂቱ ባቢሎን የምትጠፋው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ በይሖዋ ላይ ምንም ዓይነት ተቀናቃኝ ነገር እንዲኖር አለመፍቀዱን ያሳየው እንዴት ነበር?

6 ታሪኩ የሐሰት ሃይማኖት ተከታዮች የሚጠቀሙባቸውን የአምልኮ ሕንፃዎች ወይም በሐሰት አምልኮ የተጠመዱ ሰዎችን ለማጥፋት ሥልጣን እንዳለን አያሳይም። ይሖዋ የጽድቅ ፍርዶቹን ለማስፈጸም የሾመው ታላቁን ኢዩ ማለትም የላቀ ክብር የተቀዳጀውን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው እንጂ ዘመናዊ ምሥክሮቹን አይደለም። ሰማያዊው ንጉሥ የፖለቲካ ኃይላት ተባብረው ለታላቂቱ ባቢሎን ያላቸውን ጥላቻ እንዲገልጹ በመፍቀድ በዓለም ያለውን የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ድምጥማጡን እንዲያጠፉ ያደርጋል። (ራእይ 6:2፤ 17:16፤ 19:1, 2) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ለሰይጣን ክብር አንድ ጊዜ እንኳን ወድቆ ለመስገድ እምቢ ብሎ ነበር። የአምላክ ቃል ተሽሮ በሰው ወግ መተካቱንና የይሖዋ አምልኮ የትርፍ ማግኛ መሣሪያ መደረጉን በጥብቅ አውግዟል። ይሖዋን የሚቀናቀን አንድም ነገር እንዲኖር አልፈቀደም። — ሉቃስ 4:5–8፤ ማቴዎስ 15:3–9፤ 21:12, 13

7. (ሀ) ዘመናዊ የበኣል አምልኮ እንዳለ የሚያሳዩ አንዳንድ ማስረጃዎች ምንድን ናቸው? (ለ) ክርስቶስ ንጉሥ ቢሆንም እነዚህን ነገሮች የታገሣቸው ለምንድን ነው?

7 ታዲያ አሁን በጠላቶቹ መካከል በመግዛት ላይ ያለው ክርስቶስ የበኣል አምልኮ እየተጠናከረ እንዳለ በሚመስልበት ጊዜ ዝም ብሎ የሚመለከተው ለምንድን ነው? ሰዎች የይሖዋን ትእዛዛት ወደ ጎን በማድረግ የዚህን የነገሮች ሥርዓት አምላክ ሲያከብሩ ምንም ቅጣት ያላመጣባቸው ለምንድን ነው? የፆታ ብልግናቸውን፣ የፍቅረ ነዋይ አኗኗር መምራታቸውን፣ ክርስቲያን ነን እያሉ በመናፍስታዊ ሥራ መሳተፋቸውንና ባቢሎናዊ መሠረተ ትምህርቶችን እንደ አምላክ ቃል አድርገው ማስተማራቸውን አምላክ እንደማይቃወም አድርገው ሲያስቡ ለምን ይታገሣቸዋል? ሰው ሁሉ ማንን እንደሚያመልክና በዚህም ምክንያት መዳን ወይስ መጥፋት ይገባው እንደሆነ በግልጽ እንዲያሳይ ለመፈተን ሲል እርምጃ ከመውሰድ የታቀበ መሆኑን ጥንታዊው ድራማ ያሳየናል።

8. እኛ ልንጠይቃቸው የሚገቡን አሳሳቢ ጥያቄዎች ምንድን ናቸው?

8 አንተስ የትኛውን መንገድ መርጠሃል? ዘመናዊውን የበኣል አምልኮ ከሚከተሉት ወገን የሚያስቆጥሩ ድርጊቶችን ሁሉ ትተሃልን? ራስህን ከዓለም ለይተህ እውነተኛ የይሖዋ አምላኪ እንደሆንህ የሚያረጋግጥ አቋም ወስደሃልን? — 2 ቆሮንቶስ 6:17

9. (ሀ) በእርግጥ እንደ ኢዮናዳብ ከሆንን ምን እያደረግን መሆን ይኖርብናል? (ለ) ምዕራፍና ቁጥራቸው የተሰጡት ጥቅሶች የእነዚህን ነገሮች አስፈላጊነት የሚያጎሉት እንዴት ነው?

9 እስራኤላዊ ሳይሆን ይሖዋን ያመልክ የነበረው ኢዮናዳብ በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት በአሁኑ ጊዜ እየተሰበሰቡ ያሉትን “ሌሎች በጎች” ያመለክታል። አንተስ የኢዮናዳብን መንፈስ ታንጸባርቃለህን? ከታላቁ ኢዩና እየቀረበ ያለውን “አምላካችን የሚበቀልበትን ቀን” ከሚያውጁት በምድር ላይ ካሉት ቅቡዓን ተከታዮቹ ጎን የቆምክ መሆንህን በግልጽ ለማሳወቅ ፈቃደኛ ነህን? በዚህ አጣዳፊ ሥራ ከእነርሱ ጋር ተሰልፈሃልን? (ኢሳይያስ 61:1, 2፤ ሉቃስ 9:26፤ ዘካርያስ 8:23) ይሖዋ በልብህ ውስጥ ሊኖረው የሚገባውን ሥፍራ ለማንም ሳታጋራ ለእርሱ ብቻ የተወሰነ አምልኮ ትሰጠዋለህን? (ማቴዎስ 6:24፤ 1 ዮሐንስ 2:15–17) ከማንም፣ ከምንም ነገር የምታስበልጠው ሀብትህ ከይሖዋ ጋር ያለህ ዝምድና መሆኑን፣ ሌላው ነገር ሁሉ ግን በዚህ መሠረት ላይ የሚገነባ መሆኑን አኗኗርህ ያሳያልን? — መዝሙር 37:4፤ ምሳሌ 3:1–6

ምልክቱ አለህን?

10. በሕይወት የሚተርፉት ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች ብቻ መሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያሳየው እንዴት ነው?

10 አንድ ሰው “ጥሩ” ነገር እያደረገ በአምላክ ቃል ውስጥ በግልጽ የተወገዙትን ነገሮች ከሚያደርግ ሃይማኖት ርቆ ቢኖር ሌላ ነገር አይፈለግበትም ብሎ መደምደም ከባድ ስህተት ነው። ከጥፋት ተርፈው ወደ “አዲስ ምድር” ለመግባት ተስፋ የሚያደርጉ ሁሉ የይሖዋ አምላኪዎች መሆናቸውን በማያሻማ መንገድ ለይቶ የሚያሳውቅ ነገር ሊታይባቸው ይገባል። (ራእይ 14:6, 7፤ መዝሙር 37:34፤ ኢዩኤል 2:32) ኢየሩሳሌም በ607 ከዘአበ ከመጥፋቷ በፊት ለነቢዩ ሕዝቅኤል የመጣለት ራእይ ይህን መልእክት ያስተላልፋል።

11. (ሀ) በሕዝቅኤል 9:1–11 ላይ የተመዘገበውን ራእይ አብራራ። (ለ) ለመዳን ቁልፉ ምን ነበር?

11 ይሖዋ እምነት አጉዳይዋን ኢየሩሳሌምንና ነዋሪዎቿን ለማጥፋት የተመደቡትን ኃይሎች ሲጠራ ሕዝቅኤል ሰምቶ ነበር። ማጥፊያ መሣሪያ የታጠቁ ስድስት ሰዎችን እንዲሁም የተልባ እግር ልብስ የለበሰና በወገቡ የጸሐፊ ቀለም ቀንድ የያዘ ሰው ተመለከተ። በመጀመሪያ የተልባ እግር ልብስ ለለበሰው ሰው ይሖዋ “በከተማይቱ በኢየሩሳሌም መካከል እለፍ፣ በመካከልዋም ስለ ተሠራው ርኩሰት ሁሉ በሚያለቅሱና በሚተክዙ ሰዎች ግምባር ላይ ምልክት ጻፍ አለው።” ከዚያም ለስድስቱ “እርሱን ተከትላችሁ በከተማይቱ መካከል እለፉ ግደሉም፤ ዓይናችሁ አይራራ አትዘኑም፤ ሽማግሌውንና ጐበዙን ቆንጆይቱንም ሕፃናቶቹንና ሴቶቹን ፈጽማችሁ ግደሉ፤ ነገር ግን ምልክቱ ወዳለበት ሰው ሁሉ አትቅረቡ፤ በመቅደሴም ጀምሩ አላቸው።” ሕዝቅኤል ያን ተከትሎ የመጣውን ጥፋት በራእይ ተመልክቷል። ጥፋቱ በጣም ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ገና በምድሪቱ ላይ የነበረው የእስራኤል ሕዝብ በጠቅላላ የተደመሰሰ ይመስል ነበር። (ሕዝቅኤል 9:1–11) ከጥፋቱ ለመትረፍ ቁልፉ ምን ነበር? የጸሐፊ ቀለም ቀንድ የያዘው ሰው ግምባር ላይ የሚያደርገው ምልክት ነበር።

