የይሖዋን ልብ ደስ የሚያሰኙ ወጣቶች

የይሖዋን ልብ ደስ የሚያሰኙ ወጣቶች

የይሖዋን ልብ ደስ የሚያሰኙ ወጣቶች

“ልጄ ሆይ፣ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው፣ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ።”—⁠ምሳሌ 27:11

እነዚህ የጥናት ርዕሶች በተለይ በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ለሚገኙ ወጣቶች የተዘጋጁ ናቸው። ስለሆነም ይህን ርዕስ በጥንቃቄ እንዲያጠኑና በጉባኤ በሚጠናበት ወቅት በነጻነት ሐሳብ እንዲሰጡ እናበረታታቸዋለን።

1, 2. (ሀ) ዓለም የሚያቀርባቸው ነገሮች ማራኪ መስለው ስለታዩህ ብቻ ክርስቲያን ለመሆን አልበቃም ብለህ ማሰብ የሌለብህ ለምንድን ነው? (ሮሜ 7:​21) (ለ) ከአሳፍ ምሳሌ ምን ትምህርት ታገኛለህ? (በገጽ 13 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።)

 ልብስ ለመግዛት ገበያ ወጥተሃል እንበል። ሱቅ ውስጥ ገብተህ እያማተርክ ሳለ ወዲያው ዓይንህ ውስጥ የሚገባ አንድ ልብስ ታያለህ። የልብሱ ቀለምና ስፌት ልክ የምትፈልገው ዓይ​ነት ነው፤ ዋጋውም ውድ አይደለም። ከመግዛትህ በፊት ግን አገላብጠህ አየኸው። በዚህ ጊዜ ኮሌታውና እጅጌው የተበላና ስፌቱም ጥራት የጎደለው እንደሆነ ስታይ ተገረምክ። ልብሱ ሲያዩት ቆንጆ ቢመስልም ጥራት ይጎድለዋል። እንዲህ ያለ መናኛ ልብስ ለመግዛት ገንዘብ ታወጣለህ?

2 ይህን ምሳሌ ክርስቲያን ወጣት በመሆንህ ከሚያጋጥምህ ሁኔታ ጋር ልታዛምደው ትችላለህ። ይህ ዓለም የሚያቀርበው ነገር ላይ ላዩን ሲታይ ልክ እንደ ልብሱ በጣም ማራኪ ይመስል ይሆናል። ለምሳሌ ያህል አብረውህ የሚማሩ ልጆች በየጭፈራ ቤቶች ይዝናኑ፣ ዕፅ ይወስዱ፣ ይጠጡ፣ ተቀጣጥረው ይጫወቱ አልፎ ተርፎም ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ይፈጽሙ ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱ ሕይወት አንዳንድ ጊዜ ያስቀናሃል? እነርሱ ነጻነት የሚሉትን ሕይወት ለማየት ትጓጓለህ? እንዲህ ዓይነት ስሜት ቢመጣብህም እንኳ ክፉ ልብ ስላለኝ ክርስቲያን ለመሆን አልበቃም የሚል መደምደሚያ ላይ ለመድረስ አትቸኩል። ይህ ዓለም አምላክን ደስ ማሰኘት ለሚፈልግ ሰው እንኳ ሳይቀር ማራኪ መስሎ ሊታይ እንደሚችል መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 4:​10

3. (ሀ) ዓለም የሚያቀርባቸውን ነገሮች ማሳደድ ከንቱ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) አንዲት ክርስቲያን ዓለም ከንቱ መሆኑን የገለጸችው እንዴት ነው?

