በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልዩ ትዝታ ያለው የስብከት ሥራ

ልዩ ትዝታ ያለው የስብከት ሥራ

ልዩ ትዝታ ያለው የስብከት ሥራ

“አናት ከሚበሳው የፀሐይ ሙቀት ጋር ተዳምሮ አቀበት ቁልቁለቱ ቢሄዱት ቢሄዱት የሚገፋ አይመስልም። ቢሆንም ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ያሰብንበት መንደር ደረስን። በመንደሩ ውስጥ የመጀመሪያውን ቤት አንኳኩተን ሰዎቹ ወዳጃዊ በሆነ መንፈስ ሲቀበሉን ድካማችን በደስታ ተተካ። ቀኑ ሲገባደድ የያዝናቸውን ጽሑፎች በሙሉ አበርክተንና በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አስጀምረን ነበር። ሰዎቹ አዲስ ነገር የማወቅ ጉጉት አላቸው። አሁን የመመለሻችን ሰዓት ተቃርቧል፤ ቢሆንም በሌላ ጊዜ ተመልሰን ለመምጣት አስበናል።”

በሜክሲኮ ለሚያገለግል አንድ የአቅኚዎች ቡድን እንዲህ ዓይነቱ ውሎ የተለመደ ነው። እነዚህ አቅኚዎች ኢየሱስ ክርስቶስ “እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ የሰጠውን ተልዕኮ ለመፈጸም በሚደረገው እንቅስቃሴ በቅንዓት ለመካፈል ቆርጠዋል። (ሥራ 1:8) ሜክሲኮ ውስጥ በየትኛውም ጉባኤ ሥር ባለመታቀፋቸው ምክንያት የአምላክ መንግሥት ምሥራች በቋሚነት የማይሰበክባቸውን ክልሎች ለመሸፈን ልዩ የስብከት ዘመቻዎች ተዘጋጅተዋል። በአብዛኛው እነዚህ ክልሎች ጉባኤ ካለባቸው አካባቢዎች በጣም ርቀው የሚገኙ ከመሆኑም በላይ ለጉዞ አመቺ አይደሉም። በገለልተኛ አካባቢዎች የሚገኙና ሰፊ የአገልግሎት ክልል ያላቸውን ጉባኤዎችም ለመርዳት ዝግጅት ተደርጓል።

በሜክሲኮ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በአገሪቱ ውስጥ ካሉት ክልሎች መካከል የትኞቹ በዚህ ልዩ የአቅኚዎች ዘመቻ እንደሚሸፈኑ ለመወሰን የክልሎቹን ሁኔታ ያጠናል። a ከዚያም እነዚህን ክልሎች የሚሸፍኑ ልዩ አቅኚዎች በቡድን ሆነው ይመደባሉ። ወጣ ገባና ኮረኮንቻማ ለሆኑት መንገዶች የሚስማሙ መኪናዎችም ይሰጧቸዋል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ መኪናዎቹ የጽሑፍ ማከማቻና ለአቅኚዎቹ ማደሪያ ሆነው ያገለግላሉ።

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቀረቡ

ከጥቅምት 1996 ጀምሮ ሌሎች የምሥራቹ ሰባኪዎችም ከልዩ አቅኚዎቹ ጋር በዚህ ሥራ እንዲካፈሉ ጥሪ ይቀርብ ነበር። የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባቸው አካባቢዎች ሄደው ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑ አስፋፊዎችና የዘወትር አቅኚዎች በተለያየ ጊዜ በዘመቻው ለመካፈል ራሳቸውን አቅርበዋል። አንዳንዶች ክልሉን ለመሸፈንና ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ተመላልሰው ለመርዳት እንዲችሉ በዘመቻ በሚሸፈኑት አካባቢዎች ውስጥ ባሉ ጉባኤዎች እንዲያገለግሉ ተመደቡ። በርካታ ወጣት አስፋፊዎችና አቅኚዎች ለጥሪው ምላሽ የሰጡ ሲሆን እንደዚህ በማድረጋቸውም የሚያበረታቱ ተሞክሮዎች አግኝተዋል።

ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ የሞባይል ስልክ ኩባንያ ውስጥ ጥሩ ደመወዝ የሚያስገኝ ሥራ የነበረው አቢማኤል የተባለ ወጣት ክርስቲያን ራቅ ብለው በሚገኙት ክልሎች ውስጥ በሚደረገው የስብከት ዘመቻ ለመካፈል ወሰነ። አሠሪዎቹ ሥራውን ሊተው እንደሆነ ሲያውቁ የደረጃ እድገትና የደመወዝ ጭማሪ ሊሰጡት ፈለጉ። የሥራ ባልደረቦቹ ይህን በቀላሉ የማይገኝ ዕድል አልቀበልም ማለት ሞኝነት እንደሆነ በመግለጽ ሥራውን እንዳይለቅ ጎተጎቱት። አቢማኤል ግን ለሦስት ወራት ያህል በዚህ ልዩ የስብከት ዘመቻ ለመካፈል ቆርጦ ነበር። በዘመቻው ከተካፈለ በኋላ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ገለልተኛ ጉባኤ ውስጥ ላልተወሰነ ጊዜ ለመቆየት ወሰነ። በአሁኑ ወቅት በአነስተኛ ደመወዝ ተቀጥሮ የሚሰራ ሲሆን ኑሮውን ቀላል ማድረግ ተምሯል።

ኩሊሳ ደግሞ ወደተመደበችበት የአገልግሎት ክልል ለመድረስ በአውቶቡስ ለ22 ሰዓታት ያህል መጓዝ ነበረባት። በጉዞዋ መጨረሻ ላይ አውቶቡስ አመለጣት። ይሁን እንጂ ሠራተኞችን የሚያጓጉዝ አንድ የጭነት መኪና አየች። ኩሊሳ እንደ ምንም ራስዋን አደፋፍራ አብራቸው መጓዝ ትችል እንደሆነ ጠየቀቻቸው። ተሳፋሪዎቹ በሙሉ ወንዶች ስለነበሩ ስጋት አድሮባት ነበር። ለአንድ ወጣት ስትመሰክርለት የይሖዋ ምሥክር እንደሆነ ነገራት። “በጣም የሚገርመው ደግሞ የመኪናው ሹፌር በተመደብኩበት ጉባኤ የሚያገለግል ሽማግሌ ነበር!” በማለት ተናግራለች።

አረጋውያንም በዘመቻው ተካፍለዋል

በዚህ የአገልግሎት ዘመቻ የሚካፈሉት ወጣቶች ብቻ አይደሉም። አቴላ የሚባሉ አንዲት አረጋዊት እህት በስብከቱ ሥራ የበለጠ ተሳትፎ ለማድረግ ሁልጊዜ ይመኙ ነበር። በዚህ ልዩ የአገልግሎት ዘመቻ እንዲካፈሉ ግብዣ ሲቀርብላቸው ይህን ፍላጎታቸውን ለማሟላት የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ አገኙ። እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “በተመደብኩበት ክልል ውስጥ ባከናወንኩት አገልግሎት በጣም ስለተደሰትኩ እዚያው መቆየት እንደምፈልግ ለጉባኤው ሽማግሌዎች ነገርኳቸው። ዕድሜዬ ቢገፋም በይሖዋ አገልግሎት ጠቃሚ ድርሻ ለማበርከት በመቻሌ ተደስቻለሁ።”

ማርታ የተባሉ አንዲት የ60 ዓመት እህትም ለይሖዋ ባላቸው አድናቆትና ለሰዎች ባላቸው ፍቅር በመገፋፋት በዘመቻው ለመካፈል ራሳቸውን አቅርበዋል። እርሳቸው የተመደቡበት የአቅኚዎች ቡድን የሚያገለግልበት ክልል ሩቅ መሆኑና የመልክዓ ምድሩ አስቸጋሪነት ምሥራቹን ለሁሉም ሰዎች ለማካፈል እንቅፋት እንደሆነባቸው ሲመለከቱ ለአገልግሎት የሚጠቀሙበት መኪና ገዙ። እኚህ እህት ያደረጉት አስተዋጽኦ ብዙ የአገልግሎት ክልሎችን ለመሸፈንና የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለበርካታ ሰዎቸ ለማዳረስ አስችሏል።

