በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህ የአምልኮ ቦታችን ነው

ይህ የአምልኮ ቦታችን ነው

“ለቤትህ ያለኝ ቅንዓት ይበላኛል።”—ዮሐ. 2:17

መዝሙሮች፦ 127, 118

1, 2. (ሀ) ቀደም ባሉት ዘመናት የኖሩት የይሖዋ አገልጋዮች የትኞቹን የአምልኮ ቦታዎች ይጠቀሙ ነበር? (ለ) ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ስለሚገኘው የአምላክ ቤተ መቅደስ ምን አመለካከት ነበረው? (ሐ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

ከጥንት ጀምሮ የአምላክ አገልጋዮች ለንጹሕ አምልኮ የተዘጋጁ ቦታዎች ነበሯቸው። አቤል ለአምላክ መባ ያቀረበው በመሠዊያ ላይ ሊሆን ይችላል። (ዘፍ. 4:3, 4) ኖኅ፣ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብና ሙሴም መሠዊያ አቁመዋል። (ዘፍ. 8:20፤ 12:7፤ 26:25፤ 35:1፤ ዘፀ. 17:15) እስራኤላውያን የይሖዋን መመሪያ በመከተል የማደሪያውን ድንኳን ሠርተዋል። (ዘፀ. 25:8) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ለይሖዋ አምልኮ ቤተ መቅደስ ገነቡ። (1 ነገ. 8:27, 29) አይሁዳውያን ከባቢሎን ግዞት ከተመለሱ በኋላ በምኩራቦች ውስጥ አዘውትረው ይሰበሰቡ ነበር። (ማር. 6:2፤ ዮሐ. 18:20፤ ሥራ 15:21) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ደግሞ በጉባኤ አባላት ቤት ውስጥ ይሰበሰቡ ነበር። (ሥራ 12:12፤ 1 ቆሮ. 16:19) በዛሬው ጊዜም የይሖዋ ሕዝቦች ከእሱ ለመማርና እሱን ለማምለክ በዓለም ዙሪያ በአሥር ሺዎች በሚቆጠሩ የመንግሥት አዳራሾች ውስጥ ይሰበሰባሉ።

2 ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ለነበረው የይሖዋ ቤተ መቅደስ ታላቅ ፍቅር ያለው ከመሆኑም ሌላ በጣም ከፍ አድርጎ ይመለከተው ነበር፤ በመሆኑም አንድ የወንጌል ጸሐፊ “ለቤትህ ያለኝ ቅንዓት በልቶኛል” የሚለው ትንቢት በኢየሱስ ላይ እንደተፈጸመ ገልጿል። (መዝ. 69:9፤ ዮሐ. 2:17) እርግጥ ነው፣ በኢየሩሳሌም ከነበረው ቤተ መቅደስ ጋር በሚመጣጠን ደረጃ “የይሖዋ ቤት” ሊባል የሚችል አንድም የመንግሥት አዳራሽ የለም። (2 ዜና 5:13፤ 33:4) ያም ቢሆን በዘመናችን ያሉትን የአምልኮ ቦታዎች እንዴት ልንጠቀምባቸው እንደሚገባና ለእነዚህ ቦታዎች ሊኖረን የሚገባውን አክብሮት የሚያሳዩ መሠረታዊ ሥርዓቶችን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እናገኛለን። በዚህ ርዕስ ውስጥ ከእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች አንዳንዶቹን እንመረምራለን፤ ይህን ማድረጋችንም ለመንግሥት አዳራሾቻችን ሊኖረን ስለሚገባው አመለካከት እንዲሁም ለአዳራሹ የገንዘብ ድጋፍ ስለ ማድረግና አዳራሹን ስለ መንከባከብ ትምህርት ለማግኘት ያስችለናል። *

ለንጹሕ አምልኮ አክብሮት ማሳየት

3-5. የመንግሥት አዳራሾች ዓላማ ምንድን ነው? ይህስ በዚያ ለሚካሄዱት ስብሰባዎቻችን ያለንን አመለካከት የሚነካው እንዴት ነው?

