በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የክርስቶስ ፍቅር እኛም ለሌሎች ፍቅር እንዲኖረን ያነሳሳናል

የክርስቶስ ፍቅር እኛም ለሌሎች ፍቅር እንዲኖረን ያነሳሳናል

የክርስቶስ ፍቅር እኛም ለሌሎች ፍቅር እንዲኖረን ያነሳሳናል

“[ኢየሱስ] በዓለም ያሉትን ቀድሞውኑ ይወዳቸው የነበሩትን ተከታዮቹን እስከ መጨረሻው ወደዳቸው።”—ዮሐ. 13:1

1, 2. (ሀ) ኢየሱስ ያሳየውን ፍቅር በጣም አስደናቂ የሚያደርገው ምንድን ነው? (ለ) ፍቅር ማሳየት የሚቻልባቸውን የትኞቹን መንገዶች በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን?

ኢየሱስ ፍቅር በማሳየት ረገድ ፍጹም ምሳሌ ነው። በሁሉም የሕይወቱ ዘርፎች ይኸውም በንግግሩ፣ በምግባሩ፣ በትምህርቱና ራሱን መሥዋዕት አድርጎ በማቅረቡ ፍቅሩን አሳይቷል። ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወቱ እስካበቃበት ጊዜ ድረስ ለሰዎች በሙሉ በተለይም ለደቀ መዛሙርቱ ፍቅሩን አሳይቷል።

2 ኢየሱስ ፍቅር በማሳየት ረገድ የተወው ግሩም አርዓያ ደቀ መዛሙርቱ ሊከተሉት የሚገባ የላቀ መሥፈርት ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ የተወው ምሳሌ ለመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲሁም ለሌሎች ሰዎች ሁሉ ተመሳሳይ ፍቅር እንድናሳይ ያነሳሳናል። የተሳሳተ እርምጃ ለወሰዱ ሌላው ቀርቶ ከባድ ስህተት ለፈጸሙ ሰዎች እንኳ ፍቅር በማሳየት ረገድ የጉባኤ ሽማግሌዎች ከኢየሱስ ምን ትምህርት ሊያገኙ እንደሚችሉ በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ እንመለከታለን። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ያሳየው ፍቅር ክርስቲያኖች፣ የኢኮኖሚ ችግር ወይም አደጋ አሊያም ሕመም ያጋጠማቸውን ወንድሞቻቸውንና ሌሎች ሰዎችን ለመርዳት የሚያነሳሳቸው እንዴት እንደሆነ እናያለን።

3. ጴጥሮስ ከባድ ስህተት ቢፈጽምም ኢየሱስ ለእሱ ምን አመለካከት ነበረው?

3 ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ የራሱ ሐዋርያ የሆነው ጴጥሮስ ሦስት ጊዜ ካደው። (ማር. 14:66-72) ይሁን እንጂ ክርስቶስ አስቀድሞ እንደተናገረው ጴጥሮስ ተጸጽቶ ሲመለስ ኢየሱስ ይቅር ብሎታል። ከዚያም ለጴጥሮስ ከበድ ያሉ ኃላፊነቶችን ሰጥቶታል። (ሉቃስ 22:32፤ ሥራ 2:14፤ 8:14-17፤ 10:44, 45) ኢየሱስ ከባድ ስህተት ለፈጸሙ ሰዎች ከነበረው አመለካከት ምን መማር እንችላለን?

ስህተት የሠሩ ሰዎችን በተመለከተ የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ማንጸባረቅ

4. በተለይ በየትኛው ሁኔታ ውስጥ የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ማንጸባረቅ ያስፈልገናል?