አስደሳች ምላሽ

የዚህ ልዩ የስብከት ዘመቻ ዓላማ ሰዎችን ‘ደቀ መዛሙርት ማድረግ’ ሲሆን በዚህ ረገድም አስደሳች ውጤቶች ተገኝተዋል። በገለልተኛ ክልሎች የሚኖሩት ሰዎች ሕይወት አድን የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በደስታ ተቀብለዋል። (ማቴዎስ 28:19, 20) በርካታ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምረዋል። እነዚህን ሰዎች በአቅራቢያው የሚኖሩ አስፋፊዎችና በክልሉ ማገልገላቸውን የቀጠሉ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ያስጠኗቸዋል። በአንዳንድ ቦታዎች የተወሰኑ አስፋፊዎች ያሉባቸው ቡድኖች የተቋቋሙ ሲሆን በሌሎች ቦታዎች ደግሞ አነስተኛ ጉባኤዎች ተመሥርተዋል።

ማግዳሌኖ እና የአገልግሎት ጓደኞቹ ወደተመደቡበት ገለልተኛ ክልል ለመድረስ በሕዝብ ትራንስፖርት ይጠቀሙ ነበር። በጉዞ ላይ እያሉ አጋጣሚውን በመጠቀም ለሹፌሩ መሰከሩለት። ማግዳሌኖ እንዲህ ይላል:- “ከአንድ ሳምንት በፊት እሱ በሌለበት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤቱ መጥተው እንደነበረ ነገረን። ወደ ቤቱ ሲመለስ ቤተሰቡ ከምሥክሮቹ የሰሙትን በሙሉ ነግረውት ነበር። እኛም የምንኖረው በዚያ አካባቢ እንዳልሆነና በዚህ ልዩ የስብከት ዘመቻ ለመካፈል በራሳችን ወጪ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እንደመጣን ገለጽንለት። ሹፌሩ በነገሩ በጣም ስለተነካ በዚያው ሳምንት እሱና ቤተሰቡ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንደሚጀምሩ ተናገረ። እንዲሁም ለስብከት ዘመቻው የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ ሲል የጉዞውን ሒሳብ አላስከፈለንም።”

ማግዳሌኖ በቺያፓስ ተራሮች ላይ የሚኖሩት ሰዎች ለምሥራቹ በሰጡት ምላሽ በጣም ተደስቷል። “እኔና ባለቤቴ የፕሪስባይቴሪያን ቤተ ክርስቲያን አባላት ለሆኑ 26 ወጣቶች የመንግሥቱን መልእክት የመስበክ አጋጣሚ አግኝተን ነበር። ለግማሽ ሰዓት ያህል ስለ ይሖዋ ዓላማዎች በዝርዝር ስንነግራቸው ሁሉም የራሳቸውን መጽሐፍ ቅዱስ አውጥተው በትኩረት ይከታተሉ ነበር። አብዛኛው ሕዝብ በዜልታል ቋንቋ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ አለው።” በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች የተጀመሩ ሲሆን አሁን እድገት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

ተቃውሞው ረገብ አለ

በቺያፓስ በሚገኝ አንድ መንደር አንዳንዶቹ ነዋሪዎች ሥራችንን ይቃወሙ ስለነበር ከሁለት ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት አልተሰበከላቸውም። ቴሬሳ የተባለች አንዲት የሙሉ ጊዜ አገልጋይ አንዳንድ ምሥክሮች በዚያ መንደር ለመስበክ እንደሚፈሩ ተመለከተች። “የመንደሯ ነዋሪዎች ምሥራቹን ለመስማት ፈቃደኞች መሆናቸውን ስንመለከት ግን ሁላችንም ተገረምን። አገልግሎታችንን ስንጨርስ ኃይለኛ ዝናብ መጣል ስለ ጀመረ ለመጠለል ሴባስቲያን ወደተባለ አንድ እንግዳ ተቀባይ ሰው ቤት አመራን፤ ሰውየው ወደ ውስጥ እንድንገባና ከዝናቡ እንድንጠለል ፈቀደልን። ቤት ውስጥ ከገባን በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው አነጋግረውት እንደሆነ ጠየቅሁት። መጥተው እንደማያውቁ ሲነግረኝ ምሥራቹን ከነገርኩት በኋላ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት በተባለው መጽሐፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመርን። b ጥናታችንን ጨርሰን ልንሄድ ስንል ሴባስቲያን በሌላ ጊዜም መጥተን እንድናስጠናው እያለቀሰ ለመነን።”

