በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ማቴዎስ 6:33—“ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥት . . . ፈልጉ”

ማቴዎስ 6:33—“ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥት . . . ፈልጉ”

 “እንግዲያው ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ ፈልጉ፤ እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይሰጧችኋል።”—ማቴዎስ 6:33 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።”—ማቴዎስ 6:33 የ1954 ትርጉም

የማቴዎስ 6:33 ትርጉም

 የአምላክ መንግሥት የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም የሚያደርግ በሰማይ ያለ መንግሥት ነው። (ማቴዎስ 6:9, 10) አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ለአምላክ መንግሥት የመጀመሪያውን ቦታ ከሰጠ የአምላክን መንግሥት እየፈለገ ነው ሊባል ይችላል። a ይህም ግለሰቡ ስለ አምላክ መንግሥት ለመማር ባለው ፍላጎት ይገለጻል፤ ከዚህም በተጨማሪ የአምላክን መንግሥት የሚያስቀድም ሰው፣ መንግሥቱ ወደፊት ስለሚያመጣቸው መልካም ነገሮች ለሌሎች ይናገራል። (ማቴዎስ 24:14) እንዲሁም ይህ መንግሥት እንዲመጣ ይጸልያል።—ሉቃስ 11:2

 የአምላክ ጽድቅ አምላክ ትክክል ወይም ስህተት ስለሆኑ ነገሮች ያወጣቸውን መሥፈርቶች ይጨምራል። (መዝሙር 119:172) ስለዚህ የአምላክን ጽድቅ የሚፈልግ ሰው፣ አምላክ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር ሕጎች ይታዘዛል፤ እነዚህ ሕጎች ደግሞ ምንጊዜም ጠቃሚ ናቸው።—ኢሳይያስ 48:17

 እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይሰጧችኋል የሚለው ሐሳብ፣ አምላክ ቃል የገባልን ነገር እንዳለ ያሳያል፤ አምላክ በሕይወታቸው ውስጥ ለእሱ መንግሥትና ለመሥፈርቶቹ ቅድሚያ ለሚሰጡ ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል።—ማቴዎስ 6:31, 32

የማቴዎስ 6:33 አውድ

 ኢየሱስ ይህን ሐሳብ የተናገረው፣ ከማቴዎስ ምዕራፍ 5-7 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው የተራራ ስብከቱ ላይ ነው። ኢየሱስን ያዳምጡት ከነበሩት ሰዎች ብዙዎቹ ድሆች እንደነበሩ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። ስለዚህ በሕይወታቸው ውስጥ በዋነኝነት የሚያሳስባቸው ነገር ኑሮን የማሸነፍ ጉዳይ ሊሆን ይችላል፤ ይህ ደግሞ የአምላክን መንግሥት ለመፈለግ ጊዜ ያሳጣቸዋል። ሆኖም ኢየሱስ፣ አምላክ ተክሎችንና እንስሳትን እንዴት እንደሚንከባከብ ልብ እንዲሉ አበረታቷቸዋል። አምላክ ለመንግሥቱ ቅድሚያ የሚሰጡ ሰዎችንም እንደሚንከባከባቸው ቃል ገብቷል።—ማቴዎስ 6:25-30

ሰዎች ስለ ማቴዎስ 6:33 ያላቸው የተሳሳተ ግንዛቤ

 የተሳሳተ ግንዛቤ፦ የአምላክን መንግሥት የሚፈልግ ሰው ሀብታም ይሆናል።

 እውነታው፦ ለአምላክ መንግሥት ቅድሚያ የሚሰጡ ሰዎች፣ ምግብና ልብስን ጨምሮ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች እንደሚያገኙ ኢየሱስ ተናግሯል። (ማቴዎስ 6:25, 31, 32) የቅንጦት ሕይወት እንደሚኖራቸው ግን ቃል አልገባም፤ አምላክ የሚሰጠው በረከት የሚለካው አንድ ሰው በሚያገኘው ሀብት መጠን እንደሆነም አልተናገረም። እንዲያውም ኢየሱስ፣ ሀብት ለማግኘት መጣጣር አደገኛ እንደሆነ አድማጮቹን አስጠንቅቋል፤ ምክንያቱም እንዲህ የሚያደርግ ሰው፣ የአምላክን መንግሥት ማስቀደም ከባድ ይሆንበታል። (ማቴዎስ 6:19, 20, 24) ሐዋርያው ጳውሎስ ለአምላክ መንግሥት ሲል ብዙ ደክሟል፤ ሆኖም አንዳንድ ነገሮችን ያጣበት ጊዜ ነበር። እንደ ኢየሱስ ሁሉ እሱም ሀብታም ለመሆን መጣጣር አደገኛ እንደሆነ አስጠንቅቋል።—ፊልጵስዩስ 4:11, 12፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:6-10

 የተሳሳተ ግንዛቤ፦ ክርስቲያኖች፣ መተዳደሪያ ለማግኘት መሥራት አያስፈልጋቸውም።

 እውነታው፦ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው፣ ክርስቲያኖች ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር መሥራት ይኖርባቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 4:11, 12፤ 2 ተሰሎንቄ 3:10፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:8) ኢየሱስ ያለው ‘መንግሥቱን ብቻ ፈልጉ’ ሳይሆን ‘አስቀድማችሁ መንግሥቱን ፈልጉ’ ነው።

 የአምላክን መንግሥት የሚያስቀድሙና መተዳደሪያ ለማግኘት ጠንክረው የሚሠሩ ሁሉ አምላክ ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንደሚሰጣቸው መተማመን ይችላሉ።—1 ጢሞቴዎስ 6:17-19

a “ፈልጉ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ግስ፣ ቀጣይነት ያለው ድርጊትን ያመለክታል፤ ሐሳቡ “መፈለጋችሁን ቀጥሉ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ስለዚህ የአምላክ መንግሥት በሕይወታችን ውስጥ ሁልጊዜም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነገር እንጂ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ትኩረት የምንሰጠው ጉዳይ አይደለም።