በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፈጣሪ ስለመኖሩ እምነት ማዳበር ይቻላል?

ፈጣሪ ስለመኖሩ እምነት ማዳበር ይቻላል?

ፈጣሪ ስለመኖሩ እምነት ማዳበር ይቻላል?

“ፈጣሪ ሊኖር ይችላል ብዬ ሳስብ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰውን ሥቃይ ማስቆም የሚያስችል ኃይል እያለው ይህን ኃይሉን መጠቀም የማይፈልግ አካል እንዳለ ስለሚሰማኝ በጣም እናደዳለሁ!” ይህን የተናገረው በናዚ እልቂት የቤተሰቡን አባላት ያጣና አምላክ የለም ብሎ ያምን የነበረ ሰው ነው። ይሁንና እንዲህ የሚሰማው እሱ ብቻ አይደለም።

ሰዎች ጭካኔና ግፍ ሲደርስባቸው ብዙዎች አምላክ አለ ብሎ ማመን አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል፤ አሊያም አምላክ የለም የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ በመከተል ማጽናኛ ለማግኘት ይሞክራሉ። አንዳንድ ሰዎች አምላክ የለም እንዲሉ የሚያደርጓቸው ዋና ዋና ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው? አንዳንዶች እንደሚሰማቸው ሰዎች ያለ አምላክ ወይም ያለ ሃይማኖት የተሻለ ሕይወት መምራት ይችላሉ? በአምላክ መኖር የማያምን አንድ ሰው አፍቃሪ በሆነ ፈጣሪ ላይ እምነት ማዳበር ይችላል?

ሃይማኖት የሚሠራው ስህተት

አምላክ የለም ለሚለው ጽንሰ ሐሳብ መፈጠር ዋነኛው ምክንያት ሃይማኖት መሆኑ በጣም ያስገርማል። ታሪክ ጸሐፊ የሆኑት አለስተር መግራዝ እንዲህ ብለዋል፦ “ሰዎች አምላክ የለም ብለው እንዲያምኑ የሚያደርጋቸው ዋነኛው ነገር የሃይማኖት መብዛት እንዲሁም ሃይማኖታዊ ድርጅቶች የሚፈጽሙት ስህተት የሚፈጥርባቸው የጥላቻ ስሜት ነው።” ሃይማኖት ብዙውን ጊዜ የጦርነትና የዓመፅ መንስኤ እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። በአምላክ መኖር የማያምነው ሚሸል ኦንፍሬ የተባለው ፈላስፋ፣ ‘አንድ ሃይማኖታዊ መጽሐፍ በሁለት ጽንፍ ያሉ ሰዎችን ይኸውም አንደኛውን “እጅግ ቅዱስ የመሆን ምኞት” እንዲኖረው ሌላኛውን ደግሞ “ሰብዓዊነት የጎደለው የጭካኔ ድርጊት” ማለትም ሽብርተኝነት እንዲፈጽም እንዴት ሊያነሳሳ ይችላል?’ የሚለው ጥያቄ ያሳስበው ነበር።

ብዙ ሰዎች ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ መጥፎ ትዝታ አላቸው። በርትል የተባለ ስዊድናዊ ወጣት፣ ወታደር በነበረበት ጊዜ በሠራዊቱ ውስጥ ያለ አንድ ቄስ ጦርነቱ ትክክል መሆኑን ለማስረዳት ኢየሱስ ሰይፍ የሚመዙ ሁሉ በሰይፍ እንደሚጠፉ የተናገረውን ሐሳብ ጠቅሶ ነበር። ቀጥሎም ቄሱ ሰይፍ የሚመዙትን ለመቅጣት ሰይፍ የሚይዝ ሌላ ሰው መኖር እንዳለበት ከጠቀሰ በኋላ አንድ ወታደር የአምላክ አገልጋይ እንደሆነ ተናገረ!—ማቴዎስ 26:52 *

