በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ “ቃል” ይጠብቅህ

የይሖዋ “ቃል” ይጠብቅህ

የይሖዋ “ቃል” ይጠብቅህ

በ490 ከክርስቶስ ልደት በፊት በተደረገው ታሪካዊ የማራቶን ጦርነት ላይ ከ10 እስከ 20 ሺህ የሚቆጠረው የአቴና ሠራዊት በቁጥር በጣም ከሚበልጠው የፋርስ ጦር ጋር ውጊያ ገጠመ። ግሪኮች የተጠቀሙበት ዋነኛው የጦር ስልት ፌላንክስ ይባል የነበረ ሲሆን በዚህ የጦር ስልት መሠረት በቡድን ያሉ ወታደሮች በጣም ተጠጋግተው በመሰለፍ ወደ ፊት ይገሰግሳሉ። ገጣጥመው የያዟቸው ጋሻዎቻቸውም እንደማይጣስ የብረት ግድግዳ ይሆኑላቸዋል። በተጨማሪም ወታደሮቹ ጦራቸውን ይሰብቃሉ። አቴናውያን ይህን የጦር ስልት በመጠቀም በቁጥር ብዙ እጥፍ የሚበልጣቸውን የፋርስ ሠራዊት ድል ለማድረግ ችለዋል።

እውነተኛ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ውጊያ ውስጥ ይገኛሉ። የሚዋጉትም ኃይለኛ ከሆኑ ጠላቶቻቸው ማለትም ከማይታዩት የዚህ ክፉ ሥርዓት ገዢዎች ጋር ነው። እነዚህን ጠላቶች መጽሐፍ ቅዱስ ‘የዚህ ጨለማ ዓለም ገዦች እንዲሁም በሰማያዊ ስፍራ ያሉ ርኩሳን መናፍስት ሰራዊት’ ሲል ይጠራቸዋል። (ኤፌሶን 6:12፤ 1 ዮሐንስ 5:19) የአምላክ ሕዝቦች ድል ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፤ ሆኖም እንዲህ ሊያደርጉ የቻሉት በራሳቸው ጥንካሬ አይደለም። መዝሙር 18:30 “የእግዚአብሔር ቃል የነጠረ ነው። መጠጊያ ለሚያደርጉት ሁሉ፣ እርሱ ጋሻ ነው” ስለሚል ለሁሉም ነገር መመስገን ያለበት ከጥቃት እየጋረዳቸውና እያስተማራቸው ያለው ይሖዋ ነው።

አዎን፣ ይሖዋ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በሚገኘው የጠራ ‘ቃሉ’ አማካኝነት ታማኝ አገልጋዮቹን ሊደርስባቸው ከሚችል መንፈሳዊ አደጋ ይጋርዳቸዋል። (መዝሙር 19:7-11፤ 119:93) ሰሎሞን በአምላክ ቃል ውስጥ የተገለጠውን ጥበብ አስመልክቶ “አትተዋት፤ እርሷም ከለላ ትሆንሃለች፤ አፍቅራት፤ እርሷም ትጠብቅሃለች” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 4:6፤ መክብብ 7:12) መለኮታዊ ጥበብ ከጉዳት ሊጠብቀን የሚችለው እንዴት ነው? እስቲ የጥንት እስራኤላውያንን ምሳሌ ተመልከት።

