በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓሣ መብላት ለሕመም ሲዳርግህ

ዓሣ መብላት ለሕመም ሲዳርግህ

ዓሣ መብላት ለሕመም ሲዳርግህ

ፊጂ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

አርቦንቶ፣ ‘ልብላው ወይስ ይቅርብኝ?’ እያለ ያመነታል። ዓሣውን መብላቱ ሊያሳምመው እንደሚችል ቢያውቅም በጣም እርቦታል። በዚያ ላይ ደግሞ የተጠበሰው ዓሣ ሽታ ያውዳል። አርቦንቶ የመብላት ፍላጎቱ ስላየለበት ዓሣውን በላው። ብዙም ሳይቆይ ግን ማቅለሽለሽና ሆድ ቁርጠት ጀመረው፤ ከዚያም ‘ምነው በቀረብኝ’ እስኪል ደረስ ትውከትና ተቅማጥ ያጣድፈው ጀመር።

የአርቦንቶ ጓደኞች መኖሪያቸው በሆነችው አነስተኛ የፓስፊክ ደሴት ላይ ወደሚገኘው ሆስፒታል ሲያደርሱት በከፊል ራሱን ስቶ፣ የሰውነቱ ፈሳሽ ከመሟጠጡ የተነሳ ደክሞ እንዲሁም የደም ግፊቱና የልቡ ምት በአደገኛ ሁኔታ ቀንሶ ነበር። ደረቱ አካባቢም ሕመም ነበረው። በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ከራስ ምታት፣ ከድብታና ከድካም ስሜት በተጨማሪ እግሩን ይደነዝዘው፣ ሽንቱን በሚሸናበት ጊዜ ደግሞ ከፍተኛ ሕመም ይሰማው እንዲሁም ቀዝቃዛ ነገር ሲነካ ይሞቀውና የሞቀ ነገር ሲነካ ደግሞ በተቃራኒው ይቀዘቅዘው ነበር። ከስምንት ቀናት በኋላ የልቡ ምት መስተካከል የጀመረ ቢሆንም የመደንዘዝና የድካም ስሜቱ ግን ለበርካታ ሳምንታት ቀጠለ።

አርቦንቶ የተመገበው ዓሣ፣ በተፈጥሮ የሚገኝ ኃይለኛ መርዝ በመብላቱ ሳቢያ ተመርዞ ነበር። ለወትሮው ይህ ዓሣ በሞቃታማ አካባቢ ከሚኖሩና ለምግብነት ከሚውሉ ዝርያዎች የሚመደብ ነው። አርቦንቶ ያጋጠመው ችግር ሲጓትራ ፊሽ ፖይዝኒንግ (ሲ ኤፍ ፒ) በመባል የሚታወቅ ሲሆን በሕንድ ውቅያኖስ፣ በፓስፊክ ውቅያኖስና በካሪቢያን ባሕር አቅራቢያ ባሉ ሐሩራማና ከፊል ሞቃታማ አካባቢዎች በብዛት ይከሰታል። በእነዚህ ክልሎች የሚኖሩ ሰዎች ዋነኛ ምግባቸው በአካባቢው የሚጠመዱ ዓሦች ናቸው።

ሲጓትራ ፊሽ ፖይዝኒንግ አዲስ በሽታ አይደለም። በባሕር ይጓዙ የነበሩ የጥንት አውሮፓውያን አሳሾች በዚህ በሽታ በጣም ይቸገሩ ነበር። በአሁኑ ጊዜም ቢሆን በርካታ አገር ጎብኚዎችን ለከባድ ሥቃይ ሲዳርጋቸው ይታያል። ይህ በሽታ በብዙ ደሴቶች ላይ የሚካሄደውን የዓሣ ማስገርና የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እንደሚጎዳ ግልጽ ነው። ከዚህም በላይ ከነሕይወታቸው ወይም ቀዝቅዘው ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚሸጡ በባሕር ጠረፎች አካባቢ ባሉ አለቶች ውስጥ የሚኖሩ ዓሦች፣ በሽታው ከሐሩራማ አካባቢዎች አልፎ በቀላሉ ወደማይታወቅባቸው ሌሎች አገሮችም እንዲሰራጭ ምክንያት ሆነዋል። *

