በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛ ትሕትናን አዳብሩ

እውነተኛ ትሕትናን አዳብሩ

እውነተኛ ትሕትናን አዳብሩ

“ትሑቶችን ታድናለህ።”2 ሳሙኤል 22:28 የ1980 ትርጉም

1, 2. ብዙዎቹ የዓለም መንግሥታት ምን የሚያመሳስላቸው ነገር አለ?

 የግብፅ ፒራሚዶች በአንድ ወቅት የዚያች አገር ገዢዎች ስለነበሩት ሰዎች ማንነት ይገልጻሉ። የአሦር ንጉሥ ሰናክሬብ፣ የግሪክ ንጉሥ ታላቁ እስክንድርና የሮም ንጉሥ ጁሊየስ ቄሣርም በታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ከነበራቸው መሪዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። እነዚህ ነገሥታት በሙሉ አንድ የሚያመሳስላቸው ነገር አለ። አንዳቸውም ቢሆኑ እውነተኛ ትሕትና እንደነበራቸው የሚያሳይ ታሪክ አልተዉም።—ማቴዎስ 20:25, 26

2 ከላይ ከተገለጹት ነገሥታት ማንኛቸውም ቢሆኑ በግዛታቸው ውስጥ ካሉት ሰዎች መካከል መጽናኛ የሚያሻቸው ችግረኛ ሰዎችን የመፈለግ ልማድ የነበራቸው ይመስልሃል? በፍጹም አያደርጉትም! የተጨቆኑ ሰዎችን ለማበረታታት ደሳሳ ወደሆነው ጎጆአቸው ለመሄድም ቢሆን ጨርሶ አያስቡም። እነዚህ ነገሥታት ዝቅተኛ ኑሮ ላላቸው ሰዎች ያላቸው አመለካከት የአጽናፈ ዓለም ገዢ ከሆነው ከይሖዋ አምላክ ፈጽሞ የተለየ ነው!

ታላቁ የትሕትና ምሳሌ

3. የአጽናፈ ዓለሙ ገዢ ሰብዓዊ አገልጋዮቹን የሚይዛቸው እንዴት ነው?

3 የይሖዋ ታላቅነት ፈጽሞ የማይመረመር ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ “በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉ” ይላል። (2 ዜና መዋዕል 16:9) ይሖዋ በተለያዩ መከራዎች የተነሳ መንፈሳቸው የተደቆሰ ችግረኛ አምላኪዎቹን ሲያገኝ ምን ያደርጋል? “የተዋረዱትን መንፈሳቸውን ለማነሣሣት፣ የተሰበረ ልብ ያላቸውን ለማነቃቃት” ሲል በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት ከእነርሱ ጋር ‘ይኖራል።’ (ኢሳይያስ 57:15) በመሆኑም አምላኪዎቹ መንፈሳቸው ታድሶ እርሱን በደስታ ማገልገላቸውን ለመቀጠል የሚያስችል የበለጠ ኃይል ይኖራቸዋል። በእርግጥም አምላክ ታላቅ ትሕትና አሳይቷል!

4, 5. (ሀ) መዝሙራዊው ስለ አምላክ አገዛዝ ምን ተሰምቶታል? (ለ) አምላክ “ድኻውን” ለመርዳት “ራሱን ወደ ታች ዝቅ የሚያደርግ” መሆኑ ምን ትርጉም አለው?

4 በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ኃጢአተኛ የሰው ልጆችን ለመርዳት ሲል የይሖዋን ያህል ራሱን ዝቅ ያደረገ ማንም የለም። በመሆኑም መዝሙራዊው እንዲህ ብሎ ለመጻፍ ችሏል:- “እግዚአብሔር ከሕዝቦች ሁሉ በላይ ከፍ ያለ ነው፤ ክብሩም ከሰማያት በላይ ነው። እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር፣ በላይ በዙፋኑ የተቀመጠ ማን ነው? በሰማይና በምድር ያሉትንስ ለማየት፣ ራሱን ወደ ታች ዝቅ የሚያደርግ ማን ነው? ድኻውን ከትቢያ ያነሣል፤ ችግረኛውን ከዐመድ ከፍ ከፍ ያደርጋል።”—መዝሙር 113:4-7

