በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከኢየሱስ ተአምራት ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ?

ከኢየሱስ ተአምራት ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ?

ከኢየሱስ ተአምራት ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ?

ኢየሱስ በምድር ላይ ስላሳለፈው ሕይወት የሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች “ተአምርን” ለማመልከት የሚያገለግለውን ዋነኛ የግሪክኛ ቃል ፈጽሞ እንዳልተጠቀሙ ስታውቅ ትገረም ይሆናል። በአንዳንድ ቦታዎች ላይ “ተአምር” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል (ቴናሚስ) በቀጥታ ሲወሰድ “ኀይል” ማለት ነው። (ሉቃስ 8:46) በተጨማሪም ይህ ቃል “ችሎታ” ወይም ታላቅ ሥራ ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። (ማቴዎስ 25:15) አንድ ምሑር እንደተናገሩት ይህ የግሪክኛ ቃል “የተከናወነውን ታላቅ ሥራ በተለይም ድርጊቱ የተከናወነበትን ኃይል ያመለክታል። ክንውኑም የአምላክ ኃይል በተግባር የታየበት ክስተት እንደሆነ ተደርጎ ይገለጻል።”

ሌላኛው የግሪክኛ ቃል (ቴራስ) ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ “ድንቅ ነገሮች” ተብሎ የሚተረጎመው ነው። (ዮሐንስ 4:48፤ የሐዋርያት ሥራ 2:19) ይህ ቃል ተአምራቱ በታዛቢዎች ላይ ያሳደሩትን ስሜት የሚያንጸባርቅ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ሕዝቡና ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ በሚፈጽማቸው ተአምራት ይገረሙና ይደነቁ ነበር።—ማርቆስ 2:12፤ 4:41፤ 6:51፤ ሉቃስ 9:43

የኢየሱስን ተአምራት ለማመልከት የተሠራበት ሦስተኛው የግሪክኛ ቃል (ሴሜኦን) “ምልክት” የሚል ትርጉም አለው። ሮበርት ደፊንባው የተባሉት ምሑር እንዳሉት ይህ ቃል “በተአምራቱ ትርጉም ላይ ያተኩራል።” አክለውም “ምልክት ስለ ጌታችን ኢየሱስ አንድ እውነታ የሚነግረን ተአምር ነው” ብለዋል።

ተአምራቱ የተፈጸሙት በማጭበርበር ነው ወይስ ከአምላክ በተገኘ ኃይል?

መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስ ተአምራት ሰዎችን ለማዝናናት ተብለው የተፈጸሙ የማታለል ድርጊቶች ወይም የማስመሰል ክንውኖች እንደሆኑ አይናገርም። ኢየሱስ ከአንድ ልጅ አጋንንት እንዳስወጣ የሚናገረው ታሪክ እንደሚያሳየው ‘የእግዚአብሔር ታላቅነት’ መገለጫ ነበሩ። (ሉቃስ 9:37-43) ሁሉን ቻይ የሆነውና ‘ታላቅ ኃይል’ እንዳለው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተነገረለት አምላክ እንዲህ ያለውን ተአምር መፈጸም ይሳነዋል? (ኢሳይያስ 40:26) እንደማይሳነው የታወቀ ነው!

በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ 35 የሚሆኑ የኢየሱስ ተአምራት ተጠቅሰዋል። በጠቅላላው ምን ያህል ተአምራት እንደፈጸመ ግን አልተገለጸም። ለምሳሌ ያህል፣ ማቴዎስ 14:14 “ኢየሱስም . . . ብዙ ሕዝብ አይቶ ራራላቸው፤ ሕመምተኞቻቸውንም ፈወሰላቸው” ይላል። በዚህ ወቅት ኢየሱስ ምን ያህል የታመሙ ሰዎች እንደፈወሰ አናውቅም።

