በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 28

መዝሙር 123 ለቲኦክራሲያዊ ሥርዓት በታማኝነት መገዛት

እውነትን ለይተህ ማወቅ ትችላለህ?

እውነትን ለይተህ ማወቅ ትችላለህ?

“ወገባችሁን በእውነት ቀበቶ ታጥቃችሁ . . . ጸንታችሁ ቁሙ።”ኤፌ. 6:14

ዓላማ

ከይሖዋ በተማርነው እውነት እና ሰይጣንና ተቃዋሚዎቻችን በሚያስፋፉት ውሸት መካከል ያለውን ልዩነት ማስተዋል እንድንችል ራሳችንን ማሠልጠን።

1. እውነትን በተመለከተ ምን ይሰማሃል?

 የይሖዋ ሕዝቦች በአምላክ ቃል ውስጥ ላለው እውነት ፍቅር አላቸው። እምነታችን የተገነባው በእሱ ላይ ነው። (ሮም 10:17) ይሖዋ የክርስቲያን ጉባኤን “የእውነት ዓምድና ድጋፍ” አድርጎ እንዳቋቋመው እርግጠኞች ነን። (1 ጢሞ. 3:15) በተጨማሪም በመካከላችን ሆነው ‘አመራር የሚሰጡን’ ወንድሞች እውነትን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሲያብራሩልንና ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ መመሪያ ሲሰጡን በደስታ እንታዘዛለን።—ዕብ. 13:17

2. ያዕቆብ 5:19 እንደሚለው እውነትን ከተቀበልን በኋላ ምን ዓይነት አደጋ ሊያጋጥመን ይችላል?

2 ይሁንና እውነትን ከተቀበልንና የአምላክ ድርጅት አስተማማኝ መመሪያ እንደሚሰጥ ከተገነዘብን በኋላም መንገድ ስተን ልንወጣ እንችላለን። (ያዕቆብ 5:19ን አንብብ።) ሰይጣን በመጽሐፍ ቅዱስና የአምላክ ድርጅት በሚሰጠን መመሪያ ላይ እምነት እንድናጣ ለማድረግ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም።—ኤፌ. 4:14

3. እውነትን አጥብቀን መያዝ ያለብን ለምንድን ነው? (ኤፌሶን 6:13, 14)

3 ኤፌሶን 6:13, 14ን አንብብ። በቅርቡ ዲያብሎስ ሁሉንም ብሔራት አታሎ ይሖዋን እንዲቃወሙ ለማድረግ ኃይለኛ ፕሮፓጋንዳ ይጠቀማል። (ራእይ 16:13, 14) ሰይጣን የይሖዋን ሕዝቦች ለማሳት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያፋፍምም እንጠብቃለን። (ራእይ 12:9) ስለዚህም እውነትና ውሸት የሆነውን ነገር መለየትና ለእውነት መታዘዝ እንድንችል ራሳችንን ማሠልጠናችን አስፈላጊ ነው። (ሮም 6:17፤ 1 ጴጥ. 1:22) ከታላቁ መከራ መትረፋችን የተመካው በዚህ ላይ ነው!

4. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

4 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን እውነት ለይተን ለማወቅና የአምላክ ድርጅት የሚሰጠንን መመሪያ ለመታዘዝ የሚረዱንን ሁለት ባሕርያት እንመለከታለን። ከዚያም እውነትን አጥብቀን ለመያዝ ማድረግ ያለብንን ሦስት ነገሮች እንመረምራለን።

እውነትን ለይተን ለማወቅ የሚረዱን ባሕርያት

5. ይሖዋን መፍራት እውነትን ለይተን እንድናውቅ የሚረዳን እንዴት ነው?

5 ይሖዋን መፍራት። ለይሖዋ ተገቢውን ፍርሃት ስናዳብር እሱን ከመውደዳችን የተነሳ የሚያሳዝነውን ምንም ነገር ከማድረግ እንቆጠባለን። የይሖዋን ሞገስ ማግኘት ስለምንፈልግ ትክክልና ስህተት እንዲሁም እውነትና ውሸት በሆነው ነገር መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ እንነሳሳለን። (ምሳሌ 2:3-6፤ ዕብ. 5:14) ለሰዎች የሚያድርብን የፍርሃት ስሜት ለአምላክ ካለን ፍቅር እንዲበልጥ ፈጽሞ መፍቀድ አይኖርብንም፤ ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ ሰዎችን የሚያስደስተው ነገር ይሖዋን የሚያሳዝነው ነገር ነው።

6. አሥሩን የእስራኤል የነገድ አለቆች የሰው ፍርሃት እውነቱን አዛብተው እንዲያቀርቡ ያደረጋቸው እንዴት ነው?

