በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረው ሐሳብ ሰዎች ያመነጩት ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረው ሐሳብ ሰዎች ያመነጩት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረው ሐሳብ ሰዎች ያመነጩት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ በውስጡ ያሉትን ሐሳቦች ማን እንደጻፋቸው በግልጽ ይናገራል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት መጻሕፍት መካከል አንዳንዶቹ የሚጀምሩት “የነህምያ ቃል፣” ‘ኢሳይያስ ያየው ራእይ’ እንዲሁም “ወደ ኢዩኤል የመጣው የእግዚአብሔር ቃል” እንደሚሉት ባሉ ሐረጎች ነው። (ነህምያ 1:1፤ ኢሳይያስ 1:1፤ ኢዩኤል 1:1) አንዳንድ ታሪኮች ደግሞ ጋድ፣ ናታን ወይም ሳሙኤል እንደጻፏቸው ተደርገው ተገልጸዋል። (1 ዜና መዋዕል 29:29) በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ በሚገኙት አብዛኞቹ መዝሙሮች መግቢያ ላይ ያሉት መግለጫዎች ያቀናበሩትን ሰዎች ማንነት ይገልጻሉ።—መዝሙር 79፣ 88፣ 89፣ 90፣ 103 እና 127

አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች ስለተጻፈ መጽሐፉ እንደማንኛውም ሌላ መጽሐፍ የሰው አእምሮ ያመነጨው እንደሆነ ይናገራሉ። ይሁንና ይህ ዓይነቱ አመለካከት ትክክል ነው?

አርባ ሰዎች ቢጽፉትም ምንጩ አንድ ነው

አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ብቻውን እውነተኛ አምላክ የሆነው ይሖዋ መጽሐፉን እንዲጽፉ ሥልጣን እንደሰጣቸውና በእሱ ወይም ወኪሉ በሆነ አንድ መልአክ ተመርተው እንደጻፉ ገልጸዋል። (ዘካርያስ 1:7, 9) የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን የጻፉት ነቢያት ከ300 ጊዜ በላይ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” በማለት ተናግረዋል። (አሞጽ 1:3፤ ሚክያስ 2:3፤ ናሆም 1:12) አብዛኞቹ ጽሑፎቻቸው የሚጀምሩት “ወደ ሆሴዕ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው” እንደሚሉት ባሉ ሐረጎች ነው። (ሆሴዕ 1:1፤ ዮናስ 1:1) ሐዋርያው ጴጥሮስ የአምላክን ነቢያት አስመልክቶ ሲናገር “ከእግዚአብሔር የተላኩ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናገሩት” ብሏል።—2 ጴጥሮስ 1:21

በመሆኑም እርስ በርሳቸው የሚስማሙ የተለያዩ መጻሕፍትን ያቀፈው መጽሐፍ ቅዱስ፣ በአምላክ መንፈስ መሪነት እንደተጻፈ በተናገሩ በርካታ ሰዎች የተጻፈ መጽሐፍ ነው። በሌላ አባባል አምላክ ሐሳቡን በጽሑፍ ለማስፈር ሰዎችን ተጠቅሟል። ታዲያ ይህን ያደረገው እንዴት ነው?

‘የአምላክ መንፈስ ያለበት’

ሐዋርያው ጳውሎስ “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው” በማለት ገልጿል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ‘የአምላክ መንፈስ ያለበት’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ቀጥተኛ ፍቺው “አምላክ የተነፈሰበት” የሚል ነው። ይህም ሲባል አምላክ መልእክቱን ወደ ጸሐፊዎቹ አእምሮ በማስተላለፍ አስተሳሰባቸውን ለመምራት የማይታየውን ኃይሉን ተጠቅሟል። በድንጋይ ላይ የተቀረጹት አሥርቱ ትእዛዛት ግን በቀጥታ በይሖዋ የተጻፉ ናቸው። (ዘፀአት 31:18) አምላክ ለአገልጋዮቹ መልእክቱን በቃል የተናገረባቸው ጊዜያትም አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ዘፀአት 34:27 “እግዚአብሔር ሙሴን፣ ‘እነዚህን ቃሎች ጻፋቸው’” ብሎ እንዳዘዘው ይናገራል።

በሌሎች ጊዜያት ደግሞ አምላክ በጽሑፍ እንዲሰፍር የፈለገውን ነገር ሰዎች በራእይ እንዲመለከቱት አድርጓል። ሕዝቅኤል “እኔም የእግዚአብሔርን ራእይ አየሁ” ያለው በዚህ ምክንያት ነው። (ሕዝቅኤል 1:1) በተመሳሳይም “ዳንኤል በዐልጋው ላይ ተኝቶ ሳለ ሕልም አለመ፤ ራእይም አየ፤ የሕልሙንም ዋና ሐሳብ ጻፈው።” (ዳንኤል 7:1) የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ መጽሐፍ የሆነው ራእይ ለሐዋርያው ዮሐንስ የተላለፈውም በዚህ መንገድ ነው። ዮሐንስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- ‘በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፤ የመለከትን ድምፅ የሚመስል ታላቅ ድምፅ ከበስተ ኋላዬ ሰማሁ፤ ድምፁም፣ “የምታየውን በጥቅልል መጽሐፍ” ጻፍ አለኝ።’—ራእይ 1:10, 11

