በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሥራህን የሚያይልህ ሰው አለመኖሩ ለውጥ ያመጣል?

ሥራህን የሚያይልህ ሰው አለመኖሩ ለውጥ ያመጣል?

ግንባታ ለባስልኤልና ለኤልያብ አዲስ ነገር አልነበረም። በግብፅ ባሪያዎች ሳሉ በጣም ብዙ ጡብ ሠርተው ሊሆን ይችላል። አሁን ግን እነዚያ ዓመታት አልፈዋል። የማደሪያው ድንኳን ሲሠራ ግንባር ቀደም ሠራተኞች እንዲሆኑ ስለተመደቡ ሙያቸውን ለላቀ ዓላማ ሊያውሉት ነው። (ዘፀ. 31:1-11) እንደዚያም ሆኖ ከሠሯቸው አስደናቂ ነገሮች አንዳንዶቹን የሚያዩአቸው ጥቂቶች ብቻ ናቸው። ታዲያ ሥራቸው የማይታይላቸው መሆኑ ያሳዝናቸው ይሆን? ደግሞስ ሥራቸውን ማን ያየዋል የሚለው ጉዳይ ለውጥ ያመጣል? አንተ በዚህ ረገድ ምን ይሰማሃል?

ጥቂቶች ብቻ ያዩት ድንቅ የጥበብ ሥራ

በማደሪያው ድንኳን ውስጥ የነበሩት አንዳንድ ዕቃዎች ድንቅ የእጅ ጥበብ ውጤቶች ናቸው። በቃል ኪዳኑ ታቦት ላይ የሚቀመጡትን የወርቅ ኪሩቦች እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ሐዋርያው ጳውሎስ ኪሩቦቹን “ክብራማ” በማለት ገልጿቸዋል። (ዕብ. 9:5) ከተጠፈጠፈ ወርቅ የተሠሩት እነዚያ ኪሩቦች ምን ያህል ውብ እንደሆኑ እስቲ አስበው!—ዘፀ. 37:7-9

ባስልኤልና ኤልያብ የሠሯቸው ዕቃዎች በዛሬው ጊዜ ቢገኙ ለሕዝብ እንዲታዩ በታላላቅ ሙዚየሞች ውስጥ ተቀምጠው የብዙኃኑን አድናቆት ባተረፉ ነበር። ይሁን እንጂ በተሠሩበት ዘመን ውበታቸውን ያዩ ምን ያህል ሰዎች ነበሩ? ኪሩቦቹ የሚቀመጡት በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ በመሆኑ የሚያያቸው ሊቀ ካህናቱ ብቻ ነበር፤ እሱም ቢሆን ይህን አጋጣሚ የሚያገኘው በዓመት አንድ ጊዜ በስርየት ቀን ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ሲገባ ነው። (ዕብ. 9:6, 7) በዚህም ምክንያት ኪሩቦቹን ያዩዋቸው በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው።

ከሰዎች አድናቆት ባናገኝም በሥራችን መደሰት

በባስልኤል ወይም በኤልያብ ቦታ ብትሆንና እንደዚህ ያሉትን ዕፁብ ድንቅ የጥበብ ሥራዎች ከሠራህ በኋላ የሚያዩዋቸው ጥቂት ሰዎች ብቻ እንደሆኑ ብታውቅ ምን ይሰማህ ነበር? በዛሬው ጊዜ ሰዎች ጥሩ ሥራ እንዳከናወኑ የሚሰማቸው ሌሎች ውዳሴና አድናቆት ሲቸሯቸው ነው። ልፋታቸው ምን ያህል ዋጋ እንዳለው የሚለካው በዚህ እንደሆነ ይሰማቸዋል። የይሖዋ አገልጋዮች ግን አመለካከታቸው ከዚህ የተለየ ነው። እንደ ባስልኤልና ኤልያብ ሁሉ እኛም እርካታ የምናገኘው የይሖዋን ፈቃድ በመፈጸማችንና የእሱን ሞገስ በማግኘታችን ነው።