በአምላክ ጥበብ ጥበቃ ያገኘ ሕዝብ

የይሖዋ ሕግ በሁሉም የኑሯቸው ዘርፍ ለእስራኤላውያን ጥበቃና መመሪያ ሆኖላቸዋል። ለምሳሌ ያህል አመጋገብን፣ ንጽሕናንና የታመመ ሰው ከሕዝብ ተገልሎ እንዲቆይ ማድረግን አስመልክቶ የተሰጧቸው ሕጎች ሌሎች ሕዝቦችን ክፉኛ ያጠቁ በሽታዎች በእነርሱ ዘንድ እንዳይዛመቱ አድርገዋል። በዚህ ረገድ ሳይንስ ከአምላክ ሕግ ጋር መስማማት የጀመረው በ19ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ የባክቴርያ መኖር ከተረጋገጠ በኋላ ብቻ ነው። የመሬት ይዞታን፣ መቤዠትን፣ ዕዳ ስረዛንና አራጣ ማበደርን አስመልክቶ የተሰጡት ሕጎች ጠንካራ የኢኮኖሚ አቋም ያለው የተረጋጋ ኅብረተሰብ በማስገኘት የእስራኤልን ማኅበረሰብ ጠቅመዋል። (ዘዳግም 7:12, 15፤ 15:4, 5) ሌላው ቀርቶ የይሖዋ ሕግ የእስራኤላውያን መሬት ለምነቱን እንዳያጣ እርዳታ አበርክቷል። (ዘፀአት 23:10, 11) የሐሰት አምልኮን የሚያወግዙት ሕጎች ሕዝቡ በድን ለሆኑ ጣዖታት መስገድን ከመሰሉ ወራዳ ተግባሮች እንዲታቀብ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ በአጋንንታዊ ተጽዕኖ ሥር ከመውደቅ፣ ልጆቻቸውን መሥዋዕት ከማድረግና እነዚህን የመሰሉ መጥፎ ድርጊቶችን ከመፈጸም በመከላከል መንፈሳዊ ጥበቃ አድርገውላቸዋል።—ዘፀአት 20:3-5፤ መዝሙር 115:4-8

የይሖዋ “ቃል” ለእስራኤላውያን እንዲያው ‘ባዶ ቃል’ እንዳልነበር ግልጽ ነው፤ ከዚህ ይልቅ ቃሉን ለሚጠብቁ ሁሉ ሕይወታቸው አልፎ ተርፎም ረጅም ዘመን ለመኖር የሚያስችላቸው መንገድ ነበር። (ዘዳግም 32:47) ክርስቲያኖች በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር ባይሆኑም እንኳ ዛሬም ቢሆን የይሖዋን ጥበብ አዘል ቃላት ለሚጠብቁ ሁሉ ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። (ገላትያ 3:24, 25፤ ዕብራውያን 8:8) እርግጥ ነው፣ ክርስቲያኖች በጽሑፍ በሰፈረው ሕግ ፋንታ ሊመሩባቸውና ጥበቃ ሊያስገኙላቸው የሚችሉ በርካታ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች አሏቸው።

መሠረታዊ ሥርዓት ጥበቃ የሆነለት ሕዝብ

ሕጎች በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ ያተኮሩ ከመሆናቸውም በላይ ጊዜያዊ ናቸው። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ግን መሠረታዊ እውነቶች እንደመሆናቸው መጠን አብዛኛውን ጊዜ በርካታ ነገሮችን ያካተቱና ዘላቂ ጠቀሜታ ያላቸው ናቸው። ለአብነት ያህል በያዕቆብ 3:17 ላይ የተገለጸውን መሠረታዊ ሥርዓት ተመልከት። ጥቅሱ “ከሰማይ የሆነችው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፤ በኋላም ሰላም ወዳድ” ይላል። ይህ መሠረታዊ እውነት በዛሬው ጊዜ ለሚኖሩ የይሖዋ ሕዝቦች ጋሻ የሆነላቸው እንዴት ነው?

ንጹሕ መሆን ማለት በሥነ ምግባር እንከን የለሽ መሆን ማለት ነው። በመሆኑም ለንጽሕና ላቅ ያለ ግምት የሚሰጡ ሰዎች ከሥነ ምግባር ርኩሰት በተጨማሪ ወደዚህ ችግር ሊመሩ ከሚችሉ፣ ፍትወትን እንደማውጠንጠንና የብልግና ምስሎችን እንደመመልከት ከመሳሰሉ ሁኔታዎች ይርቃሉ። (ማቴዎስ 5:28) በያዕቆብ 3:17 ላይ የተጠቀሰውን ሥርዓት ተግባራዊ የሚያደርጉ ለጋብቻ በመጠናናት ላይ ያሉ ጥንዶች ስሜታቸው ከቁጥጥር ውጪ እንዲሆን ከሚያደርግ ተገቢ ያልሆነ ቅርርብ ይታቀባሉ። በመሠረታዊ ሥርዓቶች ስለሚመሩ ሕግ እስካልጣስን ድረስ ምግባራችን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት አለው ብለው በማሰብ ንጽሕናቸውን የሚያጎድፍ ነገር አያደርጉም። ይሖዋ ‘ልብን እንደሚያይ’ ስለሚያውቁ በአኗኗራቸው ይህን ለማስመስከር ጥረት ያደርጋሉ። (1 ሳሙኤል 16:7፤ 2 ዜና መዋዕል 16:9) እነዚህ ጠቢብ ሰዎች የይሖዋን መመሪያዎች ሥራ ላይ በማዋላቸው ዛሬ በእጅጉ ተስፋፍተው ከሚገኙ በጾታ ግንኙነት ከሚተላለፉ በሽታዎች ተርፈዋል፤ እንዲሁም አእምሯዊና ስሜታዊ ጤንነታቸውም ተጠብቆላቸዋል።

