በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የእሳት ሐይቅ ምንድን ነው? ገሃነም ነው? ወይስ ሲኦል?

የእሳት ሐይቅ ምንድን ነው? ገሃነም ነው? ወይስ ሲኦል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 የእሳት ሐይቅ ዘላማዊ ጥፋትን የሚያመለክት አገላለጽ ነው። የእሳት ሐይቅና ገሃነም አንድ ናቸው፤ ይሁን እንጂ የእሳት ሐይቅ፣ ሲኦልን ይኸውም የሰው ልጆች መቃብርን አያመለክትም።

በእውን ያለ ሐይቅ አይደለም

 “የእሳት ሐይቅ” በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተጠቀሰባቸው አምስት ቦታዎች በሙሉ የተሠራበት ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ነው፤ በመሆኑም በእውን ያለ አንድ ሐይቅ አይደለም። (ራእይ 19:20፤ 20:10, 14, 15፤ 21:8) ወደ እሳት ሐይቅ የሚጣሉት እነማን ናቸው?

  •   ዲያብሎስ፦ (ራእይ 20:10) ዲያብሎስ መንፈሳዊ አካል ያለው ፍጥረት እንደመሆኑ መጠን እሳት ሊጎዳው አይችልም።—ዘፀአት 3:2፤ መሳፍንት 13:20

  •   ሞት፦ (ራእይ 20:14) የሕይወት ተቃራኒና ከሕልውና ውጭ መሆንን የሚያመለክት ነገር እንጂ አካል ያለው ነገር አይደለም። (መክብብ 9:10) በመሆኑም ሞት በእሳት ሊቃጠል አይችልም።

  •   “አውሬው” እና “ሐሰተኛው ነቢይ”፦ (ራእይ 19:20) እነዚህ ነገሮች ምሳሌያዊ ትርጉም ያላቸው ነገሮች ናቸው፤ ታዲያ እነሱ የተጣሉበት ሐይቅም ምሳሌያዊ ትርጉም ያለው እንጂ በእውን ያለ ሐይቅ አይደለም ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ አይሆንም?—ራእይ 13:11, 12፤ 16:13

ዘላለማዊ ጥፋትን ያመለክታል

 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ስለ እሳት ሐይቅ ሲናገር “ሁለተኛው ሞት ማለት ነው” ይላል። (ራእይ 20:14፤ 21:8) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጸው የመጀመሪያው ሞት በአዳም ኃጢአት ምክንያት የመጣው ሞት ነው። በአዳም ኃጢአት ምክንያት የሞቱ ሰዎች በትንሣኤ አማካኝነት እንደገና ሕይወት ማግኘት ይችላሉ፤ ደግሞም ወደፊት አምላክ ሞትን ያስወግደዋል።—1 ቆሮንቶስ 15:21, 22, 26

ምሳሌያዊ ትርጉም ካለው የእሳት ሐይቅ መውጣት የሚቻልበት መንገድ የለም

 የእሳት ሐይቅ ግን ከዚህ የሚለይ ሲሆን ሁለተኛውን ሞት ያመለክታል። ይህ ዓይነቱ ሞትም ሙሉ በሙሉ ከሕልውና ውጭ መሆን ማለት ነው፤ ይሁን እንጂ ለሁለተኛው ሞት ትንሣኤ እንደሚኖር መጽሐፍ ቅዱስ አይገልጽም። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ “የሞትና የሲኦል መክፈቻ” እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፤ ይህም ኢየሱስ በአዳም ኃጢአት ምክንያት የሞቱ ሰዎችን ከሞት እስራት የማስለቀቅ ሥልጣን እንዳለው የሚያሳይ ነው። (ራእይ 1:18፤ 20:13 አ.መ.ት) ይሁንና የእሳት ሐይቅ መክፈቻ ለኢየሱስም ሆነ ለማንም አልተሰጠም። ይህ ምሳሌያዊ ሐይቅ፣ ዘላለማዊ ቅጣትን ይኸውም ለዘለቄታው መጥፋትን የሚያመለክት ነው።—2 ተሰሎንቄ 1:9

ከገሃነም ማለትም ከሄኖም ሸለቆ ጋር አንድ ነው

 ገሃነም ተብሎ የተትረጎመው ጌኤና የሚለው ግሪክኛ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 12 ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። ልክ እንደ እሳት ሐይቅ ሁሉ ገሃነምም ዘላለማዊ ጥፋትን ያመለክታል። በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ ይህ ቃል “ሲኦል” (በዕብራይስጥ ሺኦል፣ በግሪክኛ ሔዲስ) ተብሎ ቢተረጎምም ገሃነምና ሲኦል የተለያዩ ነገሮች ናቸው።

