በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ባሕር ጨዋማ የሆነው ለምንድን ነው?

ባሕር ጨዋማ የሆነው ለምንድን ነው?

ባሕር ጨዋማ የሆነው ለምንድን ነው?

ውቅያኖሶችና ባሕሮች ውስጥ ያለው ጨው በሙሉ ወጥቶ በምድር ላይ ቢነጠፍ 150 ሜትር ከፍታ ይኖረዋል፤ በሌላ አነጋገር 44 ፎቅ ያለው ሕንጻ የሚያክል ክምር ይወጣዋል! ከፍተኛ መጠን ያለው የጅረቶችና የወንዞች ጨው አልባ ውኃ ወደ ውቅያኖሶች እየገባ ይሄ ሁሉ የጨው ክምችት ከየት መጣ? ሳይንቲስቶች ጨዉ የተለያዩ ምንጮች እንዳሉት ደርሰውበታል።

አንዱ የጨው ምንጭ እኛ የቆምንበት ምድር ነው። የዝናብ ውኃ ወደ አፈርና ወደ አለቶች ሲሰርግ ጨውንና በውስጡ ያሉ ኬሚካሎችን ጨምሮ ጥቃቅን የሆኑ ማዕድናትን ያሟሟል፤ ከዚያም እነዚህ የሟሙ ነገሮች በጅረቶችና በወንዞች አማካኝነት ባሕር ውስጥ ይገባሉ (1)። ሆኖም በጅረቶችና በወንዞች ውኃ ውስጥ ያለው የጨው መጠን በጣም አነስተኛ በመሆኑ ብንቀምሰውም ጣዕሙ አይሰማንም።

በውቅያኖሶች ወለል ላይ በሚገኘው የላይኛው የምድር ንጣፍ ውስጥ ያሉት ጨውን የሚያስገኙ ማዕድናትም ሌሎቹ የጨው ምንጮች ናቸው። ውኃ በባሕር ወለል ላይ በሚገኙ ስንጥቆች ሰርጎ ይገባና በከፍተኛ ሁኔታ ይፈላል፤ ከዚያም የሟሙ ማዕድናትን ይዞ ተመልሶ ወደ ላይ ይወጣል። በውቅያኖስ ወለል ላይ በሚገኙ ጥልቀት ያላቸው ስንጥቆች የሟሙ ማዕድናትንና ሌሎች ነገሮችን ይዞ የወጣው ፍልውኃ ወደ ባሕር ይገባል (2)

ከላይ ከተገለጸው ተቃራኒ በሆነ መንገድ ጨው ወደ ባሕር የሚገባበት ሂደት አለ፤ ከውቅያኖስ ሥር የሚፈነዳ እሳተ ገሞራ ከፍተኛ መጠን ያለው የቀለጠ ዓለት ወደ ውቅያኖሶች ይተፋል። በዚህ ጊዜ ዓለቱ ውስጥ ያሉት ኬሚካሎች ውኃው ውስጥ ይረጫሉ (3)። የተለያዩ የማዕድናት ቅንጣቶችን ውኃ ውስጥ የሚያስገባው ሌላው ነገር ነፋስ ነው (4)። እነዚህ ሁሉ ሂደቶች፣ የባሕር ውኃ አሉ የሚባሉ ንጥረ ነገሮች ሁሉ ውሁድ እንዲሆን አድርገውታል ለማለት ይቻላል። ዋነኛው የጨው ንጥረ ነገር ሶድየም ክሎራይድ ማለትም ምግብ ውስጥ የሚጨመረው የጨው ዓይነት ነው። ባሕር ውስጥ ከሚገኘው ጨው ውስጥ 85 በመቶ ያህሉ ሶድየም ክሎራይድ ሲሆን ውኃው የጨው ጣዕም እንዲኖረው ያደረገው ምክንያት ይኸው ነው።

በባሕር ውስጥ ያለው የጨው መጠን የማይለዋወጠው ለምንድን ነው?