5 ይሖዋ አምላክ ንጹሕና ቅዱስ በመሆኑ “ትዕቢት” የሚባል ነገር አይታይበትም። (ማርቆስ 7:22, 23) “ራሱን ወደ ታች ዝቅ የሚያደርግ” የሚለው ሐረግ አንድ ግለሰብ በማኅበራዊ ሁኔታ ከእርሱ ወደሚያንስ ሰው ደረጃ ራሱን ዝቅ ማድረጉን አሊያም የበታቹ ከሆነ ሰው ጋር ባለው ግንኙነት ከቦታው ወይም ከማዕረጉ ወረድ ማለቱን ሊያመለክት ይችላል። መዝሙር 113:6 ትሑት የሆነው አምላካችን ፍጹማን ያልሆኑት አምላኪዎቹ የሚያስፈልጋቸውን ለማሟላት የሚያደርገውን ፍቅራዊ እንክብካቤ ግሩም አድርጎ ይገልጻል!—መዝሙር 18:35

ኢየሱስ ትሑት የነበረው ለምንድን ነው?

6. ይሖዋ ታላቅ ትሕትና ያሳየበት ድርጊት የትኛው ነው?

6 አምላክ ለሰው ልጆች መዳን ሲል የሚወደው የበኩር ልጁ ሰው ሆኖ በምድር ላይ እንዲወለድ በማድረግ ታላቅ ትሕትናና ፍቅር አሳይቷል። (ዮሐንስ 3:16) ኢየሱስ በሰማይ ስለሚገኘው አባቱ የሚገልጸውን እውነት ያስተማረን ከመሆኑም በላይ “የዓለምን ኀጢአት” ለማስወገድ ሲል ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል። (ዮሐንስ 1:29፤ 18:37) ትሕትናውን ጨምሮ የአባቱ ፍጹም ነጸብራቅ የነበረው ኢየሱስ፣ አምላክ የጠየቀውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ ነበር። በዚህም ከአምላክ ፍጡራን መካከል ማንም ያላሳየው ታላቅ የትሕትናና የፍቅር ምሳሌ ትቷል። ሆኖም የኢየሱስን ትሕትና ያደነቁት ሁሉም ሰዎች አልነበሩም፤ ጠላቶቹ “ከሰውም የተዋረደ” እንደሆነ አድርገው ቆጥረውታል። (ዳንኤል 4:17 የ1954 ትርጉም) ያም ሆኖ ግን ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልደረቦቹ ኢየሱስን መምሰል እንዳለባቸውና እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ትሑቶች ሊሆኑ እንደሚገባ ተገንዝቦ ነበር።—1 ቆሮንቶስ 11:1፤ ፊልጵስዩስ 2:3, 4

7, 8. (ሀ) ኢየሱስ ትሕትናን የተማረው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ለሚሆኑት ሰዎች ምን ግብዣ አቅርቧል?

7 ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ ሲጽፍ የኢየሱስን ተወዳዳሪ የሌለው ምሳሌነት ጎላ አድርጎ ገልጿል:- “በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን። እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፣ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፣ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፣ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።”—ፊልጵስዩስ 2:5-8 የ1954 ትርጉም

8 አንዳንዶች ‘ኢየሱስ ትሕትናን የተማረው እንዴት ነው?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። ቁጥር ሥፍር ለሌላቸው በርካታ ዓመታት በሰማይ ካለው አባቱ ጋር ተቀራርቦ በመኖሩ ነው፤ በዚህ ወቅት በሁሉም የፍጥረት ሥራዎች ላይ የአምላክ “ዋና ባለሙያ” ሆኖ ሠርቷል። (ምሳሌ 8:30) በዔድን ከተቀሰቀሰው ዓመጽ በኋላ የአምላክ የበኩር ልጅ አባቱ ኃጢአተኛ ከሆኑት የሰው ልጆች ጋር በነበረው ግንኙነት ትሑት እንደነበረ መመልከት ችሏል። በመሆኑም ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የአባቱን ትሕትና ያንጸባረቀ ሲሆን የሚከተለውን ግብዣ አቅርቧል:- “ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ።”—ማቴዎስ 11:29፤ ዮሐንስ 14:9

9. (ሀ) ኢየሱስ ልጆች የሚማርኩት ለምን ነበር? (ለ) ኢየሱስ በአንድ ትንሽ ልጅ አማካኝነት ምን ትምህርት ሰጠ?

