ዕንባቆም 1:1-17
1 ነቢዩ ዕንባቆም* በራእይ የተቀበለው መልእክት፦
2 ይሖዋ ሆይ፣ እርዳታ ለማግኘት ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው?+
ከግፍ እንድታስጥለኝ ስለምን ጣልቃ የማትገባው እስከ መቼ ነው?*+
3 ለምን በደል ሲፈጸም እንዳይ ታደርገኛለህ?
ጭቆናንስ ለምን ዝም ብለህ ታያለህ?
ጥፋትና ግፍ በፊቴ የሚፈጸመው ለምንድን ነው?
ጠብና ግጭትስ ለምን በዛ?
4 ስለዚህ ሕግ ላልቷል፤ፍትሕም ጨርሶ የለም።
ክፉው ጻድቁን ከቦታልና፤ከዚህ የተነሳ ፍትሕ ተጣሟል።+
5 “ብሔራትን እዩ፣ ደግሞም ልብ በሉ!
በመገረም ተመልከቱ፤ ተደነቁም፤እናንተ ቢነገራችሁም እንኳ የማታምኑት አንድ ነገርበዘመናችሁ ይከናወናልና።+
6 እነሆ፣ ጨካኝና ፈጣን የሆነውን ብሔር ይኸውምከለዳውያንን አስነሳለሁና።+
የእነሱ ያልሆኑ ቤቶችን ለመውረስ፣ሰፋፊ የምድር ክፍሎችን ይወራሉ።+
7 እነሱ አስደንጋጭና አስፈሪ ናቸው።
የገዛ ራሳቸውን ፍትሕና ሥልጣን* ያቋቁማሉ።+
8 ፈረሶቻቸው ከነብር ይልቅ ፈጣኖች ናቸው፤ከሌሊት ተኩላዎችም ይልቅ ጨካኞች ናቸው።+
የጦር ፈረሶቻቸው በፍጥነት ይጋልባሉ፤ፈረሶቻቸው ከሩቅ ስፍራ ይመጣሉ።
ለመብላት እንደሚጣደፍ ንስር ተምዘግዝገው ይወርዳሉ።+
9 ሁሉም ዓመፅ ለመፈጸም ቆርጠው ይመጣሉ።+
እንደ ምሥራቅ ነፋስ ፊታቸውን ያቀናሉ፤+ምርኮኞችንም እንደ አሸዋ ያፍሳሉ።
10 በነገሥታት ይሳለቃሉ፤በከፍተኛ ባለሥልጣናትም ላይ ይስቃሉ።+
በተመሸገ ስፍራ ሁሉ ላይ ይስቃሉ፤+የአፈር ቁልልም ሠርተው ይይዙታል።
11 ከዚያም እንደ ነፋስ ወደ ፊት እየገሰገሱ በምድሪቱ ላይ ያልፋሉ፤ይሁንና በደለኛ ይሆናሉ፤+ምክንያቱም የኃይላቸው ምንጭ አምላካቸው እንደሆነ* ይናገራሉ።”+
12 ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ከዘላለም አንስቶ ያለህ አይደለህም?+
ቅዱስ የሆንከው አምላኬ ሆይ፣ አንተ አትሞትም።*+
ይሖዋ ሆይ፣ እነሱን ፍርድ ለማስፈጸም ሾመሃቸዋል፤ዓለቴ+ ሆይ፣ ቅጣት ለማስፈጸም* አቋቁመሃቸዋል።+
13 ዓይኖችህ ክፉ የሆነውን ነገር እንዳያዩ እጅግ ንጹሐን ናቸው፤ክፋትንም ዝም ብለህ ማየት አትችልም።+
ታዲያ ከዳተኛውን ዝም ብለህ የምትመለከተው ለምንድን ነው?+ደግሞስ ክፉ ሰው ከእሱ ይልቅ ጻድቅ የሆነውን ሲውጥ ለምን ዝም ትላለህ?+
14 ሰው እንደ ባሕር ዓሣ፣ገዢም እንደሌላቸው መሬት ለመሬት የሚሳቡ ፍጥረታት እንዲሆን ለምን ትፈቅዳለህ?
15 እሱ* እነዚህን ሁሉ በመንጠቆ ጎትቶ ያወጣል።
በመረቡ ይይዛቸዋል፤በዓሣ ማጥመጃ መረቡም ይሰበስባቸዋል።
በዚህም እጅግ ሐሴት ያደርጋል።+
16 በመሆኑም ለመረቡ መሥዋዕት ይሠዋል፤ለዓሣ ማጥመጃ መረቡም መሥዋዕት* ያቀርባል፤በእነሱ የተነሳ ድርሻው በቅባት ተሞልቷል፤ምግቡም ምርጥ ነው።
17 ታዲያ መረቡን ሁልጊዜ ያራግፋል?*
ብሔራትንስ ያለርኅራኄ መፍጀቱን ይቀጥላል?+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ “አጥብቆ ማቀፍ” የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል።
^ ወይም “የማታድነው እስከ መቼ ነው?”
^ ወይም “ክብር።”
^ “ኃይላቸው አምላካቸው እንደሆነ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ “እኛ አንሞትም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ወይም “እንዲወቅሱ።”
^ ከለዳዊ የሆነ ጠላትን ያመለክታል።
^ ወይም “የሚጨስ መሥዋዕት።”
^ “ሁልጊዜ ሰይፉን ይመዛል?” ማለትም ሊሆን ይችላል።