ያዕቆብ 3:17 ከሰማይ የሆነችው ጥበብ “ሰላም ወዳድ” እንደሆነችም ይናገራል። ሰይጣን በልባችን ውስጥ የዓመጸኝነት መንፈስ በመዝራት እኛን ከይሖዋ ለማራቅ እንደሚፈልግ እናውቃለን። ይህን ለማድረግ ከሚጠቀምባቸው ዘዴዎች መካከል አጠያያቂ የሆኑ ጽሑፎች፣ ፊልሞች፣ ሙዚቃዎችና የኮምፒውተር ጨዋታዎች ይገኙበታል። ከእነዚህ ጨዋታዎች ውስጥ አንዳንዶቹ ተጫዋቾቹ ለማመን የሚያዳግት የጭካኔ ድርጊት እንዲፈጽሙና ነፍሰ ገዳይ እንዲሆኑ የሚያነሳሱ ናቸው! (መዝሙር 11:5) ዓመጽና ወንጀል እየተባባሱ መሄዳቸው ሰይጣን በዚህ ረገድ እንደተሳካለት የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ይህን የመሰሉ ወንጀሎችን አስመልክቶ የአውስትራሊያው ዘ ሲድኒ ሞርኒንግ ሄራልድ “ሲሪየል ኪለር” (ልማደኛ ነፍሰ ገዳይ) የተሰኘውን ስያሜ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሙትን ሮበርት ራስለርን በመጥቀስ አንድ ዘገባ አውጥቶ ነበር። ራስለር እንዳሉት በ1970ዎቹ ዓመታት ቃለ መጠይቅ ያደረጉላቸው ነፍሰ ገዳዮች፣ ወንጀል ለመፈጸም የተደፋፈሩት ወሲባዊ ምስሎችን አዘውትረው በመመልከታቸው ነበር። ይሁንና እነዚህ ወሲባዊ ምስሎች “በዘመናችን ካሉት ጋር ሲወዳደሩ ብልግና በግልጽ የሚታይባቸው” አልነበሩም። በመሆኑም ራስለር “የወደፊቱ ጊዜ የብዙዎችን ሕይወት የሚያጠፉ ነፍሰ ገዳዮች እንደ አሸን የሚፈሉበት ተስፋው የጨለመ አዲስ ክፍለ ዘመን” እንደሚሆን ገልጸዋል።