9 ኢየሱስ ከልቡ ትሑት ስለነበረ ትንንሽ ልጆች አልፈሩትም። እንዲያውም ከእርሱ ጋር መሆን ይፈልጉ ነበር። እርሱም በበኩሉ ልጆችን ይወድ የነበረ ከመሆኑም በላይ ትኩረት ሰጥቷቸዋል። (ማርቆስ 10:13-16) ኢየሱስ ልጆች የዚህን ያህል የማረኩት ለምን ነበር? ደቀ መዛሙርቱ የሌሏቸውን መልካም ባሕርያት በልጆች ላይ ስለተመለከተ እንደሆነ ግልጽ ነው። ልጆች፣ ትላልቅ ሰዎችን ከእነርሱ እንደሚበልጡ አድርገው እንደሚመለከቷቸው የታወቀ ነው። የሚያነሷቸው በርካታ ጥያቄዎች ለዚህ ማስረጃ ሊሆኑ ይችላሉ። በእርግጥም ከትላልቅ ሰዎች አንጻር ሲታይ ልጆችን ማስተማር ቀላል ከመሆኑም በላይ የኩራት ዝንባሌም አይታይባቸውም። በአንድ ወቅት ኢየሱስ አንድ ትንሽ ልጅ በመካከላቸው አቁሞ ተከታዮቹን እንዲህ አላቸው:- “ካልተለወጣችሁ እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ ፈጽሞ ወደ መንግሥተ ሰማይ አትገቡም። . . . በመንግሥተ ሰማይ ከሁሉ የሚበልጥ እንደዚህ ሕፃን ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ነው።” (ማቴዎስ 18:3, 4) ኢየሱስ “ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ራሱንም ዝቅ ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ከፍ ይላል” የሚል መመሪያ ሰጥቷል።—ሉቃስ 14:11፤ 18:14፤ ማቴዎስ 23:12

10. የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

10 ይህ ሐቅ ትኩረት የሚያሻቸው አንዳንድ ጥያቄዎችን ያስነሳል። የዘላለም ሕይወት ማግኘታችን በተወሰነ መጠን የተመካው እውነተኛ ትሕትናን በማዳበራችን ላይ ነው፤ ታዲያ አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖች ትሑት መሆን የሚያስቸግራቸው ለምንድን ነው? ኩራታችንን ዋጥ አድርገን የሚያጋጥሙንን ችግሮች በትሕትና መወጣት ከባድ የሚሆንብን ለምንድን ነው? እውነተኛ ትሕትናን ለማዳበርስ ምን ሊረዳን ይችላል?—ያዕቆብ 4:6, 10

ትሑት መሆን የሚከብደው ለምንድን ነው?

11. ትሕትናን ለማዳበር ትግል የሚጠይቅብን መሆኑ የማያስገርመው ለምንድን ነው?

