ደስታ የሰፈነበት ትዳር መመሥረት የሚቻለው እንዴት ነው?
ደስታ የሰፈነበት ትዳር መመሥረት የሚቻለው እንዴት ነው?
“ሰው . . . ከሚስቱ ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።” —ዘፍጥረት 2:24
ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ አምላክ ጋብቻን ያቋቋመው በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል ዘላቂ ጥምረት እንዲመሠረት አስቦ ነው። ይህን በሚመለከት ዘፍጥረት 2:18, 22-24 እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር አምላክ፣ ‘ሰው ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለምና የሚስማማውን ረዳት አበጅለታለሁ’ አለ። እግዚአብሔር አምላክ ከአዳም የወሰዳትን ዐጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት። አዳምም እንዲህ አለ፤ ‘እነሆ፤ ይህች ዐጥንት ከዐጥንቴ፤ ሥጋም ከሥጋዬ ናት። ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል።’ ስለዚህ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ ከሚስቱ ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።”
ዘላቂና አስደሳች ትዳር መመሥረት ቀላል አይሁን እንጂ የማይቻል 1 ቆሮንቶስ 7:33, 34) ይህ ደግሞ ብዙ ትግል ይጠይቃል። እናንተም ትዳራችሁ የሚያስፈልገውን ጊዜ ለመስጠትና ጥረት ለማድረግ ፈቃደኞች ከሆናችሁ ለረዥም ዘመን የሚዘልቅ አስደሳች ትዳር ሊኖራችሁ ይችላል።
ነገር ግን አይደለም። ብዙ ባልና ሚስቶች ለ50፣ ለ60 ወይም ከዚያ ለሚበልጡ ዓመታት በትዳር ተጣምረው በደስታ መኖር ችለዋል። እንዴት ሊሳካላቸው ቻለ? ጋብቻቸው እንዲሳካ በቁርጠኝነት ያላሰለሰ ጥረት ስለሚያደርጉና ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ የትዳር ጓደኛቸውን “ደስ ለማሰኘት” ስለሚጥሩ ነው። (መመሪያውን በጥንቃቄ ተከተሉ
አንድ እምነት የሚጣልበት ሕንጻ ተቋራጭ የሚገነባውን ሕንጻ ንድፍ አስቀድሞ ሳይመለከት በፍጹም ግንባታውን አይጀምርም። በተመሳሳይ እኛም አምላክ ለጋብቻ ያዘጋጀውን ንድፍ በጥንቃቄ ካልመረመርን አስደሳች ትዳር መመሥረት አንችልም። አስደሳች ትዳር ለመመሥረት የሚረዳው ንድፍ ወይም መመሪያ በአምላክ ቃል ውስጥ ይገኛል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ . . . ለማቅናት . . . ይጠቅማሉ” ሲል ጽፏል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16
ባሎችም ሆኑ ሚስቶች፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የያዘበትን መንገድ በማስተዋል ስለ ትዳር ብዙ ነገር መማር ይችላሉ። እንዴት? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ በኢየሱስና ከእሱ ጋር በሰማይ አብረውት በሚገዙት መካከል ያለው ዝምድና በባልና በሚስት መካከል ባለው ዝምድና ተመስሏል። (2 ቆሮንቶስ 11:2) ኢየሱስ በጣም አስቸጋሪ በሆነ ወቅትም እንኳን ሳይቀር ለወዳጆቹ ታማኝ ሆኗል። መጽሐፍ ቅዱስ “እስከ መጨረሻ ወደዳቸው” ይላል። (ዮሐንስ 13:1 የ1954 ትርጉም) ኢየሱስ ርኅሩኅ መሪ እንደመሆኑ መጠን ምንጊዜም የተከታዮቹን የአቅም ገደብና ድካም ከግምት ያስገባ ነበር። ከአቅማቸው በላይ ምንም ነገር እንዲያደርጉለት ወይም እንዲሰጡት ጠይቆ አያውቅም።—ዮሐንስ 16:12