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ፈረንሳይ ውስጥ አባቷ የተገደለባት በርናዴት የተባለች ሴት፣ የሦስት ዓመት ልጅ የነበረችው የአክስቷ ልጅ ስትሞት በተደረገው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ቄሱ “አምላክ ይህችን ልጅ መልአክ እንድትሆን ወስዷታል” ብሎ መናገሩ በጣም አናዷት እንደነበር ታስታውሳለች። ከጊዜ በኋላ በርናዴት የአካል ጉዳት ያለበት ልጅ የወለደች ሲሆን በዚህ ጊዜም ከቤተ ክርስቲያኒቱ ምንም ማጽናኛ አላገኘችም።

ሰሜን አየርላንድ በብጥብጥ ትታመስ በነበረበት ወቅት የኖረው ኪረን፣ ስለ ገሃነመ እሳት የሚናገረው መሠረተ ትምህርት ያንገሸግሸው ነበር። ለሚታየው ክፋት ሁሉ ተጠያቂ የሚሆንን ማንኛውንም አምላክ እንደሚጠላ ከመናገሩም በላይ ‘በእርግጥ ካለህ እስቲ ግደለኝ’ በማለት አምላክን ይገዳደር ነበር። ቤተ ክርስቲያን ለምታስተምራቸው እንዲህ ላሉ ዘግናኝ መሠረተ ትምህርቶች ጥላቻ ያለው ኪረን ብቻ አይደለም። እንዲያውም የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ለዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ መፈጠር መንገድ ሳይጠርግ አልቀረም። አለስተር መግራዝ እንዳሉት ከሆነ ዳርዊን አምላክ መኖሩን እንዲጠራጠር ያደረገው በዝግመተ ለውጥ ማመኑ ሳይሆን ለገሃነመ እሳት መሠረተ ትምህርት የነበረው “ከፍተኛ ጥላቻ” ነው። መግራዝ አክለውም ዳርዊን “ሴት ልጁን በሞት በማጣቱ ምክንያት በጣም አዝኖ እንደነበር” ተናግረዋል።

አንዳንዶች ሃይማኖተኛ መሆንን ከሞኝነትና ከአክራሪነት ጋር ያያይዙታል። ትርጉም በሌላቸው ሃይማኖታዊ ስብከቶችና ዕለት ዕለት በሚደረጉ ቅዳሴዎች የተማረረችው ኢሪነ “ሃይማኖተኛ የሆኑ ሰዎች የሚያስቡ አይመስለኝም ነበር” በማለት ተናግራለች። ልዊ ደግሞ አክራሪዎች የሚፈጽሙት ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ምን ያህል ያንገሸግሸው እንደነበር ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ለብዙ ዓመታት ሃይማኖት አሰልቺ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር፤ አሁን ግን በሰዎች ላይ አስከፊ መዘዝ እንደሚያስከትል መገንዘብ ቻልኩ። ስለሆነም ሁሉንም ሃይማኖቶች ክፉኛ መቃወም ጀመርኩ።”

ሰዎች ያለ አምላክ የተሻለ ሕይወት መምራት ይችላሉ?

ብዙ ሰዎች ሃይማኖትን ለሰው ልጅ እድገትና ሰላም እንቅፋት እንደሆነ አድርገው ቢመለከቱት ምንም አያስገርምም። ሌላው ቀርቶ አንዳንዶች፣ ‘ሰዎች ያለ አምላክ ወይም ያለ ሃይማኖት የተሻለ ሕይወት መምራት ይችላሉ’ የሚል አስተሳሰብ አላቸው። ይሁንና ሃይማኖትን በጅምላ መጥላት የራሱ የሆነ ችግር ይኖረው ይሆን?