11 የትሕትናን ባሕርይ ለማዳበር እየታገልህ ከሆነ ብቻህን አይደለህም። በ1920፣ መጽሐፍ ቅዱስ የትሕትናን አስፈላጊነት አስመልክቶ የሚሰጠውን ምክር የሚያብራራ እንዲህ የሚል ሐሳብ በመጠበቂያ ግንብ ላይ ወጥቶ ነበር:- “ጌታ ለትሕትና ምን ያህል ትልቅ ቦታ እንደሚሰጥ መመልከታችን እውነተኛ ደቀ መዛሙርት በሙሉ ይህንን ባሕርይ በየዕለቱ ለማዳበር ጥረት እንድናደርግ ሊያበረታታን ይገባል።” መጽሔቱ አክሎም እንዲህ በማለት በግልጽ አስፍሯል:- “ቅዱሳን ጽሑፎች ይህን ሁሉ ምክር ቢሰጡንም ፍጹም ባልሆነው ሰብዓዊ ተፈጥሯችን ምክንያት፣ የጌታ ሕዝቦች የሆኑትና በዚህ መንገድ ለመመላለስ ቃል የገቡት ሰዎች ከሌሎች ባሕርያት ይልቅ ይህንን ባሕርይ ማዳበር የበለጠ ትግል የሚጠይቅ ነገር ሆኖባቸዋል።” ይህ አባባል እውነተኛ ክርስቲያኖች ትሕትናን ማዳበር ትግል የሚጠይቅብን ኃጢአተኛ የሆነው ሰብዓዊ ተፈጥሯችን የማይገባንን ክብር ስለሚፈልግ እንደሆነ ይጠቁመናል። ለዚህም ምክንያቱ ለራስ ወዳድነት ምኞታቸው የተሸነፉት የኃጢአተኞቹ ባልና ሚስት ይኸውም የአዳምና የሔዋን ዝርያ መሆናችን ነው።—ሮሜ 5:12

12, 13. (ሀ) ዓለም ክርስቲያኖች ትሕትናን እንዳያዳብሩ እንቅፋት የሚሆንባቸው እንዴት ነው? (ለ) ትሕትናን ለማዳበር የምናደርገውን ጥረት ይበልጥ አስቸጋሪ የሚያደርግብን ማን ነው?

12 ትሕትናን ማሳየት ከባድ እንዲሆንብን የሚያደርገው ሌላው ምክንያት ሰዎች ከሌሎች በልጠው ለመታየት እንዲጥሩ በሚያበረታታ ዓለም ውስጥ የምንኖር መሆኑ ነው። በዚህ ዓለም ላይ ሰዎች ከሚከታተሏቸው የተለመዱ ግቦች መካከል የኃጢአተኛውን “ሥጋ ምኞት [እና] የዐይን አምሮት” ለማርካት የሚደረገው ሩጫ እንዲሁም “የኑሮ ትምክሕት” ይገኙበታል። (1 ዮሐንስ 2:16) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ግን በእነዚህ ዓለማዊ ምኞቶች ከመመራት ይልቅ ጤናማ ወይም ቀላል ዓይን ሊኖራቸውና የአምላክን ፈቃድ ሊያስቀድሙ ይገባል።—ማቴዎስ 6:22-24, 31-33፤ 1 ዮሐንስ 2:17

13 ትሕትናን ማዳበርና ይህንን ባሕርይ ማንጸባረቅ አስቸጋሪ እንዲሆን የሚያደርገው ሦስተኛው ምክንያት የትዕቢት ምንጭ የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ዓለምን የሚገዛ መሆኑ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:4፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:6) ሰይጣን መጥፎ ባሕርያቱን ለማስፋፋት ይጥራል። ለአብነት ያህል፣ ኢየሱስ እርሱን ቢያመልከው በምላሹ “የዓለምንም መንግሥታት ከነክብራቸው” እንደሚሰጠው ነግሮት ነበር። ትሑት የነበረው ኢየሱስ የዲያብሎስን ግብዣ በፍጹም አልተቀበለም። (ማቴዎስ 4:8, 10) በተመሳሳይ ሁኔታ ሰይጣን ክርስቲያኖች ለራሳቸው ክብር እንዲፈልጉ በማነሳሳት ይፈትናቸዋል። ትሑት የሆኑ ክርስቲያኖች ግን በፈተናው ከመውደቅ ይልቅ የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ክብርና ውዳሴ የሚገባው አምላክ እንደሆነ ይገልጻሉ።—ማርቆስ 10:17, 18

እውነተኛ ትሕትናን ማዳበርና በተግባር ማሳየት

14. “ዐጒል ትሕትና” ምንድን ነው?

