በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ተስፋ የሚሰጥ ነገር ከየት ማግኘት እችላለሁ?

ተስፋ የሚሰጥ ነገር ከየት ማግኘት እችላለሁ?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 አምላክ ‘የተሻለ ሕይወትና ተስፋ’ a ሊሰጠን እንደሚፈልግ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኤርምያስ 29:11) ደግሞም አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን ለእኛ የሰጠበት አንዱ ምክንያት “ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ ተስፋ ይኖረን ዘንድ” ነው። (ሮም 15:4) ከዚህ ቀጥሎ እንደምናየው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ ያዘለ ምክር በየዕለቱ የሚያጋጥሙንን ችግሮች አዎንታዊ አመለካከት ይዘን እንድንወጣ ይረዳናል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጪው ጊዜ የሚናገራቸው ሐሳቦች ደግሞ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩህ ተስፋ እንዲኖረን ያደርጋሉ።

እዚህ ገጽ ላይ፦

 መጽሐፍ ቅዱስ አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረን የሚረዳን እንዴት ነው?

 መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወታችን የተሻለ እንዲሆን ልንወስዳቸው የሚገቡንን እርምጃዎች ይነግረናል፤ እነዚህን እርምጃዎች መውሰዳችን ስለ ሕይወት አዎንታዊ አመለካከት እንድንይዝ ይረዳናል። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

  •   ጠቃሚ መመሪያ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስን አንብብ። መዝሙር 119:105 “ቃልህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው” ይላል። ጥሩ የእጅ ባትሪ ሁለት ነገሮች ሊያደርግልን ይችላል። አንደኛ፣ አጠገባችን ምን እንዳለ ያሳየናል፤ ሁለተኛ ደግሞ ከርቀት ምን እንዳለ ለማየት ያስችለናል። በተመሳሳይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ጠቃሚ መመሪያዎች፣ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የሚያጋጥሙንን ችግሮች ስኬታማ በሆነ መንገድ እንድንወጣቸው ይረዱናል፤ ይህም እያንዳንዱን ዕለት ብሩህ አመለካከት ይዘን ለማሳለፍ ያስችለናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ኃይል ያድሳሉ፤ እንዲሁም “ልብን ደስ ያሰኛሉ።” (መዝሙር 19:7, 8) ከመጽሐፍ ቅዱስ የምናገኘው ሌላም ጥቅም አለ፤ ወደፊት አምላክ ለሰው ልጆችም ሆነ ለምድር ሊያደርግ ስላሰበው አስደናቂ ነገር ይነግረናል። ይህ ተስፋ ዘላቂ ደስታና እርካታ እንዲኖረን ያደርጋል።

  •   የሌሎችን እርዳታ ተቀበል። ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ሲያጋጥመን ራሳችንን ከቤተሰባችን ወይም ከወዳጆቻችን ማግለል ሊቀናን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ማድረግ ጎጂ እንደሆነ ይናገራል፤ የሞኝነት ውሳኔ ወደ ማድረግ ወይም የሞኝነት እርምጃ ወደ መውሰድ ሊመራን ይችላል። (ምሳሌ 18:1) ቤተሰቦቻችንና ወዳጆቻችን በትክክል እንድናስብ ይረዱናል። የገጠመንን አስቸጋሪ ሁኔታ እንዴት እንደምንወጣ ጠቃሚ ምክር ሊሰጡንም ይችላሉ። (ምሳሌ 11:14) ሌላው ቢቀር፣ ‘አይዞህ/አይዞሽ’ በማለት ያበረታቱናል እንዲሁም ያጽናኑናል፤ ይህም ያለንበት ሁኔታ እስኪለወጥ ድረስ ጥንካሬ እንድናገኝ ይረዳናል።—ምሳሌ 12:25

