ዘፀአት 31:1-18

  • በአምላክ መንፈስ የተሞሉ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች (1-11)

  • በአምላክና በእስራኤላውያን መካከል ምልክት የሆነው ሰንበት (12-17)

  • ሁለቱ የድንጋይ ጽላቶች (18)

31  ይሖዋ እንዲህ በማለት ሙሴን ማነጋገሩን ቀጠለ፦  “እንግዲህ እኔ ከይሁዳ ነገድ የሆነው የሁር ልጅ ዖሪ+ የወለደውን ባስልኤልን+ መርጬዋለሁ።*  ደግሞም ጥበብ፣ ማስተዋልና እውቀት በመስጠት በማንኛውም ዓይነት የእጅ ሙያ የተካነ እንዲሆን በአምላክ መንፈስ እሞላዋለሁ፤  ይህን የማደርገው የተለያዩ ንድፎችን እንዲያወጣ፣ በወርቅ፣ በብርና በመዳብ የተለያዩ ነገሮችን እንዲሠራ፣  ፈርጥ የሚሆኑትን ድንጋዮች እንዲቀርጽና በቦታቸው እንዲያስቀምጥ+ እንዲሁም ከእንጨት ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን እንዲሠራ ነው።+  በተጨማሪም ከዳን ነገድ የሆነውን የአሂሳማክን ልጅ ኤልያብን+ ረዳት እንዲሆነው መርጬዋለሁ፤ እኔ ያዘዝኩህን የሚከተሉትን ነገሮች በሙሉ እንዲሠሩ ጥሩ ችሎታ* ባላቸው ሰዎች ሁሉ ልብ ውስጥ ጥበብን አኖራለሁ፦+  የመገናኛ ድንኳኑን፣+ የምሥክሩን ታቦትና+ በላዩ ላይ ያለውን መክደኛ፣+ የድንኳኑን ዕቃዎች በሙሉ፣  ጠረጴዛውንና+ ዕቃዎቹን፣ ከንጹሕ ወርቅ የሚሠራውን መቅረዝና ዕቃዎቹን በሙሉ፣+ የዕጣን መሠዊያውን፣+  የሚቃጠል መባ የሚቀርብበትን መሠዊያና+ ዕቃዎቹን በሙሉ፣ መታጠቢያ ገንዳውንና መቆሚያውን፣+ 10  ጥሩ ሆነው የተሸመኑትን ልብሶች፣ የካህኑን የአሮንን ቅዱስ ልብሶች፣ ወንዶች ልጆቹ ካህናት ሆነው ሲያገለግሉ የሚለብሷቸውን ልብሶች፣+ 11  የቅብዓት ዘይቱንና ለመቅደሱ የሚሆነውን ጥሩ መዓዛ ያለው ዕጣን።+ ማንኛውንም ነገር ልክ እኔ ባዘዝኩህ መሠረት ይሠሩታል።” 12  በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 13  “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘እናንተን የምቀድሳችሁ እኔ ይሖዋ መሆኔን እንድታውቁ የሚያደርግ፣ በትውልዶቻችሁ ሁሉ በእኔና በእናንተ መካከል ያለ ምልክት ስለሆነ በተለይ ሰንበቴን ማክበር አለባችሁ።+ 14  ለእናንተ የተቀደሰ ስለሆነ ሰንበትን አክብሩ።+ ሰንበትን የሚያረክስ ሰው ይገደል። ማንም ሰው በዚያ ቀን ሥራ ቢሠራ ያ ሰው* ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ መደረግ አለበት።+ 15  ስድስት ቀን ሥራ መሥራት ይቻላል፤ ሰባተኛው ቀን ግን ሙሉ በሙሉ የሚታረፍበት ሰንበት ነው።+ ለይሖዋ የተቀደሰ ነው። በሰንበት ቀን ሥራ የሚሠራ ማንም ሰው ይገደል። 16  እስራኤላውያን ሰንበትን መጠበቅ አለባቸው፤ በትውልዶቻቸው ሁሉ ሰንበትን ማክበር አለባቸው። ይህ ዘላቂ ቃል ኪዳን ነው። 17  በእኔና በእስራኤል ሕዝብ መካከል ያለ ዘላለማዊ ምልክት ነው፤+ ምክንያቱም ይሖዋ ሰማያትንና ምድርን በስድስት ቀናት ውስጥ ሠርቶ በማጠናቀቅ ሥራውን ያቆመውና ያረፈው በሰባተኛው ቀን ነው።’”+ 18  በሲና ተራራ ላይ ከእሱ ጋር ተነጋግሮ እንደጨረሰ የምሥክሩን ሁለት ጽላቶች+ ይኸውም በአምላክ ጣት+ የተጻፈባቸውን የድንጋይ ጽላቶች ለሙሴ ሰጠው።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “በስም ጠርቼዋለሁ።”
ቃል በቃል “ጥበበኛ ልብ።”
ወይም “ነፍስ።”