በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት እንድንጥል የሚያደርጉ ምክንያቶች

5. ፍጻሜ ያገኙ ትንቢቶች

5. ፍጻሜ ያገኙ ትንቢቶች

አንድ የአየር ሁኔታ ትንበያ ባለሙያ የሚያቀርባቸው ዘገባዎች በሙሉ ለረጅም ጊዜ በትክክል ሲፈጸሙ ቆይተዋል እንበል። አንድ ቀን ይህ ሰው ዝናብ እንደሚጥል የሚገልጽ ዘገባ ቢያቀርብ ጃንጥላህን ቤትህ ጥለህ ትሄዳለህ?

መጽሐፍ ቅዱስ በትንቢቶች የተሞላ መጽሐፍ ነው። * ታሪክ እንደሚያረጋግጠው መጽሐፍ ቅዱስ ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶችን በመያዝ ረገድ ጥሩ ስም አትርፏል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ትንቢት ምንጊዜም ትክክል ነው።

ልዩ የሚያደርጓቸው ነገሮች።

የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ብዙውን ጊዜ ተፈላጊውን ጉዳይ በግልጽ ለይተው የሚጠቅሱ ከመሆናቸውም በላይ በውስጣቸው የተገለጹት ጥቃቅን የሚመስሉ ዝርዝር ሐሳቦች እንኳ ሳይቀሩ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ። ደግሞም አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸውን ጉዳዮች የሚያነሱ ሲሆን በተጻፉበት ዘመን የሚኖሩ ሰዎች ከሚያስቡት ተቃራኒ የሆኑ ነገሮች እንደሚከናወኑ ይናገራሉ።

ዓይነተኛ ምሳሌ።

ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ባለው የኤፍራጥስ ወንዝ ላይ የተቆረቆረችው የጥንቷ ባቢሎን “የጥንቱ የምሥራቅ ዓለም የፖለቲካ፣ የሃይማኖትና የባሕል ማዕከል” ተብላ ተጠርታ ነበር። በ732 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ ነቢዩ ኢሳይያስ ባቢሎን እንደምትወድቅ የሚገልጽ አስፈሪ ትንቢት ጻፈ። ኢሳይያስ ሁኔታውን እንዲያው በደፈናው ሳይሆን የሚፈጸሙትን ነገሮች በዝርዝር ለይቶ ጠቅሷል። ለምሳሌ “ቂሮስ” የሚባል ገዢ ባቢሎንን ድል እንደሚያደርጋት፣ እንደ መከላከያ የምትጠቀምባቸው ውኃዎቿ ‘እንደሚደርቁ’ እና በሮቿ ‘ክፍት’ እንደሚተዉ ተናግሯል። (ኢሳይያስ 44:27 እስከ 45:3) ይህ ከተነገረ 200 ከሚያህሉ ዓመታት በኋላ ማለትም ጥቅምት 5, 539 ከክርስቶስ ልደት በፊት ትንቢቱ አንድም ሳይቀር ተፈጸመ። ግሪካዊው ታሪክ ጸሐፊ ሄሮዶቱስ (ከክርስቶስ ልደት በፊት በአምስተኛው መቶ ዘመን) ባቢሎን በትንቢቱ ላይ በተገለጸው ሁኔታ መውደቋን አረጋግጧል። *

ድፍረት የሚጠይቅ ሐሳብ።

ኢሳይያስ ባቢሎንን በሚመለከት “በዘመናት ሁሉ የሚቀመጥባት አይኖርም” የሚል አንድ አስፈሪ ትንቢት ጨምሮ ተናግሯል። (ኢሳይያስ 13:19, 20) በስትራቴጂያዊ ቦታ ላይ ተንሰራፍታ የተቀመጠችው ከተማ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደምትጠፋ የሚገልጽ ትንቢት መናገር በእርግጥም ድፍረት የሚጠይቅ ነው። እንዲህ ያለች ከተማ ብትጠፋም እንኳ እንደገና ትሠራለች ብለህ ትጠብቅ ይሆናል። ምንም እንኳ ባቢሎን ድል ከተደረገች በኋላ ለጥቂት ጊዜያት ብትቆይም የኢሳይያስ ቃላት የኋላ ኋላ መፈጸማቸው አልቀረም። ስሚዝሶኒያን የተሰኘ አንድ መጽሔት እንደዘገበው የጥንቷ ባቢሎን የነበረችበት ቦታ በዛሬው ጊዜ “ለጥ ያለ ሜዳ፣ ሞቃት፣ በረሃማና በአቧራ የተሸፈነ ነው።”

የኢሳይያስ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘበትን መጠን ቆም ብለን ካሰላሰልንበት እጅግ የሚያስደንቅ ሆኖ እናገኘዋለን። ኢሳይያስ የተነበየው ነገር እንደ ኒው ዮርክ ወይም ለንደን ያለች ዘመናዊ ከተማ ከ200 ዓመታት በኋላ እንደምትጠፋና ከዚያ በኋላ ፈጽሞ ሰው ሊኖርባት እንደማይችል ጠበቅ አድርጎ ከመናገር የማይተናነስ ነው። እርግጥ ነው፣ ከሁሉ ይበልጥ የሚያስደንቀው የኢሳይያስ ትንቢት መፈጸሙ ነው! *

መጽሐፍ ቅዱስ ኃያሏ ባቢሎን ቂሮስ በሚባል ገዢ ድል እንደምትደረግ በትክክል ተንብዮ ነበር

እስካሁን ባየናቸው ተከታታይ ርዕሶች ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበት ነው ብለው እንዲያምኑ ካደረጓቸው ማስረጃዎች ውስጥ አንዳንዶቹን መርምረናል። በመሆኑም መጽሐፉ እርምጃቸውን ለመምራት የሚያስችል አስተማማኝ መመሪያ እንደያዘ ይተማመኑበታል። አንተም እምነት ልትጥልበት የምትችል መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ እንድትማር እንጋብዝሃለን።

^ አን.4 የአየር ሁኔታ ትንበያዎች ፍጻሜያቸውን የማያገኙበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ግን በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ናቸው፤ አምላክ ደግሞ ከፈለገ ጣልቃ ገብቶ ትንቢቶቹ ፍጻሜያቸውን ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይችላል።

^ አን.6 ኢሳይያስ የተናገረውን ትንቢት ፍጻሜ በሚመለከት ዝርዝር ሐሳቦችን ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ የተሰኘውን ብሮሹር ገጽ 27-29 ተመልከት።

^ አን.8 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተነገሩት ትንቢቶችና ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ ስለሚያረጋግጡት የታሪክ ማስረጃዎች ተጨማሪ ምሳሌዎችን ለማግኘት ከፈለግህ መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተሰኘውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ገጽ 117-133 ተመልከት።