በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘አምላክን ምሰሉ’

‘አምላክን ምሰሉ’

 ወደ አምላክ ቅረብ

‘አምላክን ምሰሉ’

ኤፌሶን 4:32 እስከ 5:2

ደግነት፣ ርኅራኄ፣ ይቅር ባይነትና ፍቅር። በዛሬው ጊዜ እንዲህ የመሰሉ ባሕርያትን የሚያሳዩ ሰዎች ጥቂት መሆናቸው የሚያሳዝን ነው። አንተስ እንዲህ ያሉትን ባሕርያት ታንጸባርቃለህ? እነዚህን ግሩም ባሕርያት ለማዳበር የምታደርገው ጥረት ከንቱ እንደሆነ ይሰማሃል? ራስህን የመውቀስ ዝንባሌ ካለህ፣ ያለብህን ሥር የሰደደ መጥፎ ልማድ ወይም ያሳለፍከውን አሳዛኝ ሕይወት አሊያም እነዚህን የመሳሰሉ አንዳንድ እንቅፋቶችን በማሰብ ቀደም ሲል የተገለጹትን ግሩም ባሕርያት ማዳበር እንደማትችል ሆኖ ሊሰማህ ይችላል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፈጣሪያችን መልካም የሆኑ ባሕርያትን ለማዳበር የሚያስችል አቅም እንዳለን የሚያውቅ መሆኑን በመግለጽ ያበረታታናል።

የአምላክ ቃል እውነተኛ ክርስቲያኖችን ‘እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች አምላክን ምሰሉ’ በማለት ይመክራቸዋል። (ኤፌሶን 5:1) እነዚህ ግሩም ቃላት አምላክ በአገልጋዮቹ እንደሚተማመን ያሳያሉ። እንዴት? ይሖዋ አምላክ ሰውን የፈጠረው በመልኩ ወይም በአምሳሉ ነው። (ዘፍጥረት 1:26, 27) በመሆኑም አምላክ ለሰው ልጆች የእሱን ባሕርያት የማንጸባረቅ ችሎታ ሰጥቷቸዋል። * ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖችን ‘አምላክን የምትመስሉ ሁኑ’ ብሎ ሲመክራቸው፣ ይሖዋ እንደሚከተለው ያላቸው ያህል ነው፦ ‘በእናንተ እተማመናለሁ። ፍጹማን ባትሆኑም በተወሰነ ደረጃ እኔን መምሰል እንደምትችሉ እርግጠኛ ነኝ።’

ልናንጸባርቃቸው ከምንችላቸው የአምላክ ባሕርያት መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? በኤፌሶን 5:1 ዙሪያ ያለው ሐሳብ መልሱን ይሰጠናል። ጳውሎስ፣ አምላክን እንድንመስል የሰጠውን ምክር የጀመረው “እንግዲህ” በሚለው ቃል መሆኑ ልብ ሊባል ይገባዋል። ይህ ቃል ደግነትን፣ ርኅራኄንና ይቅር ባይነትን አስመልክቶ ከሚናገረው ቀደም ሲል ከተጠቀሰው ሐሳብ ጋር ለማያያዝ ተብሎ የገባ ነው። (ኤፌሶን 4:32፤ 5:1) ጳውሎስ፣ አምላክን እንድንመስል ከሰጠው ምክር ቀጥሎ በሚገኘው ጥቅስ ላይ ክርስቲያኖች ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር እንዳላቸው በሚያሳይ መንገድ መኖር እንዳለባቸው ገልጿል። (ኤፌሶን 5:2) ደግነት፣ ርኅራኄና ፍቅር በማሳየት ብሎም ሌሎችን በነፃ ይቅር በማለት ረገድ ልንኮርጀው የሚገባ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ይሖዋ አምላክ ነው።

አምላክን ለመምሰል መፈለግ ያለብን ለምንድን ነው? ጳውሎስ እንዲህ እንድናደርግ የሚያነሳሳን ምን እንደሆነ ሲገልጽ ‘እንደ ተወደዱ ልጆች አምላክን ምሰሉ’ ብሏል። ይህ እንዴት ልብ የሚነካ ሐሳብ ነው! ይሖዋ እሱን የሚያመልኩትን እንደ ልጆቹ አድርጎ የሚመለከታቸው ከመሆኑም ሌላ ከልብ ይወዳቸዋል። አንድ ትንሽ ልጅ አባቱን ለመምሰል እንደሚሞክር ሁሉ እውነተኛ ክርስቲያኖችም በተቻላቸው መጠን የሰማዩ አባታቸውን ለመምሰል ይጥራሉ።

ይሖዋ፣ እሱን እንድንመስል አያስገድደንም። ከዚህ ይልቅ የመምረጥ ነፃነት በመስጠት እንደሚያከብረን አሳይቷል። በመሆኑም አምላክን መምሰል ወይም አለመምሰል የግል ምርጫ ነው። (ዘዳግም 30:19, 20) ይሁንና አምላካዊ ባሕርያትን የማንጸባረቅ ችሎታ እንዳለህ ፈጽሞ አትዘንጋ። እርግጥ ነው፣ አምላክን ለመምሰል መጀመሪያ የእሱን ባሕርያትና መንገዶች ማወቅ ይኖርብሃል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች፣ የአምላክን ግሩም ባሕርያት በማወቃቸው እሱን ለመምሰል ተገፋፍተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንተም የአምላክን ባሕርያትና መንገዶች እንድታውቅ ይረዳሃል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 ቈላስይስ 3:9, 10 በአምላክ መልክ መፈጠር ሲባል ባሕርያቱን ከማንጸባረቅ ጋር የተያያዘ መሆኑን ይጠቁማል። አምላክን ማስደሰት የሚፈልጉ ሰዎች ‘የፈጣሪውን [የአምላክን] መልክ እንዲመስል የሚታደሰውን አዲሱን ሰው’ እንዲለብሱ ተመክረዋል።