በ18ኛው መቶ ዘመን የኖረው ቮልቴር የተባለ ፈላስፋ፣ ምግባረ ብልሹ የሆነችው ቤተ ክርስቲያን በወቅቱ የምትፈጽመውን የጭካኔ ድርጊት አጥብቆ ይቃወም ነበር። ይሁንና ከሰው ልጆች የሚበልጥ ኃይል ያለው አንድ አካል አለ ብሎ ማመን ሥነ ምግባራችንን ጠብቀን ለመኖር መሠረታዊ ነገር እንደሆነ ያስብ ነበር። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ፍሬድሪክ ኒትሽ የተባለው ጀርመናዊ ፈላስፋ፣ አምላክ ሞቷል ብሎ በይፋ ተናግሮ ነበር፤ በሌላ በኩል ግን አምላክ የለም የሚል አስተሳሰብ መያዝ ሊያስከትለው የሚችለው ጉዳትና የሥነ ምግባር ውድቀት ፍርሃት አሳድሮበት ነበር። ይሁንና እንዲህ ያለው ፍርሃት ምክንያታዊ ነው?

የሰው ዘር ወደ ሥልጣኔ ዘመን ከገባ በኋላ የጭካኔ ድርጊት እየቀነሰ ከመሄድ ይልቅ “ከዚያ በፊት ሰዎች አስበውት በማያውቁት ሁኔታ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደደረሰ” ኪዝ ዎርድ የተባሉ ደራሲ ተናግረዋል። አምላክ የለም የሚለው ጽንሰ ሐሳብም ቢሆን ሰዎችን ምግባረ ብልሹነትንና ጽንፈኝነትን ጨምሮ ከሰብዓዊ አለፍጽምና ነፃ ሊያወጣቸው አልቻለም። እነዚህ እውነታዎች አምላክ የለም የሚሉትን ጨምሮ በርካታ አስተዋይ ሰዎች አምላክ አለ ብሎ ማመን ከሥነ ምግባር አንጻር ያለውን ጠቀሜታ እንዲገነዘቡ አድርጓቸዋል።

ኪዝ ዎርድ በአምላክ ማመን የሚያሳድረውን በጎ ተጽዕኖ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “አንድ ሰው እምነት ያለው መሆኑ አምላክ ለፈጠረው ዓለም አሳቢነት የማሳየት የሞራል ግዴታ እንዳለበት እንዲሰማው ያደርገዋል።” በቅርብ የተደረጉ በርካታ ጥናቶች እንዳሳዩት ለሌሎች ጥቅም የማሰብ ዝንባሌ ይበልጥ የሚታየው ሃይማኖተኛ በሆኑ ሰዎች ዘንድ ነው። እንዲህ ያለው ዝንባሌ ደግሞ ሰዎች በተወሰነ መጠን እርካታ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። እነዚህ ጥናቶች፣ ኢየሱስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” ብሎ የተናገረውን መሠረታዊ ሥርዓት እውነተኝነት ያጠናክራሉ።—የሐዋርያት ሥራ 20:35

በአምላክ መኖር የማያምን የነበረ አንድ የማኅበራዊ ግንኙነት ሠራተኛ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች ሕይወት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ አስገርሞታል። ይህ ሰው እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ሰዎች ራሳቸውንም ሆነ ሌሎችን ከሚጎዳ ባሕርይ እንዲላቀቁ ለመርዳት ለረጅም ዓመታት ጥረት ባደርግም ያገኘሁት ውጤት ያን ያህል አርኪ አይደለም፤ ይሁንና ሰዎች አስገራሚ ለውጥ አድርገው የተሻለ ሕይወት መምራት እንዲችሉ [መጽሐፍ ቅዱስ] ሲረዳቸው መመልከቴ አስደንቆኛል። ሰዎቹ ያደረጉት ለውጥ ቀጣይነት እንዳለውም ተመልክቻለሁ።”

ያም ሆኖ በአምላክ መኖር የማያምኑ አንዳንድ ግለሰቦች እንደሚናገሩት ሰዎች ሃይማኖተኛ መሆናቸው ጥሩዎችና ለሌሎች ጥቅም የሚያስቡ እንዲሆኑ ከማድረግ ይልቅ እርስ በርስ እንዲጨፋጨፉና ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ ምክንያት ሆኗል። እነዚህ ሰዎች፣ እምነት በአንዳንድ ሰዎች ላይ ጥሩ ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል ይገነዘቡ ይሆናል፤ ይሁንና በአምላክ ማመን ጥሩ እንደሆነ አምኖ መቀበል ይከብዳቸዋል። ለምን?