እንዲህ ያሉት ተአምራት ኢየሱስ የአምላክ ልጅና ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ መሆኑን ለማረጋገጥ አስፈላጊ ነበሩ። ቅዱሳን ጽሑፎች ኢየሱስ ተአምራት መፈጸም የቻለው ከአምላክ ባገኘው ኃይል እንደሆነ በግልጽ ያሳያሉ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “እናንት ራሳችሁ እንደምታውቁት፣ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ታምራትን፣ ድንቅ ነገሮችንና ምልክቶችን በእርሱ በኩል በማድረግ ለናዝሬቱ ኢየሱስ መስክሮለታል” ብሏል። (የሐዋርያት ሥራ 2:22) በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ጴጥሮስ “እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስና በኀይል ቀባው፤ እርሱም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ በደረሰበት ሁሉ መልካም እያደረገ በዲያብሎስ ሥልጣን ሥር የነበሩትን ሁሉ ፈወሰ” በማለት ተናግሯል።—የሐዋርያት ሥራ 10:37, 38

የኢየሱስ ተአምራትና መልእክቱ የማይነጣጠሉ ናቸው። ማርቆስ 1:21-27 ሕዝቡ ትምህርቱን ሲያዳምጡና ተአምር ሲፈጽም ሲመለከቱ ምን እንደተሰማቸው ይናገራል። ማርቆስ 1:22 “ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ” ይላል፤ ቁጥር 27 ደግሞ አጋንንት ባወጣ ጊዜ ሕዝቡ እንደተገረሙ ይናገራል። ኢየሱስ ያከናወናቸው ተአምራትም ሆኑ ያስተምር የነበረው ትምህርት ተስፋ የተጣለበት መሲሕ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን በአፉ በመናገር ብቻ ለማሳወቅ አልሞከረም፤ ከተናገራቸው ቃላትና ካደረጋቸው ነገሮች በተጨማሪ ተአምራቱን ለመፈጸም የተጠቀመበት ከአምላክ ያገኘው ኃይል መሲሕ መሆኑን ያረጋግጣል። የመጣበትን ዓላማና ማን እንደላከው ለተነሳው ጥያቄ በድፍረት ሲመልስ “እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክርነት የላቀ ምስክር አለኝ፤ እንድፈጽመው አብ የሰጠኝ፣ እኔም የምሠራው ሥራ አብ እንደ ላከኝ ይመሰክራል” ብሏል።—ዮሐንስ 5:36

ለእውነተኝነታቸው ማረጋገጫ

የኢየሱስ ተአምራት እውነተኛ መሆናቸውን ማረጋገጥ የምንችለው እንዴት ነው? እስቲ አንዳንድ ማስረጃዎችን እንመልከት።

ኢየሱስ ተአምራት በፈጸመበት ጊዜ ሁሉ የሰዎችን ትኩረት ወደ ራሱ ለመሳብ አልሞከረም። በእያንዳንዱ ተአምር አምላክ እንዲወደስና እንዲከበር አድርጓል። ለምሳሌ ያህል ማየት የተሳነውን አንድ ሰው ከመፈወሱ በፊት ተአምሩን የሚፈጽመው “የእግዚአብሔር ሥራ [በዓይነ ስውሩ] ሕይወት እንዲገለጥ” እንደሆነ ተናግሯል።—ዮሐንስ 9:1-3፤ 11:1-4

