በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጊዜ የማይሽረው የአምላክ ፍቅር መግለጫ

ጊዜ የማይሽረው የአምላክ ፍቅር መግለጫ

ጊዜ የማይሽረው የአምላክ ፍቅር መግለጫ

“የጥንቱ ዓለም ሰባት አስደናቂ ነገሮች” የተሰኙት ድንቅ ሥራዎች ይህንን ስያሜ ያገኙት በሰዎች አእምሮ ውስጥ ከፍተኛ የአድናቆት ስሜት በመፍጠራቸው ነው። ይሁን እንጂ ከፒራሚዶች በስተቀር ሁሉም በአሁኑ ጊዜ አይገኙም። በሌላ በኩል ግን መጽሐፍ ቅዱስ ትሑት የሆኑ ሰዎች በቀላሉ ሊበላሹ በሚችሉ ነገሮች ላይ የጻፉት ቢሆንም ትክክለኛነቱን እንደጠበቀ እስከ ዘመናችን መቆየት ችሏል። በዚህ ልዩ መጽሐፍ ላይ ሙሉ እምነት መጣል እንችላለን።—ኢሳይያስ 40:8፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

ይሖዋ አምላክ ሐሳቡን በጽሑፍ እንዲሰፍር ማድረጉ መልእክቱ ውስን የሆነ የማስታወስ ችሎታ ባላቸው የሰው ልጆች እንዳይዛባ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በተጨማሪም አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጻፍ የተጠቀመባቸው ሰዎች መጽሐፉን ቀለል ባለ መንገድ መጻፋቸው ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ያላቸው ሰዎችም እንኳ አንብበው እንዲረዱት አስችሏል። (የሐዋርያት ሥራ 4:13) አንተም ብትሆን ከፈጣሪ እንዲሁም መጽሐፉን እንዲጽፉ በመንፈሱ ካነሳሳቸው ጸሐፊዎች የምትጠብቀው ይህንን አይደል? ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ በሰፊው መሰራጨቱ አምላክ፣ በየትኛውም አካባቢ ለሚኖሩና ማንኛውንም ዓይነት ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎች ከፍተኛ ፍቅር እንዳለው የሚያረጋግጥ ነው። (1 ዮሐንስ 4:19) መጽሐፍ ቅዱስ እንደልብ የሚገኝ መሆኑ ዋጋማነቱን አይቀንሰውም፤ እንዲያውም ተፈላጊነቱን የሚያሳይ ነው!

የመጽሐፍ ቅዱስ ይዘትም ስለ አምላክ ፍቅር ተጨማሪ ማረጋገጫ ይሰጠናል። ቀደም ባሉት ርዕሶች ላይ እንደተመለከትነው የአምላክ ቃል፣ ወደ ሕልውና የመጣነው እንዴት እንደሆነ፣ ሕይወት ይህን ያህል አጭር የሆነውና በመከራ የተሞላው ለምን እንደሆነ እንዲሁም አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት ለችግሩ መፍትሔ የሚያመጣበትን መንገድ ይገልጽልናል። በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜም እንኳ በሕይወታችን ደስታና እርካታ እንድናገኝ የሚያስችሉንን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች ተመልክተናል። (መዝሙር 19:7-11፤ ኢሳይያስ 48:17, 18) ከሁሉም በላይ ፈጣሪያችን፣ ሰይጣን በተናገረው ሐሰት ምክንያት በስሙ ላይ የመጣውን ነቀፋ የሚያስወግደው እንዴት እንደሆነ አይተናል።—ማቴዎስ 6:9

በዘመናችን ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ጠቃሚ ምክሮችን የያዘ ብሎም ችግር ለሚፈራረቅበት የሰው ዘር ተስፋን የሚፈነጥቅ ሌላ ምን መጽሐፍ አለ? በእርግጥም፣ የሐሰት አማልክትንና ኃያላን ሰዎችን ለማወደስ ተብለው ከተሠሩት የጥንቱ ዓለም ሰባት አስደናቂ ነገሮች በተለየ መልኩ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ለሰብዓዊ ፍጥረታቱ ያለውን ጊዜ የማይሽረውንና ራስ ወዳድነት የሌለበትን ፍቅሩን የሚያሳይ ነው።

ከዚህ ቀደም መጽሐፍ ቅዱስን አንብበህ የማታውቅ ከሆነ ከአሁን ጀምሮ ለምን አትመረምረውም? በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ ከስድስት ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎችን በነፃ መጽሐፍ ቅዱስ እያስጠኑ ነው። እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥም እምነት የሚጣልበትና በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ የአምላክ ቃል መሆኑን ቅን የሆኑ ሰዎች እንዲገነዘቡ መርዳት መቻላቸውን እንደ ትልቅ መብት ይቆጥሩታል።—1 ተሰሎንቄ 2:13