ሰዎች በአምላክ እንዳያምኑ የሚያደርጓቸው ተጨማሪ ምክንያቶች

ብዙዎች ዝግመተ ለውጥ መሠረት ያለው እውነት እንደሆነ ተምረዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አኒላ የተማረችው አምላክ የለም የሚለው አመለካከት በተስፋፋባት አገር በአልባኒያ ነው። እንዲህ በማለት ትናገራለች፦ “በትምህርት ቤት ውስጥ አምላክ መኖሩን ማመን ሞኝነትና ኋላ ቀርነት እንደሆነ ተምረናል። ስለ ዕፅዋትና ሕይወት ስላላቸው ሌሎች ነገሮች አስገራሚ ነገሮችን ሁልጊዜ እማር የነበረ ቢሆንም ሁሉንም ነገር የዝግመተ ለውጥ ውጤት እንደሆነ አድርጌ አስብ ነበር፤ እንዲህ ያለውን አመለካከት የምንይዘው ሳይንሳዊ አስተሳሰብ እንዳለን ሆኖ እንዲሰማን ያደርገን ስለነበር ነው።” አክላም “ያን ጊዜ የሚሰጡንን ማስረጃዎች በጭፍን መቀበል ነበረብን” ብላለች።

አንዳንድ ሰዎች በሁኔታዎች መመረራቸው በአምላክ መኖር እንዳያምኑ እንቅፋት ሊሆንባቸው ይችላል። የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት በመሄድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ተስፋ በሚሰብኩበት ወቅት ብዙውን ጊዜ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች ያጋጥሟቸዋል። ቀደም ሲል የተጠቀሰውን በርትልን አንድ ወጣት የይሖዋ ምሥክር አነጋግሮት ነበር። በርትል ከዚህ ወጣት ጋር ሲገናኝ በልቡ ‘ውይ ምስኪን! የማይሆን ቦታ ነው የመጣኸው!’ ብሎ እንደነበር ያስታውሳል። እንዲህ ብሏል፦ “ቤት እንዲገባ ከጋበዝኩት በኋላ ለአምላክ፣ ለመጽሐፍ ቅዱስና ለሃይማኖት ያለኝን ጥላቻ የሚገልጹ ቃላት አዥጎደጎድኩበት።”

ገስ የተባለ ስኮትላንዳዊ ፍትሕ የጎደለው ድርጊት ሲፈጸም መመልከት በጣም ያስጨንቀው ነበር። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ውይይት ማድረግ ሲጀምር በጣም ይጨቃጨቅና ይከራከር ነበር። ገስ ይጠይቃቸው የነበሩት ጥያቄዎች ዕብራዊው ነቢይ ዕንባቆም “ስለ ምን በደልን እንዳይ አደረግኸኝ? እንዴትስ ግፍ ሲፈጸም ትታገሣለህ?” በማለት ለአምላክ ካቀረበው ጥያቄ ጋር ይመሳሰላሉ።—ዕንባቆም 1:3

በተጨማሪም ሰዎች፣ አምላክ ለክፋት ግድየለሽ እንደሆነ አድርገው ማሰባቸው ለጭንቀት ዳርጓቸዋል። (መዝሙር 73:2, 3) ሲሞን ደቦቭዋር የተባለች ፈረንሳዊት ጸሐፊ እንዲህ ብላ ነበር፦ “በዓለም ላይ የሚታዩትን እነዚህን ሁሉ ችግሮች ዝም ብሎ የሚመለከት ፈጣሪ አለ ብዬ ከማሰብ ይልቅ ዓለም ፈጣሪ የለውም ብዬ ባስብ ይቀለኛል።”