14 ሐዋርያው ጳውሎስ ለቈላስይስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ሰዎችን ለማስደመም ሲባል ትሑት ለመምሰል የመሞከርን ዝንባሌ እንዲያስወግዱ አስጠንቅቋቸዋል። ጳውሎስ እንዲህ ዓይነቱን ባሕርይ “ዐጒል ትሕትና” በማለት ጠርቶታል። ትሑት እንደሆኑ ለማስመሰል የሚጥሩ ሰዎች መንፈሳዊነት ይጎድላቸዋል። ድርጊታቸውም ቢሆን በትዕቢት ‘ራሳቸውን እንደሚክቡ’ የሚያጋልጥ ነው። (ቈላስይስ 2:18, 23) ኢየሱስ እንደዚህ ያለ ከልብ ያልሆነ ትሕትና ስለሚያሳዩ ሰዎች ተናግሮ ነበር። ፈሪሳውያን ለታይታ የሚያቀርቡትን ጸሎት እንዲሁም በሚጾሙበት ጊዜ ፊታቸውን በማጎሳቆልና ያዘኑ በማስመሰል ሰዎች መጾማቸውን እንዲያውቁላቸው የሚያደርጉትን ጥረት አውግዟል። ከዚህ በተቃራኒ በግላችን የምናቀርባቸው ጸሎቶች በአምላክ ፊት ዋጋ እንዲኖራቸው በትሕትና ሊቀርቡ ይገባል።—ማቴዎስ 6:5, 6, 16

15. (ሀ) ትሕትናን ለማዳበር ምን ማድረግ እንችላለን? (ለ) በትሕትና ረገድ ግሩም አርዓያ ከሚሆኑት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ እነማን ናቸው?

15 ክርስቲያኖች፣ ከሁሉ የላቁ የትሕትና ምሳሌ በሆኑት በይሖዋ አምላክ እና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ትኩረት ማድረጋቸው እውነተኛ ትሕትና ለማዳበር ይረዳቸዋል። ይህም መጽሐፍ ቅዱስንና “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያዘጋጃቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች አዘውትሮ ማጥናትን ይጨምራል። (ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም) ክርስቲያን ሽማግሌዎች ‘ልባቸው በወንድሞቻቸው ላይ እንዳይኮራ’ ጥበቃ ስለሚሆንላቸው እንዲህ ያለው ጥናት በጣም ይጠቅማቸዋል። (ዘዳግም 17:19, 20 የ1954 ትርጉም፤ 1 ጴጥሮስ 5:1-3) የትሕትና ዝንባሌ በማሳየታቸው በተባረኩት እንደ ሩት፣ ሐና እና ኤልሳቤጥ ባሉት ሴቶች እንዲሁም በሌሎች በርካታ ምሳሌዎች ላይ አሰላስል። (ሩት 1:16, 17፤ 1 ሳሙኤል 1:11, 20፤ ሉቃስ 1:41-43) በይሖዋ አገልግሎት በትሕትና የተካፈሉትን እንደ ዳዊት፣ ኢዮስያስ፣ መጥምቁ ዮሐንስና ሐዋርያው ጳውሎስ ያሉ ከፍተኛ ቦታ የነበራቸውን አርዓያ የሚሆኑ ወንዶችም አስብ። (2 ዜና መዋዕል 34:1, 2, 19, 26-28፤ መዝሙር 131:1፤ ዮሐንስ 1:26, 27፤ 3:26-30፤ የሐዋርያት ሥራ 21:20-26፤ 1 ቆሮንቶስ 15:9) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ስለሚገኙት በርካታ ዘመናዊ የትሕትና ምሳሌዎችስ ምን ለማለት ይቻላል? እውነተኛ ክርስቲያኖች በእነዚህ ምሳሌዎች ላይ ማሰላሰላቸው “እርስ በርስ . . . ትሕትና” እንዲያሳዩ ይረዳቸዋል።—1 ጴጥሮስ 5:5

16. ክርስቲያናዊ አገልግሎት ትሕትናን እንድናዳብር የሚረዳን እንዴት ነው?

