በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዘመናችን የደረሰው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዘመናችን የደረሰው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዘመናችን የደረሰው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዘመናችን ድረስ ሳይበረዝ መቆየቱ በራሱ ተአምር ነው። ይህ መጽሐፍ ተጽፎ የተጠናቀቀው ከ1,900 ዓመታት በፊት ሲሆን መጀመሪያ የተጻፈውም በቀላሉ ሊበላሹ በሚችሉ ነገሮች ማለትም ከፓፒረስ በተዘጋጁ ወረቀቶችና ከቆዳ በተሠሩ ብራናዎች ላይ ነበር። በመጀመሪያ የተጻፈው በዛሬው ጊዜ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሕዝቦች በሚነጋገሩባቸው ቋንቋዎች ነው። ከዚህም በላይ ነገሥታትንና የሃይማኖት መሪዎችን ጨምሮ ኃያላን የሆኑ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ብርቱ ትግል አድርገዋል።

ታዲያ ይህ አስደናቂ መጽሐፍ በየዘመናቱ ያጋጠመውን ውጣ ውረድ አልፎ በሰው ዘሮች ሁሉ ዘንድ እጅግ ታዋቂ መጽሐፍ ለመሆን የበቃው እንዴት ነው? እስቲ ሁለት ምክንያቶችን ብቻ እንመልከት።

በብዛት መገልበጡ መጽሐፉን ከጥፋት አድኖታል

የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፎች በአደራ ተሰጥተዋቸው የነበሩት እስራኤላውያን የመጀመሪያዎቹን ጥቅልሎች በጥንቃቄ ያስቀምጧቸው የነበረ ከመሆኑም በላይ በየጊዜው ይገለብጧቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ የእስራኤል ነገሥታት ‘የዚህን ሕግ ቅጅ ከሌዋውያን ካህናት ወስደው በጥቅልል መጽሐፍ ለራሳቸው እንዲጽፉ’ ተነግሯቸዋል።—ዘዳግም 17:18

ብዙ እስራኤላውያን ቅዱሳን መጻሕፍትን ማንበብ ይወዱ የነበረ ሲሆን እነዚህ ጽሑፎች የአምላክ ቃል እንደሆኑ ይገነዘቡ ነበር። በመሆኑም መጽሐፎቹን የመገልበጡ ሥራ የሚካሄደው በከፍተኛ ጥንቃቄና በጣም በሠለጠኑ ጸሐፍት ነበር። ዕዝራ የተባለው ፈሪሃ አምላክ የነበረው ጸሐፊ “የእስራኤልም አምላክ እግዚአብሔር በሰጠው በሙሴ ሕግ ፈጣን ጸሐፊ ነበረ” ተብሎ ተነግሮለታል። (ዕዝራ 7:6 የ1954 ትርጉም) ከክርስቶስ ልደት በኋላ በስድስተኛውና በአሥረኛው መቶ ዘመናት መካከል የኖሩትና የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን ወይም “ብሉይ ኪዳንን” የገለበጡት ማሶሬቶች ስህተቶች እንዳይገቡ ከነበራቸው ፍላጎት የተነሳ በጽሑፉ ውስጥ ያሉትን ፊደላት ይቆጥሩ ነበር። በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚካሄደው እንዲህ ያለው የመገልበጥ ሥራ የጽሑፉን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የረዳ ከመሆኑም በላይ ጠላቶች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥፋት እልህ አስጨራሽ ሙከራ ቢያደርጉም ሳይጠፋ እንዲቆይ አስችሏል።

ለምሳሌ ያህል፣ የሶርያ ገዢ የነበረው አንታይከስ አራተኛ በ168 ከክርስቶስ ልደት በፊት በመላዋ የፓለስቲና ምድር ያገኛቸውን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች በሙሉ ለማጥፋት ሙከራ አድርጎ ነበር። የአይሁዶችን ታሪክ የሚተርክ አንድ ጽሑፍ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲገልጽ “ያገኟቸውን የሕጉን ጥቅልሎች በሙሉ ቀዳደው አቃጠሏቸው” በማለት ይናገራል። ዘ ጂዊሽ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚከተለው በማለት ይናገራል:- “ይህ ትእዛዝ የተሰጣቸው ሹማምንት ተልእኳቸውን ይፈጽሙ የነበረው በከፍተኛ ስሜት ነበር። . . . ቅዱሱን መጽሐፍ ይዞ መገኘት . . . በሞት ያስቀጣ ነበር።” ያም ሆኖ ግን በፓለስቲናም ሆነ በሌሎች አገሮች በሚኖሩ አይሁዶች ዘንድ የነበሩ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ከመጥፋት ሊድኑ ችለዋል።