በእርግጥም ይህ ዘገባ ከወጣ ከጥቂት ወራት በኋላ በስኮትላንድ ደንብሌን ከተማ አንድ መሣሪያ የታጠቀ ሰው መዋዕለ ሕፃናት ውስጥ በመግባት 16 ሕፃናትንና አስተማሪያቸውን ከገደለ በኋላ የራሱንም ሕይወት አጥፍቷል። በቀጣዩ ወር በአውስትራሊያ፣ የታዝማኒያ ግዛት ሰላማዊ ከተማ በሆነችው ፖርት አርተር አንድ መሣሪያ የታጠቀ ሰው 32 ሰዎችን ገደለ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ በትምህርት ቤት ውስጥ በሚፈጸሙ በርካታ ግድያዎች ታምሳለች። ይህም ብዙዎቹን አሜሪካውያን ‘ለምን?’ ብለው እንዲጠይቁ አስገድዷቸዋል። በሰኔ 2001 ጃፓን ውስጥ አገሪቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ የመነጋገሪያ ርዕስ ያደረገ አንድ አስደንጋጭ ሁኔታ ተከሰተ። የአእምሮ ችግር ያለበት አንድ ሰው ወደ አንድ ትምህርት ቤት በመግባት የአንደኛና የሁለተኛ ክፍል ተማሪ የሆኑ 8 ልጆችን በስለት ወግቶ ገደለ፤ ሌሎች 15 ሰዎችንም አቆሰለ። ይህን መሰሉ የጭካኔ ድርጊት መንስኤ ውስብስብ እንደሆነ አይካድም። ይሁንና በመገናኛ ብዙኃን የሚታዩ የጭካኔ ድርጊቶች በከፊል አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ እሙን ነው። ፊሊፕ አዳምስ የተባሉ አውስትራሊያዊ የጋዜጣ ዓምድ አዘጋጅ “ለ60 ሴኮንድ የሚቀርብ አንድ የንግድ ማስታወቂያ ገበያውን ማናወጥ ከቻለ ከፍተኛ ገንዘብ የወጣበት የሁለት ሰዓት ፊልም በተመልካቾች አስተሳሰብ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ የማይቀር ነው” ሲሉ ጽፈዋል። የሚገርመው ነገር ፖሊሶች በፖርት አርተር ከሚኖረው መሣሪያ የታጠቀ ነፍሰ ገዳይ ቤት 2,000 የሚያህሉ ዓመጽንና ልቅ ወሲብን የሚያሳዩ የቪዲዮ ፊልሞችን ወርሰዋል።

የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥብቅ የሚከተሉ ሁሉ ለዓመጽ ከሚገፋፋ ማንኛውም ዓይነት መዝናኛ አእምሯቸውንና ልባቸውን ይጠብቃሉ። ስለሆነም ‘የዓለም መንፈስ’ በአስተሳሰባቸውም ሆነ በፍላጎታቸው ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድር አይፈቅዱም። ከዚህ ይልቅ ‘[ከአምላክ] መንፈስ ይማራሉ’ እንዲሁም ሰላምን ጨምሮ ለሌሎች የመንፈስ ፍሬዎች ያላቸውን ፍቅር ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። (1 ቆሮንቶስ 2:12, 13፤ ገላትያ 5:22, 23) ይህንንም የሚያደርጉት አዘውትረው መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት፣ በመጸለይና በማሰላሰል ነው። በተጨማሪም የዓመጸኝነት ዝንባሌ ካላቸው ሰዎች ጋር አይወዳጁም፤ ከዚህ ይልቅ ይሖዋ የሚያመጣውን ሰላም የሰፈነበት አዲስ ዓለም በናፍቆት ከሚጠብቁ ሰዎች ጋር ይቀራረባሉ። (መዝሙር 1:1–3፤ ምሳሌ 16:29) አዎን፣ ከሰማይ የሆነችው ጥበብ ታላቅ ጥበቃ ታደርግልናለች!

የይሖዋ “ቃል” ልብህን ይጠብቅ

ኢየሱስ በበረሃ ውስጥ በተፈተነ ጊዜ የአምላክን ቃል በትክክል በመጥቀስ የሰይጣንን ሐሰተኝነት አጋልጧል። (ሉቃስ 4:1-13) ሆኖም እዚህ ላይ ኢየሱስ ምን ያህል ከፍተኛ የማስተዋል ችሎታ እንዳለው ለማሳየት ከሰይጣን ጋር የቃላት ጦርነት አልገጠመም። በዔድን ውስጥ ስኬታማ የነበረው የሰይጣን ዘዴ በኢየሱስ ላይ ሊሠራ ያልቻለው፣ ኢየሱስ የመከላከያ ሐሳቦቹን በጥቅስ አስደግፎ ከልቡ በመናገሩ ነው። እኛም ልባችንን በይሖዋ ቃል የምንሞላ ከሆነ የሰይጣንን ሽንገላ መቋቋም እንችላለን። ይህን ከማድረግ የበለጠ አስፈላጊ ጉዳይ አይኖርም፤ ምክንያቱም “[ልባችን] የሕይወት ምንጭ ነው።”—ምሳሌ 4:23