6 ከአምላክ ይልቅ ሰዎችን የምንፈራ ከሆነ ከእውነት ልንርቅ እንችላለን። ይሖዋ እስራኤላውያን እንደሚወርሱት ቃል የገባላቸውን ምድር እንዲሰልሉ የተላኩትን 12 የነገድ አለቆች እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አሥሩ ሰላዮች ለከነአናውያን ያደረባቸው ፍርሃት ለይሖዋ ካላቸው ፍቅር ይበልጥ ነበር። ለእስራኤላውያን ወገኖቻቸው “ሰዎቹ ከእኛ ይልቅ ብርቱዎች ስለሆኑ ወጥተን ልንዋጋቸው አንችልም” ብለዋቸው ነበር። (ዘኁ. 13:27-31) እርግጥ ከሰብዓዊ እይታ አንጻር ከነአናውያን ከእስራኤላውያን ይበልጥ ብርቱ መሆናቸው እውነት ነው። ነገር ግን እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን ማሸነፍ አይችሉም የሚለው ሐሳብ ይሖዋን ከግንዛቤ ያስገባ አልነበረም። እነዚህ አሥር ሰላዮች ይሖዋ እስራኤላውያን እንዲያደርጉ በሚፈልገው ነገር ላይ ማተኮር ነበረባቸው። በተጨማሪም ከዚህ ትንሽ ቀደም ብሎ ባደረገላቸው ነገር ላይ ማሰላሰል ነበረባቸው። እንዲህ ቢያደርጉ ኖሮ ከነአናውያን ያላቸው ብርታት ሁሉን ቻይ ከሆነው ከይሖዋ ኃይል አንጻር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ይገነዘቡ ነበር። ከእነዚህ እምነት የለሽ ሰላዮች በተቃራኒው ኢያሱና ካሌብ የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ፈልገው ነበር። ለሕዝቡ እንዲህ ብለዋል፦ “ይሖዋ በእኛ ከተደሰተ ወተትና ማር ወደምታፈሰው ወደዚህች ምድር በእርግጥ ያስገባናል፤ ደግሞም ይህችን ምድር ይሰጠናል።”—ዘኁ. 14:6-9

7. ለይሖዋ ያለንን ፍርሃት ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

7 ለይሖዋ ያለንን ፍርሃት ለማጠናከር ማንኛውንም ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት እሱን የሚያስደስተው ምን እንደሆነ ማሰብ ይኖርብናል። (መዝ. 16:8) የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ስታነብ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘እኔ በዚያ ሁኔታ ውስጥ ብሆን ኖሮ ምን ዓይነት ውሳኔ አደርግ ነበር?’ ለምሳሌ አሥሩ የእስራኤል የነገድ አለቆች አሉታዊ ነገር በሚናገሩበት ወቅት በቦታው እንደነበርክ አድርገህ አስብ። እነሱ ያመጡትን ወሬ አምነህ ለፍርሃት እጅ ትሰጥ ነበር? ወይስ ለይሖዋ ያለህ ፍቅርና እሱን ለማስደሰት ያለህ ፍላጎት ያሸንፍ ነበር? በወቅቱ የነበረው የእስራኤል ትውልድ ኢያሱና ካሌብ የተናገሩት ነገር እውነት መሆኑን ሳይገነዘብ ቀርቷል። በመሆኑም ወደ ተስፋይቱ ምድር የመግባት አጋጣሚውን አጣ።—ዘኁ. 14:10, 22, 23

ማንን ታምን ነበር? (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት)


8. የትኛውን ባሕርይ ለማዳበር ተግተን መሥራት ይኖርብናል? ለምንስ?