ኢየሱስ ተአምር ይፈጽም የነበረው ምትሃተኞች፣ አስማተኞችና በእምነት እንፈውሳለን የሚሉ ሰዎች እንደሚያደርጉት የሰዎችን አእምሮ በመቆጣጠር፣ በማታለያ ዘዴዎች፣ ትኩረት በሚስቡ ትዕይንቶች፣ በድግምት ወይም ለየት ያለ ሥነ ሥርዓት በማከናወን አልነበረም። የጥንቆላ ድርጊቶችን ወይም እንደ ቅዱስ ተደርገው የሚታዩ ሃይማኖታዊ ዕቃዎችን አልተጠቀመም። ኢየሱስ በጣም ቀላል በሆነ ሁኔታ ማየት የተሳናቸውን ሁለት ሰዎች እንዴት እንደፈወሳቸው ተመልከት። ዘገባው “ኢየሱስም ራራላቸው፤ ዐይኖቻቸውንም ዳሰሰ፣ ወዲያው አዩ፤ ተከተሉትም” ይላል። (ማቴዎስ 20:29-34) የተለየ ሥነ ሥርዓት ወይም የሰዎችን ትኩረት የሚስብ ነገር አላደረገም። ኢየሱስ ተአምራቱን ይፈጽም የነበረው ከሰው እይታ ሳይደበቅ እንዲያውም አብዛኛውን ጊዜ በርካታ የዓይን ምሥክሮች በተሰበሰቡበት ነበር። የተለየ መብራት፣ መድረክና ቁሳቁስ አላስፈለገውም። በተቃራኒው በዛሬው ጊዜ ይፈጸማሉ የሚባሉትን ተአምራት በሚመለከት አስተማማኝ መረጃ ማግኘት አይቻልም።—ማርቆስ 5:24-29፤ ሉቃስ 7:11-15

ኢየሱስ አንዳንድ ጊዜ ተአምር የፈጸመላቸው ሰዎች እምነት እንዳላቸው ይናገር የነበረ ቢሆንም ግለሰቡ እምነት የሌለው በመሆኑ ተአምር ሳይፈጽም የቀረበት አንድም አጋጣሚ የለም። በገሊላ በምትገኘው በቅፍርናሆም በነበረበት ወቅት ሕዝቡ “በአጋንንት የተያዙ ብዙ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ እርሱም መናፍስትን በቃሉ አስወጣ፤ በሽተኞችንም ሁሉ ፈወሰ።”—ማቴዎስ 8:16

ኢየሱስ ተአምር ይፈጽም የነበረው ታዛቢዎችን ለማስደመም ሳይሆን የሰዎችን መሠረታዊ ችግር ለመቅረፍ ነበር። (ማርቆስ 10:46-52፤ ሉቃስ 23:8) ከዚህም በላይ ኢየሱስ በምንም ዓይነት መልኩ የግል ጥቅም ለማግኘት ብሎ ተአምር አልፈጸመም።—ማቴዎስ 4:2-4፤ 10:8

የወንጌል ዘገባዎችስ እምነት የሚጣልባቸው ናቸው?

ኢየሱስ ስለፈጸማቸው ተአምራት ለማወቅ የቻልነው በአራቱ ወንጌሎች ውስጥ በሰፈረው ዘገባ አማካኝነት ነው። በእነዚህ ዘገባዎች ላይ ተመርኩዞ ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት እውነተኛ ናቸው ማለት ይቻላል? አዎን፣ ይቻላል።

ከላይ እንደተመለከትነው የኢየሱስ ተአምራት በበርካታ የዓይን ምሥክሮች ፊት በአደባባይ የተፈጸሙ ናቸው። ቀደምት የሚባሉት የወንጌል ዘገባዎች የተጻፉት ከእነዚህ የዓይን ምሥክሮች መካከል አብዛኞቹ በሕይወት እያሉ ነበር። የወንጌል ዘገባዎችን ሐቀኝነት በሚመለከት ዘ ሚራክልስ ኤንድ ዘ ሬዘረክሽን የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “የወንጌል ጸሐፊዎች ለሃይማኖታዊ ፕሮፓጋንዳ ብለው በርካታ የፈጠራ ተአምራትን በዘገባቸው ውስጥ በማስገባት ታሪካዊው እውነታ እንዲዋጥ ያደርጋሉ ብሎ ማለት ጨርሶ የማይመስል ነገር ነው። . . . እውነታውን በሐቀኝነት ለመዘገብ ይፈልጉ ነበር።”