3 የመንግሥት አዳራሽ በአንድ አካባቢ ለሚካሄደው ንጹሕ አምልኮ ማዕከል ነው። ይሖዋ እኛን በመንፈሳዊ ለመመገብ ካደረጋቸው ዝግጅቶች መካከል በመንግሥት አዳራሾች ውስጥ የሚከናወኑት ሳምንታዊ ስብሰባዎች ይገኙበታል። በድርጅቱ በኩል አስፈላጊ የሆነ መንፈሳዊ ምግብና መመሪያ የሚሰጠን በስብሰባዎቻችን ላይ ነው። ወደ ስብሰባዎች የሚመጡ ሁሉ እንዲህ የሚያደርጉት ይሖዋና ኢየሱስ ስለጋበዟቸው ነው ሊባል ይችላል። “ከይሖዋ ማዕድ” እንድንመገብ ሁልጊዜም ግብዣ ይቀርብልናል፤ ይህ መሆኑ ግን ግብዣውን አቅልለን እንድንመለከተው በፍጹም ሊያደርገን አይገባም።—1 ቆሮ. 10:21

4 ይሖዋ፣ ለአምልኮና እርስ በርስ ለመበረታታት የሚያስችሉን እነዚህ አጋጣሚዎች በጣም አስፈላጊ እንደሆኑ ስለሚያውቅ መሰብሰባችንን ቸል እንዳንል የሚያሳስብ መልእክት ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት እንዲጽፍ አድርጓል። (ዕብራውያን 10:24, 25ን አንብብ።) በማይረባ ምክንያት ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የምንቀር ከሆነ ለይሖዋ አክብሮት እያሳየን ነው ማለት እንችላለን? በሌላ በኩል ግን ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በመዘጋጀትና በሙሉ ልብ ተሳትፎ በማድረግ ለይሖዋና ለዝግጅቱ ምን ያህል አድናቆት እንዳለን ማሳየት እንችላለን።—መዝ. 22:22

5 ለመንግሥት አዳራሹ ይኸውም ለሕንፃውም ሆነ በዚያ ለሚካሄዱት መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ያለን አመለካከት፣ ለእነዚህ ነገሮች ተገቢ አክብሮት እንዳለን የሚያሳይ ሊሆን ይገባል። በዚህ ረገድ ያለን ስሜት፣ ብዙውን ጊዜ በመንግሥት አዳራሹ ምልክት ላይ ለሚጻፈው የአምላክ ስም ካለን አመለካከት ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ነው ቢባል አትስማማም?—ከ1 ነገሥት 8:17 ጋር አወዳድር።

6. አንዳንዶች ስለ መንግሥት አዳራሾቻችንም ሆነ በዚያ ስለሚሰበሰቡት ሰዎች ምን ተናግረዋል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

6 ለአምልኮ ቦታችን ምን ያህል አክብሮት እንዳለን የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎችም ብዙውን ጊዜ ያስተውላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በቱርክ የሚኖር አንድ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “የመንግሥት አዳራሹ ንጽሕና ብሎም በአግባቡ የተያዘ መሆኑ በጣም አስገረመኝ። በዚያ ያሉት ሰዎች ሥርዓታማ አለባበስ ያላቸውና በፊታቸው ላይ ፈገግታ የሚነበብ ከመሆኑም ሌላ ሞቅ ባለ መንገድ ተቀበሉኝ። ይህም ማረከኝ።” ይህ ሰው በስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘት ጀመረ፤ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ተጠመቀ። በኢንዶኔዥያ በሚገኝ አንድ ከተማ ውስጥ ያለ ጉባኤ፣ አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ሠርቶ ለይሖዋ አምልኮ እንዲወሰን ከማድረጉ በፊት የአካባቢው ባለሥልጣናትና በአቅራቢያው የሚኖሩ ሰዎች አዳራሹን መጥተው እንዲጎበኙት ግብዣ አቀረበ። የከተማው ከንቲባም ግብዣውን ተቀብሎ ተገኘ። ከንቲባው ሕንፃው በጥራት መሠራቱ፣ የሚሰጠው ጥቅም እንዲሁም ውብ የአትክልት ቦታው በጣም አስገረመው። “የአዳራሹ ንጽሕና በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት እንዳላችሁ ያሳያል” ብሏል።