ከውቅያኖስ ላይ የሚተነው ንጹሕ ውኃ ብቻ በመሆኑ በባሕር ውስጥ ጨው ይከማቻል። ሌሎች ማዕድናትም ባሕር ውስጥ ይቀራሉ። ተጨማሪ ማዕድናት ውቅያኖስ ውስጥ መግባታቸውን አያቆሙም፤ ነገር ግን የጨዉ መጠን አይለዋወጥም። ምንጊዜም ቢሆን ከአንድ ሺህ እጁ የባሕር ውኃ ውስጥ 35 እጅ የሚያህለው ክፍል ጨው ነው። ወደ ባሕር የሚገባውና ከባሕር የሚወጣው የጨውና የሌሎች ማዕድናት መጠን ተመሳሳይ እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ይህም ‘ጨዉ ወዴት ይሄዳል?’ የሚል ጥያቄ ያስነሳል።

ሕይወት ያላቸው ነገሮች ጨው ውስጥ የሚገኙ በርካታ ንጥረ ነገሮችን ይጠቀማሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ፖሊፕስ የሚባሉ ትናንሽ የባሕር ውስጥ ፍጥረታት፣ ባለ ዛጎል ፍጥረታትና ክርስቴይሽን የሚባሉት ፍጥረታት ለዛጎላቸውና ለአጥንታቸው የሚያስፈልገውን ካልሲየም የተባለ ጨው ውስጥ የሚገኝ ንጥረ ነገር ይመገባሉ። በአጉሊ መነጽር ብቻ የሚታዩት ዳይአተም የሚባሉት አልጌዎች ሲልከንን ይጠቀማሉ። ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሲሞቱ ደግሞ ባክቴሪያዎችና ሌሎች ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት ይመገቧቸዋል። እነዚህ ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት ሲሞቱ በሰውነታቸው ውስጥ ያለው ጨውና ማዕድን ቀስ በቀስ በባሕሩ ወለል ላይ ይከማቻል፤ በሌሎች ፍጥረታት ሲበሉ ደግሞ በኩስ መልክ ባሕሩ ወለል ላይ ይጠራቀማል (5)

ከላይ በተጠቀሰው መንገድ ያልተወገደው ጨው በሌላ መንገድ ይወገዳል። ለምሳሌ ያህል በወንዞች፣ በመሬት መሸርሸርና በእሳተ ገሞራ ፍንዳታ አማካኝነት ወደ ውቅያኖሶች የሚገቡት አፈርና ሌሎች የምድር ማዕድናት የተወሰነውን ጨው ይዘው ባሕር ወለል ላይ ሊዘቅጡ ይችላሉ። እንዲሁም የተወሰነው ጨው ዓለት ላይ ይከማቻል። ስለዚህ በተለያዩ ሂደቶች አማካኝነት አብዛኛው ጨው በውቅያኖስ ወለል ላይ ይከማቻል (6)

በርካታ ተመራማሪዎች ጨውና ማዕድናት ከባሕር የሚወጡበትና ወደ ባሕር የሚመለሱበት ዑደት ረጅም ጊዜ የሚፈጅ ተፈጥሯዊ ሂደት እንደሆነ ያምናሉ። ላይኛው የምድር ንጣፍ የተሠራው ከግዙፍ ንብርብሮች ነው። አንዳንዶቹ ንብርብሮች አጠገባቸው ካለው ተመሳሳይ ንጣፍ ሥር ዝቅ ይሉና ኃይለኛ ሙቀት ወዳለበት ሁለተኛው የምድር ንጣፍ (mantle) ይሰምጣሉ፤ እነዚህ ንብርብሮች የሚገናኙበት ቦታ ግብተ ምድር ቀጣና (subduction zone) ይባላል። ብዙውን ጊዜ ወደታች የሚሰምጠው በአካባቢው ካሉት የበለጠ ክብደት ያለው ንጣፍ ሲሆን በዚህ ወቅት እላዩ ላይ ያሉት ጨዋማ ዝቃጮችም አብረው ይሰምጣሉ። በዚህ ኡደት አማካኝነት አብዛኛው የምድር የላይኛው ንጣፍ ቀስ በቀስ ቦታው ይቀያየራል (7)። ይህ ሂደት መከሰቱ የሚታወቅባቸው ሦስት ነገሮች የመሬት መንቀጥቀጥ፣ እሳተ ገሞራና የሸለቆዎች መፈጠር ናቸው። *