በቺያፓስ ያገለገሉ ሌሎች አቅኚዎች ደግሞ እንዲህ ብለዋል:- “በይሖዋ እርዳታ ጥሩ ውጤት ማግኘት ችለናል። በመጀመሪያው ሳምንት 27 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አስጀመርን፤ በሁለተኛው ሳምንት የመንደሩን ነዋሪዎች መጽሐፍ ቅዱስ—በአንተ ሕይወት ውስጥ ያለው ኃይል የተባለውን የቪዲዮ ፊልም እንዲመለከቱ ጋበዝናቸው። ስልሳ የሚያህሉ ሰዎች ፊልሙን ለመመልከት የመጡ ሲሆን ሁሉም በጣም ተደስተው ነበር። ፊልሙ ሲያበቃ መጽሐፍ ቅዱስን በቡድን ሆነው እንዲያጠኑ ሐሳብ አቀረብንላቸው። በዚህ መንደር ውስጥ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድኖች ተመሥርተዋል።

“የተመደብንበትን ክልል ከሸፈንን በኋላ ፍላጎት ያሳዩትን ሰዎች ለማበረታታትና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድኖቹ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለመመልከት በድጋሚ ወደ መንደሩ ሄድን። የሕዝብ ስብሰባና የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ለማድረግ ነዋሪዎቹን ጋበዝናቸው። ሆኖም ስብሰባውን ለማካሄድ የሚያስችል በቂ ቦታ አልነበረም። በቡድን የሚደረገው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚካሄድበት ቤት ባለቤት ‘ስብሰባውን ከቤቴ ጓሮ ባለው ቦታ ላይ ማካሄድ እንችላለን’ አለ።”

በዚያው ሳምንት ቅዳሜና እሁድ ላይ አቅኚዎቹና ፍላጎት ያሳዩት ሰዎች አንድ ላይ በመረባረብ ቦታውን ለስብሰባ እንዲያመች አድርገው አዘጋጁት። ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው ስብሰባ ላይ 103 ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር። በአሁኑ ወቅት በዚያ መንደር ውስጥ 40 የሚያህሉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ያጠናሉ።

“ግሩም አጋጣሚ”

በዚህ ዘመቻ የተካፈሉት ምሥክሮች በስብከቱ ሥራ አስደሳች ውጤቶች ከማግኘታቸውም በተጨማሪ ራሳቸውም በጣም ተጠቅመዋል። በዘመቻው የተካፈለች ማሪያ የተባለች አንዲት ወጣት አቅኚ እንዲህ በማለት የተሰማትን ገልጻለች:- “ዘመቻው በስብከቱ ሥራ የማገኘው ደስታ እንዲጨምርና ከይሖዋ ጋር የበለጠ እንድቀራረብ ስለረዳኝ ግሩም አጋጣሚ ነበር ማለት እችላለሁ። በአንድ ወቅት በተራራማ አካባቢ ወደሚኖሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እየተጓዝን እያለን በጣም ደከመን። ይሖዋ ኃይል እንዲሰጠን ከጸለይን በኋላ ‘በእግዚአብሔር የሚተማመኑ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ’ የሚሉት በኢሳይያስ 40:29-31 ላይ የሚገኙት ቃላት በእኛ ላይ ሲፈጸሙ ተመልክተናል። ከይሖዋ ባገኘነው ኃይል ተበረታተን ያሰብንበት ቦታ ከመድረሳችንም በላይ በጉጉት ሲጠባበቁን የነበሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንን ማስጠናት ችለናል።”

ክላውዲያ የተባለች አንዲት የ17 ዓመት ወጣት አቅኚ ደግሞ እንዲህ ትላለች:- “ይህ ዘመቻ በጣም ጠቅሞኛል። በአገልግሎቴ ይበልጥ ውጤታማ በመሆኔ ደስታዬ ከመጨመሩም በላይ መንፈሳዊ ግቦች እንዳወጣ ረድቶኛል። በመንፈሳዊ ሁኔታም እድገት አድርጌአለሁ። እቤት እያለሁ ሁሉንም ነገር የምትሠራልኝ እናቴ ነበረች። አሁን የበለጠ ልምድ ስላገኘሁ ኃላፊነት ይሰማኛል። ለምሳሌ ያህል፣ በፊት በምግብ በኩል መራጭ ነበርኩ። አሁን ግን ብዙ ነገር ስላሳለፍኩ ያገኘሁትን እበላለሁ። በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ መካፈሌ ጥሩ ጓደኞች ለማፍራት አስችሎኛል። ከጓደኞቼ ጋር ያለንን የምንካፈል ሲሆን እርስ በርሳችንም እንረዳዳለን።”