4 የክርስቶስን አስተሳሰብ ከምናንጸባርቅባቸው በርካታ አጋጣሚዎች መካከል አንዱና አስጨናቂ የሆነው የቤተሰባችን አሊያም የጉባኤያችን አባል ከባድ ስህተት በሚፈጽምበት ጊዜ የሚኖረው ሁኔታ ነው። የሚያሳዝነው፣ የሰይጣን ሥርዓት ወደ መደምደሚያው ይበልጥ እየተቃረበ ሲሄድ የዓለም መንፈስ በሥነ ምግባር ረገድ ከምንጊዜውም በበለጠ መጥፎ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው። በሥነ ምግባር ረገድ በዓለም ላይ የሚታየው መጥፎና ግዴለሽነት የሚንጸባረቅበት ዝንባሌ ወጣት አዋቂ ሳይል በሁላችንም ላይ ተጽዕኖ በማሳደር በጠባቡ መንገድ ለመሄድ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ሊሸረሽረው ይችላል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ከጉባኤ ተወግደዋል፤ ሌሎች ደግሞ ተግሣጽ ተሰጥቷቸዋል። ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። (1 ቆሮ. 5:11-13፤ 1 ጢሞ. 5:20) ያም ቢሆን ሽማግሌዎች እንደነዚህ ያሉትን ጉዳዮች በሚይዙበት ጊዜ የክርስቶስ ዓይነት ፍቅር ማሳየታቸው ስህተት በሠራው ግለሰብ ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።

5. ሽማግሌዎች ስህተት የፈጸሙ ሰዎችን በተመለከተ የክርስቶስን አስተሳሰብ ማንጸባረቅ የሚችሉት እንዴት ነው?

5 እንደ ኢየሱስ ሁሉ ሽማግሌዎች በማንኛውም ጊዜ የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች ከፍ አድርገው መመልከት ይኖርባቸዋል። እንዲህ በሚያደርጉበት ጊዜ እንደ ገርነት፣ ደግነትና ፍቅር ያሉትን የይሖዋን ባሕርያት ያንጸባርቃሉ። አንድ ሰው በፈጸመው ስህተት ‘ልቡና መንፈሱ ተሰብሮ’ እውነተኛ ንስሐ ሲገባ “እንዲህ ዓይነቱን ሰው በገርነት መንፈስ ለማስተካከል ጥረት” ማድረግ ከባድ ላይሆን ይችላል። (መዝ. 34:18፤ ገላ. 6:1) ሆኖም ግለሰቡ ምክር የማይሰማና ምንም ዓይነት የጸጸት ስሜት የማይታይበት ከሆነ ሽማግሌዎች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?

6. ሽማግሌዎች ስህተት የሠሩ ሰዎችን ጉዳይ በሚይዙበት ጊዜ ምን ማድረግ የለባቸውም? ለምንስ?

6 ስህተት የፈጸመው ግለሰብ የተሰጠውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ለመቀበል እምቢተኛ ቢሆን ወይም ስህተቱን በሌሎች ላይ ቢያሳብብ ሁኔታው ሽማግሌዎችንም ሆነ ሌሎች ሰዎችን ያስቆጣ ይሆናል። እነዚህ ሰዎች ሰውየው የወሰደው እርምጃ ያስከተለውን መጥፎ ውጤት ስለሚያውቁ የግለሰቡን ድርጊትና ዝንባሌ በተመለከተ ስሜታቸውን ለመግለጽ ይፈተኑ ይሆናል። ሆኖም ቁጣን መግለጽ ጉዳት የሚያስከትል ከመሆኑም ሌላ ‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ አያንጸባርቅም። (1 ቆሮ. 2:16፤ ያዕቆብ 1:19, 20ን አንብብ።) ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን አንዳንድ ሰዎች በግልጽ ያስጠነቀቃቸው ቢሆንም ጥላቻ የሚንጸባረቅበት ወይም ስሜት የሚጎዳ ነገር አንድም ጊዜ ተናግሮ አያውቅም። (1 ጴጥ. 2:23) ከዚህ በተቃራኒ ስህተት የሠሩ ሰዎች ንስሐ መግባትና እንደገና የይሖዋን ሞገስ ማግኘት እንደሚችሉ በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ ግልጽ አድርጓል። በእርግጥም ኢየሱስ ወደ ዓለም ከመጣባቸው ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ “ኃጢአተኞችን ለማዳን” ነው።—1 ጢሞ. 1:15

7, 8. ሽማግሌዎች የፍርድ ጉዳዮችን በሚያዩበት ጊዜ ነገሮችን እንዴት ሊይዙ ይገባል?