ከዚህም በተጨማሪ ሳናቋርጥ ልባችንን መጠበቅ ይገባናል፤ ይህን ለማድረግ ፈጽሞ መታከት አይኖርብንም። ሰይጣን በበረሃ ውስጥ ያደረገው ሙከራ ከከሸፈበት በኋላም ኢየሱስን መፈተኑን አላቆመም። (ሉቃስ 4:13) እኛም አቋማችንን እንድናላላ ለማድረግ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የማያቋርጥ ጥረት ያደርጋል። (ራእይ 12:17) በመሆኑም ለአምላክ ቃል ጥልቅ ፍቅር በማዳበር እንዲሁም ጥበብንና መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት አዘውትረን በመጸለይ የኢየሱስን ምሳሌ እንኮርጅ። (1 ተሰሎንቄ 5:17፤ ዕብራውያን 5:7) ይሖዋም በበኩሉ እሱን መጠጊያ የሚያደርጉትን ሁሉ ከማንኛውም መንፈሳዊ ጉዳት እንደሚጠብቃቸው ቃል ገብቷል።—መዝሙር 91:1-10፤ ምሳሌ 1:33

የይሖዋ ቃል ጉባኤውን ይጠብቃል

ሰይጣን ትንቢት የተነገረለት “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ታላቁን መከራ በሕይወት እንዳያልፍ ሊያግድ አይችልም። (ራእይ 7:9, 14) ያም ሆኖ ሰይጣን አንዳንድ የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት የአምላክን ሞገስ እንዲያጡ ለማድረግ ሲል የክርስቲያኖችን የሥነ ምግባር አቋም ለማበላሸት ይፍጨረጨራል። ይህ ዓይነቱ ዘዴ በጥንት እስራኤላውያን ላይ የሠራ ሲሆን በዚሁም ምክንያት ተስፋይቱ ምድር ለመግባት በተቃረቡበት ወቅት 24,000 የሚያህሉ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። (ዘኍልቍ 25:1-9) እርግጥ ነው፣ ኃጢአት የሠሩ ክርስቲያኖች እውነተኛ ንስሐ እስከገቡ ድረስ መንፈሳዊነታቸውን ለማደስ እንዲችሉ ፍቅራዊ እርዳታ ይደረግላቸዋል። ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን እንደነበረው ዘንበሪ ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ ያልሆኑ ኃጢአተኞች የሌሎችን ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ደህንነት አደጋ ላይ ይጥላሉ። (ዘኍልቍ 25:14) ይህ በፌላንክስ የውጊያ ስልት የሚዋጉ ወታደሮች ጋሻቸውን ቢጥሉ ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን አጋሮቻቸውን ጭምር ለጥቃት ከሚያጋልጡበት ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል።

በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “‘ወንድም ነኝ’ እያለ ከሚሴስን ወይም ከሚስገበገብ ወይም ጣዖትን ከሚያመልክ ወይም ከሚሳደብ ወይም ከሚሰክር ወይም ከሚቀማ ጋር እንዳትተባበሩ ነው፤ ከእንደዚህ ዐይነቱ ሰው ጋር ምግብ እንኳ አትብሉ። . . . ‘ክፉውን ሰው ከመካከላችሁ አስወግዱት’” የሚል ትእዛዝ ይሰጣል። (1 ቆሮንቶስ 5:11, 13) እነዚህ ጥበብ ያዘሉ ‘ቃላት’ የጉባኤውን ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ንጽሕና ይጠብቃሉ ቢባል አትስማማም?