የጸሐፊዎቹ ስሜት ተንጸባርቆበታል

መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሳሽነት ተጽፏል ሲባል ጸሐፊዎቹ ምንም ዓይነት ጥረት አላደረጉም ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የመክብብ መጽሐፍ ጸሐፊ ‘ትክክለኛውን ቃል ለማግኘት እንደተመራመረ እንዲሁም ቅንና እውነት የሆነውን እንደጻፈ’ ገልጿል። (መክብብ 12:10) ዕዝራ ታሪካዊ ዘገባዎቹን ለማጠናቀር ቢያንስ 14 የሚያህሉ ጽሑፎችን አመሳክሯል፤ ከእነዚህም መካከል ‘የንጉሥ ዳዊት መዝገብ’ እንዲሁም ‘የይሁዳና የእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መዛግብት’ ይገኙበታል። (1 ዜና መዋዕል 27:24፤ 2 ዜና መዋዕል 16:11) ወንጌል ጸሐፊው ሉቃስም ‘ሁሉን ከመሠረቱ በጥንቃቄ ከመረመረ በኋላ፣ ታሪኩን ቅደም ተከተሉን በጠበቀ ሁኔታ ጽፏል።’—ሉቃስ 1:3

አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የጸሐፊውን ማንነት ይጠቁማሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ከመሆኑ በፊት ቀረጥ ሰብሳቢ የነበረው ማቴዎስ ዘገባውን በአኃዝ አስደግፎ ያቀርብ ነበር። ከወንጌል ጸሐፊዎች መካከል ኢየሱስ አልፎ የተሰጠው ‘በሠላሳ ጥሬ ብር’ መሆኑን የዘገበው እሱ ብቻ ነው። (ማቴዎስ 27:3፤ ማርቆስ 2:14) ሐኪም የነበረው ሉቃስ ከሕክምና ሙያ አንጻር ዝርዝር ሐሳቦችን ይጠቅስ ነበር። ኢየሱስ የፈወሳቸው አንዳንድ ሰዎች የነበሩበትን ሁኔታ ሲገልጽ “ኀይለኛ ትኩሳት” እና “ለምጽ የወረሰው” እንደሚሉት ያሉ አባባሎችን ተጠቅሟል። (ሉቃስ 4:38፤ 5:12፤ ቈላስይስ 4:14) ከዚህ መመልከት እንደሚቻለው ይሖዋ ጸሐፊዎቹ መልእክቱን በራሳቸው አባባልና የአጻጻፍ ስልት ተጠቅመው እንዲያሰፍሩት ፈቅዶላቸዋል፤ ያም ሆኖ ግን እሱ የሚፈልገውን ሐሳብ በትክክል እንዲጽፉ ለማድረግ አእምሯቸውን ይመራ ነበር።—ምሳሌ 16:9

የመጨረሻው ውጤት

በተለያዩ ቦታዎች ይኖሩ የነበሩ አርባ የሚያክሉ ሰዎች ከ1,600 በሚበልጡ ዓመታት ውስጥ የጻፉት መጽሐፍ ሙሉ በሙሉ እርስ በርሱ የሚስማማና አንድ ጭብጥ ያለው መሆኑ አያስገርምም? (በገጽ 19 ላይ የሚገኘውን “መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ስለ ምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።) ጸሐፊዎቹ ያሰፈሩት ሐሳብ ከአንድ አካል የመነጨ ባይሆን ኖሮ ይህ ሊሆን አይችልም ነበር።

ይሖዋ ቃሉን ለማስጻፍ የግድ በሰዎች መጠቀም ያስፈልገው ነበር? በጭራሽ። ይሁንና እንዲህ ማድረጉ ጥበቡን የሚያሳይ ነው። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ዙሪያ ሰዎችን የሚማርክ እንዲሆን ካደረጉት ነገሮች ውስጥ አንዱ ጸሐፊዎቹ ሰዎች የሚሰሟቸውን ስሜቶች ሁሉ በግልጽ ማስቀመጣቸው ነው። ንጉሥ ዳዊትን እንደ ምሳሌ ብንወስድ የአምላክን ምሕረት ለማግኘት የሚፈልግ አንድ ኃጢአት የሠራ ሰው የሚሰማውን የጥፋተኝነት ስሜት ገልጿል።—መዝሙር 51:2-4, 13, 17፣ በምዕራፉ መግቢያ ላይ ያለው መግለጫ

ምንም እንኳ ይሖዋ ቅዱሳን መጻሕፍትን ለማስጻፍ በሰዎች ቢጠቀምም የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በመጽሐፉ ላይ የነበራቸው ዓይነት እምነት ሊኖረን ይችላል። እነዚህ ክርስቲያኖች ቃሉን የተቀበሉት ‘እንደ ሰው ቃል ሳይሆን እንደ አምላክ ቃል አድርገው’ ነበር።—1 ተሰሎንቄ 2:13

ይህን አስተውለኸዋል?

▪ ‘በቅዱሳን መጻሕፍት’ ውስጥ የሰፈረው ሐሳብ ምንጭ ማን ነው?—2 ጢሞቴዎስ 3:16

▪ ይሖዋ አምላክ ሐሳቡን ለማስተላለፍ ምን ዘዴዎችን ተጠቅሟል?—ዘፀአት 31:18፤ 34:27፤ ሕዝቅኤል 1:1፤ ዳንኤል 7:1

▪ በመንