በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስ ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምንድን ነው?

 ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ መረጃዎች

 •   መጽሐፍ ቅዱስን የጻፈው ማን ነው? መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው አምላክ ነው፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጻፍ 40 ገደማ የሚሆኑ ሰዎችን ተጠቅሟል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ሙሴ፣ ንጉሥ ዳዊት፣ ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ እና ዮሐንስ ይገኙበታል። a አምላክ ሐሳቡን በእነዚህ ሰዎች አእምሮ ውስጥ በመክተት በጽሑፍ እንዲያሰፍሩት አድርጓል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

   ለምሳሌ ያህል፣ የአንድ ድርጅት ባለቤት በእሱ ስም ደብዳቤ እንድትጽፍለት ጸሐፊውን ሊጠይቃት ይችላል፤ ምናልባትም የደብዳቤውን አንኳር ሐሳብ ይነግራት ይሆናል፤ ደብዳቤውን እሷ ብትጽፈውም እንኳ የደብዳቤው ባለቤት ሰውየው ነው። በተመሳሳይም አምላክ መልእክቱን ለማስጻፍ ሰዎችን ቢጠቀምም እንኳ የመልእክቱ ምንጭ እሱ ነው።

 •   መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው መቼ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ መጻፍ የጀመረው በ1513 ዓ.ዓ. ሲሆን ተጽፎ የተጠናቀቀው ደግሞ ከ1,600 ዓመት በላይ ካለፈ በኋላ ማለትም በ98 ዓ.ም. ገደማ ነው።

 •   የመጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ የሚገኘው የት ነው? ከመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የመጀመሪያ ቅጂዎች መካከል እስካሁን የተገኘ የለም። ይህ የሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ለመጻፍ የተጠቀሙት እንደ ፓፒረስና ብራና ያሉትን በዘመኑ የነበሩ በቀላሉ የሚበላሹ መሣሪያዎች ስለሆነ ነው። ሆኖም ጠንቃቃ የሆኑ ገልባጮች መጽሐፍ ቅዱስን ለበርካታ መቶ ዓመታት በተደጋጋሚ ሲገለብጡ ቆይተዋል፤ ይህም መልእክቱ ከዘመናት በኋላ ለሚኖሩ አንባቢዎችም ተጠብቆ እንዲቆይ አስችሏል።

 •   “ብሉይ ኪዳን” እና “አዲስ ኪዳን” ምንድን ናቸው? በተለምዶ “ብሉይ ኪዳን” ተብሎ የሚጠራው በዋነኝነት በዕብራይስጥ b የተጻፈው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሲሆን ይህ ክፍል “የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት” በመባልም ይጠራል። “አዲስ ኪዳን” ተብሎ የሚጠራው ክፍል ደግሞ የተጻፈው በግሪክኛ ነው፤ “የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት” ተብሎም ይጠራል። ሁለቱ ክፍሎች አንድ ላይ ሆነው የተሟላ መጽሐፍ ይፈጥራሉ፤ ይህ መጽሐፍ “ቅዱሳን መጻሕፍት” በመባልም ይታወቃል። c

 •   መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይዟል? የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ታሪክ፣ ሕግ፣ ትንቢት፣ ግጥም፣ ምሳሌ፣ መዝሙር እና ደብዳቤ ይዘዋል።—“ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ዝርዝር” የሚለውን ተመልከት።

መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ስለ ምንድን ነው?

  መጽሐፍ ቅዱስ የሚጀምረው ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ሰማያትንና ምድርን እንደፈጠረ በሚገልጸው አጭር ዘገባ ነው። አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ስሙ ይሖዋ እንደሆነ ተናግሯል፤ በዚህ መንገድ ሰዎች እሱን እንዲያውቁት ግብዣ አቅርቧል።—መዝሙር 83:18

 መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ስሙ ነቀፋ እንደተሰነዘረበት የሚናገር ከመሆኑም ሌላ ስሙን መልሶ የሚያስቀድሰው እንዴት እንደሆነ ይገልጻል።

 መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ለሰዎችና ለምድር ያለውን ዓላማ ይገልጻል። አምላክ በሰዎች ላይ መከራ የሚያስከትሉ ነገሮችን ወደፊት የሚያስወግደው እንዴት እንደሆነም ይናገራል።

 መጽሐፍ ቅዱስ ለዕለት ተዕለት ሕይወታችን የሚጠቅሙ ምክሮችን ይዟል። ከእነዚህ ምክሮች መካከል አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት፦

 •   ከሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን ማድረግ። “እንግዲህ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም አድርጉላቸው።”—ማቴዎስ 7:12

   ትርጉሙ፦ ሌሎችን ልንይዝ የሚገባው እኛን እንዲይዙን በምንፈልግበት መንገድ ነው።

 •   ውጥረትን መቋቋም። “ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ፤ ምክንያቱም ነገ የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉት።”—ማቴዎስ 6:34

   ትርጉሙ፦ ወደፊት ሊያጋጥሙን ስለሚችሉ ነገሮች ከልክ በላይ ከመጨነቅ ይልቅ ስለ ዛሬ ብቻ ብናስብ የተሻለ ነው።

 •   ትዳራችንን የሰመረ ማድረግ። “ከእናንተ እያንዳንዱ ራሱን እንደሚወድ ሁሉ ሚስቱንም ይውደድ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሚስት ባሏን በጥልቅ ታክብር።”—ኤፌሶን 5:33

   ትርጉሙ፦ ለሰመረ ትዳር ቁልፉ ፍቅርና አክብሮት ነው።

 መጽሐፍ ቅዱስ ተቀይሯል?