3 ለመግዛት ያሰብከውን ልብስ በጥንቃቄ እንደምትመለከተው ሁሉ ይህ ዓለም የሚያቀርባቸውንም ነገሮች እስቲ በጥሞና ተመልከት። ‘ይህ ሥርዓት ምን ያህል አስተማማኝ ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ዓለም አላፊ’ መሆኑን ይገልጻል። (1 ዮሐንስ 2:​17) ከዚህ ዓለም የሚገኘው ደስታ ሁሉ ጊዜያዊ ነው። ከዚህም በላይ ዓለማዊ አኗኗር የከፋ መዘዝ ስለሚያስከትል ፈጽሞ የሚያዋጣ አይደለም። ‘የወጣትነት ሕይወቷን ያበላሸች አንዲት ልጅ ያሳለፈችውን ስቃይ’ እንዲህ ስትል ገልጻለች:- “ዓለም አስደሳችና ማራኪ መስሎ ይታይ ይሆናል። ምንም ጉዳት ሳይደርስባችሁ ዓለም የሚሰጠውን ደስታ ማግኘት እንደምትችሉ ሊያሳምናችሁ ይፈልጋል። ይህ ግን ፈጽሞ የማይመስል ነገር ነው። ዓለም ይጠቀምባችሁና ሲበቃው ይጥላችኋል።” a የወጣትነት ሕይወታችሁን አልባሌ በሆነ መንገድ ለምን ታሳልፋላችሁ?

‘ከክፉው’ ጥበቃ ማግኘት

4, 5. (ሀ) ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ለይሖዋ ምን ልመና አቅርቧል? (ለ) ያቀረበው ልመና ተገቢ የነበረው ለምንድን ነው?

4 በይሖዋ ምሥክሮች መካከል የሚገኙ ወጣቶች ይህ ሥርዓት አንድም የረባ ነገር እንደሌለው በመገንዘብ የዓለም ወዳጅ ላለመሆን ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። (ያዕቆብ 4:​4) አንተስ ከእነዚህ ታማኝ ወጣቶች መካከል ነህን? ከሆንክ ልትመሰገን ይገባሃል። የእኩዮችን ተጽእኖ መቋቋምና ከእነርሱ የተለየ አቋም መያዝ ቀላል እንደማይሆን የታወቀ ነው። ሆኖም እርዳታ ማግኘት ትችላለህ።

5 ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ይሖዋ ደቀ መዛሙርቱን ‘ከክፉው እንዲጠብቃቸው’ ለምኗል። (ዮሐንስ 17:​15) ኢየሱስ ይህን ልመና ያቀረበበት ጥሩ ምክንያት ነበረው። ተከታዮቹ በየትኛውም ዕድሜ ላይ ቢገኙ ታማኝነትን ጠብቆ መኖር ቀላል እንደማይሆንላቸው ያውቃል። ከባድ የሚያደርገው ምንድን ነው? አንደኛ ነገር ደቀ መዛሙርቱ በዓይን የማይታየው ‘ክፉው’ ሰይጣን ዲያብሎስ ኃይለኛ ጠላታቸው እንደሚሆን ተረድቷል። ይህ ክፉ መንፈሳዊ ፍጡር ‘የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ እንደሚዞር’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።​—⁠1 ጴጥሮስ 5:8

6. ሰይጣን ለወጣቶች እንደማይራራ እንዴት ማወቅ እንችላለን?

6 ሰይጣን በታሪክ ዘመናት ሁሉ በሰው ልጆች ላይ ጭካኔ የሞላባቸው መከራዎችን በማምጣት ሲደሰት ቆይቷል። በኢዮብና በቤተሰቡ ላይ ያደረሰው አሠቃቂ ጥፋት ምሳሌ ሊሆነን ይችላል። (ኢዮብ 1:​13-19፤ 2:​7) ምናልባትም አንተ ራስህ ያየኸው ወይም የሰማኸው የሰይጣን መንፈስ የተንጸባረቀበት አረመኔያዊ ድርጊት ይኖር ይሆናል። የሚውጠውን ፈልጎ የሚዞረው ዲያብሎስ ለወጣቶች ምንም ርኅራኄ የለውም። ለምሳሌ ያህል በመጀመሪያው መቶ ዘመን መባቻ ላይ ሄሮድስ በቤተ ልሔም የሚኖሩ ሁለት ዓመትና ከዚያ በታች የሆናቸውን ወንዶች ልጆች አስገድሏል። (ማቴዎስ 2:​16) ሄሮድስን የገፋፋው ሰይጣን ሊሆን ይችላል፤ ይህም ወደፊት ተስፋ የተገባለት የአምላክ መሲህ የሚሆነውንና በሰይጣን ላይ የአምላክን ፍርድ የሚያስፈጽመውን ልጅ ለማስገደል ያደረገው ጥረት ነበር። (ዘፍጥረት 3:​15) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ሰይጣን ለወጣቶች ቅንጣት ታህል ርኅራኄ የለውም። ዋነኛ ዓላማው በተቻለው መጠን ብዙ ሰዎችን መዋጥ ነው። በተለይ ደግሞ ሰይጣን ከሰማይ ወደ ምድር ሲጣል “ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቊጣ” በመምጣቱ ብዙዎችን ለመዋጥ እንደሚፍጨረጨር እሙን ነው።​—⁠ራእይ 12:9, 12