የሄኖም ሸለቆ

 ገሃነም ቃል በቃል ሲተረጎም “የሄኖም ሸለቆ” ማለት ነው፤ ይህ ከኢየሩሳሌም ውጭ የሚገኝ ስፍራ ነው። በጥንት ዘመን የከተማይቱ ነዋሪዎችን በዚህ ሸለቆ ውስጥ ቆሻሻ ይጥሉ ነበር። በዚያ የሚጣለውን ቆሻሻ ለማቃጠል ሲባል እሳቱ ሁልጊዜ እንዲነድ ይደረግ ነበር፤ እሳቱ ያልደረሰበትን ደግሞ ትሎች ይበሉታል።

 ኢየሱስ ገሃነምን የጠቀሰው ዘላለማዊ ጥፋትን ለማመልከት ነው። (ማቴዎስ 23:33) “በገሃነም ትላቸው አይሞትም፤ እሳቱም አይጠፋም” በማለት ተናግሯል። (ማርቆስ 9:47, 48) ኢየሱስ የተናገረው ይህ ሐሳብ፣ በሄኖም ሸለቆ ያለውን ሁኔታ እንዲሁም በኢሳይያስ 66:24 ላይ የሚገኘውን “ወጥተውም በእኔ ላይ ያመፁትን ሰዎች ሬሳ ያያሉ፤ ትላቸው አይሞትም፤ እሳታቸው አይጠፋም” የሚለውን ትንቢት ያስታውሰናል። በመሆኑም የኢየሱስ ምሳሌ የሚገልጸው መሠቃየትን ሳይሆን ሙሉ በሙሉ መጥፋትን ነው። ትሎቹ እና እሳቱ የሚበሉት ሬሳዎችን እንጂ በሕይወት ያሉ ሰዎችን አይደለም።

 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከገሃነም መውጣት እንደሚቻል የሚጠቁም ሐሳብ አይገኝም። “የእሳት ሐይቅ” እና “እሳታማ ገሃነም” የሚያመለክቱት ትንሣኤ የሌለውን ዘላለማዊ ጥፋት ነው።—ራእይ 20:14, 15፤ 21:8፤ ማቴዎስ 18:9

“ከዘላለም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሠቃያሉ” ሲባል ምን ማለት ነው?

 የእሳት ሐይቅ ዘላለማዊ ጥፋትን የሚያመለክት ምሳሌያዊ አባባል ከሆነ ዲያብሎስ፣ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ በእሳት ሐይቅ ውስጥ “ከዘላለም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት [እንደሚሠቃዩ]” መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ለምንድን ነው? (ራእይ 20:10) በዚህ ጥቅስ ላይ የተገለጸው ሥቃይ፣ ቃል በቃል እንዳልሆነ የሚጠቁሙ አራት ምክንያቶችን እስቲ እንመልከት፦

  1.   ሰይጣን ለዘላለም እንዲሠቃይ ከተፈለገ ለዘላለም እንዲኖር ይደረጋል ማለት ነው። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ሰይጣን እንዳልነበረ እንደሚደረግ ይኸውም ከሕልውና ውጭ እንደሚሆን ነው።—ዕብራውያን 2:14

  2.   ለዘላለም መኖር ቅጣት ሳይሆን የአምላክ ስጦታ ነው።—ሮም 6:23

  3.   አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ምሳሌያዊ ነገሮች በመሆናቸው ቃል በቃል ሥቃይ ሊሰማቸው አይችልም።

  4.   በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከሚገኙት ሌሎች ሐሳቦች እንደምንረዳው ዲያብሎስ እንደሚሠቃይ የሚገልጸው ሐሳብ ለዘላለም እንደሚታገድ ወይም እንደሚጠፋ የሚያመለክት ነው።

 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘መሠቃየትን’ ለማመልከት የተሠራበት ቃል “መታገድን” ጭምር ሊያመለክት ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በማቴዎስ 18:34 ላይ የተጠቀሱትን ‘የወኅኒ ቤት ጠባቂዎች’ ለማመልከት የገባው ቃል በግሪክኛ ‘የሚያሠቃዩ ሰዎች’ (የ1954 ትርጉም) የሚል ትርጉም አለው፤ ይህም በግሪክኛ ‘መሠቃየት’ እና ‘መታገድ’ በሚሉት ቃላት መካከል ዝምድና እንዳለ ይጠቁማል። ከዚህም በተጨማሪ፣ በማቴዎስ 8:29 ላይ የተጠቀሰው ‘መሠቃየት’ ተመሳሳይ ዘገባ በያዘው በሉቃስ 8:30, 31 ላይ “ጥልቁ” ተብሏል፤ “ጥልቁ” የሚለው ቃል ደግሞ እንቅስቃሴ ማድረግ አለመቻልን ወይም መሞትን የሚያመለክት ምሳሌያዊ ቦታ ነው። (ሮም 10:7፤ ራእይ 20:1, 3) እንዲያውም በራእይ መጽሐፍ ውስጥ በበርካታ ቦታዎች ላይ ‘ሥቃይ’ የሚለው ቃል የተሠራበት ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ነው።—ራእይ 9:5፤ 11:10፤ 18:7, 10