7 በዚህ ረገድ ኢየሱስ የተወው ምሳሌ በጉባኤ ውስጥ እርማት ሊሰጣቸው ስለሚገባ ሰዎች ባለን አመለካከት ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይገባል? በጉባኤ ውስጥ የፍርድ እርምጃ ለመውሰድ መሠረት የሆነው ቅዱስ ጽሑፋዊ ዝግጅት መንጋውን ከመንፈሳዊ አደጋ የሚጠብቅ ከመሆኑም ሌላ ስህተት የሠራው ሰው ንስሐ እንዲገባ ሊያነሳሳው እንደሚችል አስታውስ። (2 ቆሮ. 2:6-8) አንዳንዶች ንስሐ ባለመግባታቸው የሚወገዱ መሆኑ ያሳዝናል፤ ይሁንና ከእነዚህ መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከጊዜ በኋላ ወደ ይሖዋና ወደ ጉባኤው መመለሳቸው የሚያስደስት ነው። ሽማግሌዎች የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ የሚያንጸባርቁ ከሆነ ግለሰቡ አካሄዱን አስተካክሎ መመለስ ቀላል ይሆንለታል። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ፣ ስህተት ከሠሩት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ሽማግሌዎች የሰጧቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በሙሉ አያስታውሱ ይሆናል፤ ሆኖም ሽማግሌዎቹ አክብሮትና ፍቅር አሳይተዋቸው እንደነበር እንደሚያስታውሱ ምንም ጥርጥር የለውም።

8 በመሆኑም ሽማግሌዎች ሁኔታው ከባድ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ ‘የመንፈስ ፍሬን’ በተለይ ደግሞ የክርስቶስ ዓይነት ፍቅርን ማንጸባረቅ ይኖርባቸዋል። (ገላ. 5:22, 23) ሽማግሌዎች ስህተት የሠራውን ሰው ከጉባኤው ለማስወገድ በፍጹም መቸኮል የለባቸውም። ከዚህ ይልቅ ስህተት የሠሩ ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲመለሱ እንደሚፈልጉ ማሳየት አለባቸው። አብዛኞቹ ስህተት የሠሩ ሰዎች ከጊዜ በኋላ ንስሐ ይገባሉ፤ በዚህ ወቅት ለይሖዋ እንዲሁም ወደ ጉባኤው መመለስ ቀላል እንዲሆንላቸው ላደረጉት ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ አመስጋኝ ይሆናሉ።—ኤፌ. 4:8, 11, 12

በፍጻሜው ዘመን የክርስቶስ ዓይነት ፍቅር ማሳየት

9. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ያለውን ፍቅር በተግባር ያሳየበትን አንድ ምሳሌ ጥቀስ።

9 የኢየሱስ ፍቅር በተግባር የታየበትን አንድ ሁኔታ ሉቃስ ዘግቧል። ክርስቶስ ከጊዜ በኋላ የሮም ወታደሮች ጥፋት የተፈረደባትን ኢየሩሳሌምን እንደሚከቡና በዚያ ወቅት ማንም ከተማዋን ጥሎ መሸሽ እንደማይችል ያውቅ ነበር። በመሆኑም “ኢየሩሳሌም በጦር ሠራዊት ተከባ ስታዩ መጥፊያዋ እንደቀረበ እወቁ” በማለት ደቀ መዛሙርቱን በፍቅር ተነሳስቶ አስጠነቀቃቸው። ታዲያ ደቀ መዛሙርቱ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሚከተለውን ግልጽና ዝርዝር መመሪያ ሰጣቸው፦ “በዚህ ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በከተማይቱ ውስጥ ያሉም ከዚያ ይውጡ፤ በገጠር ያሉም ወደ እሷ አይግቡ፤ ምክንያቱም የተጻፈው ነገር ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይህ የፍትሕ እርምጃ የሚወሰድበት ጊዜ ነው።” (ሉቃስ 21:20-22) በ66 ዓ.ም. የሮም ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ከከበበ በኋላ ታዛዥ የሆኑ ሰዎች ይህን መመሪያ ተግባራዊ አድርገዋል።