በኢየሱስ ዘመን፣ የሃይማኖት መሪዎች ሌሎችን የሚያስደምም ጸሎት ማቅረባቸው የተለመደ ነበር። ኢየሱስ ግን ሰዎች ከዚህ የተለየ ነገር እንዲያደርጉ ይኸውም በሌሎች የመወደስ ፍላጎት ሳይኖራቸው ከልብ የመነጨ ጸሎት እንዲያቀርቡ አስተምሯል። ይህን ምክር መከተል ምን ውጤት ያስገኛል? ኢየሱስ “በስውር የሚያይ አባትህም መልሶ ይከፍልሃል” ብሏል። (ማቴ. 6:5, 6) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ስለምናቀርበው ጸሎት ሌሎች ያላቸው አመለካከት ሳይሆን የይሖዋ አመለካከት ነው። ጸሎታችን ትልቅ ዋጋ እንዲኖረው የሚያደርገው የእሱ አመለካከት ነው። በቅዱስ አገልግሎታችን ከምናከናውነው ከማንኛውም ሥራ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ጠቃሚ ሥራ እንደሠራን የሚሰማን ሌሎች ስላወደሱን ሳይሆን ሥራችንን ‘በስውር የሚያየው’ ይሖዋ ስለተደሰተብን ነው።

የማደሪያው ድንኳን ተሠርቶ ሲጠናቀቅ ደመና “የመገናኛ ድንኳኑን ሸፈነው፤ የይሖዋም ክብር የማደሪያ ድንኳኑን ሞላው።” (ዘፀ. 40:34) የመገናኛ ድንኳኑ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኘ የሚያሳይ እንዴት ያለ ግልጽ ምልክት ነው! በዚያ ወቅት ባስልኤልና ኤልያብ ምን የተሰማቸው ይመስልሃል? ምንም እንኳ በሥራዎቻቸው ላይ ስማቸው ባይቀረጽም አምላክ ጥረታቸውን እንደባረከላቸው በማወቃቸው እርካታ ተሰምቷቸው መሆን አለበት። (ምሳሌ 10:22) ከዚያ በኋላ በነበሩት ዓመታትም ሥራቸው ለይሖዋ አገልግሎት እንደዋለ ማየታቸው ልባቸው በደስታ እንዲሞላ እንዳደረገ ጥርጥር የለውም። ባስልኤልና ኤልያብ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ትንሣኤ ሲያገኙ ደግሞ የማደሪያው ድንኳን በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ 500 ለሚያህሉ ዓመታት አገልግሎት እንደሰጠ ማወቃቸው በጣም እንደሚያስደስታቸው ጥርጥር የለውም።

በትሕትና እና በፈቃደኝነት የምታቀርበውን አገልግሎት ማንም ሰው ባያይልህ እንኳ ይሖዋ ያየዋል!

በዛሬው ጊዜም በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የሚያገለግሉት ሙዚቀኞች፣ ሠዓሊዎች፣ ተርጓሚዎች፣ የአኒሜሽን ባለሙያዎች፣ ጸሐፊዎችና ፎቶግራፍ አንሺዎች ሁሉ ስማቸው አይገለጽም። በመሆኑም ሥራቸውን ማንም “አያየውም” ሊባል ይችላል። በመላው ዓለም ከ110,000 በላይ በሆኑት ጉባኤዎች ውስጥ እየተሠራ ያለውን አብዛኛውን ሥራም ቢሆን ማንም አያየውም ማለት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል፣ የሒሳብ አገልጋይ የሆነው ወንድም በወሩ መጨረሻ ላይ የሚያከናውነውን አስፈላጊ ሥራ ማን ያየዋል? የጉባኤው ጸሐፊ የጉባኤውን የመስክ አገልግሎት ሪፖርት ሲያጠናቅር ማን ይመለከተዋል? በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ አስፈላጊውን ጥገና የሚያከናውኑትን ወንድሞችና እህቶችስ ማን ያያቸዋል?

ባስልኤልና ኤልያብ አስደናቂ ንድፍና ጥራት ያለው ሥራ በማከናወናቸው በሕይወታቸው ፍጻሜ ላይ የሚኮሩበት ዋንጫ፣ ኒሻን ወይም ሌላ ሽልማት አልተሰጣቸውም። ያም ቢሆን ከዚህ እጅግ የሚበልጥ ዋጋ ያለው ነገር አግኝተዋል፤ ይኸውም ይሖዋን ደስ አሰኝተውታል። ይሖዋ ሥራቸውን እንዳስተዋለው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እኛም በትሕትና እና በፈቃደኝነት የማገልገል መንፈስ ያሳዩትን የእነዚህን ሰዎች ምሳሌ እንከተል።