ምግባራችን ለአምላክ አክብሮት እንደሌለን ሊያሳይ ይችላል (አንቀጽ 7, 8ን ተመልከት)

7, 8. በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ሁሉ የትኞቹን ጠቃሚ ማሳሰቢያዎች ሊያስታውሱ ይገባል?

7 ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ለጋበዘን አምላክ አክብሮት እንዳለን ጨዋነት በሚንጸባረቅበት ምግባራችን፣ በአለባበሳችንና በአጋጌጣችን ልናሳይ ይገባል። አክብሮት ካለን ከተለመደው ወጣ ያሉ ነገሮችን ከማድረግም እንቆጠባለን። አንዳንዶች በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ልናሳየው የሚገባውን ተገቢ ምግባር በተመለከተ ከመጠን በላይ ጥብቅ ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ በጣም ልል እንደሚሆኑ ተስተውሏል። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ አገልጋዮቹም ሆነ ተጋባዦች በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ነፃነት እንዲሰማቸው ይፈልጋል። በሌላ በኩል ግን ወደ አዳራሾቻችን የሚመጡ ሰዎች በአለባበሳቸው ግዴለሽ የሚሆኑ፣ ስብሰባ እየተካሄደ በስልክ መልእክት የሚጽፉ፣ የሚያወሩ፣ የሚበሉ፣ የሚጠጡ ወይም የመሳሰሉትን ነገሮች የሚያደርጉ ከሆነ ለስብሰባው አክብሮት እንደጎደላቸው እያሳዩ ነው። በተጨማሪም የመንግሥት አዳራሹ ልጆች የሚሯሯጡበት ወይም የሚጫወቱበት ስፍራ እንዳልሆነ ወላጆቻቸው ሊያስገነዝቧቸው ይገባል።—መክ. 3:1

8 ኢየሱስ በአምላክ ቤተ መቅደስ ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ያካሂዱ በነበሩት ሰዎች በጣም ስለተቆጣ አባርሯቸዋል። (ዮሐ. 2:13-17) የመንግሥት አዳራሾቻችንም ንጹሕ አምልኮ የሚከናወንባቸውና መንፈሳዊ ትምህርት የምናገኝባቸው ቦታዎች ናቸው። በመሆኑም ንግድን ጨምሮ ከመንፈሳዊ ነገሮች ጋር ምንም ግንኙነት የሌለውን ማንኛውንም እንቅስቃሴ በዚያ ማከናወን አይኖርብንም።—ከነህምያ 13:7, 8 ጋር አወዳድር።

የመንግሥት አዳራሾችን መገንባትና የገንዘብ መዋጮ ማድረግ

9, 10. (ሀ) አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾች የሚገነቡትና ለግንባታው የሚያስፈልገው ገንዘብ የሚገኘው እንዴት ነው? ምንስ ውጤት ተገኝቷል? (ለ) የመንግሥት አዳራሽ ለመገንባት የሚያስችል የገንዘብ አቅም የሌላቸው ጉባኤዎች ከየትኛው ፍቅራዊ ዝግጅት ጥቅም አግኝተዋል?

