በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወንጌሎች ምን ያህል እምነት የሚጣልባቸው ናቸው?

ወንጌሎች ምን ያህል እምነት የሚጣልባቸው ናቸው?

ወንጌሎች ምን ያህል እምነት የሚጣልባቸው ናቸው?

“በአሁኑ ጊዜ፣ ወንጌሎች መታየት ያለባቸው የጥንት ክርስቲያኖች የጻፏቸው አፈ ታሪኮች እንደሆኑ ተደርገው ነው።”—በርተን ማክ የተባሉ በአዲስ ኪዳን ላይ ምርምር ሲያደርጉ የነበሩ ፕሮፌሰር

እንዲህ ያለ አመለካከት ያላቸው እኚህ ፕሮፌሰር ብቻ አይደሉም። በርከት ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች የኢየሱስን ሕይወትና አገልግሎት ባሰፈሩት በማቴዎስ፣ በማርቆስ፣ በሉቃስና በዮሐንስ ወንጌሎች ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ ያነሳሉ። አንዳንድ ሰዎች የወንጌል ዘገባዎችን አፈ ታሪክ እንደሆኑ አድርገው የሚመለከቷቸው ለምንድን ነው? እነዚህ ሰዎች የሚሰጡት ሐሳብ የወንጌል ዘገባዎችን ትክክለኛነት እንድትጠራጠር ሊያደርግህ ይገባል? እስቲ ይህን አስመልክቶ አንዳንድ ማስረጃዎችን እንመርምር።

በወንጌሎች ትክክለኛነት ላይ የተነሳ ጥያቄ

ከክርስቶስ ልደት በኋላ እስከ 17ኛው መቶ ዘመን ድረስ በወንጌሎች ትክክለኛነት ላይ ይህ ነው የሚባል ጥያቄ ተነስቶ አያውቅም። ይሁን እንጂ በተለይ ከ19ኛው መቶ ዘመን በኋላ በርካታ ምሁራን፣ ወንጌሎች በአምላክ መንፈስ መሪነት እንደተጻፉ ሳይሆን የሰዎች የፈጠራ ታሪክ እንደሆኑ አድርገው መመልከት ጀመሩ። እነዚህ ምሁራን፣ የወንጌል ጸሐፊዎች ኢየሱስ ስለተናገራቸውና ስላከናወናቸው ነገሮች የዓይን ምሥክሮች ስላልነበሩ ትክክለኛ ታሪክ ሊጽፉ አይችሉም በማለት ይከራከራሉ። ከዚህም በላይ በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወንጌሎች (አንዳንድ ጊዜ ሲኖፕቲክ ማለትም “በተመሳሳይ አቅጣጫ ያተኮሩ” ተብለው በሚጠሩት) ላይ የሚታየው የአጻጻፍ ስልትና የይዘት መመሳሰል የወንጌል ጸሐፊዎች አንዳቸው የሌላውን ጽሑፍ ገልብጠዋል ወደሚል መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል። ሌላው ቀርቶ ኢየሱስ ስላከናወናቸው ተአምራትና ከሞት ስለመነሳቱ የሚገልጹትን የወንጌል ዘገባዎች እንኳ አይቀበሉም። እንዲያውም አንዳንዶች ኢየሱስ ጭራሽ በምድር ላይ የኖረ ሰው አይደለም ብለው ይናገራሉ!