12. (ሀ) ምልክት የተደረገባቸው ሰዎች ‘የሚያለቅሱባቸውና የሚተክዙባቸው’ ርኩሰቶች ምን ነበሩ? (ለ) ይሖዋ እነዚህን ነገሮች የሚፀየፋቸው ለምንድን ነው?

12 ከጥፋቱ እንዲድኑ ግምባራቸው ላይ ምልክት የተደረገባቸው በኢየሩሳሌም ውስጥ ስለሚሠራው ርኩሰት ‘የሚያለቅሱና የሚተክዙ ሰዎች’ ብቻ ነበሩ። እነዚያ ርኩስ ነገሮች ምን ነበሩ? አምስቱ እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል:- (1) በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጠኛ አደባባይ መግቢያ ላይ የተተከለ “የቅንዓት ጣዖት” ነበር። መልኩ ምንም ዓይነት ይሁን እስራኤላውያን ለይሖዋ መስጠት ይገባቸው የነበረውን አምልኮ ‘ለቅንዓቱ ጣዖት’ ሰጥተውታል። (1 ነገሥት 14:22–24) (2) በቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ግድግዳ ላይ በሆዳቸው የሚሳቡና የሌሎች እንስሳት ምስል ተስሎ እጣን እየተጨሰለት ነበር። (3) ሴቶች ተቀምጠው ተሙዝ ለተባለ አምላክ ሲያለቅሱ ነበር። ይህም በይሖዋ ላይ ያመፀው የናምሩድ ሌላው ስም ነው። (ዘፍጥረት 10:9 አዓት ) (4) ጀርባቸውን ለይሖዋ ቤተ መቅደስ ሰጥተው ለፀሐይ የሚሰግዱ ሰዎች የሚዘገንን ድፍረት አሳይተዋል። (ዘዳግም 4:15–19) (5) የመጨረሻውም ንቀት ምድሪቱን በዓመፅ መሙላታቸውና “ቅርንጫፉን” (ምናልባት የሩካቤ ሥጋ ምስል ሊሆን ይችላል) ወደ ይሖዋ አፍንጫ ማስጠጋታቸው ነው። የእነርሱ ነገር ይሖዋን ለምን እንዳንገፈገፈው አሁን ይታይሃልን? — ሕዝቅኤል 8:5–17

13. (ሀ) ከእነዚህ ‘ርኩሰቶች’ ጋር የሚመሳሰሉትን ዘመናዊ ድርጊቶች አንድ በአንድ አብራራ። (ለ) ስለነዚህ ድርጊቶች ምን ይሰማሃል?