ክርስትናን ይቃወሙ የነበሩት አይሁዳውያንም በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ የተካተቱትን ተአምራት እውነተኝነት በሚመለከት ምንም ተቃውሞ አላነሱም። ጥያቄ ያነሱት ተአምራቱ የሚፈጸሙት በማን ኃይል ነው በሚለው ጉዳይ ላይ ብቻ ነበር። (ማርቆስ 3:22-26) ከጊዜ በኋላ የተነሱ ተቺዎችም ተአምራቱ አልተፈጸሙም ብለው አፋቸውን ሞልተው መናገር አልቻሉም። በአንጻሩ ኢየሱስ ስለፈጸማቸው ተአምራቶች የሚናገሩ በአንደኛውና በሁለተኛው ክፍለ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የተጻፉ መረጃዎች አሉ። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ስለ ተአምራቱ የሚናገሩት የወንጌል ዘገባዎች እውነተኛ ናቸው ብሎ ለመደምደም የሚያስችል አሳማኝ ምክንያት አለ።

ተአምራቶቹን የፈጸመው ማን ነው?

የኢየሱስን ተአምራት እውነተኝነት ስንመረምር ስለ ራሱ ስለ ኢየሱስ ሳናነሳ ሌሎች ማስረጃዎችን ማቅረቡ ብቻ በቂ አይሆንም። ስለ ተአምራቱ የሚናገሩት የወንጌል ዘገባዎች ኢየሱስ ጥልቅ ስሜትና ወደር የለሽ ርኅራኄ እንዳለው እንዲሁም ለሰዎች ደኅንነት ከልብ እንደሚያስብ ይጠቁማሉ።

ወደ ኢየሱስ ቀርቦ “ብትፈቅድ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” በማለት አንጀት የሚበላ ልመና ስላቀረበው ለምጻም የሚናገረውን ታሪክ ተመልከት። ኢየሱስ “ለሰውየው በመራራት” እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና “እፈቅዳለሁ፣ ንጻ” አለው። ሰውየውም ወዲያውኑ ከለምጹ ተፈወሰ። (ማርቆስ 1:40-42) በዚህ አጋጣሚ ኢየሱስ ከአምላክ ባገኘው ኃይል ተአምር እንዲፈጽም የሚገፋፋው የአዘኔታ ባሕርይ እንዳለው አሳይቷል።

ኢየሱስ ከናይን ከተማ ወጥተው ወደ ቀብር የሚጓዙ ሰዎች ባጋጠሙት ጊዜስ ምን አደረገ? ሟቹ ወጣት የአንዲት መበለት ብቸኛ ልጅ ነበር። ኢየሱስ ለመበለቲቱ “ራራላትና፣ አይዞሽ፣ አታልቅሺ” አላት። ከዚያም ልጅዋን ከሞት አስነሳላት።—ሉቃስ 7:11-15

ኢየሱስ ካከናወናቸው ተአምራት አንድ የሚያጽናና ትምህርት እናገኛለን። ይኸውም ‘ርኅሩኅ’ እንደሆነና የተቸገሩ ሰዎችን እንደሚረዳ ያሳዩናል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያሉት ተአምራት እንዲያው ታሪክ ሆነው የሚቀሩ አይደሉም። ዕብራውያን 13:8 “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንት፣ ዛሬም ለዘላለምም ያው ነው” ይላል። በአሁኑ ወቅት ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ በመግዛት ላይ ሲሆን ከአምላክ ያገኘውን ተአምር የመፈጸም ኃይል ሰው ሆኖ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ከተጠቀመበት በበለጠ መንገድ በሥራ ላይ ለማዋል ዝግጁ ከመሆኑም በላይ ችሎታውም አለው። በቅርቡ ኢየሱስ ይህን ኃይሉን ተጠቅሞ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች ፈውስ ያመጣላቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ስላለው አስደሳች የወደፊት ተስፋ ይበልጥ ለማወቅ እንድትችል ሊረዱህ ፈቃደኛ ናቸው።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኢየሱስ ተአምራት ‘የእግዚአብሔር ታላቅነት’ መገለጫ ነበሩ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ የርኅራኄ ስሜት ያለው ሰው ነበር