9 የይሖዋ ድርጅት፣ ብዙ ወጪ የማያስወጡና መጠነኛ የሆኑ የመንግሥት አዳራሾችን ለመገንባት እንዲሁም ለእነዚህ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። ታዲያ ይህ ዝግጅት ምን ውጤት አስገኝቷል? በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ጉባኤዎች ከኅዳር 1, 1999 ወዲህ ከ28,000 በላይ ውብ የሆኑ አዳዲስ የአምልኮ ማዕከሎች ተገንብተዋል። በሌላ አባባል ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ በየዓመቱ በአማካይ በቀን አምስት አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾች ተሠርተዋል።

10 የመንግሥት አዳራሾች በሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች ሁሉ እንዲገነቡ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው። ፍቅር የሚንጸባረቅበት ይህ ዝግጅት የአንዳንዶች ትርፍ የሌሎችን ጉድለት እንዲሸፍን ማድረግን በሚያበረታታው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ላይ የተመሠረተ ነው፤ ይህም “ሸክሙን እኩል [ለመጋራት] ያስችላል።” (2 ቆሮንቶስ 8:13-15ን አንብብ።) በመሆኑም የገንዘብ ድጋፍ ባያገኙ ኖሮ በራሳቸው የመንግሥት አዳራሽ የመገንባት አቅም ለሌላቸው ጉባኤዎች ለንጹሕ አምልኮ የሚውሉ ውብ አዳራሾች ተገንብተውላቸዋል።

11. አንዳንድ ወንድሞች ስለ አዲሱ የመንግሥት አዳራሻቸው ምን ብለዋል? ይህን ስታውቅ ምን ተሰማህ?

11 በኮስታ ሪካ የሚገኝና ከዚህ ዝግጅት የተጠቀመ አንድ ጉባኤ የሚከተለውን ጽፏል፦ “የመንግሥት አዳራሹን ስንመለከት ሕልም እንጂ እውን አይመስለንም! ማመን ከብዶናል። ውብ የሆነው አዳራሻችን ሙሉ በሙሉ ተሠርቶ የተጠናቀቀው በስምንት ቀናት ውስጥ ነው! አዳራሽ ልናገኝ የቻልነው በይሖዋ በረከት፣ በድርጅቱ በኩል ባደረገው ዝግጅት እንዲሁም በውድ ወንድሞቻችን እርዳታ ነው። ይህ የአምልኮ ቦታ በእርግጥም ውድ ስጦታ እንዲሁም ከይሖዋ ያገኘነው ታላቅ ሀብት እንደሆነ ይሰማናል። እጅግ በጣም ተደስተናል።” አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾችን በተመለከተ እንዲህ ያሉ የአድናቆት መግለጫዎችን ስትሰማ እንዲሁም በዓለም ዙሪያ በሺዎች በሚቆጠሩ ቦታዎች የሚኖሩ ወንድሞችም ተመሳሳይ ደስታ እያገኙ እንደሆነ ስታውቅ ልብህ ሐሴት አያደርግም? ይሖዋ ሥራውን እየባረከው እንደሆነ በግልጽ ማየት ይቻላል፤ ምክንያቱም አብዛኛውን ጊዜ አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾች ተሠርተው እንደተጠናቀቁ፣ ስለ አፍቃሪው ፈጣሪያቸው ለማወቅ በሚፈልጉ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ይሞላሉ።—መዝ. 127:1

12. ለመንግሥት አዳራሽ ግንባታ አስተዋጽኦ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

12 በርካታ ወንድሞችና እህቶች በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ መካፈል በመቻላቸው በጣም ተደስተዋል። በግንባታው ሥራ በቀጥታ መሳተፍ ባንችልም እንኳ ሁላችንም ለእነዚህ የግንባታ ፕሮጀክቶች መዋጮ የማድረግ መብት አለን። በጥንት ዘመን የአምላክ አገልጋዮች ለንጹሕ አምልኮ ያላቸው ቅንዓት ቲኦክራሲያዊ ፕሮጀክቶችን በገንዘብ እንዲደግፉ አነሳስቷቸዋል፤ ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው፤ እንዲህ ማድረጋችን ደግሞ ለይሖዋ ክብር ያመጣል።—ዘፀ. 25:2፤ 2 ቆሮ. 9:7

የመንግሥት አዳራሽ ጽዳት

13, 14. የመንግሥት አዳራሻችንን ንጹሕና ሥርዓታማ እንዲሆን ለማድረግ የሚያነሳሱን የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ናቸው?