በባሕር ጠረፎች አካባቢ ባሉ አለቶች ውስጥ የሚኖሩ ዓሦችን የሚመርዛቸው ምንድን ነው? የተመረዘን ዓሣ ለይቶ ማወቅ ይቻላል? ለብዙ አሥርተ ዓመታት የተካሄደ ጥናት ምን እንደሚያሳይ ተመልከት።

መንስኤውን ለይቶ ማወቅ

ሲጓትራ ፊሽ ፖይዝኒንግ የተባለውን በሽታ የሚያስከትለውን መርዛማ ንጥረ ነገር የሚያመነጩት ዳይኖፍላጅሌት የተባሉ ረቂቅ ተሕዋስያን እንደሆኑ በሰፊው ይታመናል። * እነዚህ ረቂቅ ተሕዋስያን በትናንሽ የባሕር እንስሳት አጽምና አልጌዎች ላይ ተጣብቀው ይኖራሉ። ትናንሽ ዓሦች አልጌዎቹን በሚበሉበት ጊዜ ዳይኖፍላጅሌቶች የሚያመነጩት ሲጓቶክሲን የተሰኘው መርዛማ ንጥረ ነገር ወደ ሰውነታቸው ይገባል። እነዚህ ትናንሽ ዓሦች በሌሎች ከፍ ያሉ ዓሦች ይበላሉ፣ እነርሱ ራሳቸው ደግሞ በሌሎች ትላልቅ ዓሦች ይበላሉ። እንዲህ እንዲህ እያለ መርዛማው ንጥረ ነገር የምግብ ሠንሠለቱን ተከትሎ ይዛመታል። ያም ሆኖ፣ ይህ መርዛማ ንጥረ ነገር በዓሦቹ ላይ ምንም ጉዳት አያስከትልም።

ሲጓቶክሲን በገዳይነታቸው ከሚታወቁ ባይሎጂያዊ ንጥረ ነገሮች መካከል አንዱ ነው። ደግነቱ ግን “ሲጓትራ ፊሽ ፖይዝኒንግ የሚባለውን በሽታ ሊያስከትሉ የሚችሉት ጥቂት የዓሣ ዝርያዎች ብቻ” እንደሆኑ የአውስትራሊያ መንግሥት ያወጣው ሪፖርት ይገልጻል። ሲጓቶክሲን የዓሣው መልክ፣ ሽታ ወይም ጣዕም እንዲለወጥ አያደርግም፤ ከዚህም በተጨማሪ ዓሣውን በማብሰል፣ በማድረቅ፣ ጨው ነስንሶ በማቆየት፣ በጭስ በማጠን አሊያም በቅመም በመዘፍዘፍ ይህን መርዝ ማጥፋት አይቻልም። አርቦንቶ፣ አደገኛ የሆነ የአንጀት መታወክ እንዲሁም የልብና የነርቭ ሕመም እስከጀመረው ሰዓት ድረስ ዓሣው የተመረዘ መሆኑን የሚያመለክት ምንም ፍንጭ አላየም።

በሽታውን ለይቶ ማወቅና ሕክምና መስጠት

በአሁኑ ጊዜ ሰዎች ሲጓትራ ፊሽ ፖይዝኒንግ በተባለው በሽታ መያዛቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል የላብራቶሪ ምርመራ የለም። አንድ ሰው በዚህ በሽታ መያዙ የሚታወቀው ዓሣውን ከተመገበ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በሚታዩት የተለያዩ የሕመም ምልክቶችና ምናልባትም የተረፈው ምግብ ተመርምሮ መርዛማው ንጥረ ነገር መኖሩ ከተረጋገጠ በኋላ ነው። (በሚቀጥለው ገጽ ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) በሽታው እንደያዘህ ከተጠራጠርክ የሕክምና እርዳታ ለማግኘት መጣርህ ብልህነት ነው። ይህ መርዝ ማርከሻ የሌለው ቢሆንም ሕክምና ማግኘትህ የሚሰማህን ሕመም ያስታግስልሃል። የበሽታው ምልክቶችም ጊዜ እያለፈ ሲሄድ እየጠፉ ይሄዳሉ። ሲጓትራ ፊሽ ፖይዝኒንግ ከፍተኛ ሥቃይ ሊያስከትል ስለሚችል አፋጣኝ የሕክምና እርዳታ ማግኘት ችግሩ ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይደርስ ለመከላከል ይረዳል።