13 በዛሬው ዘመን ሕዝበ ክርስትና የምትፈጽማቸውን ከእነዚህ ‘ርኩሰቶች’ ጋር የሚወዳደሩ ድርጊቶች ስትመለከት በግልህ ምን ይሰማሃል? (1) መጽሐፍ ቅዱስ ለጣዖታት አትስገዱ ብሎ ቢያስጠነቅቅም በየቤተ ክርስቲያኑ ሰዎች ተደፍተው የሚሰግዱላቸው ምስሎች አሉ። (1 ቆሮንቶስ 10:14፤ ከ2 ነገሥት 17:40, 41 ጋር አወዳድር።) (2) ሕዝበ ክርስትና ሌላው እንደሆነው መሆን ይሻላል በሚል ፈሊጥ ሰው በአምላክ የመፈጠሩን ሐቅ ገሸሽ አድርጋ በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት ከእንስሳት የመጣ ነው በሚለው ንድፈ ሐሳብ ለመተካት አላንገራገረችም። ከዚህም ሌላ የእንስሳትና የአእዋፍ ምስል በተለጠፈባቸው ብሔራዊ አርማዎች ፊት በጦፈ ስሜት የሚደረገው ስግደት ተካፋይ ሆናለች። (3) በአምልኮቷ ውስጥ ከጥንት ዘመን ጀምሮ የተሙዝ ሃይማኖታዊ አርማ የሆነውን መስቀል በሰፊው ትገለገልበታለች። የናምሩድን መንፈስ በማንፀባረቅ ደም በሚፋሰስባቸው ጦርነቶች ለሞቱት መታሰቢያ በሚደረጉት ሥነ ሥርዓቶች ላይ ትካፈላለች። (ዮሐንስ 17:16, 17 የሚለውን ግን ተመልከት።) (4) አምላክ በቃሉ አማካኝነት ለሚናገረው ነገር ጀርባዋን ትሰጣለች። ከዚህ ይልቅ ዘመናዊ ሳይንስና ሰብዓዊ ፍልስፍና የሚያቀርቡትን “ምሁራዊ አስተሳሰብ” ትመርጣለች። (1 ጢሞቴዎስ 6:20, 21፤ ከኤርምያስ 2:13 ጋር አወዳድር።) (5) ይህም ሁሉ ሳይበቃት በአንዳንድ ቦታዎች በመንግሥት ላይ የሚደረጉ ዓመፆችን ትደግፋለች። በአምላክ ስም አስተምራለሁ እያለች ስለ ፆታ ብልግና ልል የሆነ አቋም ይዛለች። (2 ጴጥሮስ 2:1, 2) አንዳንድ ሰዎች እነዚህን አዝማሚያዎች የነፃነት አመለካከት ናቸው ብለው ያስቡ ይሆናል። በሁሉም ነገር ላይስማሙ ቢችሉም በአንዳንዶቹ ነገሮች ተካፋይ ይሆናሉ ወይም ቢያንስ ቢያንስ ሌሎች ሲፈጽሟቸው በቸልታ ይመለከታሉ። እንደነዚህ ስላሉት፣ ሰውን ከሰው ልጅ ፈጣሪ ስለሚያርቁና አምላክን ስለሚያዋርዱ ድርጊቶች እንዴት ይሰማሃል?

14. አንድ ሰው አብያተ ክርስቲያናት የሚያስጠሉት መሆኑ ከጥፋት ለመትረፍ የማያበቃው ለምንድን ነው?

14 ብዙ ሰዎች በአብያተ ክርስቲያናት ላይ አንገት የሚያስደፋ ሁኔታ ስለሚያዩ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ትተዋል። በዓለም ውስጥ ባለው ዓመፅና ውሸትም በጣም ተረብሸው ሊሆን ይችላል። ይህ ማለት ግን ከጥፋት ለመትረፍ የሚያበቃ ምልክት ተደርጎባቸዋል ማለት አይደለም። ‘የጸሐፊ ቀለም ቀንድ በያዘው ሰው’ ምልክት እንዲደረግባቸው ያስፈልጋል። በዛሬው ጊዜ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ምልክት የማድረጉን ሥራ እያከናወነ እንዳለ ማስረጃዎቹ ያሳያሉ። — ማቴዎስ 24:45–47

15. (ሀ) ምልክቱ ምንድን ነው? (ለ) አንድ ሰው ምልክቱን የሚያገኘው እንዴት ነው?

15 የአምላክ ሞገስ እንዳላቸው የሚያሳይ ምልክት እንዲደረግባቸው የሚፈልጉ ሁሉ ይሖዋ በዚህ ‘የባሪያ’ ክፍል አማካኝነት የሚሰጣቸውን ትምህርት መቀበልና የይሖዋ እውነተኛ አምላኪ መሆን ይኖርባቸዋል። በአፋቸው ይሖዋን የሚያከብሩ፣ በሐቁ ግን የዓለምን መንገዶች የሚወዱ መሆን አይገባቸውም። (ኢሳይያስ 29:13, 14፤ 1 ዮሐንስ 2:15) ይሖዋንና የሥነ ምግባር ደረጃዎቹን መውደድና እርሱን በሚያሰድቡ ትምህርቶችና ተግባሮች ምክንያት ‘የሚያዝኑና የሚተክዙ’ ወይም ከልብ ቁጭት የሚሰማቸው መሆን ይገባቸዋል። ቃል በቃል ግምባራቸው ላይ የቀለም ምልክት አይደረግባቸውም። ምሳሌያዊ ምልክት ከተደረገባቸው ግን ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑና የተጠመቁ ክርስቲያኖች እንደሆኑና በኤፌሶን 4:24 ላይ የተገለጸውን “አዲሱን ሰው” እንደለበሱ ለማንም በግልጽ ይታያል። ሕያው እምነት አላቸው። በሰው ፊት ሲሆኑና በግላዊ ሕይወታቸው ይሖዋን የሚያስከብር ነገር ለማድረግ ይጥራሉ። ከሕዝበ ክርስትና የወጡት ብቻ ሳይሆኑ ከሌሎችም አካባቢዎች የመጡ ሰዎች የቅቡዓኑ ክፍል ተባባሪ በመሆን ከጥፋት ተርፈው ወደ “አዲስ ምድር” ለመግባት ከፈለጉ ይህ ምልክት እንዲኖራቸው ያስፈልጋል።