13 አንድ የመንግሥት አዳራሽ ተገንብቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ የምናመልከውን አምላክ ባሕርያትና ማንነት ይኸውም የሥርዓት አምላክ መሆኑን የሚያንጸባርቅ እንዲሆን በንጽሕና መያዝ አለበት። (1 ቆሮንቶስ 14:33, 40ን አንብብ።) መጽሐፍ ቅዱስ ቅድስናን እንዲሁም መንፈሳዊ ንጽሕናን ከአካላዊ ንጽሕና ጋር ያያይዘዋል። (ራእይ 19:8) በመሆኑም አንድ ሰው በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ከፈለገ ንጽሕናውንም መጠበቅ አለበት።

14 ከእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች አንጻር የአዳራሹ ሁኔታ ከምንሰብከው ምሥራች ጋር የሚስማማ መሆን አለበት፤ ይህም ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ምንጊዜም ወደ ስብሰባዎቻችን ለመጋበዝ ነፃነት እንዲሰማን ያደርጋል። የምንጋብዛቸው ሰዎች አምላካችን ቅዱስ እንደሆነ መመልከት እንዲሁም በቅርቡ ምድርን በመለወጥ ከብክለት የጸዳች ገነት እንደሚያደርጋት መገንዘብ ይችላሉ።—ኢሳ. 6:1-3፤ ራእይ 11:18

15, 16. (ሀ) የመንግሥት አዳራሹን ንጽሕና መጠበቅ ተፈታታኝ እንዲሆን የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል? ይሁንና ንጽሕና አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የጉባኤያችሁ የጽዳት ፕሮግራም ምን ይመስላል? እያንዳንዳችን ምን መብት አለን?

15 አንዳንዶች የጽዳት ጉዳይ ከሌሎች ይበልጥ ያሳስባቸዋል። እነዚህ ሰዎች ምን ያህል ማጽዳት እንዳለባቸው ያላቸው አመለካከት በአስተዳደጋቸው ላይ የተመካ ይሆናል፤ እንዲሁም እንደ ጭቃ፣ አቧራ፣ የመንገዶቹ ሁኔታ፣ በቂ ውኃና የጽዳት ዕቃዎች መኖር ያሉት ነገሮች በጽዳቱ ላይ ተጽዕኖ ያደርጋሉ። በአካባቢው ያለው አመለካከት ወይም ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ የመንግሥት አዳራሾቻችን ንጹሕና ሥርዓታማ በመሆን ረገድ አርዓያ ሊሆኑ ይገባል፤ ምክንያቱም የይሖዋ ስም የሚጠራባቸው ከመሆኑም ሌላ የንጹሕ አምልኮ ማዕከል ናቸው።—ዘዳ. 23:14

16 የመንግሥት አዳራሽ ጽዳት እንዲያው ሲመች ብቻ የሚከናወን ነገር መሆን የለበትም። የሽማግሌዎች አካል፣ የጉባኤው የአምልኮ ቦታ በላቀ ሁኔታ ላይ እንዲገኝ ለማድረግ የጽዳት ፕሮግራም መውጣቱንና በቂ የጽዳት ዕቃዎች መኖራቸውን ማረጋገጥ አለበት። አንዳንድ ነገሮችን ከእያንዳንዱ ስብሰባ በኋላ ማጽዳት የሚያስፈልግ ሲሆን ሌሎች ነገሮችን ደግሞ በየተወሰነ ጊዜ ማጽዳት በቂ ሊሆን ይችላል፤ በመሆኑም ምንም ነገር ችላ እንዳይባል ጥሩ ቅንጅትና ክትትል ያስፈልጋል። ሁሉም የጉባኤው አባላት ይህን ዝግጅት የመደገፍ መብት አላቸው።

የአምልኮ ቦታችንን መንከባከብ

17, 18. (ሀ) ለንጹሕ አምልኮ የምንጠቀምባቸውን ቦታዎች በማደስ ረገድ የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ምሳሌ ይሆኑናል? (ለ) የመንግሥት አዳራሾች በጥሩ ሁኔታ መያዝ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?