እነዚህ ሰዎች፣ የማርቆስ ወንጌል በማቴዎስና በሉቃስ ዘገባዎች ውስጥ የማይገኙ ለየት ያሉ መረጃዎችን ስላልያዘ መጀመሪያ ላይ የተጻፈው እሱ መሆን አለበት የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። ከዚህም በተጨማሪ ማቴዎስና ሉቃስ በወንጌላቸው ላይ ያሰፈሯቸውን መረጃዎች ያሰባሰቡት ከማርቆስ መጽሐፍና ምሁራን ኪው (Q) ብለው ከሚጠሩት ጽሑፍ ላይ እንደሆነ ይናገራሉ። ኪው፣ ክቨል (Quelle) ከሚለው የጀርመንኛ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም “ምንጭ” ማለት ነው። አልበርተስ ፍሬደሪክ ዮሐነስ ክላይን የተባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንደገለጹት ከሆነ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው ይህ ግምታዊ አስተሳሰብ “የወንጌል ዘጋቢዎች፣ ጸሐፊዎች ሳይሆኑ [ሌሎች የጻፏቸውን] ታሪኮች አሰባስበው የጻፉ ሰዎች ናቸው” የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። ይህ ዓይነቱ አስተያየት ደግሞ ‘የወንጌል ጸሐፊዎች የሌሎችን ጽሑፎች የራሳቸው አስመስለው ለማቅረብ ሞክረዋል አሊያም በጽሑፎቻቸው ላይ ያሰፈሩት አፈ ታሪክ ነው’ ከማለት ተለይቶ አይታይም። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ፣ ሰዎች በአምላክ መንፈስ መሪነት በተጻፈው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያላቸውን እምነት የሚያዳክም ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

የወንጌል ጸሐፊዎች የሌሎችን ጽሑፎች እንደ ራሳቸው አድርገው ለማቅረብ ሞክረዋል?

ሲኖፕቲክ ተብለው በሚጠሩት ወንጌሎች መካከል መመሳሰል መኖሩ የወንጌል ጸሐፊዎች አንዳቸው ከሌላው የገለበጡ መሆኑን ያረጋግጣል? በፍጹም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስ ‘እሱ የነገራቸውን ነገር ሁሉ እንዲያስታውሱ እንደሚያደርጋቸው’ ቃል ገብቶላቸዋል። (ዮሐንስ 14:26 የ1980 ትርጉም) በመሆኑም የወንጌል ጸሐፊዎች ተመሳሳይ ክንውኖችን አስታውሰው መዘገባቸው አያስገርምም። አንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ሌሎቹ ያሰፈሯቸውን ዘገባዎች አንብበውና ከዚያም ላይ ጠቅሰው ሊሆን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁንና እንዲህ ማድረጋቸው የሌሎችን ጽሑፎች የራሳቸው አስመስለው ለማቅረብ መሞከራቸውን ሳይሆን ጥንቃቄ የተሞላበት ምርምር ማድረጋቸውን የሚጠቁም ነው። (2 ጴጥሮስ 3:15) ከዚህም በተጨማሪ ዚ አንከር ባይብል ዲክሽነሪ እንዲህ ብሏል፦ “ኢየሱስ የተናገራቸው በቀላሉ የማይረሱ ነገሮች [በወንጌል ዘገባዎች ላይ] ተመሳሳይ በሆነ መንገድ የሰፈሩት፣ ሐሳቦቹ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፉት በቃል ስለነበር ሊሆን ይችላል።”

ሉቃስ ብዙ የዓይን ምሥክሮችን እንደጠየቀና ‘ሁሉንም ከመሠረቱ በጥንቃቄ እንደመረመረ’ ገልጿል። (ሉቃስ 1:1-4) ሉቃስ ይህን ማለቱ የሌሎችን ጽሑፍ የራሱ አስመስሎ ለማቅረብ መሞከሩን ወይም የፈጠራ ታሪክ መጻፉን ያሳያል? በጭራሽ! አርኪኦሎጂስት ዊሊያም ራምዚ፣ ሉቃስ በጻፋቸው መጻሕፍት ላይ ጥልቅ ምርምር ካደረጉ በኋላ እንደሚከተለው ብለዋል፦ “ሉቃስ፣ አሉ ከተባሉት የታሪክ ጸሐፊዎች መካከል አንዱ ነው፤ የጻፋቸው ተአማኒነት ያላቸው ከመሆናቸውም ሌላ ታሪካዊ እውነታዎች እንዴት ሊጻፉ እንደሚገባ ያውቅ ነበር። . . . ይህ ጸሐፊ ከታላላቅ የታሪክ ምሁራን ተርታ ሊመደብ ይገባዋል።”