 አልተቀየረም። ምሁራን ጥንታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን በአሁኑ ጊዜ ካለው መጽሐፍ ቅዱስ ጋር በማወዳደር ዋናው መልእክት እንዳልተቀየረ አረጋግጠዋል። ይህ መሆኑ አያስገርምም፤ አምላክ ሰዎች መልእክቱን እንዲያነብቡና እንዲረዱት ስለሚፈልግ መልእክቱ እንዳይቀየር እንደሚያደርግ የታወቀ ነው። dኢሳይያስ 40:8

 ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ያሉት ለምንድን ነው?

 በዘመናችን ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈባቸውን ጥንታዊ ቋንቋዎች መረዳት አይችሉም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “በምድር ላይ ለሚኖር ብሔር፣ ነገድ፣ ቋንቋና ሕዝብ ሁሉ” የሚሆን “ምሥራች” ይዟል። (ራእይ 14:6) በመሆኑም ሰዎች የአምላክን መልእክት በትክክል ማንበብና መረዳት እንዲችሉ መጽሐፍ ቅዱስ በሚገባቸው ቋንቋ መተርጎም አለበት።

 ሦስት ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም ዘዴዎች አሉ፦

 •   የቃል በቃል ትርጉም ሐሳቡን በተቻለ መጠን ቃል በቃል ለማስቀመጥ ጥረት ያደርጋል።

 •   የሐሳብ በሐሳብ ትርጉም የመጀመሪያውን ቋንቋ መልእክት የሚያስተላልፉ ቃላት ይጠቀማል።

 •   ነፃ ትርጉም ጽሑፉ ለንባብ አስደሳች እንዲሆን ለማድረግ ሲል ሐሳቡን በፈለገው መንገድ ያስቀምጠዋል። ሆኖም እንዲህ ያለው ትርጉም የምንባቡን ትክክለኛ መልእክት ሊቀይረው ይችላል።

 ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የሚባለው የአምላክን መልእክት ለሰዎች በትክክል ለማስተላለፍ የመጀመሪያውን ቋንቋ መልእክት ሳይለቅ በቀላሉ የሚገባ ዘመናዊ ቋንቋ የሚጠቀም ትርጉም ነው። e

 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምን እንደሚካተት የወሰነው ማን ነው?

 መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው አምላክ ስለሆነ በውስጡ ምን እንደሚካተት የወሰነውም እሱ ነው። አምላክ መጀመሪያ ላይ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን እንዲጠብቁ ‘ቅዱስ ቃሉን በአደራ’ የሰጠው ለጥንቱ የእስራኤል ብሔር ነበር።—ሮም 3:2

 የጠፉ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት አሉ?

 የሉም። መጽሐፍ ቅዱስ የተሟላ መጽሐፍ ነው፤ “የጠፉ” መጻሕፍት የሉም። አንዳንዶች ለረጅም ጊዜ ጠፍተው የቆዩ አንዳንድ ጥንታዊ መጻሕፍት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሊካተቱ እንደሚገባ ይናገሩ ይሆናል። f ይሁንና የትኞቹ መጻሕፍት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሊካተቱ እንደሚገባ መሥፈርቱ ያለው በራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 1:13) ከዚህ መሥፈርት አንጻር በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ሙሉ በሙሉ እርስ በርስ ይስማማሉ። አንዳንዶች ‘በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሊካተቱ ይገባል’ የሚሏቸው ጥንታዊ መጻሕፍት ይህን መሥፈርት አያሟሉም። g

 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ማውጣት የሚቻለው እንዴት ነው?

  የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ዝርዝር

a የሁሉንም የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ስም፣ ማን እንደጻፋቸው እንዲሁም የት እንደተጻፉ ለማየት “የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ሰንጠረዥ” የሚለውን ተመልከት።

b ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የተጻፉት በአረማይክ ነው፤ አረማይክ ከዕብራይስጥ ጋር የቅርብ ተዛማጅነት ያለው ቋንቋ ነው።

c በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች “የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት” እና “የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት” የሚሉትን አጠራሮች ይመርጣሉ። ምክንያቱም እነዚህ አጠራሮች “ብሉይ ኪዳን” ጊዜ ስላለፈበት “በአዲስ ኪዳን” ተተክቷል የሚል አንድምታ የላቸውም።

e አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛና ለመረዳት ቀላል በመሆኑ ብዙዎች ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ማንበብ ያስደስታቸዋል። አዲስ ዓለም ትርጉም ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

f እነዚህ መጻሕፍት “አዋልድ መጻሕፍት” በመባል ይታወቃሉ። ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንደሚገልጸው ‘አዋልድ መጻሕፍት የሚለው አገላለጽ የሚሠራበት ተቀባይነት ካላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ውጭ ያሉትን መጻሕፍት ለማመልከት ነው።’

g ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “የአዋልድ ወንጌሎች—ስለ ኢየሱስ የተሰወሩ እውነቶችን ይዘዋል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።