17 የይሖዋ አገልጋዮች ለአምልኮ ቦታቸው ተገቢውን እድሳት ለማከናወንም ትጋት የተሞላበት ጥረት ያደርጋሉ። የይሁዳ ንጉሥ ኢዮዓስ ወደ ይሖዋ ቤት የሚመጣውን መዋጮ “በቤቱ ውስጥ የፈረሰውን ሁሉ ለመጠገን [እንዲጠቀሙበት]” ካህናቱን አዝዞ ነበር። (2 ነገ. 12:4, 5) ከ200 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ ንጉሥ ኢዮስያስም የቤተ መቅደሱን መዋጮ በመጠቀም አስፈላጊው እድሳት እንዲካሄድ አድርጓል።2 ዜና መዋዕል 34:9-11ን አንብብ።

18 ቅርንጫፍ ቢሮዎች ሪፖርት እንዳደረጉት በአንዳንድ አገሮች አብዛኛው ሕዝብ ሕንፃዎችን ወይም ዕቃዎችን ለመንከባከብ ትኩረት አይሰጥም። ምናልባትም በእነዚህ አገሮች የጥገና ሙያ ወይም ለሥራው የሚያስፈልጉት ነገሮች ያሏቸው ጥቂቶች ይሆናሉ። ይሁንና የመንግሥት አዳራሾች ጥገና ችላ ከተባለ ሕንፃው አለጊዜው እንደሚያረጅ ግልጽ ነው፤ ይህ ደግሞ ለአካባቢው ሰዎች ጥሩ ምሥክርነት የሚሰጥ አይሆንም። በሌላ በኩል ግን የጉባኤው አባላት የመንግሥት አዳራሹን በጥሩ ሁኔታ ለመያዝ የሚችሉትን ሁሉ ጥረት የሚያደርጉ ከሆነ ይህ ለይሖዋ ክብር ያመጣል፤ እንዲሁም የእምነት ባልንጀሮቻቸው ያዋጡት ገንዘብ እንዳይባክን ያደርጋል።

መንግሥት አዳራሹን ማጽዳትና መንከባከብ ችላ ልንለው የማይገባ ነገር ነው (አንቀጽ 16, 18ን ተመልከት)

19. ለንጹሕ አምልኮ የምንጠቀምባቸውን ቦታዎች በተመለከተ ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?

19 የመንግሥት አዳራሽ ለይሖዋ አምልኮ የተወሰነ ሕንፃ ነው። በመሆኑም የሕንፃው ሕጋዊ ባለቤት ማንም ይሁን ማን፣ አዳራሹ የማንኛውም ግለሰብ አሊያም ጉባኤ ንብረት እንደሆነ ተደርጎ ሊታይ አይገባም። አዳራሹ ለተሠራበት ዓላማ የሚመጥን እንዲሆን የተሟላ ትብብር እንድናደርግ ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ግድ ይሉናል። የጉባኤው አባላት በሙሉ ይህን ዓላማ ለማሳካት አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ፤ ይህን የሚያደርጉት ለአምልኮ ቦታችን ተገቢውን አክብሮት በማሳየት፣ ለአዳዲስ ግንባታዎች ገንዘብ በማዋጣት እንዲሁም ያሉትን የመንግሥት አዳራሾች በአግባቡ ለማጽዳት ብሎም ለመንከባከብ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በፈቃደኝነት በመስጠት ነው። እንዲህ በማድረግ ልክ እንደ ኢየሱስ ለይሖዋ የአምልኮ ቦታ ቅንዓት እንዳለን እናሳያለን።—ዮሐ. 2:17

^ አን.2 ይህ ርዕስ በዋነኝነት የሚያወሳው ስለ መንግሥት አዳራሾች ነው፤ ያም ቢሆን መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ከትላልቅ ስብሰባ አዳራሾችና ለንጹሕ አምልኮ ከምንጠቀምባቸው ሌሎች ቦታዎች ጋር በተያያዘም ይሠራሉ።