8 ትሕትና። ይሖዋ እውነትን የሚገልጠው ትሑት ለሆኑ ሰዎች ነው። (ማቴ. 11:25) እውነትን እንድንማር የተደረገልንን እርዳታ በትሕትና ተቀብለናል። (ሥራ 8:30, 31) ያም ቢሆን ኩራተኞች እንዳንሆን መጠንቀቅ አለብን። ኩራተኞች ከሆንን የራሳችን አመለካከት ከቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ከይሖዋ ድርጅት ከሚገኘው መመሪያ እኩል ትክክል እንደሆነ ልናስብ እንችላለን።

9. ትሑት ሆነን መቆየት የምንችለው እንዴት ነው?

9 ትሑት ሆነን ለመቆየት ከይሖዋ ታላቅነት አንጻር ከቁብ የማንቆጠር መሆናችንን ማስታወስ ይኖርብናል። (መዝ. 8:3, 4) ይሖዋ ትሑታንና ለመማር ፈቃደኞች እንድንሆን እንዲረዳን መጸለይም እንችላለን። ይሖዋ ከራሳችን አስተሳሰብ ይልቅ በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት የነገረንን የእሱን አስተሳሰብ እንድናስቀድም ሊረዳን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ ይሖዋ ትሕትናን እንደሚወድ እንዲሁም ኩራትን፣ ትዕቢትንና እብሪትን እንደሚጠላ የሚያሳዩ ነጥቦችን ለማስተዋል ሞክር። በተጨማሪም ከፍ ያለ ግምት እንዲሰጥህ የሚያደርግ የአገልግሎት መብት ካገኘህ ትሑት ለመሆን የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብሃል።

እውነትን አጥብቀን መያዝ የምንችለው እንዴት ነው?

10. ይሖዋ ለሕዝቦቹ መመሪያ ለማስተላለፍ እነማንን ተጠቅሟል?

10 በቲኦክራሲያዊ መመሪያዎች ላይ ያለህን እምነት አጠናክር። በጥንቷ እስራኤል ዘመን ይሖዋ ለሕዝቡ መመሪያዎችን ለማስተላለፍ ሙሴን ቀጥሎም ኢያሱን ተጠቅሟል። (ኢያሱ 1:16, 17) እስራኤላውያን እነዚህን ሰዎች የይሖዋ ወኪሎች አድርገው በተመለከቱባቸው ጊዜያት ተባርከው ነበር። በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ የክርስቲያን ጉባኤ ሲቋቋም 12ቱ ሐዋርያት መመሪያ ይሰጡ ነበር። (ሥራ 8:14, 15) ከጊዜ በኋላ ይህ ቡድን በኢየሩሳሌም የሚገኙ ሌሎች ሽማግሌዎችን ያካተተ ሆነ። ጉባኤዎቹ የእነዚህን ታማኝ ወንዶች መመሪያ በመከተላቸው “በእምነት እየጠነከሩና ከዕለት ወደ ዕለት በቁጥር እየጨመሩ ሄዱ።” (ሥራ 16:4, 5) በዘመናችንም የይሖዋ ድርጅት የሚሰጠንን ቲኦክራሲያዊ መመሪያ ስንከተል እንባረካለን። ይሁንና ይሖዋ ወኪሎቹ አድርጎ የሾማቸውን ሰዎች ለመታዘዝ ፈቃደኞች ባንሆን ምን ይሰማዋል? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት፣ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር እየተጓዙ በነበረበት ወቅት ምን እንዳጋጠማቸው እንመልከት።

11. በጥንቷ እስራኤል ዘመን አምላክ ለሕዝቡ መመሪያ እንዲሰጥ የመረጠውን ሙሴን የተገዳደሩት ሰዎች ምን ደርሶባቸዋል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