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ወይም “የአዲስ ኪዳን” ጸሐፊዎች ጽፈው ከጨረሱ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በመንፈስ አነሳሽነት የጻፏቸው ደብዳቤዎች፣ ትንቢቶችና ታሪካዊ ዘገባዎች በብዛት መገልበጥ ጀመሩ። ለምሳሌ ያህል፣ ዮሐንስ ወንጌሉን የጻፈው በኤፌሶን ወይም በዚህች ከተማ አቅራቢያ ነበር። ሆኖም የዚህ ወንጌል ቅጂ ቁራጭ በርካታ መቶ ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምትገኘው በግብጽ ተገኝቷል፤ ምሑራን እንደሚሉት ከሆነ ቅጂው የተጻፈው ዮሐንስ ወንጌሉን ጽፎ ካጠናቀቀ 50 ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው። ይህ ግኝት ራቅ ባሉ አገሮች የሚኖሩ ክርስቲያኖችም ከጥቂት ጊዜያት ቀደም ብሎ በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፉ መጽሐፎች የተገለበጡ ቅጂዎች እንደነበሯቸው ያመለክታል።

የአምላክ ቃል ክርስቶስ በምድር ላይ ከኖረ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላም እንኳ ሳይጠፋ እንዲቆይ አስተዋጽኦ ያበረከተው ሌላው ነገር ደግሞ በሰፊው የተሰራጨ መሆኑ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የካቲት 23, 303 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ጎሕ ሲቀድ የሮማ ንጉሠ ነገሥት የነበረው ዲዮቅላጢያን ወታደሮቹ የቤተ ክርስቲያን በሮችን ሰብረው በመግባት የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎችን እንዲያቃጥሉ እንዳደረገ ይነገራል። ዲዮቅላጢያን ቅዱሳን መጻሕፍትን በማስወገድ ክርስትናን ማጥፋት እንደሚችል ተሰምቶት ነበር። በመሆኑም በማግሥቱ በመላው የሮማ ግዛት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች በሙሉ በአደባባይ እንዲቃጠሉ የሚገልጽ አዋጅ አወጣ። ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜም ከመቃጠል የተረፉ ቅጂዎች ስለነበሩ እነዚህ እንደገና መባዛት ጀመሩ። እንዲያውም ዲዮቅላጢያን መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥፋት ዘመቻ ካካሄደ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሳይዘጋጁ እንደማይቀር የሚገመቱ ሁለት የግሪክኛ መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች በዛ ያሉ ክፍሎች አሁንም ድረስ አሉ። አንደኛው የሚገኘው በሮም ሲሆን ሌላው ደግሞ ለንደን፣ እንግሊዝ ባለው ብሪትሽ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ነው። 

በእጅ የተጻፉት የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት እስካሁን ድረስ ባይገኙም በእጅ የተገለበጡ የሙሉው ወይም የከፊሉ መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ግን አሁን ድረስ ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በጣም አርጅተዋል። ታዲያ በመጀመሪያዎቹ ጽሑፎች ላይ የነበረው መልእክት በእጅ ሲገለበጥ ተዛብቶ ይሆን? ዊልያም ሄንሪ ግሪን የተባሉ አንድ ምሑር የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚመለከት “የዚህን ያህል ትክክል የሆኑ ጥንታዊ ጽሑፎች የሉም ቢባል ማጋነን አይሆንም” ብለዋል። በእጅ ስለተገለበጡ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ብዙ ምርምር ያደረጉት ሰር ፍሬድሪክ ኬንዮን እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል:- “በመጀመሪያዎቹ በኩረ ጽሑፎችና በተገኙት እጅግ ጥንታዊ ግልባጮች መካከል ያለው የዕድሜ ልዩነት በጣም ትንሽ በመሆኑ ከቁም ነገር የሚቆጠር አይደለም፤ በመሆኑም አሁን በእጃችን የሚገኙት ቅዱሳን መጻሕፍት ተለውጠው ይሆናል የሚለው ጥርጣሬ ሙሉ በሙሉ ተወግዷል። የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት አስተማማኝነት እና አጠቃላይ ትክክለኛነት ሙሉ በሙሉ ተረጋግጧል።” በተጨማሪም እንዲህ ብለዋል:- “የመጽሐፍ ቅዱስ ይዘት ፍጹም ትክክል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። . . . በመላው ዓለም ስለሚገኝ ስለ ማንኛውም ጥንታዊ መጽሐፍ እንዲህ ማለት አይቻልም።”

የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም

መጽሐፍ ቅዱስን ከሌላ ከማንኛውም መጽሐፍ በላይ በሰዎች ሁሉ ዘንድ እጅግ እንዲታወቅ ካደረጉት ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል ሁለተኛው በብዙ ቋንቋዎች የሚገኝ መሆኑ ነው። ይህ ሐቅ አምላክ ከሁሉም ሕዝቦችና ቋንቋዎች የመጡ ሰዎች እንዲያውቁት እንዲሁም “በመንፈስና በእውነት” እንዲያመልኩት ካለው ዓላማ ጋር ይስማማል።—ዮሐንስ 4:23, 24፤ ሚክያስ 4:2

የመጀመሪያው የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም በግሪክኛ የተዘጋጀው የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ነው። ይህ ትርጉም የተዘጋጀው ከፓለስቲና ምድር ውጪ ለሚኖሩ ግሪክኛ ተናጋሪ አይሁዶች ሲባል ሲሆን ተተርጉሞ የተጠናቀቀውም ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ከመጀመሩ ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት ነው። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ጨምሮ መላው መጽሐፍ ቅዱስ ወደ በርካታ ቋንቋዎች የተተረጎመው ተጽፎ ባለቀ በጥቂት መቶ ዓመታት ውስጥ ነው። ከጊዜ በኋላ ግን ሥልጣናቸውን ተጠቅመው መጽሐፍ ቅዱስ በሰው ሁሉ እጅ እንዲገባ ማድረግ የነበረባቸው ነገሥታትና ቀሳውስት ከዚህ ተቃራኒ የሆነ እርምጃ መውሰድ ጀመሩ። ቀሳውስቱ የአምላክ ቃል ወደ ተራው ሕዝብ ቋንቋ እንዳይተረጎም በመከልከል መንጎቻቸውን በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ለማስቀረት ጥረት አድርገዋል።

ደፋር የሆኑ ሰዎች ቤተ ክርስቲያንም ሆነች መንግሥት ለሚያሳድሩት ተጽዕኖ ባለመንበርከክ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ተራው ሕዝብ ቋንቋ ለመተርጎም ሲሉ ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በኦክስፎርድ የተማረው እንግሊዛዊው ዊልያም ቲንደል በ1530 ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የመጀመሪያ የሆኑትን አምስቱን የኦሪት መጻሕፍት እትም አዘጋጀ። ብዙ ተቃውሞ ቢገጥመውም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስን ከዕብራይስጥ በቀጥታ ወደ እንግሊዝኛ ለመተርጎም የመጀመሪያው ሰው ሆኗል። ቲንደል ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም ለመጠቀምም የመጀመሪያው እንግሊዛዊ ተርጓሚ ነበር። ከመጀመሪያዎቹ የስፓንኛ መጽሐፍ ቅዱሶች መካከል አንዱን ያዘጋጀው ካሲዮዶሮ ዴ ሬይና የተባለው ስፔናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር በትርጉም ሥራው ወቅት ካቶሊክ አሳዳጆቹ እንዳይገድሉት ሁልጊዜ ይሰጋ ነበር። የትርጉም ሥራውን እስኪያጠናቅቅ ድረስ ወደ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ሆላንድና ስዊዘርላንድ ተጉዟል። *

በአሁኑ ወቅት መጽሐፍ ቅዱስ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ በመጣ ቋንቋዎች እየተተረጎመ ሲሆን በየጊዜው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቅጂዎች ይታተማሉ። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥፋት ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም እንኳ እስካሁን ቆይቶ በሰው ዘር ሁሉ ዘንድ የታወቀ መጽሐፍ ለመሆን መብቃቱ ሐዋርያው ጴጥሮስ “ሣሩ ይጠወልጋል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” በማለት በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈውን ቃል እውነተኝነት ያረጋግጣል።—1 ጴጥሮስ 1:24, 25

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.14 የሬይና ትርጉም በ1569 ታትሞ የነበረ ሲሆን በ1602 በሲፕሪያኖ ዴ ቫሌራ ታርሞና ተሻሽሎ ወጥቷል።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ማንበብ ያለብኝ የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ነው?

ብዙ ቋንቋዎች በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አሏቸው። አንዳንድ ትርጉሞች ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነ ጥንታዊ ቋንቋ ይጠቀማሉ። ሌሎች በትርጉሙ ትክክለኛነት ላይ ሳይሆን ንባቡ አስደሳችና በቀላሉ የሚገባ በመሆኑ ላይ ያተኮሩ ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ ቃል በቃል የተተረጎሙ ናቸው ሊባል ይቻላል።

የይሖዋ ምሥክሮች በእንግሊዝኛ ያዘጋጁት የአዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም ከመጀመሪያዎቹ ቋንቋዎች በቀጥታ የተተረጎመ ነው። ስማቸው እንዲጠቀስ የማይፈልጉ ሰዎችን ባቀፈ ኮሚቴ የተዘጋጀው ይህ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስን 60 በሚያህሉ ሌሎች ቋንቋዎች ለመተርጎም የሚያስችል ዋነኛ መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል። ይሁን እንጂ ወደ እነዚህ ቋንቋዎች የሚተረጉሙ ተርጓሚዎች መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈባቸው ቋንቋዎች የሚገኙ ጽሑፎችን ለማመሳከር ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። አዲስ ዓለም ትርጉም ጽሑፉ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ የነበረውን ትርጉም የማይደብቀው ከሆነ በተቻለ መጠን ቃል በቃል ለመተርጎም ታልሞ የተዘጋጀ ትርጉም ነው። ተርጓሚዎቹ በዛሬው ጊዜ ያሉ አንባቢዎች መጽሐፍ ቅዱስን በተጻፈበት ዘመን የነበሩት አንባቢዎች የተረዱትን ያህል እንዲረዱት አድርገው ለመተርጎም ጥረት ያደርጋሉ።

አንዳንድ የቋንቋ ምሑራን የአተረጓጎም ስህተት መኖሩንና ተርጓሚዎች ሃይማኖታዊ ወገናዊነት አጥቅቷቸው የማይሆን ሐሳብ ጨምረው መሆኑን ለማረጋገጥ አዲስ ዓለም ትርጉምን ጨምሮ ብዙ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን መርምረው ነበር። እንዲህ ያለውን ምርመራ ካደረጉት ምሑራን መካከል አንዱ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሰሜናዊ አሪዞና ዩኒቨርሲቲ የሃይማኖት ጥናት ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ጄሰን ዴቪድ ቤዱን ናቸው። ፕሮፌሰሩ በ2003፣ “እንግሊዝኛ ተናጋሪ በሆነው ዓለም በሰፊው ከሚሠራባቸው መጽሐፍ ቅዱሶች” ውስጥ በዘጠኙ ላይ ያደረጉትን ጥናት በሚመለከት ባለ 200 ገጽ ሪፖርት አሳትመው ነበር። * “በትርጉም ሥራ ወቅት ተርጓሚዎቹ ሃይማኖታዊ ወገናዊነት ሊያጠቃቸው የሚችለው” አወዛጋቢ ትርጉም ባላቸው ጥቅሶች ላይ በመሆኑ ፕሮፌሰሩ በጥናታቸው ላይ እንዲህ ባሉ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ላይ አተኩረዋል። ግሪክኛውን ጽሑፍ በዚህ ወቅት ከእያንዳንዱ የእንግሊዝኛ ትርጉም ጋር በማስተያየት ተርጓሚዎቹ በሃይማኖታዊ ወገናዊነት የተነሳ ትርጉሙን ለመለወጥ ሙከራ አድርገው እንደሆነ ለማረጋገጥ ጥረት አድርገዋል። ታዲያ ያገኙት ውጤት ምን ነበር?

ቤዱን እንደገለጹት ኅብረተሰቡም ሆነ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን በአዲስ ዓለም ትርጉም ላይ ያሉት ልዩነቶች የተፈጠሩት፣ ተርጓሚዎቹ እምነታቸው ተጽዕኖ ስላሳደረባቸው ነው የሚል አመለካከት አላቸው። ይሁን እንጂ ቤዱን “አብዛኞቹ ልዩነቶች የተፈጠሩት አዲስ ዓለም ትርጉም የጥንቶቹ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች የተጠቀሙባቸውን አገላለጾች ቃል በቃል እንዲሁም በጥንቃቄ በማስቀመጡና [ከሌሎቹ ትርጉሞች] ይበልጥ ትክክለኛ በመሆኑ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ቤዱን አዲስ ዓለም ትርጉም አንዳንድ ሐሳቦችን የተረጎመበትን መንገድ ባይቀበሉም ይህ ትርጉም “ከመረመርኳቸው ትርጉሞች ሁሉ በትክክለኛነቱ በእጅጉ የላቀ ነው” ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ “በጣም ግሩም” ትርጉም እንደሆነ በመናገር አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

በእስራኤል ውስጥ የዕብራይስጥ ቋንቋ ምሑር የሆኑት ዶክተር ቤንጃሚን ከዳር አዲስ ዓለም ትርጉምን በሚመለከት ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል። በ1989 እንደሚከተለው ብለው ነበር:- “ይህ ትርጉም ጥንታዊውን ቅጂ በተቻለ መጠን በትክክል ለመረዳትና ለማስቀመጥ ልባዊ ጥረት እንደተደረገ ያሳያል። . . . በአዲስ ዓለም ትርጉም ውስጥ ተርጓሚዎቹ በሃይማኖታዊ ወገናዊነት ሳቢያ ቀድሞ ያልነበረ ሐሳብ ለመጨመር እንደሞከሩ የሚያሳይ አንድም ማስረጃ አላገኘሁም።”

እንግዲያው ራስህን እንደሚከተለው እያልክ ጠይቅ:- ‘መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብ ግቤ ምንድን ነው? ለማንበብ የምፈልገው እምብዛም ትክክል ባይሆንም ለማንበብ የሚቀለኝን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ነው? ወይስ የምፈልገው በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፈው ከመጀመሪያው ጽሑፍ ጋር በተቻለ መጠን የሚቀራረብ ሐሳብ ያለውን ትርጉም ማንበብ ነው?’ (2 ጴጥሮስ 1:20, 21) ለማንበብ የተነሳህበት ዓላማ በምትመርጠው ትርጉም ላይ ለውጥ ያመጣል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.22 ከአዲስ ዓለም ትርጉም ውጪ እኚህ ምሑር ምርምር ያደረጉባቸው ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ዚ አምፕሊፋይድ ኒው ቴስታመንት፣ ዘ ሊቪንግ ባይብል፣ ዘ ኒው አሜሪካን ባይብል ዊዝ ሪቫይዝድ ኒው ቴስታመንት፣ ኒው አሜሪካን ስታንዳርድ ባይብል፣ ዘ ሆሊ ባይብልኒው ኢንተርናሽናል ቨርዥን፣ ዘ ኒው ሪቫይዝድ ስታንዳርድ ቨርዥን፣ ዘ ባይብል ኢን ቱደይስ ኢንግሊሽ ቨርዥን እና ኪንግ ጄምስ ቨርዥን ናቸው።

[ሥዕል]

“የአዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም” በአሁኑ ጊዜ በብዙ ቋንቋዎች ይገኛል

[በገጽ 12, 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የማሶራውያን ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“. . . እንግዲህ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች የበለጠ ዋጋ አላችሁ” የሚሉትን የሉቃስ 12:7 ቃላት የያዘ ቁራጭ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]

ከላይ ያለው ገጽ:- National Library of Russia, St. Petersburg; ሁለተኛውና ሦስተኛው:- Bibelmuseum, Münster; ከበስተጀርባ ያለው:- © The Trustees of the Chester Beatty Library, Dublin