10, 11. የጥንት ክርስቲያኖች ከኢየሩሳሌም ስለሸሹበት ሁኔታ መመርመራችን ‘ለታላቁ መከራ’ የሚያዘጋጀን እንዴት ነው?

10 ክርስቲያኖች ከኢየሩሳሌም በሚሸሹበት ወቅት ክርስቶስ ለእነሱ ያሳያቸው ዓይነት ፍቅር እርስ በርስ ማሳየታቸው አስፈላጊ ነበር። ያላቸውን ማንኛውንም ነገር አንዳቸው ለሌላው ማካፈል እንደነበረባቸው ግልጽ ነው። ሆኖም ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት በዚያች ጥንታዊ ከተማ ላይ ከደረሰው ጥፋት ያለፈ ፍጻሜ ነበረው። ኢየሱስ “ከዓለም መጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቅ ዳግመኛም የማይሆን ታላቅ መከራ ይከሰታል” በማለት አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴ. 24:17, 18, 21) ይህ “ታላቅ መከራ” ከመምጣቱ በፊትም ሆነ በዚያን ወቅት እኛም ልንቸገርና የሚያስፈልጉንን ነገሮች ልናጣ እንችላለን። የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ማዳበራችን ይህንን አስቸጋሪ ወቅት በጽናት ለማለፍ ይረዳናል።

11 በዚያ ወቅት ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር በማሳየት የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ይገባናል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ጳውሎስ የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል፦ “እያንዳንዳችን ባልንጀራችንን የሚጠቅመውን ይኸውም ሊያንጸው የሚችለውን ነገር በማድረግ እናስደስተው። ክርስቶስ እንኳ ራሱን አላስደሰተም፤ . . . ጽናትንና መጽናኛን የሚሰጠው አምላክ፣ ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ በመካከላችሁ እንዲሰፍን ያድርግ።”—ሮም 15:2, 3, 5

12. በአሁኑ ጊዜ ምን ዓይነት ፍቅር ልናዳብር ይገባል? ለምንስ?

12 የኢየሱስን ፍቅር የቀመሰው ጴጥሮስም በተመሳሳይ፣ ክርስቲያኖች “ግብዝነት የሌለበት የወንድማማች መዋደድ” እንዲያዳብሩ እንዲሁም ‘ለእውነት እንዲታዘዙ’ መክሯቸዋል። ክርስቲያኖች “እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ከልብ ልትዋደዱ ይገባል” የሚል ምክር ተሰጥቷቸዋል። (1 ጴጥ. 1:22) ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ዛሬ እንዲህ ያሉትን የክርስቶስ ባሕርያት ማዳበር ያስፈልገናል። አሁንም እንኳ በሁሉም የአምላክ ሕዝቦች ላይ የሚደርሰው ጫና እየተባባሰ ነው። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ያለው የኢኮኖሚ ቀውስ በግልጽ እንደሚያሳየው ማንም ሰው የዚህ አሮጌ ዓለም ክፍል በሆኑ ሥርዓቶች ላይ መተማመን የለበትም። (1 ዮሐንስ 2:15-17ን አንብብ።) ከዚህ በተቃራኒ የዚህ ሥርዓት መጨረሻ እየቀረበ ሲሄድ ወደ ይሖዋ ይበልጥ መጠጋት ይኖርብናል፤ እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ እውነተኛ ወዳጅነት በመመሥረት እርስ በርስ መቀራረብ ያስፈልገናል። ጳውሎስ እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቷል፦ “በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ። አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ።” (ሮም 12:10) ጴጥሮስም የሚከተለውን ምክር በመስጠት ይህንን ነጥብ ይበልጥ አጠናክሮታል፦ “ከሁሉም በላይ አንዳችሁ ለሌላው የጠለቀ ፍቅር ይኑራችሁ፤ ምክንያቱም ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል።”—1 ጴጥ. 4:8