በሦስተኛው መቶ ዘመን የኖረውን ኦሪጀን የተባለ የሃይማኖት ምሁር ጨምሮ የጥንት የቤተ ክርስቲያን አባቶች የሰጡት የምሥክርነት ቃል እንደሚያሳየው የመጀመሪያው የወንጌል ጸሐፊ ማቴዎስ ነው። ኦሪጀን እንደሚከተለው ሲል ጽፏል፦ “የመጀመሪያውን [ወንጌል] የጻፈው በአንድ ወቅት ቀረጥ ሰብሳቢ የነበረውና በኋላ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነው ማቴዎስ ነው። መጽሐፉን ያዘጋጀው ወደ ክርስትና ለተለወጡት አይሁዳውያን ሲሆን የጻፈውም በዕብራይስጥ ነበር።” ሐዋርያና የዓይን ምሥክር የነበረው ማቴዎስ የዓይን ምሥክር ያልነበረውን የማርቆስን ጽሑፍ የራሱ አስመስሎ ማቅረብ የሚሞክርበት ምንም ምክንያት የለም። ማቴዎስና ሉቃስ ወንጌላቸውን የጻፉት ከማርቆስና ኪው ከተባለው ሰነድ ላይ ገልብጠው ነው ስለሚለው ትችትስ ምን ማለት ይቻላል?

መጀመሪያ የተጻፈው የማርቆስ ወንጌል ነው?

መጀመሪያ የተጻፈው የማርቆስ ወንጌል ስለሆነ ለማቴዎስና ለሉቃስ የመረጃ ምንጭ በመሆን አገልግሏል የሚለው አስተያየት “በአሳማኝ ነጥብ” ላይ የተመሠረተ እንዳልሆነ ዚ አንከር ባይብል ዲክሽነሪ በግልጽ ተናግሯል። ያም ሆኖ በርካታ ምሁራን፣ ማርቆስ ወንጌሉን የጻፈው ከማቴዎስና ከሉቃስ በፊት እንደሆነ ይገልጻሉ። ለዚህ እንደ ምክንያት የሚያቀርቡት የማርቆስ ወንጌል ከሁለቱ ወንጌሎች የተለየ ሐሳብ አልያዘም የሚለውን ነው። ለአብነት ያህል፣ በ19ኛው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩት ዮሐነስ ኩን የተባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር፣ መጀመሪያ የተጻፈው የማርቆስ ወንጌል መሆን አለበት በማለት ይከራከራሉ። ይህ ካልሆነ ግን “አንድ ሰው፣ ማርቆስ የማቴዎስንና የሉቃስን ጥቅልሎች በትናንሹ ቆራርጦ ማሰሮ ውስጥ በመጨመር ከቀላቀለው በኋላ የማርቆስን ወንጌል አዘጋጀ ብሎ ማመን ሊኖርበት ነው” በማለት ኩን ተናግረዋል።

የማርቆስ ወንጌል ከሌሎቹ ወንጌሎች አጭር ስለሆነ ለየት ያሉ ጥቂት መረጃዎችን መያዙ የሚያስገርም አይደለም። ያም ሆኖ የማርቆስ መጽሐፍ አጭር መሆኑ መጀመሪያ የተጻፈው እሱ ነው ለማለት ምክንያት አይሆነንም። ከዚህም በላይ የማርቆስ ወንጌል፣ ከማቴዎስና ከሉቃስ የተለየ መረጃ አልያዘም ብሎ መናገር ስህተት ነው። ስለ ኢየሱስ አገልግሎት የሚገልጸው ኃይለኝነትና ችኩልነት የሚንጸባረቅበት የማርቆስ ዘገባ በማቴዎስና በሉቃስ ውስጥ የማይገኙ ከ180 በላይ ጥቅሶችን አሊያም የጥቅስ ክፍሎችን እንዲሁም አስደናቂ የሆኑ ዝርዝር ሐሳቦችን ይዟል። ይህ ደግሞ የማርቆስን ወንጌል ስለ ኢየሱስ ሕይወት ከሚናገሩት ዘገባዎች ሁሉ ለየት ያደርገዋል።— በገጽ 13 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።

ኪው ስለተባለው ሰነድስ ምን ማለት ይቻላል?