ከዚህ በተቃራኒ በርካታ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናትና ከሃዲዎች ከላይ የተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጊዜ ያለፈባቸው እንዲሁም ከዘመናዊው ነፃ የሥነ ምግባር አስተሳሰብ ጋር የሚቃረኑ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ስለሆነም ቀሳውስቱን ጨምሮ ብዙዎች ከባድ ኃጢአቶችን ሲፈጽሙ በቸልታ ይመለከታሉ። (2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4) ሆኖም ምሳሌ 30:5 የይሖዋ “ቃል” እንደ ጋሻ እንደሆነ ከተናገረ በኋላ ቁጥር 6 ላይ “በእርሱ ቃል ላይ አንዳች አትጨምር፤ አለዚያ ይዘልፍሃል፤ ሐሰተኛም ያደርግሃል” እንደሚል ልብ በል። አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጣመም የሚፈልጉ ሁሉ መንፈሳዊ ውሸታሞች ናቸው። ይህ ደግሞ ከሁሉ የከፋ ውሸት ነው! (ማቴዎስ 15:6-9) ለይሖዋ ቃል ጥልቅ አክብሮት ያለው ድርጅት ውስጥ በመሆናችን በእርግጥ አመስጋኞች መሆን ይገባናል።

“የክርስቶስ መዐዛ” ጥበቃ ሆኖላቸዋል

የአምላክ ሕዝቦች መጽሐፍ ቅዱስን አጥብቀው በመከተልና የያዟቸውን አጽናኝ መልእክቶች ለሌሎች በማካፈል ይሖዋ ደስ የሚሰኝበትን እንደ ዕጣን የሆነውን የሕይወትን “መዐዛ” ያሰራጫሉ። ይሁንና እነዚህ ክርስቲያኖች የሚያሰራጩት ይህ መልእክት ለክፉዎች “ወደ ሞት የሚወስድ የሞት ሽታ” ይሆንባቸዋል። አዎን፣ የክፉዎች ምሳሌያዊ የማሽተት ችሎታ በሰይጣን ሥርዓት ስለተዛባ ‘የክርስቶስን መዐዛ’ የሚያሰራጩ ሰዎች በአቅራቢያቸው መኖራቸው ምቾት ይነሳቸዋል፤ አልፎ ተርፎም የጥላቻ ስሜት ያሳድርባቸዋል። በሌላ በኩል ምሥራቹን በቅንዓት የሚያውጁት ‘በሚድኑት መካከል የክርስቶስ መዐዛ’ ይሆናሉ። (2 ቆሮንቶስ 2:14-16) ብዙውን ጊዜ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የሐሰት ሃይማኖቶች የሚያሳዩትን ግብዝነትና የሚናገሯቸውን ሃይማኖታዊ ውሸቶች ይጸየፋሉ። በመሆኑም የአምላክን ቃል ተጠቅመን የመንግሥቱን መልእክት ስናካፍላቸው ወደ ክርስቶስ ይበልጥ ይቀርባሉ እንዲሁም ተጨማሪ ነገሮችን የማወቅ ጉጉት ያድርባቸዋል።—ዮሐንስ 6:44

አንዳንዶች ለመንግሥቱ መልእክት አሉታዊ ምላሽ ቢሰጡ ተስፋ አትቁረጥ። ከዚህ ይልቅ “የክርስቶስ መዐዛ” ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ክፉ ሰዎች ወደ አምላክ ሕዝቦች መንፈሳዊ ይዞታ እንዳይቀርቡ የሚከላከል፣ ቅን ልብ ያላቸውን ደግሞ የሚማርክ ሽታ በመሆኑ መንፈሳዊ መከላከያ እንደሆነ አድርገህ መመልከት ይኖርብሃል።—ኢሳይያስ 35:8, 9

በማራቶን ጦርነት የግሪክ ወታደሮች አስቸጋሪ ሁኔታ ገጥሟቸው የነበረ ቢሆንም በጣም ተጠጋግተውና ባላቸው ኃይል ሁሉ ጋሻቸውን አጽንተው ይዘው በመዋጋታቸው ድል አድራጊዎች ለመሆን በቅተዋል። በተመሳሳይም የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ባለባቸው መንፈሳዊ ውጊያ የተሟላ ድል እንደሚያገኙ የተረጋገጠ ነው፤ ምክንያቱም ይህ ‘ርስታቸው’ ነው። (ኢሳይያስ 54:17) ስለሆነም እያንዳንዳችን “የሕይወትን ቃል አጥብቀን በመያዝ” ይሖዋን መጠጊያችን ማድረጋችንን እንቀጥል።—ፊልጵስዩስ 2:16 NW

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘ከሰማይ የሆነችው ጥበብ ንጽሕት ናት፤ በኋላም ሰላም ወዳድ’