ሕፃናት መታሸት ያስፈልጋቸዋል?
ሕፃናት መታሸት ያስፈልጋቸዋል?
ስፔን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
አኒታ የተባለች በወጣትነት ዕድሜ ላይ የምትገኝ አንዲት ናይጄሪያዊት እናት ልጅዋን ካጠበቻት በኋላ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ታሻታለች። በዚህ ወቅት እናትም ሆነች ልጅዋ በጣም ደስ ይላቸዋል። አኒታ “ይህ በናይጄሪያ የሚገኙ እናቶች ሕፃናት ልጆቻቸውን የሚንከባከቡበት ባሕላዊ መንገድ ነው” በማለት ትገልጻለች። “እናቴ እኔንና ወንድሞቼን ታሸን ነበር። ማሸት የሕፃኑ ጡንቻ እንዲጠነክርና እንዲፍታታ ለማድረግ የሚረዳ በጣም ጥሩ ዘዴ ነው። ልጄን ሳሻት እዘምርላታለሁ እንዲሁም አዋራታለሁ፤ እሷም በምላሹ የሕፃን ሳቋንና ፈገግታዋን ታጠግበኛለች። ይህ በጣም አስደሳች ነው!”
ሕፃናትን ማሸት በብዙ አገሮች የተለመደ ነገር ሲሆን በአንዳንድ ምዕራባውያን አገሮችም እየተለመደ መጥቷል። በስፔን የሕፃናት እሽትን የሚያበረታታ ማኅበር እንደሚገልጸው እሽት ወላጆች ሕፃን ልጃቸውን በመነካካት ስሜታቸውን የሚገልጹበት ረቂቅ፣ ፍቅር የተንጸባረቀበትና ደስታ የሚሰጥ ዘዴ ነው። ይህም የሕፃኑን ጀርባ፣ እግሩን (ውስጥ እግሩን ጭምር)፣ ደረቱን፣ ሆዱን፣ እጆቹንና ፊቱን በቀስታ ሆኖም ጠበቅ ባለ መንገድ ማሸትን ይጨምራል።
አንድ ሕፃን ልጅ ከመታሸት የሚያገኘው ጥቅም ምንድን ነው? ከሁሉ በፊት ማሸት የፍቅርና የርኅራኄን ስሜት ያስተላልፋል። አዲስ የተወለደ ሕፃን መመገብ ብቻ ሳይሆን የወላጅ ፍቅር ማግኘትም ያስፈልገዋል። ሕፃናት ገና ከጨቅላነታቸው ጀምሮ የመዳሰስ ስሜትን መረዳት ስለሚችሉ ወላጆች ልጆቻቸውን በቀስታ በማሻሸት ፍቅራቸውን ጉልህ በሆነ መንገድ መግለጽ ይችላሉ። ሕፃኑን በማሻሸት አካላዊም ሆነ ስሜታዊ የሆኑ ብዙ መረጃዎች ማስተላለፍ ይቻላል። በመሆኑም ማሻሸት ሕፃኑ ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ በወላጆችና በልጃቸው መካከል የጠበቀ ፍቅር ለመመሥረት ይረዳል።
ማሻሸት ፍቅርን ለመግለጽ ከማገልገሉም በተጨማሪ ሕፃኑ ዘና እንዲል ስለሚያደርገው ረዘም ላለ ጊዜ ጥሩ እንቅልፍ እንዲወስደውና ጭንቅ እንዳይለው ለማድረግ ይረዳል። በተጨማሪም ማሻሸት ጡንቻን ለማጠንከር ከመርዳቱም ሌላ የደም ዝውውርን፣ የምግብ መፈጨትንና አተነፋፈስን ለማስተካከል ሊረዳ ይችላል። ማሻሸት የሕፃኑን በሽታ የመከላከል አቅም ለማጠናከር እንደሚጠቅም የሚናገሩ ሰዎችም አሉ። ማሻሸት የሕፃኑን የመዳሰስ፣ የማየትና የመስማት ስሜት ስለሚቀሰቅሰው የማስታወስና የመማር ችሎታውንም ሊያሳድግለት ይችላል።
አንዳንድ ሆስፒታሎች አራስ ልጆችን ማሻሸት ያለውን ጠቀሜታ ለማወቅ ጥናት አካሂደው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ዘጠኝ ወር ሳይሞላቸው ከተወለዱ ሕፃናት መካከል የታሹት ሕፃናት ካልታሹት ሰባት ቀን ቀድመው ከሆስፒታል መውጣታቸውንና ክብደታቸውም ቢሆን ካልታሹት ጋር ሲነጻጸር እስከ 47 በመቶ መጨመሩን ጥናቱ አሳይቷል።
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ጥሩ እሽት የሚጠቅመው አዋቂዎችን ብቻ አይደለም! እንዲያውም መታሸት ለሕፃናት የሚሰጠው ጥቅም ጡንቻን በማፍታታት ብቻ የተወሰነ አይደለም። ከብሩህ ፈገግታ ጋር ተስማሚ ሙቀት ባላቸው ጣቶች ማሻሸት ሕፃኑ ፍቅር የሚያገኝበት መንገድ ነው።