በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ፊልጵስዩስ 4:6, 7—“ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ”

ፊልጵስዩስ 4:6, 7—“ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ”

 “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።”—ፊልጵስዩስ 4:6, 7 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋር ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለማንኛውም ነገር አትጨነቁ። ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።”—ፊልጵስዩስ 4:6, 7 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

የፊልጵስዩስ 4:6, 7 ትርጉም

 የአምላክ አገልጋዮች ከልክ በላይ የሚያስጨንቋቸውን ወይም የሚያሳስቧቸውን ነገሮች ለእሱ በጸሎት በመንገር እፎይታ ማግኘት ይችላሉ። አምላክ ውስጣዊ ሰላም እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል፤ ይህ ውስጣዊ ሰላም ጭንቀታቸውን ለመቋቋም እንዲሁም አስተሳሰባቸውንና ስሜታቸውን ለመጠበቅ ይረዳቸዋል። ቁጥር 6 እንዲህ ዓይነቱን ሰላም ለማግኘት የሚረዱ የጸሎት ዓይነቶችን ይዘረዝራል።

 ምልጃ አምላክን አጥብቆ መለመንን ወይም መማጸንን የሚጠይቅ የጸሎት ዓይነት ነው። አንድ ሰው የሚያስጨንቅ ነገር ሲያጋጥመው ወይም አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ሲገባ ለአምላክ ምልጃ ማቅረብ ይችላል፤ ኢየሱስም እንዲሁ አድርጓል። (ዕብራውያን 5:7) በአብዛኛው እንዲህ ዓይነቱ ጸሎት በተደጋጋሚ የሚቀርብ ነው።

 ልመና የምንፈልገውን ነገር ለይተን በመጥቀስ ለአምላክ የምናቀርበው የጸሎት ዓይነት ነው። የአምላክ አገልጋዮች “ስለ ሁሉም ነገር” ልመና ማቅረብ ይችላሉ። ሆኖም እነዚህ ጸሎቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጸው የአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማሙ መሆን አለባቸው።—1 ዮሐንስ 5:14

 የምስጋና ጸሎት አምላክ ከዚህ በፊት ላደረገልንና ወደፊት ለሚያደርግልን ነገሮች ያለንን አመስጋኝነት የምንገልጽበት ጸሎት ነው። አምላክን እንድናመሰግን በሚያደርጉን ምክንያቶች ላይ ማሰላሰላችን ደስታችንን ጠብቀን እንድንኖር ይረዳናል።—1 ተሰሎንቄ 5:16-18

 አምላክ ለአገልጋዮቹ ውስጣዊ ሰላም በመስጠት እንዲህ ላሉት ጸሎቶች ምላሽ ይሰጣል። “የአምላክ ሰላም” ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት የሚፈጥረው የመረጋጋት ስሜት ነው። (ሮም 15:13፤ ፊልጵስዩስ 4:9) ይህ ሰላም “ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ” ነው የተባለው ከአምላክ የሚገኝ ስለሆነና የሚያስገኘው ውጤት ከምንጠብቀው በላይ ስለሆነ ነው።

 ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ፣ የአምላክ ሰላም ልባችንን እንደሚጠብቅልን ይናገራል። እዚህ ላይ “ይጠብቃል” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል፣ ከውትድርና ጋር በተያያዘ የሚሠራበት ቃል ነው፤ ቃሉ አንድን የታጠረ ከተማ እንዲጠብቁ የተመደቡ ወታደሮችን ያመለክታል። በተመሳሳይም የአምላክ ሰላም የአንድን ሰው ስሜትና አእምሮ ይጠብቅለታል። ይህም ግለሰቡ በገጠመው አስቸጋሪ ሁኔታ ከልክ በላይ እንዳይጨነቅ ይረዳዋል።

 የአምላክ ሰላም የሚጠብቀን “በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት” ነው፤ ምክንያቱም ከአምላክ ጋር ዝምድና መመሥረት የቻልነው በኢየሱስ አማካኝነት ነው። ኢየሱስ ለኃጢአታችን ሲል ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል። በኢየሱስ ላይ እምነት ካለን የአምላክን በረከት ማግኘት እንችላለን። (ዕብራውያን 11:6) በጸሎት አምላክ ፊት መቅረብ የምንችለውም በኢየሱስ በኩል ነው። ኢየሱስ “በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ብሏል።—ዮሐንስ 14:6፤ 16:23

የፊልጵስዩስ 4:6, 7 አውድ

 የፊልጵስዩስ መጽሐፍ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በፊልጵስዩስ a ከተማ ለሚገኙ ክርስቲያኖች የጻፈው ደብዳቤ ነው። አሁን ምዕራፍ 4 ላይ በሚገኘው የመጽሐፉ ክፍል ላይ፣ ጳውሎስ በዚያ ጉባኤ ያሉትን ክርስቲያኖች ደስተኛ እንዲሆኑ አበረታቷቸዋል፤ እንዲሁም እሱም እንዲደሰት የሚያደርግ ስጦታ በመላካቸው ለልግስናቸው አመስግኗቸዋል። (ፊልጵስዩስ 4:4, 10, 18) ጸሎት የአምላክን ሰላም የሚያስገኘው እንዴት እንደሆነ ጠቁሟቸዋል፤ እንዲሁም ይህን “የአምላክ ሰላም” ለማግኘት የሚረዱ አስተሳሰቦችንና ድርጊቶችን ዘርዝሯል።—ፊልጵስዩስ 4:8, 9

a ይህች ከተማ ትገኝ የነበረው በአሁኗ ግሪክ ውስጥ ነው።