11 እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር እየተጓዙ በነበረበት ወቅት አንዳንድ ተሰሚነት የነበራቸው ሰዎች ሙሴንና ይሖዋ የሰጠውን ሥልጣን ተገዳደሩ። እንዲህ ብለዋል፦ “[ሙሴ ብቻ ሳይሆን] መላው ማኅበረሰብ እኮ ቅዱስ ነው፤ ሁሉም ቅዱስ ናቸው፤ ይሖዋም በመካከላቸው ነው።” (ዘኁ. 16:1-3) በይሖዋ ዓይን መላው ብሔር ቅዱስ መሆኑ እውነት ቢሆንም ሕዝቡን እንዲመራ ይሖዋ የመረጠው ሙሴን ነው። (ዘኁ. 16:28) እነዚህ ዓመፀኞች ሙሴን ሲተቹ ይሖዋን እንደተቹ ይቆጠራል። ያተኮሩት ይሖዋ በሚፈልገው ነገር ላይ ሳይሆን እነሱ በሚፈልጉት ማለትም ተጨማሪ ሥልጣንና ተሰሚነት በማግኘት ላይ ነበር። አምላክ ዓመፁን የቀሰቀሱትን ሰዎችና ከእነሱ ጋር የተባበሩትን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አጥፍቷቸዋል። (ዘኁ. 16:30-35, 41, 49) ዛሬም ይሖዋ ለድርጅታዊ መመሪያዎቹ አክብሮት በሌላቸው ሰዎች እንደማይደሰት እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

ማንን ትደግፍ ነበር? (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት)


12. በይሖዋ ድርጅት ላይ ምንጊዜም መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?

12 በይሖዋ ድርጅት ላይ ምንጊዜም እምነት መጣል እንችላለን። አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የተረዳንበት መንገድ ወይም የመንግሥቱ ሥራ የተደራጀበት መንገድ ማስተካከያ እንደሚያስፈልገው ግልጽ ሲሆን አመራር የሚሰጡት ወንድሞች አስፈላጊውን ማስተካከያ ከማድረግ ወደኋላ አይሉም። (ምሳሌ 4:18) ይህን የሚያደርጉት ከምንም ነገር በላይ ይሖዋን ማስደሰት ስለሚፈልጉ ነው። በተጨማሪም ውሳኔዎቻቸው የይሖዋ ሕዝቦች ሁሉ ሊከተሉት የሚገባ መሥፈርት በሆነው በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ።

13. ‘የትክክለኛው ትምህርት መሥፈርት’ ምንድን ነው? ምን ልናደርገውስ ይገባል?

13 ‘የትክክለኛውን ትምህርት መሥፈርት አጥብቀህ ያዝ።’ (2 ጢሞ. 1:13) ‘የትክክለኛው ትምህርት መሥፈርት’ የሚለው አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ክርስቲያናዊ ትምህርቶች ያመለክታል። (ዮሐ. 17:17) የምናምንባቸው ነገሮች ሁሉ የተመሠረቱት በእነዚህ ትምህርቶች ላይ ነው። የይሖዋ ድርጅት ይህን መሥፈርት አጥብቀን እንድንከተል አስተምሮናል። ይህን ማድረጋችንን እስከቀጠልን ድረስ እንባረካለን።

14. አንዳንድ ክርስቲያኖች ‘የትክክለኛውን ትምህርት መሥፈርት’ አጥብቀው ሳይዙ የቀሩት እንዴት ነው?

14 ‘የትክክለኛውን ትምህርት መሥፈርት’ አጥብቀን ባንከተል ምን ሊከሰት ይችላል? አንድ ምሳሌ እንመልከት። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች መካከል ‘የይሖዋ ቀን ደርሷል’ የሚል ወሬ መዛመት ጀምሮ የነበረ ይመስላል። እንዲህ ዓይነት ሐሳብ የያዘ በሐዋርያው ጳውሎስ የተጻፈ የሚመስል ደብዳቤ ደርሷቸው ሊሆን ይችላል። አንዳንድ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ጊዜ ወስደው እውነታውን ሳያጣሩ ወሬውን ያመኑ ከመሆኑም በተጨማሪ ለሌሎች አሰራጭተውት ነበር። ጳውሎስ ከእነሱ ጋር በነበረበት ጊዜ ያስተማራቸውን ነገር ቢያስታውሱ ኖሮ እንዲህ ባለው ወሬ ባልተታለሉ ነበር። (2 ተሰ. 2:1-5) ጳውሎስ ወንድሞቹን የሰሙትን ሁሉ እንዳያምኑ መክሯቸዋል። ጳውሎስ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በድጋሚ ለስህተት እንዳይጋለጡ ሲል ሁለተኛውን ደብዳቤውን የደመደመው እንዲህ በማለት ነው፦ “እኔ ጳውሎስ በገዛ እጄ የጻፍኩላችሁ ሰላምታ ይድረሳችሁ፤ ይህ የእጅ ጽሑፍ የደብዳቤዎቼ ሁሉ መለያ ነው፤ አጻጻፌ እንዲህ ነው።”—2 ተሰ. 3:17