7. (ሀ) በይሖዋና በሰይጣን መካከል ምን ዓይነት ልዩነት ይታያል? (ለ) ይሖዋ በሕይወትህ እንድትደሰት እንደሚፈልግ የሚያሳየው ምንድን ነው?

7 ‘ቁጡ’ ከሆነው ከሰይጣን በተቃራኒ ይሖዋ “ምሕረትና ርኅራኄ” የሚያሳይ አምላክ ነው። (ሉቃስ 1:​78) ፈጣሪያችን የፍቅር ተምሳሌት ከመሆኑም በላይ ይህን ድንቅ ባሕርይ በሚገባ የሚያንጸባርቅ ስለሆነ መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” ይላል። (1 ዮሐንስ 4:8) በዚህ ሥርዓት አምላክና አንተ በምታመልከው አምላክ መካከል ያለው ልዩነት ምንኛ ሰፊ ነው! የሰይጣን ፍላጎት ሰዎችን መዋጥ ሲሆን ይሖዋ ግን ‘ማንም እንዲጠፋ አይፈልግም።’ (2 ጴጥሮስ 3:​9) የአንተም ሆነ የሌሎች ሰዎች ሕይወት በይሖዋ ፊት እጅግ ክቡር ነው። ይሖዋ የዓለም ክፍል እንዳትሆን በቃሉ አማካኝነት ማሳሰቢያ የሚሰጥህ በሕይወትህ እንዳትደሰት ወይም ነጻነትህን ለመንፈግ አይደለም። (ዮሐንስ 15:​19) እንዲህ የሚያደርገው አንተን ከክፉው ለመጠበቅ ነው። በሰማይ የሚኖረው አባትህ ይህ ዓለም ከሚያስገኘው ቅጽበታዊ ደስታ በጣም የተሻለውን “እውነተኛውን ሕይወት” ይኸውም ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት እንድታገኝ ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 6:​17-19) ይሖዋ እንዲሳካልህ እና እዚህ ግብ ላይ እንድትደርስ ያበረታታሃል። (1 ጢሞቴዎስ 2:​4) ከዚህም በተጨማሪ አንድ ልዩ ግብዣ አቅርቦልሃል። ይህ ግብዣ ምን ይሆን?

‘ልቤን ደስ አሰኘው’

8, 9. (ሀ) ለይሖዋ ምን ዓይነት ስጦታ መስጠት ትችላለህ? (ለ) በኢዮብ ሁኔታ እንደታየው ሰይጣን ይሖዋን የሚሰድበው እንዴት ነው?

8 ለቅርብ ጓደኛህ ስጦታ ገዝተህ ስትሰጠው ከአድናቆትና ከአመስጋኝነት ስሜት የተነሳ ፊቱ በደስታ ሲፈካ ተመልክተህ ታውቃለህ? ለጓደኛዬ ምን ዓይነት ስጦታ ብሰጠው ይሻላል ብለህ ለረጅም ጊዜ አውጥተህ አውርደህ ይሆናል። ለፈጣሪህ ለይሖዋ አምላክ ምን ዓይነት ስጦታ መስጠት ትችላለህ? የሚለውን ጥያቄ አስብበት። መጀመሪያ ላይ ለእርሱ ስጦታ መስጠት የማይመስል ነገር ሆኖ ይታይህ ይሆናል። ሁሉን ቻይ አምላክ ከአንድ ተራ ሰው ምን የሚፈልገው ነገር አለ? ይሄ ይጎድለዋል ብለህ የምትሰጠው ምን ይኖራል? መጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ 27:​11 ላይ “ልጄ ሆይ፣ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው፣ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ” በማለት መልሱን ይሰጣል።