የጨዉ መጠን የማይለዋወጥ መሆኑ አስደናቂ ነው

የውቅያኖስ ጨዋማነት ከቦታ ቦታ አንዳንድ ጊዜም ከወቅት ወቅት ልዩነት አለው። በጣም ጨዋማ የሆኑት የውኃ አካላት እጅግ ከፍተኛ የውኃ ትነት ያለባቸው ተራርቀው የሚገኙት የፋርስ ባሕረ ሰላጤና ቀይ ባሕር ናቸው። የትልልቅ ወንዞች ንጹሕ ውኃ የሚገባባቸው ወይም ብዙ ዝናብ የሚያገኙ ውቅያኖሶች የጨው ይዘት ከአማካዩ ዝቅ ያለ ነው። የምድር ዋልታዎች አቅራቢያ የሚገኘው የባሕር ውኃም ብዙም ጨዋማ አይደለም። ምክንያቱም እዚያ የሚገኘው የበረዶ ግግር በሚሟሟበት ጊዜ የሚገኘው ንጹሕ ውኃ ነው። በተቃራኒው ደግሞ ውኃው በረዶ በሚሆንበት ጊዜ በአቅራቢያው ባለው ባሕር ውስጥ ያለው የጨው መጠን ከፍ ይላል። በጥቅሉ ሲታይ ግን ውቅያኖስ ውስጥ ያለው የጨው መጠን አይለዋወጥም።

ከዚህ በተጨማሪ የባሕር ውኃ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ የፒኤች (pH) መጠኑ አይቀያየርም፤ ፒኤች የአንድ ነገር የአሲድ ወይም የአልካላይ ይዘት መለኪያ ሲሆን የፒኤች መጠኑ 7 ከሆነ አሲድም አልካላይም አይደለም። የባሕር ውኃ የፒኤች መጠን በ7.4 እና በ8.3 መካከል የሚገኝ በመሆኑ በተወሰነ መጠን አልካላይነት አለው ማለት ነው። (የሰው ደም ፒኤች መጠን 7.4 ነው።) የውቅያኖስ ውኃ የፒኤች መጠን ከዚህ ውጪ ቢሆን ሁኔታው አደገኛ ይሆናል። እንዲያውም በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ ሳይንቲስቶችን ይህ ሁኔታ ያሳስባቸዋል። የሰው ልጆች ወደ ከባቢ አየር ከሚለቁት ካርቦንዳይኦክሳይድ መካከል አብዛኛው የሚሄደው ወደ ውቅያኖሶች ነው፤ ካርቦንዳይኦክሳይድ ውቅያኖሶች ውስጥ ከገባ በኋላ ከውኃው ጋር በመዋሃድ የካርቦን አሲድ ይፈጥራል። ስለዚህ የሰው ልጆች እንቅስቃሴ ውቅያኖሶችን ቀስ በቀስ ወደ አሲድነት ሊቀይራቸው ይችላል።

የባሕር ውኃ ኬሚካላዊ ይዘት እንዳይለዋወጥ ከሚያደርጉት ሂደቶች መካከል አብዛኞቹ ሙሉ በሙሉ አልተደረሰባቸውም። ቢሆንም እስከ አሁን ያወቅናቸው ነገሮች ለእጁ ሥራዎች የሚገደው አምላክ ለጥበቡ ዳርቻ እንደሌለው ያረጋግጣሉ።ራእይ 11:18

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 በኅዳር 22, 2000 ንቁ! ላይ የወጣውን “የውቅያኖስ ወለል—ምስጢሩ ተገለጠ” (እንግሊዝኛ) የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ዝናብ

1 በአለቶች ውስጥ የሚገኙ ማዕድናት

2 ማዕድናትን የያዘ ፍልውኃ ሲወጣ

3 ውቅያኖስ ውስጥ የፈነዳ እሳተ ገሞራ

4 ነፋስ

ውቅያኖስ

የውቅያኖስ ወለል

የመሬት የላይኛው ንጣፍ

5 በዓይን የማይታዩ ዳይአተም የተባሉ አልጌዎች

6 እሳተ ገሞራ ጭስ ሲተፋ

7 ግብተ ምድር ቀጣና

[ምንጮች]

የፍል ውኃው መውጫ:- © Science VU/Visuals Unlimited; እሳተ ገሞራ:- REUTERS/Japan Coast Guard/Handout; ዳይአተም:- Dr. Neil Sullivan, USC/NOAA Corps; የእሳተ ገሞራ ፎቶ:- Dept. of Interior, National Park Service

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕላዊ መግለጫ]