አንዳንዶች ለማቴዎስና ለሉቃስ ወንጌሎች የመረጃ ምንጭ በመሆን አገልግሏል ስለሚሉት ኪው ስለተባለው ሰነድስ ምን ማለት ይቻላል? የሃይማኖት ፕሮፌሰር የሆኑት ጄምስ ሮቢንሰን “ኪው፣ ካሉን የክርስቲያን ጽሑፎች መካከል ዋነኛው መሆኑ እሙን ነው” ብለዋል። ይህ አነጋገር አስገራሚ ነው! ምክንያቱም ኪው የተባለው ሰነድ በዛሬው ጊዜ የማይገኝ ሲሆን ቀደም ሲል ስለመኖሩም ማንም በእርግጠኛነት ሊናገር አይችልም። ምሁራን፣ የዚህ ሰነድ በርካታ ቅጂዎች ተሰራጭተዋል ስለሚሉ ሙሉ በሙሉ የመጥፋቱም ጉዳይ ቢሆን የሚያስደንቅ ነው። በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያን አባቶች ኪው ከተባለው ሰነድ ፈጽመው ጠቅሰው አያውቁም።

እስቲ አስበው፣ የማርቆስ ወንጌል የተጻፈው መጀመሪያ ነው የሚለውን መላምት የሚደግፍ ኪው የተባለ ሰነድ በአንድ ወቅት እንደነበረ ይገመታል። ይህ ታዲያ በአንድ ግምታዊ ሐሳብ ላይ ተመርኩዞ ሌላ መላምት መናገር አይሆንም? እንዲህ ያሉ መላምቶችን በምንሰማበት ጊዜ “ተላላ ሰው የሰማውን ሁሉ ያምናል፤ ብልኅ ሰው ግን ማስረጃ ማግኘት አስፈላጊ መሆኑን ይገነዘባል” የሚለውን ምሳሌ ማስታወሳችን ጥበብ ነው።—ምሳሌ 14:15 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል

ወንጌሎችእውነተኛና እምነት የሚጣልባቸው ዘገባዎችን ይዘዋል

የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች የሚሰነዝሯቸው ግምታዊ ሐሳቦች፣ በርካታ ሰዎች የኢየሱስን ሕይወትና አገልግሎት አስመልክቶ ትክክለኛ ዘገባ የያዙትን የወንጌል መጻሕፍትን እንዳይመረምሩ እንቅፋት ሆነዋል። እነዚህ የወንጌል ዘገባዎች የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የኢየሱስን ሕይወት፣ አገልግሎት፣ ሞትና ትንሣኤ አፈ ታሪክ አድርገው እንዳልተመለከቷቸው በግልጽ ያሳያሉ። በመቶዎች የሚቆጠሩ የዓይን ምሥክሮችም እነዚህ ነገሮች እውነት መሆናቸውን መሥክረዋል። ኢየሱስን ለመከተል ሲሉ ስደትና ሞት ለመጋፈጥ ፈቃደኞች የነበሩት እነዚህ የጥንት ክርስቲያኖች ስለ ኢየሱስ አገልግሎትና ትንሣኤ የሚገልጹት ዘገባዎች አፈ ታሪክ ከሆኑ፣ ክርስቲያን መሆናቸው ትርጉም የለሽ እንደሚሆን በሚገባ ተገንዝበው ነበር።—1 ቆሮንቶስ 15:3-8, 17, 19፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:2