13-15. በአንድ አካባቢ አደጋ ከደረሰ በኋላ አንዳንድ ወንድሞች የክርስቶስ ዓይነት ፍቅር ያንጸባረቁት እንዴት ነው?

13 የይሖዋ ምሥክሮች የክርስቶስ ዓይነት ፍቅር በማሳየት በዓለም ዙሪያ የታወቁ ናቸው። በ2005 በደቡባዊ ዩናይትድ ስቴትስ አብዛኛው ክፍል በማዕበልና በኃይለኛ አውሎ ነፋስ በተመታ ጊዜ በፈቃደኝነት እርዳታ የሰጡትን የይሖዋ ምሥክሮች እንመልከት። ከ20,000 በላይ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ በመከተል በአደጋው የተጎዱትን ወንድሞቻቸውን ለመርዳት ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል፤ ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ ምቹ መኖሪያቸውንና ሥራቸውን ትተው ወደ እነዚህ ቦታዎች ሄደዋል።

14 በአንድ አካባቢ፣ የባሕሩ ውኃ እስከ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያሉ ቦታዎችን ያጥለቀለቀ ሲሆን የውኃው ከፍታ 10 ሜትር ይደርስ ነበር። የባሕሩ ውኃ ወደ ቦታው ሲመለስ በአካባቢው ከነበሩት ቤቶችና ሌሎች ሕንፃዎች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት እንዳልነበሩ ሆነው ነበር። በፈቃደኝነት ከተለያዩ አገሮች የመጡ የይሖዋ ምሥክሮች አስፈላጊ መሣሪያዎችንና የግንባታ ቁሳቁሶችን ይዘው የመጡ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ ለሥራው የሚያስፈልገው ሙያ ነበራቸው፤ ሁሉም ማንኛውንም ሥራ ለመሥራት ፈቃደኞች ነበሩ። መበለት የሆኑ ሁለት እህትማማቾች በአንድ አነስተኛ የጭነት መኪና ላይ ዕቃቸውን ጭነው 3,000 ኪሎ ሜትር በመጓዝ እርዳታ ለመስጠት ወደዚህ ቦታ መጥተዋል። ከእነዚህ እህትማማቾች አንደኛዋ አሁንም ድረስ በዚያው አካባቢ ሆና እርዳታ ለመስጠት የተቋቋመውን ኮሚቴ የምታግዝ ከመሆኑም ሌላ የዘወትር አቅኚ ሆና እያገለገለች ነው።

15 ከ5,600 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮችም ሆነ በአካባቢው የሚገኙ የሌሎች ሰዎች ቤቶች እንደገና ተገንብተዋል ወይም እድሳት ተደርጎላቸዋል። በአደጋው አካባቢ የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ የመሰለውን ግሩም የፍቅር መግለጫ ሲመለከቱ ምን ተሰማቸው? አንዲት እህት ቤቷ ከወደመ በኋላ በአንድ ትንሽ ተንቀሳቃሽ ቤት ውስጥ መኖር ጀመረች፤ ይህ ቤት ጣሪያው የሚያፈስ ከመሆኑም በላይ የምግብ ማብሰያው ተሰብሮ ነበር። ወንድሞች ለዚህች እህት አነስ ያለ ምቹ ቤት ሠሩላት። ይህች እህት ጥሩ ሆኖ በተሠራው ቤቷ አጠገብ ሆና ይሖዋና ወንድሞቿ ያደረጉላትን ነገር ስታስብ በአመስጋኝነት ስሜት ተሞልታ እንባዋን አፈሰሰች። በአደጋው ምክንያት ከቤታቸው የተፈናቀሉ ሌሎች በርካታ ወንድሞች ቤታቸው እንደገና ከተገነባ በኋላም ለአንድ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ቆይተዋል። ለምን? ይህን ያደረጉት አዲስ በተሠራው መኖሪያቸው ውስጥ የእርዳታ ሠራተኞቹ እንዲኖሩበት ብለው ነው። ይህ የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ የተንጸባረቀበት እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!