ኢየሱስ በጣም የሚወዳቸው ወዳጆቹ ባሳዘኑት ጊዜም እንኳ በደግነት ይዟቸዋል። ስህተታቸውን በማንሳት አልዘለፋቸውም፤ ከዚህ ይልቅ አምላካዊ ትሕትናና ደግነት በማሳየት እንዲታረሙ ለመርዳት ጥሯል። (ማቴዎስ 11:28-30፤ ማርቆስ 14:34-38፤ ዮሐንስ 13:5-17) ስለዚህ እናንተም ኢየሱስ ተከታዮቹን እንዴት በርኅራኄ እንደያዘና እነሱም ላሳያቸው ፍቅር ምላሽ የሰጡበትን መንገድ በጥልቀት ብትመረምሩ አስደሳች ትዳር መመሥረት የምትችሉበትን ተግባራዊ ትምህርት ልትቀስሙ ትችላላችሁ።—1 ጴጥሮስ 2:21
ጠንካራ መሠረት ይኑራችሁ
እንደ ማዕበል ያሉ ችግሮች በትዳራችሁ ላይ ጥቃት ማድረሳቸው አይቀርም። ይህም የትዳራችሁ መሠረት ጥንካሬ እንዲፈተን ያደርጋል። ከማንኛውም ነገር በላይ ትዳርን አስደሳች ለማድረግ የሚረዳው ጠንካራ መሠረት በፍቅር ተነሳስቶ ቃል ኪዳንን በታማኝነት መጠበቅ ነው። ኢየሱስ “እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው” ብሎ በመናገር ቃል ኪዳንን የመጠበቅን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ማቴዎስ 19:6) ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርሽን የተሰኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “አምላክ ያጣመረውን ማንም አይለየው” ይላል። እዚህ ላይ “ማንም” የሚለው አገላለጽ አንዳቸው ለሌላው ታማኝ ሆነው ለመኖር ቃል የተጋቡትን ባልና ሚስትም ይጨምራል።
አንዳንዶች፣ ቃል ኪዳን በጣም ብዙ ጊዜና ወጪ እንዲሁም ከፍተኛ ጥረት እንደሚጠይቅ ስለሚሰማቸው እንደ ሸክም ይመለከቱት ይሆናል። በዛሬው
ጊዜ አብዛኛው ሰው ቃል ኪዳኑን ለመጠበቅ መሥዋዕትነት ከመክፈል ይልቅ የራሱን ምቾት ይመርጣል።ታዲያ በትዳር ውስጥ ቃል ኪዳንን ጠብቆ ለመቆየት ምን ሊረዳ ይችላል? ሐዋርያው ጳውሎስ “ባሎችም . . . ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ ሥጋቸው መውደድ ይገባቸዋል” በማለት ጽፏል። (ኤፌሶን 5:28, 29) እንግዲያውስ በትዳር ‘መጣመር’ ሲባል ለራስህ ደህንነት የምታስበውን ያህል ለትዳር ጓደኛህም ማሰብን ይጨምራል። የተጋቡ ሰዎች “የእኔ” ከማለት ይልቅ “የእኛ” ማለት እንዲሁም “እኔ” ሳይሆን “እኛ” ብለው ማሰብ ይኖርባቸዋል።
በትዳራችሁ ላይ የሚሰነዘረውን ማዕበል መሰል ጥቃት በተሳካ ሁኔታ መቋቋም ጥበበኞች ያደርጋችኋል። በዚህ መንገድ የተገኘ ጥበብ ደግሞ ደስታ ያመጣል። ምሳሌ 3:13 “ጥበብን የሚያገኛት . . . ሰው ቡሩክ [“ደስተኛ፣” NW] ነው” በማለት ይገልጻል።
እሳትን መቋቋም በሚችሉ ቁሳቁሶች ተጠቀሙ
አንድ ቤት ዘላቂነት እንዲኖረውና አስተማማኝ እንዲሆን በጥሩ ሁኔታ መገንባት አለበት። ስለዚህ ትዳራችሁን ዘላቂ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። ለዚህም ሲባል ታማኝነታችሁን የሚፈትኑ እንደ እሳት ያሉ ችግሮችን መቋቋም የሚችሉ ጠንካራ ቁሳቁሶችን ተጠቀሙ። እንደ አምላካዊ ጥበብ፣ ልግስና፣ ማስተዋል፣ ፈሪሃ አምላክ፣ ወዳጃዊ ስሜት፣ የአምላክን ሕጎች መውደድና ልባዊ አድናቆት ማሳየት እንዲሁም እውነተኛ እምነት ላሉት ውድ ባሕርያት ከፍ ያለ ግምት ይኑራችሁ።