16. ይህ ራእይ በተለይ ለልጆችና ለወላጆቻቸው በጣም አስፈላጊ ቁም ነገር ያዘለው እንዴት ነው?

16 በተለይ ሊተኮርበት የሚገባ ዐቢይ ጉዳይ የይሖዋ ፍርድ አስፈጻሚ ኃይሎች፣ በይሖዋ ላይ በደል የፈጸመውን ሰው ላለማጥፋት ዕድሜ፣ ፆታ፣ ነጠላነት ወይም ጋብቻ ምክንያት እንደማይሆናቸው የተነገራቸው መሆኑ ነው። ያገባ ግለሰብ ከጥፋቱ ለመትረፍ በግሉ የራሱን ምልክት ማግኘት አለበት ወይም አለባት። ወላጆች ልጆቻቸው ምልክት እንዳይደረግላቸው ከተከላከሉ ወይም የይሖዋ አገልጋይ አድርገው ሳያሳድጓቸው ከቀሩ በእነዚህ ልጆች ላይ ለሚደርሰው ነገር ኃላፊነቱን መቀበል ይኖርባቸዋል። አምላክን የሚያከብሩ ወላጆች ልጆቻቸው ታዛዥ ከሆኑ ይሖዋ እንደ “ቅዱስ” አድርጎ ይመለከታቸዋል፤ ዓመፀኛ ልጆችን ግን እንደዚያ አድርጎ አይመለከታቸውም። (1 ቆሮንቶስ 7:14፤ መዝሙር 102:28፤ ምሳሌ 20:11፤ 30:17) ልጆች የተጠመቁ ክርስቲያኖች ለመሆን በሚያበቃ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሆነው ሳሉ ከተጠመቁ ሰዎች የሚፈለጉትን ብቃቶች ካላሟሉ ተጠመቁም አልተጠመቁ፣ ዕድሜያቸው ከጥፋት ሊያድናቸው አይችልም። እንግዲያው ለኃላፊነት ወደሚያበቃ ዕድሜ የደረሰ እያንዳንዱ ግለሰብ ለአምላክ የተወሰነና የእርሱን ፈቃድ የሚፈጽም እንደሆነ የሚያሳይ ግልጽ ምልክት ማግኘቱ የቱን ያህል አንገብጋቢ ነው!

17. እዚህ ላይ ስለ ይሖዋ ርኅራኄ ምን ተምረናል?

17 ይሖዋ ከፊታችን ስለተደቀነው ጥፋት ሰዎችን ለማስጠንቀቅና መዳኛውን መንገድ ለመጠቆም ምሥክሮቹን በመላኩ ለሰው ልጆች ታላቅ ርኅራኄ አሳይቷል። የሐሰት ሃይማኖት ያስመዘበገውን ታሪክና ያፈራቸውን የበሰበሱ ፍሬዎች ግን ደህና አድርጎ ያውቃቸዋል። ታላቂቱ ባቢሎን በምትጠፋበት ጊዜ እርሷን የሙጥኝ ብሎ ለመቆየት የመረጠ ማንኛውም ሰው ምንም ዓይነት ርኅራኄ አይደረግለትም። ከሚመጣው የመለኮታዊ ፍርድ ቅጣት ሕይወታችንን ለማትረፍ ከፈለግን የኢየሱስ ክርስቶስን ፈለግ በመከተል የሰማይና የምድር ፈጣሪ የሆነው የይሖዋ እውነተኛ አምላኪዎች መሆን ይኖርብናል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 95 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ከጥፋት ለመዳን የሚያበቃው ምልክት በእርግጥ አለህን?