9 ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ እንደተገነዘብከው ይሖዋን የሚሰድበው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። ሰዎች አምላክን የሚያገለግሉት በራስ ወዳድነት ተነሳስተው እንጂ በፍቅር አይደለም በማለት ይከራከራል። ሰይጣን ሰዎች መከራ ከደረሰባቸው ወዲያውኑ እውነተኛውን አምልኮ እርግፍ አድርገው ይተዋሉ ብሎ ይሟገታል። ለምሳሌ ያህል ሰይጣን ጻድቁን ኢዮብን በተመለከተ ለይሖዋ ምን ብሎ እንደተናገረ ተመልከት:- “እርሱንና ቤቱን በዙሪያውም ያሉትን ሁሉ አላጠርህለትምን? የእጁን ሥራ ባርከህለታል፣ ከብቱም በምድር ላይ በዝቶአል። ነገር ግን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ዳብስ፤ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል።”​—⁠ኢዮብ 1:10, 11

10. (ሀ) ሰይጣን የኢዮብን ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ታማኝነት ጥያቄ ላይ እንደጣለ እንዴት ማወቅ እንችላለን? (ለ) ሉዓላዊነትን በተመለከተ በተነሳው ጥያቄ ገለልተኛ መሆን የማትችለው ለምንድን ነው?

10 የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንደሚያሳየው ሰይጣን ጥያቄ ውስጥ የጣለው የኢዮብን ታማኝነት ብቻ ሳይሆን የአንተንም ሆነ የሌሎች የአምላክ አገልጋዮችን ታማኝነት ጭምር ነው። እንዲያውም ሰይጣን መላውን የሰው ዘር በሚመለከት “ሰው [ኢዮብ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ሰው] ያለውን ሁሉ ስለ ሕይወቱ ይሰጣል” በማለት ለይሖዋ ተናግሯል። (ኢዮብ 2:4) ይህ አከራካሪ ጉዳይ አንተንም የሚመለከት እንደሆነ ትገነዘባለህ? በምሳሌ 27:​11 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ ለሚሰድበው ለሰይጣን መልስ መስጠት ይችል ዘንድ ለእርሱ ልታደርግለት የምትችለው ነገር እንዳለ ገልጿል። እስቲ አስበው፣ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ እስከ ዛሬ ከተነሱት አከራካሪ ጉዳዮች ሁሉ በሚበልጠው በዚህ ጉዳይ ላይ መልስ እንድትሰጥ ለአንተም ግብዣ አቅርቦልሃል። እንዴት ያለ ትልቅ ኃላፊነትና መብት አግኝተሃል! ይሖዋ የሚፈልግብህን ማድረግ ትችላለህ? ኢዮብ ለጥያቄው መልስ ሰጥቷል። (ኢዮብ 2:​9, 10) ኢየሱስም ሆነ በርካታ ወጣቶችን ጨምሮ በታሪክ ዘመናት ሁሉ የኖሩ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሌሎች የአምላክ አገልጋዮችም መልስ ሰጥተዋል። (ፊልጵስዩስ 2:​8፤ ራእይ 6:​9) አንተም እንዲሁ ማድረግ ትችላለህ። በዚህ ጉዳይ ላይ ገለልተኛ አቋም መያዝ ይቻላል ብለህ አታስብ። ሰይጣን ለሚሰነዝረው ስድብ ወይም ደግሞ ይሖዋ ለሚያቀርበው መልስ ድጋፍ እንደምትሰጥ በአኗኗርህ ታሳያለህ። ታዲያ የቱን ትመርጣለህ?

ይሖዋ ስለ አንተ ያስባል!