በሽታው የሚያስከትለው ሕመም ክብደት በተለያዩ ሁኔታዎች ላይ የተመካ ነው። ከእነዚህም መካከል በዓሣው ውስጥ የሚገኘው መርዝ መጠን፣ የተመገብነው የዓሣ መጠንና ብልት ዓይነት እንዲሁም ቀድሞውኑ በበሽተኛው አካል ውስጥ የነበረው የሲጓቶክሲን ክምችት ይገኙበታል። የመርዛማው ንጥረ ነገር ክምችት ከቦታ ቦታ ስለሚለያይ ዓሣው የተጠመደበት አካባቢም ቢሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል። አካላችን ለእነዚህ መርዛማ ንጥረ ነገሮች የመከላከያ አቅም ከማበጀት ይልቅ በተደጋጋሚ በተጠቃ ቁጥር የመቋቋም ኃይላችን እየተዳከመ ይሄዳል! አልኮል መጠጣት በሽታውን ያባብሰዋል። በስፋት እየተሰራጨ ያለውን ይህን በሽታ አስመልክቶ የተዘጋጀ አንድ ጽሑፍ በሽታው እንዳያገረሽ ከተፈለገ ችግሩ ከተከሰተበት ቀን አንስቶ ከሦስት እስከ ስድስት ወር ለሚደርስ ጊዜ በሽተኛው ዓሣ ከመብላት መታቀብ እንደሚኖርበት ይገልጻል።

በሽታው ሲከፋ ከክሮኒክ ፋቲግ ሲንድረም (ኃይለኛ ድካም የሚያስከትል በሽታ ነው) ጋር የሚመሳሰሉ የሕመም ምልክቶች የሚያስከትል ሲሆን እነዚህ ምልክቶች ለሳምንታት ወይም ለወራት፣ አንዳንዴም ለዓመታት ሊዘልቁ ይችላሉ። ያን ያህል የተለመደ ባይሆንም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ከደም ዝውውር መገታት፣ ከመተንፈሻ አካላትና ከልብ ችግር አሊያም ከሰውነት ፈሳሽ መሟጠጥ ጋር በተያያዘ ለሞት ሊያደርስ ይችላል። ይህ ሁኔታ በአብዛኛው የሚከሰተው መርዛማው ንጥረ ነገር በብዛት የሚከማችባቸውን የዓሣውን ጭንቅላትና የውስጥ ብልቶች በመመገብ ነው።

ያልተፈታ እንቆቅልሽ

እንደ እውነቱ ከሆነ፣ በባሕር ውስጥ ባሉ አለቶች አካባቢ የሚኖሩ ዓሦችና እነርሱን የሚመገቡ እንስሳት በሙሉ ሲጓቶክሲን ሊኖርባቸው ይገባ ነበር። ሁኔታው ግን እንዲህ አይደለም። በአንድ የባሕር ዳርቻ ላይ የሚኖሩ ዓሦች በከፍተኛ ደረጃ የተመረዙ ሊሆኑ ቢችሉም እንኳ በዚያው አካባቢ የሚጠመዱ ተመሳሳይ ዝርያ ያላቸው ዓሦች ደግሞ ከመርዙ ነጻ ይሆናሉ። በአንዱ የዓለም ክፍል መርዛማው ንጥረ ነገር አለባቸው ተብሎ በስፋት የሚነገርላቸው የዓሣ ዝርያዎች በሌላው የዓለም ክፍል ደግሞ ምንም ችግር እንደማይስከትሉ ተደርገው ይታያሉ። ዳይኖፍላጅሌቶች መርዛማ ንጥረ ነገሮችን የሚያመነጩት አልፎ አልፎ በመሆኑ ምክንያት የተመረዙት ዓሦች የት እንደሚገኙ ለመገመት እንኳ ያስቸግራል።