ይሁንና ብዙ ሃይማኖቶች ከላይ እንደተጠቀሱት ላሉ ችግሮች ማብራሪያ መስጠት አለመቻላቸው ትክክለኛ ማብራሪያ ማግኘት እንደማይቻል የሚያሳይ ነው? ገስ ከጊዜ በኋላ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ሁሉን ቻይ የሆነው ፈጣሪ የሰው ልጆች ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን መከራ እንዲደርስባቸው የፈቀደው ለምን እንደሆነ አጥጋቢ መልስ አገኘሁ። ይህ ደግሞ ለሕይወቴ አዲስ ምዕራፍ ከፍቶልኛል።” *

በአምላክ መኖር አናምንም የሚሉ አንዳንድ ሰዎች ስለ ዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ጥርጣሬ ሊኖራቸው ብሎም መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ማርካት እንዳለባቸው ሊሰማቸው ይችላል፤ አልፎ ተርፎም ወደ አምላክ ሊጸልዩ ይችላሉ። አምላክ የለም ወይም ስለመኖሩ ምንም ማወቅ አይቻልም ብለው ያምኑ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥተው ካሰላሰሉ በኋላ ከፈጣሪያቸው ጋር ዝምድና እንዲመሠርቱ የረዳቸው ምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

በፈጣሪ ላይ እምነት እንዲያሳድሩ የረዳቸው ምንድን ነው?

የሚገርመው ነገር፣ በርትልን ያናገረው ወጣት በእውነተኛ ክርስትና እና ክርስቲያን እንደሆኑ የሚናገሩ ሰዎች በሚከተሉት ሃይማኖት መካከል ያለውን ከፍተኛ ልዩነት ነገረው። በርትል የፈጣሪን መኖር በተመለከተ ከወጣቱ ጋር ውይይት ባደረገ ወቅት ትኩረቱን የሳበውን ነገር ሲናገር፦ “ግትር ብሆንም እኔን በትዕግሥት የያዘበት መንገድ አስገርሞኛል። . . . በጣም የተረጋጋ ሰው ከመሆኑም ሌላ ሁልጊዜ አንዳንድ ጽሑፎችን ያመጣልኝ ነበር፤ በተጨማሪም ጥሩ አድርጎ ይዘጋጅ ነበር።” *

በዝግመተ ለውጥና በኮሚኒዝም ጠንካራ እምነት የነበራት ስቭዬትላነ፣ ‘በምድር ላይ ፍጥረት የሚጣጣረው የራሱን ሕይወት ለማዳን ነው’ (ሰርቫይቫል ኦቭ ዘ ፊተስት) የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ያሳምናት ነበር። ያም ሆኖ እንዲህ ያለው ደግነት የጎደለው ፍልስፍና ያስጨንቃት ነበር። የሕክምና ትምህርት ስትወስድ የተማረችው ነገር ይበልጥ ግራ እንዳጋባት ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “አምላክ የለም በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ትምህርት በተሰጠን ወቅት ‘በምድር ላይ ፍጥረት የሚጣጣረው የራሱን ሕይወት ለማዳን ነው’ የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ተምረን ነበር። በሌላ በኩል ግን ስለ ሕክምና በተሰጠን ኮርስ ላይ ደካሞችን መርዳት እንዳለብን ተምረናል።” በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት ከጦጣ መጥተዋል የተባሉት ሰዎች፣ በጦጣዎች ላይ የማይታየው የስሜት መቃወስ ችግር የሚያጋጥማቸው ለምን እንደሆነም ግራ ያጋባት ነበር። ስቭዬትላነ ግራ ላጋቧት ጥያቄዎች ፈጽሞ ካልጠበቀችው ምንጭ መልስ አገኘች። እንዲህ ብላለች፦ “አፍራሽ ከሆኑ ስሜቶች ጋር የምንታገለው ፍጹም ባለመሆናችን ምክንያት እንደሆነ አያቴ ከመጽሐፍ ቅዱስ አብራራችልኝ።” ስቭዬትላነ ‘ንጹሐን ሰዎች መከራና ሥቃይ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?’ እንደሚሉት ላሉ ጥያቄዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ መልስ ማግኘት በመቻሏም በጣም ተደሰተች።