11, 12. ይሖዋን ለማገልገል ወይም ላለማገልገል የምታደርገው ምርጫ በእርሱ ላይ የሚያመጣው ለውጥ ይኖራልን? አብራራ።

11 የምታደርገው ምርጫ ለይሖዋ የሚያመጣው ለውጥ ይኖራልን? ይሖዋ ለሰይጣን አጥጋቢ መልስ መስጠት እንዲችል እስከ ዛሬ ድረስ በታማኝነት ያገለገሉት ሰዎች በቂ አይደሉም? እርግጥ ዲያብሎስ ይሖዋን ከፍቅር ተነሳስቶ የሚያገለግል ሰው አይገኝም በማለት ያነሳው ግድድር ውሸት መሆኑ ተረጋግጧል። ይሁንና ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ለአንተ ስለሚያስብልህ ሉዓላዊነትን በተመለከተ በተነሳው ጥያቄ ከእርሱ ጎን እንድትቆም ይፈልጋል። ኢየሱስ “ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱ እንዲጠፋ በሰማያት ያለው አባታችሁ ፈቃድ አይደለም” በማለት ተናግሯል።​—⁠ማቴዎስ 18:14

12 በግልጽ ማየት እንደሚቻለው የምትመርጠው የሕይወት ጎዳና ይሖዋን ያሳስበዋል። ከዚህም በላይ የምታደርገው ምርጫ በቀጥታ ይመለከተዋል። ሰዎች በሚያደርጉት ጥሩም ሆነ መጥፎ ተግባር የይሖዋ ስሜት በጥልቅ እንደሚነካ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያሳያል። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን በተደጋጋሚ ባመፁበት ጊዜ ይሖዋ ‘አዝኗል።’ (መዝሙር 78:​40, 41) በኖኅ ዘመን ከደረሰው የጥፋት ውኃ በፊት ‘የሰው ክፋት በምድር ላይ በመብዛቱ’ ይሖዋ ‘በልቡ አዝኖ’ ነበር። (ዘፍጥረት 6:​5, 6) ይህ ምን ማለት እንደሆነ ተመልከት። አካሄድህ መጥፎ ከሆነ ፈጣሪህን ታሳዝነዋለህ። እንዲህ ሲባል አምላክ ውስጣዊ ጥንካሬ ይጎድለዋል ወይም ስሜታዊ ነው ማለት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ይወድሃል እንዲሁም ስለ ደኅንነትህ ያስባል። በሌላ በኩል ትክክል የሆነውን ስታደርግ ይሖዋ ደስ ይሰኛል። የሚደሰተው ለሰይጣን መልስ መስጠት የሚያስችለው ተጨማሪ ምክንያት በማግኘቱ ብቻ ሳይሆን አንተንም ለመካስ የሚያስችል አጋጣሚ በማግኘቱ ነው። እንዲህ ማድረግ ያስደስተዋል። (ዕብራውያን 11:​6) ይሖዋ አምላክ ምንኛ አፍቃሪ አባት ነው!

አሁንም የምታገኘው የተትረፈረፈ በረከት

13. ይሖዋን ማገልገል በአሁኑ ጊዜም በረከት የሚያስገኘው እንዴት ነው?

13 ይሖዋን በማገልገላችን ወደፊት ብቻ ሳይሆን አሁንም ቢሆን በረከት እናገኛለን። በይሖዋ ምሥክሮች መካከል የሚገኙ ብዙ ወጣቶች አሁንም እንኳ አስደሳችና አርኪ ሕይወት ይመራሉ። መዝሙራዊው “የእግዚአብሔር ሥርዓት ቅን ነው፣ ልብንም ደስ ያሰኛል” በማለት ለደስታቸው ምክንያት የሆነውን ነገር ገልጿል። (መዝሙር 19:8) ይሖዋ ከማንም በተሻለ የሚበጀንን ያውቃል። በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል እንዲህ ብሏል:- “እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ። ትእዛዜን ብትሰማ ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር።”​—⁠ኢሳይያስ 48:17, 18

14. የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥ እንዳትገባ ሊረዱህ የሚችሉት እንዴት ነው?