በባሕር ውስጥ የሚገኘው ጨው

ሳይንቲስቶች ከመቶ ለሚበልጡ ዓመታት ስለ ባሕር ውኃ ሲያጠኑ ቢቆዩም እስከ አሁን ድረስ ስለ ኬሚካላዊ ውህደቱ ሙሉ በሙሉ አላወቁም። ነገር ግን በሟሟ ጨው ውስጥ ያሉትን የተለያዩ ንጥረ ነገሮች መለየትና መጠናቸውን ማስላት ችለዋል። ከንጥረ ነገሮቹ መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል:-

[ሥዕላዊ መግለጫ]

55 በመቶ ክሎራይድ

30.6 በመቶ ሶዲየም

7.7 በመቶ ሰልፌት

3.7 በመቶ ማግኒዚየም

1.2 በመቶ ካልሲየም

1.1 በመቶ ፖታሲየም

0.4 በመቶ ባይካርቦኔት

0.2 በመቶ ብሮማይድ

በተጨማሪም እንደ ቦሬት፣ ስትሮንቺየምና ፍሎራይድ የመሰሉ ሌሎች በርካታ ንጥረ ነገሮችም ይገኙበታል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ከውቅያኖስ የበለጠ ጨዋማ የሆነ ባሕር

በደረቅ መሬት የተከበቡ አንዳንድ የውኃ አካላት ከውቅያኖስ የበለጠ ጨዋማ ናቸው። ለዚህ ዋነኛ ምሳሌ የሚሆነው በምድር ላይ ከሚገኙት የውኃ አካላት ሁሉ በጨዋማነቱ የሚበልጠው የሙት ባሕር ነው። የሟሟ ጨውና ሌሎች ማዕድናትን የያዘ ውኃ ወደ ሙት ባሕር ይገባል፤ ይህ ባሕር በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የጨው ባሕር ይባል ነበር። (ዘኍልቍ 34:3, 12) የሙት ባሕር ዳርቻ በምድር ላይ ካሉት ሁሉ ዝቅተኛው ደረቅ ቦታ ሲሆን ውኃው የሚወገደው በአንድ መንገድ ይኸውም በትነት መልክ ብቻ ነው፤ በበጋ ወቅት ያለው ትነት ከውኃው መጠን በቀን ውስጥ 25 ሚሊ ሜትር ያህል ሊቀንስ ይችላል።

በዚህ ምክንያት ከላይኛው የውኃ ክፍል ውስጥ 30 በመቶ ገደማ የሚሆነው ጨው ይሆናል፤ ይህም ከሜዲትራኒያን ባሕር የጨው ይዘት በአሥር እጥፍ ይበልጣል። በሙት ባሕር ውስጥ ያለው የጨው መጠን በጣም ከፍተኛ ስለሆነ ዋናተኞች በቀላሉ መንሳፈፍ ይችላሉ። እንዲያውም ያለ መንሳፈፊያ በጀርባቸው ተንጋልለው ጋዜጣ ማንበብ ይችላሉ።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ጨው አየርን ለማጽዳት ይጠቅማል

ብክለትን የሚያስከትሉ በአየር ውስጥ የሚገኙ ቅንጣቶች ደመና ዝናብ ሆኖ ወደ ምድር እንዳይወርድ እንደሚያደርጉ በምርምር ተደርሶበታል። ይሁን እንጂ በካይ ነገሮች ያሉበት ከውቅያኖስ በላይ ያለ ደመና በፍጥነት ዝናብ ይፈጥራል። ይህ ልዩነት እንዲፈጠር ያደረገው ከባሕር የሚረጭ የጨው ብናኝ ነው።

በከባቢ አየር ውስጥ በሚገኙ ብክለት የሚያስከትሉ ቅንጣቶች ላይ የሚፈጠሩት የውኃ ጠብታዎች መጠናቸው በጣም አነስተኛ ስለሚሆን መዝነብ አይችሉም፤ ስለዚህ እዚያው ታግደው ይቀራሉ። ከባሕር የሚረጩት የጨው ብናኞች እነዚህ ጥቃቅን ጠብታዎች ተሳስበው ትላልቅ ጠብታዎች እንዲሆኑ በማድረግ ዝናብ እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናሉ። ዝናብ መዝነቡ በከባቢ አየር ውስጥ የሚገኙት ብክለት የሚያስከትሉ ነገሮች እንዲወገዱ ጭምር ይረዳል።