የማርቆስ ወንጌል መጀመሪያ ተጽፏል ከሚለው መላምትና ማንም ሰው አይቶት ከማያውቀው ኪው ከተባለው ሰነድ ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ክርክር አስመልክተው የሃይማኖት ፕሮፌሰር የሆኑት ጆርጅ ቢዩካነን እንዲህ ብለዋል፦ “ግምታዊ በሆኑ ሐሳቦች ላይ ማተኮር አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ቃሉን እንዳያጠና እንቅፋት ይሆንበታል።” ይህ አስተያየት ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ለጢሞቴዎስ ከሰጠው ምክር ጋር ይስማማል፦ “ለተረትና መጨረሻ ለሌለው የትውልዶች ታሪክ ራሳቸውን አሳልፈው እንዳይሰጡ እዘዛቸው። እነዚህ ነገሮች በእምነት ከሆነው ከእግዚአብሔር ሥራ ይልቅ ክርክርን ያነሣሣሉ።”—1 ጢሞቴዎስ 1:4

ወንጌሎች እምነት የሚጣልባቸው ናቸው። እነዚህ መጻሕፍት የዓይን ምሥክሮች የዘገቧቸውን እውነተኛ ታሪኮች ይዘዋል። እነዚህ ወንጌሎች ጥልቅ ምርምር የተደረጉባቸው ሲሆኑ የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወትን አስመልክቶ በርካታ አስደናቂ መረጃዎችን ይሰጡናል። በመሆኑም በጥንት ዘመን ይኖር የነበረው ጢሞቴዎስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም “በተማርኸውና በተረዳኸው ጽና” የሚለውን የጳውሎስን ምክር በተግባር እናውላለን። አራቱን ወንጌሎች ጨምሮ “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው” መሆናቸውን አምነን ለመቀበል የሚያስችል ጠንካራ ምክንያት አለን።—2 ጢሞቴዎስ 3:14-17

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

 ማርቆስ ወንጌሉን ባይጽፍ ኖሮ ስለሚከተሉት ነገሮች አናውቅም ነበር፦

ኢየሱስ በልባቸው ደንዳናነት አዝኖ በዙሪያው የቆሙትን በቁጣ እንደተመለከታቸው (ማርቆስ 3:5)

ዮሐንስና ያዕቆብ ቦአኔርጌስ ተብለው መጠራታቸውን (ማርቆስ 3:17)

ደም ሲፈሳት የኖረችው ሴት ያላትን ሁሉ መጨረሷን (ማርቆስ 5:26)

ሄሮድያዳ በመጥምቁ ዮሐንስ ላይ ቂም እንደያዘችበት እንዲሁም ሄሮድስ ዮሐንስን ይፈራውና ይጠብቀው እንደነበር (ማርቆስ 6:19, 20)

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ጥቂት እንዲያርፉ እንደነገራቸው (ማርቆስ 6:31)

ፈሪሳውያን እጃቸውን እስከ ክርናቸው ድረስ ይታጠቡ እንደነበር (ማርቆስ 7:2-4 NW)

ኢየሱስ ሕፃናቱን እንዳቀፋቸው (ማርቆስ 10:16)

ኢየሱስ ወጣት አለቃውን እንደወደደው (ማርቆስ 10:21)

ኢየሱስን ጥያቄ የጠየቁት ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስና እንድርያስ እንደነበሩ (ማርቆስ 13:3)

አንድ ወጣት ግልድሙን ጥሎ እንደሸሸ (ማርቆስ 14:51, 52)

ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ከተናገራቸው ምሳሌዎች አንዱና ከፈጸማቸው ተአምራት ሁለቱ የሚገኙት በማርቆስ መጽሐፍ ላይ ብቻ ነው።—ማርቆስ 4:26-29፤ 7:32-37፤ 8:22-26

የማርቆስ ወንጌል በሌሎች ወንጌሎች ላይ የማይገኙ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃዎችንም ይዟል። በእነዚህ ሐሳቦች ላይ ጊዜ ወስደን ስናሰላስል ለዚህ መጽሐፍ ያለን አድናቆት እንደሚጨምር ጥርጥር የለውም።