14 የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተልህ ከብዙ ሥቃይና ሐዘን ያድንሃል። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ገንዘብ ወዳድ የሆኑ ሰዎች ‘በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን እንደሚወጉ’ ይናገራል። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) ከእኩዮችህ መካከል ገንዘብ ወዳድ በመሆኑ ምክንያት ችግር ላይ የወደቀ አጋጥሞህ አያውቅም? አንዳንድ ወጣት ወንዶችና ሴቶች በጣም ውድ የሆኑ ልብሶችንና ቴክኖሎጂ ያፈራቸውን ዘመናዊ ዕቃዎች ለመግዛት ሲሉ ከባድ ዕዳ ውስጥ ይዘፈቃሉ። አቅምህ የማይፈቅድልህን ዕቃ ለመግዛት ብለህ በረጅም ጊዜ የሚከፈል ወለዱ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ መበደር ለአስከፊ ባርነት ራስን አሳልፎ መሸጥ ነው!​—⁠ምሳሌ 22:​7

15. የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት የጾታ ብልግና ከሚያስከትለው ሥቃይ እንድትጠበቅ የሚያስችልህ እንዴት ነው?

15 የጾታ ብልግናን ጉዳይ ደግሞ ተመልከት። በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ሴቶች ከጋብቻ ውጭ ያረግዛሉ። አንዳንዶቹ የሚወልዱትን ልጅ የማሳደግ ፍላጎቱም ሆነ አቅሙ የላቸውም። ሌሎች ደግሞ ውርጃ ይፈጽሙና ለሕሊና ሥቃይ ይዳረጋሉ። እንደ ኤድስ ባሉ በጾታ ግንኙነት በሚተላለፉ በሽታዎች የሚያዙም ወጣት ወንዶችና ሴቶች አሉ። ይሖዋን ለሚያውቅ ወጣት ግን ከሁሉ የከፋው መዘዝ ከእርሱ ጋር ያለው ዝምድና መበላሸቱ እንደሆነ የታወቀ ነው። b (ገላትያ 5:​19-21) መጽሐፍ ቅዱስ “ከዝሙት ሽሹ” የሚለው ያለምክንያት አይደለም።​—⁠1 ቆሮንቶስ 6:​18

‘ደስተኛውን አምላክ’ ማገልገል

16. (ሀ) ይሖዋ በወጣትነትህ ዘመን እንድትደሰት እንደሚፈልግ እንዴት ማወቅ ትችላለህ? (ለ) ይሖዋ መመሪያ የሚሰጥህ ለምንድን ነው?

16 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ “ደስተኛ አምላክ” እንደሆነ ይናገራል። (1 ጢሞቴዎስ 1:​11 NW ) አንተም ደስተኛ እንድትሆን ይፈልጋል። እንዲያውም ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ “በወጣትነትህ ጊዜ ደስ ይበልህ፤ በወጣትነትህም ዘመን ልብህ ደስ ያሰኝህ” ይላል። (መክብብ 11:​9 አ.መ.ት ) ሆኖም ይሖዋ የወደፊቱን ጊዜ አርቆ ስለሚመለከት የምታደርገው ጥሩም ሆነ መጥፎ ነገር የሚያስከትልብህን የረጅም ጊዜ ውጤት ማየት ይችላል። በዚህም ምክንያት እንዲህ ሲል በጥብቅ ይመክርሃል:- “የጭንቀት ጊዜ ሳይመጣ፣ ‘ደስ አያሰኙኝም’ የምትላቸው ዓመታት ሳይደርሱ፣ በወጣትነትህ ጊዜ፣ ፈጣሪህን አስብ።”​—⁠መክብብ 12:​1 አ.መ.ት

17, 18. አንዲት ክርስቲያን ወጣት ይሖዋን በማገልገልዋ ያገኘችውን ደስታ ምን በማለት ገልጻለች? አንተም ተመሳሳይ ደስታ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

17 በዛሬው ጊዜ ብዙ ወጣቶች ይሖዋን በማገልገላቸው ከፍተኛ ደስታ አግኝተዋል። ለምሳሌ ያህል የ15 ዓመቷ ሊና እንዲህ ትላለች:- “ሲጋራ ስለማላጨስና ዕፅ ስለማልወስድ ጥሩ ጤንነት አለኝ። የሰይጣንን መጥፎ ተጽእኖዎች መቋቋም እንድችል ከጉባኤ ጠቃሚ መመሪያ አገኛለሁ። በጉባኤ ውስጥ ጥሩ ወዳጆች ስላሉኝ ምንጊዜም ደስተኛ ነኝ። ከሁሉም በላይ ደግሞ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ወደር የሌለው ተስፋ አለኝ። በዚህም ምክንያት ምንም የሚያስፈራኝ ነገር የለም።”

