በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እምነት ሊጣልበት ይችላል

እምነት ሊጣልበት ይችላል

እንግሊዛዊው ጸሐፊ ተውኔት ዊልያም ሼክስፒር “የበሰበሰን ጣውላ አትመነው” በማለት ጽፏል። አንተም ብትሆን ከእንጨት በተሠራ ድልድይ ላይ ለመሻገር ከመሞከርህ በፊት እንጨቱ አለመበስበሱን ማረጋገጥ እንደምትፈልግ የታወቀ ነው።

እነዚህ የሼክስፒር ቃላት የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን ከዛሬ 3,000 ዓመታት በፊት “ተላላ ሰው ሁሉን ያምናል፤ አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል” በማለት ከተናገረው ሐሳብ ጋር ይስማማሉ። (ምሳሌ 14:15) አዎን፣ የሰማውን ሁሉ እየተቀበለ፣ ከንቱ በሆኑ ምክሮችና ትምህርቶች ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎችንና ተግባሮችን እያደረገ ሕይወቱን በጭፍን የሚመራ ሰው ተላላ ወይም ሞኝ ነው። በበሰበሰ የእንጨት ድልድይ ላይ ለመሻገር መሞከር አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል ሁሉ መሠረተ ቢስ በሆኑ ነገሮች ላይ እምነት መጣልም ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ታዲያ ‘እምነት ልንጥልበት የሚገባ አስተማማኝ መመሪያ ይኖራል?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።

በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ተብሎ በሚጠራው ጥንታዊ መጽሐፍ ላይ ሙሉ እምነት ጥለዋል። እነዚህ ሰዎች አካሄዳቸውን ለመምራት በዋነኝነት የሚጠቀሙት በመጽሐፍ ቅዱስ ነው። ከዚህ መጽሐፍ በሚያገኙት ምክር ላይ ተመርኩዘው ውሳኔዎችን ያደርጋሉ እንዲሁም የሚያከናውኗቸውን ነገሮች ከትምህርቶቹ ጋር ለማስማማት ይጥራሉ። እንዲህ ያሉ ግለሰቦችን በበሰበሰ ጣውላ ላይ የቆሙ ያህል አድርገን እንመለከታቸዋለን? ለዚህ ጥያቄ የምንሰጠው መልስ ‘በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት ለመጣል የሚያስችል አጥጋቢ ምክንያት አለ?’ ለሚለው ጥያቄ በምንሰጠው መልስ ላይ በእጅጉ የተመካ ነው። ይህ የንቁ! መጽሔት ልዩ እትም እምነት ለመጣል የሚያስችሉንን ማስረጃዎች ይመረምራል።

የዚህ ልዩ እትም ዓላማ አንባቢዎች አንዳንድ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ወይም አመለካከቶችን እንዲቀበሉ መገፋፋት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እምነት ሊጣልበት የሚገባ መጽሐፍ መሆኑን አምነው እንዲቀበሉ ያደረጓቸውን አሳማኝ ማስረጃዎች ማቅረብ ነው። ቀጥሎ የቀረቡትን ርዕሶች ካነበብክ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ እምነት ልትጥልበት የሚገባ መጽሐፍ መሆን አለመሆኑን ራስህ መወሰን ትችላለህ።

ይህን ርዕሰ ጉዳይ ገረፍ ገረፍ አድርገህ ማለፍ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ትኩረት ልትሰጠው ይገባል። ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ ከፈጣሪያችን የተሰጠ አስተማማኝ መመሪያ የያዘ መጽሐፍ ከሆነ አንተም ሆንክ የምትወዳቸው ሰዎች በውስጡ ያለውን ሐሳብ በቁም ነገር ብትመረምሩ ትጠቀማላችሁ።

በመጀመሪያ ግን መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ ጉልህ ሥፍራ የሚሰጣቸውን አንዳንድ ሐቆች እንመልከት። ብዙዎች እንደሚስማሙበት መጽሐፍ ቅዱስ በዓይነቱ ልዩ የሆነ መጽሐፍ ነው።