አስደሳች ውጤት

ይህ የአገልግሎት ዘመቻ ምን ውጤት አስገኝቷል? በ2002 መጀመሪያ ላይ 28, 300 የሚያህሉ አቅኚዎች በዚህ ዘመቻ ተካፍለዋል። እነዚህ አቅኚዎች ከ140, 000 የሚበልጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ያስጠኑ ሲሆን በስብከቱ ሥራ ከሁለት ሚልዮን የሚበልጥ ሰዓት አሳልፈዋል። ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲማሩ ለመርዳት ወደ 121, 000 የሚጠጉ መጽሐፎችንና 730, 000 የሚያህሉ መጽሔቶችን አበርክተዋል። አንዳንድ አቅኚዎች 20 ወይም ከዚያ በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ነበሯቸው።

በገለልተኛ ክልሎች ውስጥ የሚኖሩት ሰዎችም የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለእነርሱ ለማድረስ ለተደረገው ደግነት የተሞላበት ጥረት አመስጋኞች ነበሩ። ብዙዎቹ በኑሯቸው ድሆች ቢሆኑም ስጦታ እንዲቀበሏቸው አስፋፊዎቹን ይወተውቷቸው ነበር። አንዲት የ70 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ችግረኛ ሴት አቅኚዎቹ በመጡ ቁጥር የሆነ ነገር ይሰጧቸውና አንቀበልም ሲሏቸው ያለቅሱ ነበር። ዝቅተኛ ኑሮ ያለው አንድ ቤተሰብ ደግሞ ዶሮዋ ለአቅኚዎቹ ብላ እንቁላል እንደጣለች በመናገር እንቁላሎቹን እንዲወስዱ ይጎተጉቷቸው ነበር።

ከሁሉ በላይ ግን እነዚህ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ለመንፈሳዊ ነገሮች ልባዊ አድናቆት አሳይተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት ወጣት በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ሦስት ሰዓት ተኩል በእግርዋ የምትጓዝ ሲሆን አንድም ስብሰባ አምልጧት አያውቅም። አንዲት አረጋዊት ሴት ደግሞ እግራቸውን የሚያማቸው ቢሆንም የወረዳ የበላይ ተመልካቹ በሚያደርገው ጉብኝት ላይ የሚሰጠውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ለማዳመጥ ሲሉ ለሁለት ሰዓታት ያህል ተጉዘዋል። ማንበብና መጻፍ የማይችሉ አንዳንዶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የበለጠ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ማንበብና መጻፍ ለመማር ተገፋፍተዋል። ይህ ጥረታቸውም የተትረፈረፈ በረከት አስገኝቶላቸዋል።

ሐዋርያው ጳውሎስ “አንድ የመቄዶንያ ሰው:- ወደ መቄዶንያ ተሻገርና እርዳን እያለ ቆሞ ሲለምነው” በራ​እይ እንደተመለከተ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ዘግቧል። ጳውሎስ ጥሪውን ተቀብሎ ወደ መቄዶንያ ሄዷል። ዛሬም ብዙዎች ምሥራቹን “እስከ ምድር ዳር ድረስ” እንድናሰራጭ ለቀረበው ጥሪ ተመሳሳይ ምላሽ በመስጠት ገለልተኛ በሆኑት የሜክሲኮ ክልሎች ለማገልገል ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል።⁠—⁠ሥራ 1:8፤ 16:​9, 10

[የግርጌ ማስታወሻ]

a እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከሜክሲኮ የአገልግሎት ክልል ውስጥ ከ8 በመቶ በላይ የሚሆነው ምሥራቹ በቋሚነት አይሰበክበትም ነበር። በሌላ አባባል ምሥራቹ እምብዛም በማይሰበክባቸው ገለልተኛ ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ከ8, 200, 000 በላይ ሰዎች አሉ ማለት ነው።

b በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሜክሲኮ የሚኖሩ በርካታ ምሥክሮች በዚህ ልዩ የስብከት ዘመቻ ተካፍለዋል