የታመሙ ሰዎችን በተመለከተ የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ማንጸባረቅ

16, 17. የታመሙ ሰዎችን በተመለከተ የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ማንጸባረቅ የምንችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

16 በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አብዛኞቻችን ከባድ የተፈጥሮ አደጋ አጋጥሞን አያውቅም። ሆኖም ማንኛውም ሰው፣ ወይ ራሱ አሊያም የቤተሰቡ አባላት መታመማቸው አይቀርም። ኢየሱስ የታመሙ ሰዎችን በተመለከተ የነበረው አመለካከት ለእኛ ምሳሌ ይሆነናል። ለሰዎች የነበረው ፍቅር ለታመሙት እንዲያዝንላቸው አድርጎታል። ሕዝቡ ሕመምተኞቻቸውን ወደ እሱ ሲያመጡ ‘በጠና የታመሙትን ሁሉ ፈውሷቸዋል።’—ማቴ. 8:16፤ 14:14

17 በአሁኑ ጊዜ ክርስቲያኖች ኢየሱስ እንዳደረገው የታመሙትን በተአምር የመፈወስ ኃይል የላቸውም፤ ሆኖም ለታመሙት ሰዎች እንደ ኢየሱስ ርኅራኄ ያሳያሉ። ይህን የሚያደርጉት እንዴት ነው? ሽማግሌዎች በማቴዎስ 25:39, 40 * (አንብብ።) ላይ የተገለጸውን መሠረታዊ ሥርዓት በመከተል በጉባኤያቸው ውስጥ የታመሙትን ለመርዳት ዝግጅት በማድረግና ይህም ተግባራዊ መሆኑን በመከታተል የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ እንዳላቸው ያሳያሉ። ክርስቲያኖች የክርስቶስ ዓይነት ርኅራኄ እንዳላቸው ከሚጠቁሙት ማስረጃዎች አንዱ ይህ ነው።

18. ሁለት እህቶች እውነተኛ ፍቅር እንዳላቸው ያሳዩት እንዴት ነው? ይህስ ምን ውጤት አስገኘ?

18 እርግጥ ነው፣ ለሌሎች መልካም ለማድረግ የግድ ሽማግሌ መሆን የለብንም። የ44 ዓመት ዕድሜ ያላትን የሻርሊንን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ይህች እህት የካንሰር በሽታ እንዳለባትና በሕይወት የምትቆየው ለአሥር ቀን ብቻ እንደሆነ ተነግሯት ነበር። ሻሮን እና ኒኮሌት የተባሉ ሁለት እህቶች ሻርሊንም ሆነች እሷን በመንከባከብ የተንገላታው ባለቤቷ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ሲመለከቱ ይህችን እህት እስከ ሕይወቷ ፍጻሜ ድረስ ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው ለመርዳት ፈቃደኞች ሆኑ። ይህች እህት ከተባለው ጊዜ አልፎ ለስድስት ሳምንት የቆየች ሲሆን እነዚህ እህቶች እስከ ዕለተ ሞቷ ድረስ በመንከባከብ ፍቅራቸውን አሳይተዋል። ሻሮን እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ሰው እንደማይድን ስታውቅ ሁኔታው ከባድ ነው። ይሁንና ይሖዋ ብርታት ሰጥቶናል። ይህ ሁኔታ ወደ ይሖዋ የበለጠ እንድንጠጋ ያደረገን ከመሆኑም በላይ እርስ በርስ አቀራርቦናል።” የሻርሊን ባለቤት እንዲህ ብሏል፦ “እነዚህ ሁለት ውድ እህቶች ያሳዩኝን ደግነትና ያደረጉልኝን እርዳታ ምንጊዜም አልረሳውም። በንጹሕ ልብ ተነሳስተውና አዎንታዊ አመለካከት ይዘው ታማኟ ባለቤቴ ሻርሊን በሕይወቷ ፍጻሜ ላይ የነበራት ሥቃይ ቀለል እንዲልላት አድርገዋል፤ እኔም በጣም ያስፈልገኝ የነበረውን አካላዊም ሆነ ስሜታዊ እፎይታ እንዳገኝ ረድተውኛል። ላደረጉልኝ ነገር ምንጊዜም አመስጋኝ ነኝ። እነዚህ እህቶች ያሳዩት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ በይሖዋ ላይ ያለኝን እምነት አጠናክሮልኛል፤ እንዲሁም ለመላው የወንድማማች ማኅበር ያለኝን ፍቅር አሳድጎታል።”

