ዘፀአት 40:1-38

  • የማደሪያ ድንኳኑ ተተከለ (1-33)

  • የይሖዋ ክብር የማደሪያ ድንኳኑን ሞላው (34-38)

40  ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦  “በመጀመሪያው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የማደሪያ ድንኳኑን ይኸውም የመገናኛ ድንኳኑን ትከል።+  የምሥክሩን ታቦት በውስጡ ካስቀመጥክ+ በኋላ ታቦቱን በመጋረጃው ከልለው።+  ጠረጴዛውንም+ ካስገባህ በኋላ በላዩ ላይ የሚቀመጡትን ነገሮች አስተካክለህ አስቀምጥ፤ መቅረዙንም+ አስገብተህ መብራቶቹን+ አብራቸው።  ከዚያም ለዕጣን የሚሆነውን የወርቅ መሠዊያ+ ከምሥክሩ ታቦት በፊት አስቀምጠው፤ ለማደሪያ ድንኳኑ መግቢያ የሚሆነውን መከለያም* በቦታው አድርገው።+  “የሚቃጠል መባ የሚቀርብበትን መሠዊያም+ በማደሪያ ድንኳኑ ይኸውም በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ፊት አድርገው፤  ገንዳውንም በመገናኛ ድንኳኑና በመሠዊያው መካከል አድርገህ ውኃ ጨምርበት።+  በመገናኛ ድንኳኑም ዙሪያ ግቢ ከልልለት፤+ ለግቢውም መግቢያ መከለያ*+ አድርግለት።  የማደሪያ ድንኳኑም የተቀደሰ እንዲሆን የቅብዓት ዘይቱን+ ወስደህ ድንኳኑንና በውስጡ ያሉትን ነገሮች በሙሉ ትቀባቸዋለህ፤+ ድንኳኑንም ሆነ ዕቃዎቹን በሙሉ ትቀድሳለህ። 10  የሚቃጠል መባ የሚቀርብበትም መሠዊያ እጅግ ቅዱስ እንዲሆን መሠዊያውንና ዕቃዎቹን በሙሉ ትቀባቸዋለህ፤ መሠዊያውንም ትቀድሳለህ።+ 11  ገንዳውንና ማስቀመጫውንም ቀባ፤ ቀድሰውም። 12  “ከዚያም አሮንንና ወንዶች ልጆቹን ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያ አቅርባቸው፤ በውኃም እጠባቸው።+ 13  አሮንንም ቅዱስ የሆኑትን ልብሶች ካለበስከው+ በኋላ ቀባው፤+ እንዲሁም ቀድሰው፤ እሱም ካህን ሆኖ ያገለግለኛል። 14  ከዚያም ወንዶች ልጆቹን አቅርበህ ረጃጅሞቹን ቀሚሶች አልብሳቸው።+ 15  ካህናት ሆነውም እንዲያገለግሉኝ አባታቸውን እንደቀባኸው ሁሉ እነሱንም ቀባቸው፤+ መቀባታቸውም ክህነታቸው ለትውልዶቻቸው ሁሉ በዘላቂነት እንዲቀጥል ያስችላል።”+ 16  ሙሴም ይሖዋ ባዘዘው መሠረት አደረገ።+ ልክ እንደዚሁ አደረገ። 17  በሁለተኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የማደሪያ ድንኳኑ ተተከለ።+ 18  ሙሴም የማደሪያ ድንኳኑን ሲተክል መሰኪያዎቹን+ ከሥር በማስቀመጥ አራት ማዕዘን ቋሚዎቹን+ አደረገባቸው፤ አግዳሚ እንጨቶቹንም+ አስገባቸው፤ ዓምዶቹንም አቆማቸው። 19  ከዚያም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት የማደሪያ ድንኳኑን በድንኳኑ ጨርቅ አለበሰው፤+ በላዩም ላይ የድንኳኑን መደረቢያ ደረበበት።+ 20  ቀጥሎም የምሥክሩን ጽላቶች+ ወስዶ በታቦቱ+ ውስጥ አስቀመጣቸው፤ የታቦቱንም መሎጊያዎች+ አስገባቸው፤ መክደኛውንም+ በታቦቱ ላይ አደረገው።+ 21  ከዚያም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ታቦቱን ወደ ማደሪያ ድንኳኑ አስገባው፤ የመግቢያው መከለያ የሆነውን መጋረጃ+ በቦታው በማድረግ የምሥክሩን ታቦት ከለለው።