16 በክርስቲያናዊ አገልግሎት አዘውትሮ መካፈልም ትሕትናን ለማዳበር ሊረዳን ይችላል። ከቤት ወደ ቤት ስንሄድ ወይም በሌሎች ቦታዎች ለምናገኛቸው የማናውቃቸው ሰዎች ስንሰብክ ትሕትና ማሳየታችን ውጤታማ እንድንሆን ይረዳናል። በተለይ ደግሞ የቤቱ ባለቤቶች መጀመሪያ ላይ ለመንግሥቱ መልእክት ግዴለሾች በሚሆኑበት ወይም ጥሩ ምላሽ በማይሰጡበት ጊዜ ይህ ባሕርይ ይረዳናል። አብዛኛውን ጊዜ ስለምናምንባቸው ነገሮች ጥያቄዎች ይነሳሉ፤ ትሕትና አንድ ክርስቲያን “በገርነትና በአክብሮት” መልስ እንዲሰጥ ይረዳዋል። (1 ጴጥሮስ 3:16 የ1980 ትርጉም) ትሑት የሆኑ የአምላክ አገልጋዮች ከዚህ በፊት ወዳልተሰበከባቸው ክልሎች በመሄድ ከእነርሱ የተለየ ባሕልና የኑሮ ደረጃ ያላቸውን ሰዎች ረድተዋል። እነዚህ አገልጋዮች ምሥራቹን የሚሰብኩላቸውን ሰዎች በተሻለ ሁኔታ ለመርዳት ሲሉ አዲስ ቋንቋ መማሩ አስቸጋሪ ቢሆንባቸውም እንኳ ይህን ሁኔታ በትሕትና ተወጥተውታል። ለዚህ ከፍተኛ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል!—ማቴዎስ 28:19, 20

17. ትሑት እንድንሆን የሚጠይቁብን የትኞቹ ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶች ናቸው?

17 ብዙዎች ትሑት በመሆን በርካታ ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶቻቸውን የሚወጡ ሲሆን ይህን ሲያደርጉም ከራሳቸው ይልቅ የሌሎችን ጥቅም ያስቀድማሉ። ለአብነት ያህል፣ አንድ አባት ሊሠራቸው ከሚፈልጋቸው ነገሮች ጊዜውን ዋጅቶ ከልጆቹ ጋር ውጤታማ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግ ሲል መዘጋጀትና ጥናቱን መምራት ትሕትና ይጠይቅበታል። ትሕትና፣ ልጆች ፍጹማን ያልሆኑትን ወላጆቻቸውን እንዲያከብሩና እንዲታዘዙ ያነሳሳቸዋል። (ኤፌሶን 6:1-4) የማያምን ባል ያላቸው ሚስቶች “ንጹሕና ፍጹም አክብሮት የተሞላ[በት]” ባሕርይ በማንጸባረቅ የትዳር ጓደኛቸው እውነትን እንዲቀበል ለመርዳት በሚያደርጉት ጥረት አብዛኛውን ጊዜ ትሕትና እንዲያሳዩ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ይገጥሟቸዋል። (1 ጴጥሮስ 3:1, 2) የታመሙና በዕድሜ የገፉ ወላጆችን በፍቅር በምንንከባከብበት ጊዜም ትሕትናና ከራስ ወዳድነት ነጻ የሆነ ፍቅር ማሳየት በጣም ጠቃሚ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 5:4

ትሕትና ችግሮችን ለመፍታት ይረዳል

18. ትሕትና ችግሮችን ለመፍታት የሚረዳን እንዴት ነው?

18 የአምላክ ሰብዓዊ አገልጋዮች በሙሉ ፍጽምና ይጎድላቸዋል። (ያዕቆብ 3:2) አልፎ አልፎ በሁለት ክርስቲያኖች መካከል የሐሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ምናልባትም አንደኛው ክርስቲያን በሌላው ላይ ቅሬታ እንዲያድርበት የሚያደርገው በቂ ምክንያት ይኖር ይሆናል። ብዙውን ጊዜ የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ እንደዚህ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ይረዳል:- “እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ጌታ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ሌላውን ይቅር በሉ።” (ቈላስይስ 3:13) ይህንን ምክር መከተል ቀላል እንዳልሆነ አይካድም፤ ሆኖም ትሕትና ይህንን ለማድረግ ይረዳናል።

19. የበደለንን ሰው ስናነጋግር የትኛውን ነጥብ ማስታወስ ይኖርብናል?