ከዚህም በተጨማሪ መርዛማ ዓሦችን ለይቶ ለማወቅ የሚያስችል አስተማማኝና ውድ ያልሆነ ምርመራ አለመኖሩ ችግሩን አባብሶታል። በአሁኑ ጊዜ፣ የጤና ባለሙያዎች ለሕዝቡ ሊሰጡት የሚችሉት እገዛ ቢኖር ምን ዓይነት ዓሦችን መመገብ እንደሌለባቸው መጠቆምና በሽታው ስለተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚገልጹ መረጃዎችን በማሰባሰብ ከእነዚህ አካባቢዎች የተጠመዱ ዓሦችን እንዳይበሉ ማሳሰብ ብቻ ነው። መርዛማው ንጥረ ነገር ይኖርባቸዋል ተብለው ከሚጠረጠሩት የዓሣ ዝርያዎች መካከል ባራኩዳ፣ ግሩፐር፣ ኪንግፊሽ፣ ሬድ ባስ፣ ሮክፊሽ፣ ስናፐር እና ሞራ ኢል ይገኙበታል። ትላልቅና ያረጁ ዓሦች የመመረዛቸው አጋጣሚ ከፍተኛ ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች ጤነኛነቱ ያልተረጋገጠ ዓሣ መሸጥ በሕግ የተከለከለ ነው። በባሕር ዳርቻ ላይ ባሉ አለቶች ውስጥ የሚኖሩ ዓሦችን የማይመገቡ የውቅያኖስ ዓሦች እና ሞቃታማ ባልሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ዓሦች ከችግሩ ነፃ እንደሆኑ ይታመናል።

በሲጓትራ ፊሽ ፖይዝኒንግ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እንደሚያሻቅብ ይገመታል። እንዲህ የተባለበት አንዱ ምክንያት፣ ትናንሽ የባሕር እንስሳት የሞቱበት አካባቢ መርዛማ ለሆኑት ዳይኖፍላጅሌቶች መባዛት ተስማሚ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው ስለሚታመንና እነዚህ እንስሳት እየታመሙ ወይም እየሞቱ መሆናቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶች እየተበራከቱ በመሄዳቸው ነው።

ሲጓትራ ፊሽ ፖይዝኒንግ የተባለው ሕመም ባሕርይ ተለዋዋጭ ቢሆንም እንኳ አንዳንድ መሠረታዊ መመሪያዎችን ተግባራዊ በማድረግ ራስህን ከጉዳት መጠበቅ ትችላለህ። (ከላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።) አርቦንቶ እነዚህን መመሪያዎች ችላ በማለቱ ሕይወቱን ሊያጣ ነበር። ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል የሚታወቀውንና በባሕር ጠረፎች አካባቢ ባሉ አለቶች ውስጥ የሚኖረውን የዓሣ ዝርያ ጭንቅላትና ሌሎች የውስጥ ብልቶች ተመግቧል። ከዚህ ቀደም እንዲህ ዓይነት ዓሣ በልቶ ምንም ጉዳት ስላላገኘው ልክ እንደ ሌሎቹ የደሴቲቱ ነዎሪዎች እርሱም ከልክ በላይ የመተማመን ስሜት አድሮበት ነበር።