+ 22  በመቀጠልም ጠረጴዛውን+ በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ በስተ ሰሜን በኩል ባለው የማደሪያ ድንኳኑ ጎን ከመጋረጃው ውጭ አደረገው፤ 23  በላዩም ላይ ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት የተነባበረውን ኅብስት በይሖዋ ፊት አስቀመጠ።+ 24  መቅረዙንም+ በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ ከጠረጴዛው ትይዩ፣ በስተ ደቡብ በኩል ባለው የማደሪያ ድንኳኑ ጎን አስቀመጠው። 25  ከዚያም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት መብራቶቹን+ በይሖዋ ፊት አበራቸው። 26  የወርቅ መሠዊያውንም+ በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ ከመጋረጃው በፊት አስቀመጠው፤ 27  ይህን ያደረገውም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ጥሩ መዓዛ ያለው ዕጣን+ እንዲጨስበት+ ነው። 28  ቀጥሎም የማደሪያ ድንኳኑን መግቢያ መከለያ*+ በቦታው አደረገው። 29  ከዚያም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት የሚቃጠለውን መባና የእህሉን መባ በላዩ ላይ እንዲያቀርብበት የሚቃጠል መባ የሚቀርብበትን መሠዊያ+ በማደሪያ ድንኳኑ ይኸውም በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ አደረገው። 30  በመቀጠልም ገንዳውን በመገናኛ ድንኳኑና በመሠዊያው መካከል አደረገው፤ ለመታጠቢያ የሚሆን ውኃም ጨመረበት።+ 31  ሙሴ እንዲሁም አሮንና ወንዶች ልጆቹ እጃቸውንና እግራቸውን ታጠቡበት። 32  ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ወደ መገናኛ ድንኳኑ በሚገቡበትና ወደ መሠዊያው በሚቀርቡበት ጊዜ ሁሉ ይታጠቡ ነበር።+ 33  በመጨረሻም በማደሪያ ድንኳኑና በመሠዊያው ዙሪያ ግቢውን ከለለ፤+ ለግቢውም መግቢያ መከለያ* አደረገለት።+ በዚህ መንገድ ሙሴ ሥራውን አጠናቀቀ። 34  ደመናውም የመገናኛ ድንኳኑን ሸፈነው፤ የይሖዋም ክብር የማደሪያ ድንኳኑን ሞላው።+ 35  ደመናው በመገናኛ ድንኳኑ ላይ አርፎ ስለነበርና የይሖዋም ክብር የማደሪያ ድንኳኑን ስለሞላው ሙሴ ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግባት አልቻለም ነበር።+ 36  እስራኤላውያንም በጉዟቸው ወቅት ሁሉ ደመናው ከማደሪያ ድንኳኑ ላይ በሚነሳበት ጊዜ ድንኳናቸውን ነቅለው ይንቀሳቀሱ ነበር።+ 37  ሆኖም ደመናው ካልተነሳ፣ ደመናው እስከሚነሳበት ቀን ድረስ ድንኳናቸውን ነቅለው አይንቀሳቀሱም ነበር።+ 38  መላው የእስራኤል ቤት በሚጓዝበት ወቅት ሁሉ ቀን ቀን የይሖዋ ደመና፣ ሌሊት ሌሊት ደግሞ እሳት በማደሪያ ድንኳኑ ላይ ሆኖ ያይ ነበር።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “መጋረጃም።”
ወይም “መጋረጃ።”
ወይም “መጋረጃ።”
ወይም “መጋረጃ።”