19 አንዳንድ ጊዜ አንድ ክርስቲያን በጣም እንደተበደለና ሁኔታውን ማለፍ እንደሚከብደው ይሰማው ይሆናል። በዚህ ጊዜም ቢሆን ትሕትና፣ ሰላም ለመፍጠር በማሰብ በደለኝ ያለውን ሰው ቀርቦ እንዲያነጋግረው ይረዳዋል። (ማቴዎስ 18:15) አንዳንድ ጊዜ በክርስቲያኖች መካከል የሚፈጠሩ ችግሮችን መፍታት አስቸጋሪ የሚሆነው አንደኛው ወገን አሊያም ሁለቱም ጥፋተኛ መሆናቸውን እንዳያምኑ ኩራት እንቅፋት ስለሚሆንባቸው ነው። ወይም ደግሞ ሌላኛውን ወገን ቀርቦ ለማነጋገር የተነሳው ወንድም ይህን የሚያደርገው ራሱን ለማመጻደቅ ወይም ወንድሙን ለመኮነን በማሰብ ይሆናል። ከዚህ በተቃራኒ ግን እውነተኛ ትሕትና በርካታ ችግሮችን ለመፍታት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

20, 21. ትሑት ለመሆን የሚረዳን ከሁሉ የላቀው ነገር ምንድን ነው?

20 ትሕትናን ለማዳበር ቁልፉ የአምላክን እርዳታና መንፈሱን ለማግኘት መጸለይ ነው። “እግዚአብሔር . . . ለትሑታን ግን ጸጋን [መንፈስ ቅዱሱንም ጭምር] ይሰጣል” የሚለውን ጥቅስ አስታውስ። (ያዕቆብ 4:6) ስለዚህ ከእምነት ባልንጀራህ ጋር አለመግባባት ከተፈጠረ ይሖዋ ቀላልም ሆኑ ከበድ ያሉ ጥፋቶችህን በትሕትና አምነህ መቀበል እንድትችል እንዲረዳህ ለምነው። ተበድለህ ከሆነና ያጠፋው ሰው ከልቡ “ይቅርታ” ከጠየቀህ ደግሞ ትሑት ሆነህ ይቅር በለው። እንዲህ ማድረግ ከከበደህ በውስጥህ የቀረውን የትዕቢት ዝንባሌ ለማስወገድ እንዲረዳህ ወደ ይሖዋ ጸልይ።

21 ትሕትና የሚያስገኛቸውን በርካታ ጥቅሞች መገንዘባችን ይህንን ውድ ባሕርይ ለማዳበርና በተግባር ለማዋል ጥረት እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል። ለዚህም ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ግሩም አርዓያ ትተውልናል! “ትሕትናና እግዚአብሔርን መፍራት፣ ሀብትን፣ ክብርንና ሕይወትን ያስገኛል” በማለት የተሰጠንን መለኮታዊ ማረጋገጫ ፈጽሞ አትዘንጉ።—ምሳሌ 22:4

ለማሰላሰል የሚረዱ ነጥቦች

• በትሕትና ረገድ ከሁሉ የላቀ አርዓያ የተዉልን እነማን ናቸው?

• ትሕትናን ማዳበር አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው?

• ትሑት እንድንሆን ምን ሊረዳን ይችላል?

• ትሑት መሆን ያን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ከልቡ ትሑት ነበር

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዓለም ሰዎች ከሌሎች በልጠው ለመታየት እንዲጥሩ ያበረታታል

[ምንጭ]

WHO photo by L. Almasi/K. Hemzǒ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ትሕትና በአገልግሎታችን ላይ የማናውቃቸውን ሰዎች ቀርበን ለማነጋገር ይረዳናል

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብዛኛውን ጊዜ ትሑት ሆነን ጉዳዩን በፍቅር መሸፈናችን ልዩነቶችን ለመፍታት ይረዳል

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያኖች ትሕትና የሚያሳዩባቸው በርካታ መንገዶች አሉ