እንዲህ ሲባል ግን የእረፍት ጊዜህን ለማሳለፍ ወደ ሞቃታማ አካባቢ ብትሄድ ከባሕር ውስጥ የሚገኙ ምግቦችን በፍጹም መመገብ የለብህም ማለት ነው? በጭራሽ። ከዚህ ይልቅ የተሰጡትን ማስጠንቀቂያዎች ማስተዋልና የምትመገበውን ዓሣ በጥንቃቄ መምረጥ ብልህነት ነው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.6 የበሽታው ምልክት በትክክል ባለመታወቁና የተጠቂዎቹ ቁጥር በተገቢ ሁኔታ ሪፖርት ባለመደረጉ ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ ምን ያህል ሰዎች በዚህ በሽታ እንደሚያዙ አይታወቅም። ያም ሆኖ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው አንዳንድ ምንጮች በየዓመቱ 50,000 የሚሆኑ ሰዎች በበሽታው እንደሚጠቁ ይገምታሉ።

^ አን.9 ዳይኖፍላጅሌቶች ጋምቢርዲስከስ ቶክሲከስ ከሚባለው ዝርያ ይመደባሉ።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የተለመዱ የሕመም ምልክቶች

▪ ተቅማጥ፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስና የሆድ ቁርጠት

▪ ብርድ ብርድ ማለት፣ ላብ፣ ድብታ፣ ራስ ምታትና የማሳከክ ስሜት

▪ በአፍ፣ በእጅ ወይም በእግር አካባቢ እንደ መደንዘዝና መንዘር ያለ ስሜት

▪ ቀዝቃዛ ነገር ሲነካ የሙቀት ስሜት መሰማትና የሞቀ ነገር ሲነኩ ደግሞ መቀዝቀዝ

▪ በጡንቻዎችና በመገጣጠሚያዎች ላይ እንዲሁም ሽንት በሚሸናበት ጊዜ የሚፈጠር ከፍተኛ የሕመም ስሜት

▪ የልብ ምትና የደም ግፊት መቀነስ እንዲሁም ከፍተኛ ድካም

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በበሽታው የመያዝ አጋጣሚን መቀነስ

▪ የትኞቹን የዓሣ ዓይነቶች መብላት እንደሌለብህና መርዛማ የሆኑት ዓሦች ብዙውን ጊዜ የሚጠመዱት ከየት ቦታ እንደሆነ ለማወቅ በአካባቢው ያለውን የዓሣ አስጋሪዎች ማኅበር ወይም ልምድ ያላቸውን ዓሣ አጥማጆች ጠይቅ።

▪ በቅርቡ ሲጓትራ ተገኘ ከተባለበት አካባቢ የተጠመደ ዓሣ አትብላ።

▪ ትላልቅና ያረጁ ዓሣዎችን ከመብላት ተቆጠብ።

▪ የዓሣውን ጭንቅላት ወይም ጉበት አሊይም ሌሎች የውስጥ ብልቶች አትመገብ።

▪ ከባሕር ዳርቻ ላይ ዓሣ ካጠመድክ ወዲያውኑ የሆድ ዕቃውን በደንብ አድርገህ አውጣው።

[በገጽ 20, 21 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ሲጓትራ ፊሽ ፖይዝኒንግ ያስከትላሉ ተብለው የሚጠረጠሩ የዓሣ ዝርያዎች

(ስሞቹ ከቦታ ቦታ ሊለያዩ ይችላሉ)

ባራኩዳ

ግሩፐር

ሮክፊሽ

ስናፐር

ኪንግፊሽ

ሞራ ኢል

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መርዛማውን ንጥረ ነገር የሚያመነጨው ዳይኖፍላጅሌት

[በገጽ 20 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]

ከሞራ ኢል ዓሣ በቀር ሁሉም ዓሦች:- Illustrated by Diane Rome Peebles - Provided by the Florida Fish and Wildlife Conservation Commission, Division of Marine Fisheries Management; ሞራ ኢል:- Photo by John E. Randall; ዳይኖፍላጅሌት:- Image by D. Patterson and R. Andersen, provided courtesy of micro*scope (http://microscope.mbl.edu)

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ጽሑፍ የሰፈረባቸው የዓሣ ምስሎች:- Illustrated by Diane Rome Peebles - Provided by the Florida Fish and Wildlife Conservation Commission, Division of Marine Fisheries Management