በትዳር ውስጥ ደስታና እርካታ ማግኘታችሁ የተመካው በልባችሁና በአእምሯችሁ ላይ እንጂ ባፈራችሁት ቁሳዊ ንብረት ወይም በሥራ ቦታችሁ ባገኛችሁት የደረጃ ዕድገት ላይ አይደለም። እነዚህ ባሕርያት የሚጠናከሩት ደግሞ ከአምላክ ቃል በሚገኘው እውነት ነው። “እያንዳንዱ እንዴት እንደሚገነባ መጠንቀቅ አለበት” የሚለው ምክር በትዳር ረገድም ይሠራል።—1 ቆሮንቶስ 3:10
ችግሮች ሲፈጠሩ
አንድ ሕንጻ ለረዥም ጊዜ እንዲያገለግል ከተፈለገ ጥሩ ጥገና ሊደረግለት ይገባል። ባልና ሚስትም ግቦቻቸውን ለማሳካት ዘወትር የሚደጋገፉና አንዳቸው ለሌላው አክብሮት የሚያሳዩ ሲሆኑ ትዳራቸው ጸንቶ ይቆማል። እንዲህ ካደረጉ ራስ ወዳድነት ቦታ አይኖረውም፤ እንዲሁም ቁጣቸውን መቆጣጠር አያቅታቸውም።
ሥር የሰደደና የታመቀ ንዴት ወይም ብስጭት በትዳር ውስጥ ሊኖር የሚገባውን ፍቅርና መዋደድ ሊያጠፋ ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ ወንዶችን ሲመክር “ባሎች ሆይ፤ ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ መራራም [“ቁጡ፣” NW] አትሁኑባቸው” ብሏል። (ቈላስይስ 3:19) ይኸው መሠረታዊ ሥርዓት በሚስቶችም ላይ ይሠራል። የትዳር ጓደኛሞች አሳቢ፣ ደግና የሰው ስሜት የሚገባቸው ለመሆን ሲጥሩ የሚያገኙት ደስታና እርካታ ይጨምራል። ችግሮች በሚፈጠሩበት ጊዜ ቁጣንና ንትርክን ማስወገድ እንዳትጣሉ ይረዳችኋል። ጳውሎስ “ይቅር ተባባሉ፤ እርስ በርሳችሁ ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ” በማለት መክሯል።—ኤፌሶን 4:32
የትዳር ጓደኛችሁ እንደማይሰማችሁ፣ እንደሚያበሳጫችሁ ወይም እንደማያደንቃችሁ ቢሰማችሁ ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? ያሳሰባችሁን ነገር ለትዳር ጓደኛችሁ በረጋ መንፈስ ገልጻችሁ ተናገሩ። ጥቃቅን ነገሮችን ግን በፍቅር ሸፍኖ ማለፉ የተሻለ ሊሆን ይችላል።—1 ጴጥሮስ 4:8
በ35 ዓመት የትዳር ዘመኑ ብዙ ችግሮች ያሳለፈ አንድ ባል፣ በትዳር ጓደኛችሁ ላይ የቱንም ያህል ብትቆጡ “ፈጽሞ አትኮራረፉ” በማለት ይናገራል። አክሎም “ማፍቀራችሁንም ቢሆን ፈጽሞ አታቁሙ” በማለት ጥበብ ያዘለ ምክር ሰጥቷል።
አስደሳች ትዳር መመሥረት ትችላላችሁ
አስደሳች ትዳር መመሥረት ቀላል አለመሆኑ እውነት ነው። ይሁን እንጂ የትዳር ጓደኛሞች አምላክን በትዳራቸው ውስጥ ለማስገባት በቁርጠኝነት ጠንክረው ከሠሩ ደስታ ያገኛሉ፣ የሚያሰጋቸው ነገርም አይኖርም። በመሆኑም ቤተሰብህ በመንፈሳዊ ጉዳዮች ረገድ ያለበትን ሁኔታ ትኩረት ሰጥተህ ተከታተል፤ የጋብቻ ቃል ኪዳንህ የጸና ይሁን። ደግሞም ኢየሱስ እንደተናገረው ደስታ ለሰፈነበት ትዳር የሚመሰገኑት ባል ወይም ሚስት ብቻ እንዳልሆኑ አስታውስ። ከዚህ ይልቅ በዋነኝነት ምስጋና የሚገባው የጋብቻ መሥራች የሆነው ይሖዋ አምላክ ነው። “እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው።”—ማቴዎስ 19:6
ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት
ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተሰኘው በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ አስደሳችና የተሳካ ትዳር ለመመሥረት የሚረዱ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ምክሮችን ያቀርባል። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ባልና ሚስቶች ይህ መጽሐፍ የያዛቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ምክሮች የቤተሰብ ሕይወታቸው እንዲሻሻል እንደረዷቸው ተገንዝበዋል።—በዚህ መጽሔት ላይ ገጽ 32ን ተመልከት።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አስደሳች ትዳር ለመመሥረት ምን ሊረዳችሁ ይችላል?
▪ ዘወትር የአምላክን ቃል አብራችሁ አጥኑ፤ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችላችሁን እርዳታና አመራር ለማግኘት ወደ አምላክ ጸልዩ።—ምሳሌ 3:5, 6፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
▪ የጾታ ፍላጎታችሁ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ብቻ እንዲወሰን አድርጉ።—ምሳሌ 5:15-21፤ ዕብራውያን 13:4
▪ ስለ ችግራችሁና በመካከላችሁ ስላሉት ልዩነቶች በግልጽ፣ በሐቀኝነትና ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ተነጋገሩ።—ምሳሌ 15:22፤ 20:5፤ 25:11
▪ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ስትነጋገሩ በደግነትና አሳቢነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ይሁን፤ በቁጣ መገንፈልን፣ ንዝንዝንና ነቀፋ አዘል አስተያየቶችን አስወግዱ።—ምሳሌ 15:1፤ 20:3፤ 21:9፤ 31:26, 28፤ ኤፌሶን 4:31, 32
▪ የትዳር ጓደኛችሁ ማድረግ ያለበትን ወይም ያለባትን ሁሉ እንዳላደረገ ወይም እንዳላደረገች ቢሰማችሁም እንኳን የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በትሕትና ተግባራዊ አድርጉ።—ሮሜ 14:12፤ 1 ጴጥሮስ 3:1, 2
▪ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን መንፈሳዊ ባሕርያት ለመኮትኮት ጠንክራችሁ ሥሩ።—ገላትያ 5:22, 23፤ ቈላስይስ 3:12-14፤ 1 ጴጥሮስ 3:3-6
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ጋብቻን በሚመለከት አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰጠውን መመሪያ ተከተሉ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ትዳራችሁ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ፍቅርና በታማኝነት ላይ የተመሠረተ ይሁን
[በገጽ 8 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
እንደ እሳት ያሉ ፈተናዎችን መቋቋም የሚችሉ መንፈሳዊ ባሕርያት አዳብሩ
[በገጽ 8 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
አስደሳች ትዳር የማያቋርጥ ጥረት ያሻዋል