የስካንዲኔቪያ ተወላጅ የሆነውና በዝግመተ ለውጥ ጠንካራ እምነት የነበረው ሌፍ መጽሐፍ ቅዱስ የተረት መጽሐፍ እንደሆነ ይሰማው ነበር። ይሁንና በአንድ ወቅት ጓደኛው “ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አንዲት ነገር እንኳ ሳታውቅ ሰዎች የሚሉትን ብቻ ተቀብለህ እየተናገርክ እንዳለህ ታውቃለህ?” ብሎ በተናገረው ጊዜ ያምንበት የነበረውን ነገር መጠራጠር ጀመረ። ሌፍ ጓደኛው የተናገረው ነገር በሕይወቱ ላይ ምን ለውጥ እንዳመጣ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “በዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ላይ ምንም ጥያቄ አንስቼ አላውቅም፤ ከዚህ ይልቅ የተነገረኝን ነገር ሁሉ ያለ ምንም ማንገራገር እቀበል ነበር። . . . በአምላክ መኖር የማያምን አንድ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ትንቢቶችና የሚኖራቸውን ፍጻሜ ማወቁ ብቻ እንኳ ቆም ብሎ እንዲያስብ ሊረዳው እንደሚችል ይሰማኛል።”—ኢሳይያስ 42:5, 9

ቀደም ሲል የተጠቀሰው ኪረን ለዓመታት በፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ ቢያደርግም ሁኔታዎች እንደጠበቃቸው ሳይሆኑ በመቅረታቸው ተስፋ ቆርጦ ነበር። ሕይወትን በተመለከተ በሚያሰላስልበት ወቅት ‘በምድር ላይ ላሉት ችግሮች መፍትሔ ሊያመጣም ሆነ ካለብኝ ሥቃይ ሊገላግለኝ የሚችለው ኃያል የሆነ አፍቃሪ አምላክ ካለ ብቻ ነው’ የሚል ሐሳብ ወደ አእምሮው መጣ። ከዚያም በልቡ ‘ምናለ እንዲህ ዓይነት አምላክ ቢኖርና ባውቀው?’ ብሎ አሰበ። ከዚያም በከፍተኛ ጭንቀት ተውጦ እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “በእርግጥ እየሰማኸኝ ከሆነ ካለብኝ ችግርም ሆነ የሰው ልጆች እየደረሰባቸው ካለው ሥቃይ መገላገል የምችለው እንዴት እንደሆነ በሆነ መንገድ አሳየኝ።” ከጥቂት ቀናት በኋላ አንድ የይሖዋ ምሥክር በሩን አንኳኳ። ይህ የይሖዋ ምሥክር ከሰብዓዊ አገዛዝ በስተጀርባ ያለውን ክፉ ኃይል በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ሐሳብ ለኪረን አሳየው። (ኤፌሶን 6:12) ኪረን፣ የተሰጠው ማብራሪያ ራሱ የደረሰበትን መደምደሚያ ያረጋገጠለት ሲሆን የማወቅ ጉጉቱንም አነሳስቶለታል። ለበርካታ ጊዜያት መጽሐፍ ቅዱስን ካጠና በኋላ አፍቃሪ በሆነው ፈጣሪ ላይ ያለው እምነት እየተጠናከረ ሄደ።