  •   ወደ አምላክ ጸልይ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል፤ እሱም ይደግፍሃል። ጻድቁ እንዲወድቅ ፈጽሞ አይፈቅድም።” b (መዝሙር 55:22) ይሖዋ “ተስፋ የሚሰጠው አምላክ” ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው። (ሮም 15:13) ስለ አንተ እንደሚያስብ ተማምነህ ‘የሚያስጨንቅህን ነገር ሁሉ’ ንገረው። (1 ጴጥሮስ 5:7) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ሲናገር “ጽኑ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል፤ ደግሞም ያጠነክራችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል” ይላል።—1 ጴጥሮስ 5:10

  •   የሕይወት ፈተናዎች ተስፋህን እንዲያለመልሙት እንጂ እንዲያጨልሙት አትፍቀድ። አምላክ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲህ ሲል ቃል ገብቶልናል፦ “እኔን የሚሰማ ሰው ግን ተረጋግቶ ይኖራል፤ መከራ ይደርስብኛል የሚል ስጋትም አያድርበትም።” (ምሳሌ 1:33) በአውስትራሊያ የምትኖረው ማርጋሬት፣ ቤቷ በአውሎ ነፋስ በተመታበት ወቅት አብዛኛውን ንብረቷን አጣች። ሆኖም ማርጋሬት በደረሰባት ነገር ተስፋ አልቆረጠችም። ከዚህ ይልቅ ይህ ሁኔታ አንድ ትልቅ ትምህርት አስተምሯት አልፏል፤ ይኸውም ሀብትና ንብረት አላፊ ጠፊ እንደሆነ ተምራለች። ይህ ሁኔታ ከደረሰባት በኋላ፣ በሕይወት ውስጥ በጣም አስፈላጊ በሆኑት ነገሮች ላይ ይበልጥ ትኩረት ለማድረግ ወሰነች፤ ለቤተሰቧና ለወዳጆቿ፣ ከአምላክ ጋር ላላት ዝምድና እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኘው ተስፋ ትኩረት ለመስጠት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቆረጠች።—መዝሙር 37:34፤ ያዕቆብ 4:8

 መጽሐፍ ቅዱስ የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ለሰው ልጆች ምን ተስፋ ይሰጣል?

 መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆችንም ሆነ ምድርን በተመለከተ የሚሰጠው ተስፋ ብሩህ ነው። ይህ ተስፋ ደግሞ በቅርቡ ይፈጸማል። እንዲያውም ዛሬ የሰውን ዘር እያጋጠሙ ያሉት ችግሮች፣ የምንኖረው በዚህ ክፉ ዓለም ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ ውስጥ እንደሆነ የሚጠቁሙ ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) በቅርቡ አምላክ ምድርን ሙሉ በሙሉ ማስተዳደር ይጀምራል፤ ከዚያም ግፍና መከራን ያስወግዳል። ይህን የሚያደርገው የአምላክ መንግሥት ተብሎ በሚጠራ ዓለም አቀፍ መንግሥት አማካኝነት ነው። (ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 11:15) ኢየሱስ፣ ባስተማረው የጸሎት ናሙና ላይ “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ . . . በምድርም ላይ ይፈጸም” ያለው ሰማይ ላይ ያለውን ይህን መንግሥት በአእምሮው ይዞ ነው።—ማቴዎስ 6:9, 10

 አምላክ ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በግልጽ ተቀምጧል። የአምላክ መንግሥት ከሚያስወግዳቸው ችግሮች መካከል አንዳንዶቹን ተመልከት።

  •   ረሃብ ይወገዳል። “ምድር ፍሬዋን ትሰጣለች።”—መዝሙር 67:6

  •   በሽታ ይወገዳል። “በዚያም የሚቀመጥ ማንኛውም ሰው ‘ታምሜአለሁ’ አይልም።”—ኢሳይያስ 33:24

  •   ሞት ይወገዳል። አምላክ “እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”—ራእይ 21:3, 4

a ለማግኘት የምንመኘውን ወይም አንድ ቀን እናገኘዋለን ብለን የምናስበውን ነገር በተስፋ እንጠብቀዋለን። ወደፊት ይሆናል ብለን በጉጉት የምንጠብቀው ነገርም ተስፋ ሊባል ይችላል።

b መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ ስም ይሖዋ ነው።