19, 20. (ሀ) ከክርስቶስ አስተሳሰብ ጋር በተያያዘ የትኞቹን አምስት ነገሮችን መርምረናል? (ለ) ምን ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃል?

19 በእነዚህ ሦስት ተከታታይ የጥናት ርዕሶች ላይ ከኢየሱስ አስተሳሰብ ጋር በተያያዘ አምስት ነገሮችን መርምረናል፤ እንዲሁም በአስተሳሰባችንም ሆነ በተግባራችን የእሱን አርዓያ መከተል የምንችለው እንዴት እንደሆነ ተመልክተናል። እንደ ኢየሱስ ‘ገርና በልባችን ትሑት’ እንሁን። (ማቴ. 11:29) ሌሎች ፍጹማን ባለመሆናቸውና በድካም የተነሳ ስህተት በሚፈጽሙበት ጊዜም እነሱን በደግነት ለመያዝ ጥረት እናድርግ። በተጨማሪም ችግሮች በሚያጋጥሙን ጊዜም እንኳ ይሖዋ ያወጣቸውን መሥፈርቶች በሙሉ በድፍረት እንታዘዝ።

20 ክርስቶስ እንዳደረገው ለወንድሞቻችን በሙሉ “እስከ መጨረሻው” የክርስቶስ ዓይነት ፍቅር እናሳያቸው። እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች መሆናችንን ያሳውቃል። (ዮሐ. 13:1, 34, 35) አዎን፣ “የወንድማማችነት ፍቅራችሁ ቀጣይ ይሁን።” (ዕብ. 13:1) ይህን ከማድረግ ወደኋላ አትበሉ! በሕይወታችሁ ይሖዋን ለማወደስና ሌሎችን ለመርዳት ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ! ይሖዋ የምታደርጉትን ልባዊ ጥረት ይባርካል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.17 በጥቅምት 15, 1986 መጠበቂያ ግንብ (መግ 10-107 ገጽ 11) ላይ የወጣውን “‘እሳት ሙቅ፣ በደንብ ብላ’ ብለህ ከመናገር የበለጠ ነገር አድርግ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

ልታብራራ ትችላለህ?

• ሽማግሌዎች ስህተት የፈጸሙ ሰዎችን በተመለከተ የክርስቶስን አስተሳሰብ ማንጸባረቅ የሚችሉት እንዴት ነው?

• በተለይ በፍጻሜው ዘመን የክርስቶስ ዓይነት ፍቅር ማሳየት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

• የታመሙ ሰዎችን በተመለከተ የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሽማግሌዎች ስህተት የሠራ ሰው ወደ ይሖዋ እንዲመለስ ይፈልጋሉ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከኢየሩሳሌም ሸሽተው የወጡት ክርስቲያኖች የክርስቶስን አስተሳሰብ ያንጸባረቁት እንዴት ነው?

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች የክርስቶስ ዓይነት ፍቅር በማሳየት የታወቁ ናቸው