15. እውነት መስለው ከሚቀርቡ ውሸቶች ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? አንድ ምሳሌ ጥቀስ። (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

15 ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ከተናገረው ሐሳብ ምን እንማራለን? ከመጽሐፍ ቅዱስ ከተማርናቸው እውነቶች ጋር የማይስማማ ነገር ወይም አስደንጋጭ ወሬ ስንሰማ የማስተዋል ችሎታችንን መጠቀም ይኖርብናል። በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ውስጥ ጠላቶቻችን ከዋናው መሥሪያ ቤት የተላከ የሚመስል ደብዳቤ አሰራጭተው ነበር። ደብዳቤው አንዳንድ ወንድሞች የራሳቸውን ድርጅት እንዲያቋቁሙ የሚያበረታታ ነበር። ደብዳቤው ሲታይ እውነተኛ ይመስላል። ታማኝ የሆኑ ወንድሞች ግን በዚህ አልተታለሉም። ደብዳቤው የያዘው መልእክት አስቀድመው ከተማሯቸው ነገሮች ጋር እንደማይስማማ አስተዋሉ። ዛሬም የእውነት ጠላቶች አንዳንድ ጊዜ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ግራ እንድንጋባና በመካከላችን መከፋፈል እንዲፈጠር ለማድረግ ይጥራሉ። ‘የማመዛዘን ችሎታችን በቀላሉ እንዲናወጥ’ ከመፍቀድ ይልቅ የሰማነው ወይም ያነበብነው ነገር ከተማርናቸው እውነቶች ጋር የሚስማማ መሆን አለመሆኑን በመመዘን ራሳችንን መጠበቅ እንችላለን።—2 ተሰ. 2:2፤ 1 ዮሐ. 4:1

እውነት መስለው በቀረቡ ውሸቶች አትታለል (አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት) a


16. በሮም 16:17, 18 መሠረት አንድ ሰው እውነትን አጥብቆ ካልያዘ ምን ልናደርግ ይገባል?

16 ለይሖዋ ታማኝ ከሆኑት ጋር ያለህን አንድነት ጠብቅ። ይሖዋ አንድነት ባለው መንገድ እንድናመልከው ይፈልጋል። እውነትን አጥብቀን እስከያዝን ድረስ አንድነታችንን መጠበቅ እንችላለን። እውነትን አጥብቀው የማይዙ ሰዎች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ መከፋፈል ይፈጥራሉ፤ በመሆኑም አምላክ ከእነሱ ‘እንድንርቅ’ አሳስቦናል። አለዚያ እኛ ራሳችን ከእውነት ልንርቅ እንችላለን።—ሮም 16:17, 18ን አንብብ።

17. እውነትን ለይተን በማወቃችንና አጥብቀን በመያዛችን ምን በረከቶችን እናገኛለን?

17 እውነትን ለይተን ስናውቅና አጥብቀን ስንይዝ መንፈሳዊ ደህንነታችንና ጤንነታችን ይጠበቃል። (ኤፌ. 4:15, 16) ከሰይጣን የሐሰት ትምህርቶችና ፕሮፓጋንዳ እንጠበቃለን። እንዲሁም በታላቁ መከራ ወቅት የይሖዋን ጥበቃና እንክብካቤ እናገኛለን። እንግዲያው እውነት የሆነውን ነገር አጥብቀህ ያዝ፤ ‘የሰላምም አምላክ ከአንተ ጋር ይሆናል።’—ፊልጵ. 4:8, 9

መዝሙር 122 ጸንታችሁ ቁሙ፣ አትነቃነቁ!

a የሥዕሉ መግለጫ፦ ከአሥርተ ዓመታት በፊት በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት የነበሩ ወንድሞቻችን ከዋናው መሥሪያ ቤት የተላከ የሚመስል በጠላቶቻችን የተዘጋጀ ደብዳቤ ሲደርሳቸው የሚያሳይ ትወና። በዛሬው ጊዜ ጠላቶቻችን ኢንተርኔትን ተጠቅመው ስለ ይሖዋ ድርጅት አሳሳች መረጃ ሊያሰራጩ ይችላሉ።