የሰው ልጆች ፈጣሪና አንተ

ሃይማኖታዊ ግብዝነት፣ እንደ ዝግመተ ለውጥ የመሳሰሉ አምላክ የለሽ ትምህርቶች እንዲሁም የክፋት መብዛት ብዙዎች በፈጣሪ መኖር እንዲጠራጠሩ ወይም ከነጭራሹ የለም ብለው እንዲያምኑ አድርገዋቸዋል። ይሁንና ፈቃደኛ ከሆንክ መጽሐፍ ቅዱስ በአእምሮህ ለሚነሱት ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ሊሰጥህ ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ የአምላክ አሳብ ‘ፍጻሜና ተስፋ የሚሰጥ የሰላም አሳብ እንጂ የክፉ ነገር አሳብ እንዳልሆነ’ እንድትገነዘብ ያስችልሃል። (ኤርምያስ 29:11 የ1954 ትርጉም) የአካል ጉዳት ያለበት ልጅ የወለደችውና በፈጣሪ መኖር ትጠራጠር የነበረችው በርናዴት ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ማወቋ ለደረሰባት የስሜት ቁስል ፈውስ አስገኝቶላታል።

ፈጣሪ የለም ብለው ያምኑ የነበሩ ብዙ ሰዎች፣ አምላክ መከራና ሥቃይ የፈቀደበትን ምክንያት በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ማብራሪያ ልባቸውን ነክቶታል። አንተም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ላሉት ወሳኝ ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ ለማወቅ ጊዜ በመመደብ አምላክ በእርግጥ ‘ከእያንዳንዳችን የራቀ እንዳልሆነ’ መገንዘብ ትችላለህ።—የሐዋርያት ሥራ 17:27

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.6 እውነተኛ ክርስቲያኖች በጦርነት መካፈል ይኖርባቸው እንደሆነና እንዳልሆነ ለመረዳት “ክርስትና ጦርነትን ይደግፋል?” የሚለውን ከገጽ 29 እስከ 31 ላይ የሚገኘውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.22 አምላክ ክፋት እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 106 እስከ 114⁠ን ተመልከት።

^ አን.25 ‘ሕይወት የመጣው በፍጥረት ነው’ ለሚለው ሐሳብ ማስረጃ የሚሆኑ አንዳንድ ነጥቦችን ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን “በእርግጥ ፈጣሪ አለ?” የተባለውን የመስከረም 2006 ንቁ! መጽሔት ተመልከት።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ዝግመተ ለውጥ መልስ ያላገኘላቸው ጥያቄዎች

• ሕይወት ከሌለው ነገር እንዴት ሕይወት ሊገኝ ይችላል?—መዝሙር 36:9

• እንስሳትም ሆኑ ዕፅዋት ዘር የሚተኩት እንደየወገናቸው ብቻ የሆነው ለምንድን ነው?—ዘፍጥረት 1:11, 21, 24-28

• ሰዎች የተገኙት ከእነሱ ከሚያንሱ ጦጣዎች ከሆነ ረቀቅ ያለ ችሎታ ያለው አንድ እንኳ ሰው መሰል ዝንጀሮ የሌለው ለምንድን ነው?—መዝሙር 8:5, 6

• ‘ማንኛውም ፍጥረት የሚጣጣረው የራሱን ሕይወት ለማዳን ነው’ የሚለው የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ‘ሰዎች ለሌሎች ጥቅም ያስባሉ’ ከሚለው አመለካከት ጋር እንዴት ሊስማማ ይችላል?—ሮም 2:14, 15

• የሰው ልጆች የተረጋገጠ የወደፊት ተስፋ አላቸው?—መዝሙር 37:29

[በገጽ 12, 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አፍቃሪ የሆነው አምላክ፣ ትንንሽ ልጆች የሚሠቃዩበትን ዓለም እንዴት ሊፈጥር ይችላል?

ሃይማኖታዊ ግብዝነት ብዙዎች ለአምላክ ጀርባቸውን እንዲሰጡ አድርጓቸዋል