18 ልክ እንደ ሊና ሁሉ ብዙ ክርስቲያን ወጣቶች ለእምነታቸው ብርቱ ተጋድሎ ያደርጋሉ፤ ይህም ደስታ ያመጣላቸዋል። አልፎ አልፎ በሕይወታቸው ውስጥ ፈታኝ ሁኔታዎች የሚያጋጥሟቸው ቢሆንም ትክክለኛ ዓላማና የወደፊት ተስፋ አላቸው። በመሆኑም ከልብ የሚያስብላችሁን አምላክ ማገልገላችሁን ቀጥሉ። የይሖዋን ልብ አስደስቱ፤ እርሱም አሁንም ሆነ ለዘላለም ደስተኞች እንድትሆኑ ያስችላችኋል!​—⁠መዝሙር 5:​11

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በሚያዝያ–ሰኔ 1997 የንቁ! መጽሔት እትም ላይ የወጣውን “እውነት ሕይወቴን አተረፈልኝ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

b አንድ ሰው ተጸጽቶ መጥፎ አካሄዱን ሲተውና ኃጢአቱን ሲናዘዝ ይሖዋ ሙሉ በሙሉ ‘ይቅር’ እንደሚለው ማወቁ ያጽናናል።​—⁠ኢሳይያስ 55:​7

ታስታውሳለህን?

• ‘ከክፉው’ ማለትም ከሰይጣን ጥበቃ ማግኘት የሚያስፈልግህ ለምንድን ነው?

• የይሖዋን ልብ ማስደሰት የምትችለው እንዴት ነው?

• መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ስለ አንተ እንደሚያስብ የሚያሳየው እንዴት ነው?

• ይሖዋን ማገልገል ምን በረከቶች ያስገኛል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 40 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ለመሰናከል ተቃርቦ የነበረ ጻድቅ ሰው

አሳፍ በጥንቷ እስራኤል በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚያገለግል የታወቀ ሌዋዊ ዘማሪ ነበር። ይህ ሰው በአምልኮ ሥርዓት ወቅት የሚዘመሩ መዝሙሮችንም አቀናብሯል። ሆኖም ልዩ የአገልግሎት መብቶች ቢኖሩትም የአምላክን ሕግ ጥሰው ምንም እርምጃ ባልተወሰደባቸው ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ቀንቶ ነበር። ከጊዜ በኋላ እንዲህ ሲል ሐቁን ተናግሯል:- “እግሮቼ ሊሰናከሉ፣ አረማመዴም ሊወድቅ ትንሽ ቀረ። የኃጢአተኞችን ሰላም አይቼ በዓመፀኞች ቀንቼ ነበርና።”​—⁠መዝሙር 73:2, 3

በኋላም አሳፍ ወደ አምላክ ቤተ መቅደስ ሄዶ የተሰማውን በጸሎት ገለጸ። ጉዳዩን እንደገና በመንፈሳዊ ዓይን በማየቱ ይሖዋ ክፋትን እንደሚጠላና ክፉዎችም ሆኑ ጻድቃን በጊዜው የዘሩትን እንደሚያጭዱ ተገነዘበ። (መዝሙር 73:​17-20፤ ገላትያ 6:​7, 8) በእርግጥም፣ ክፉዎች በድጥ ላይ የቆሙ ያህል ነው። በመጨረሻ ይሖዋ ይህን ክፉ ሥርዓት ሲደመስስ መውደቃቸው አይቀርም።​—⁠ራእይ 21:​8

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ከልብ የሚያስብልህ ሲሆን የሰይጣን ዓላማ ግን አንተን ማጥፋት ነው

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙ ወጣቶች ከእምነት አጋሮቻቸው ጋር ሆነው ይሖዋን በማገልገል ታላቅ ደስታ አግኝተዋል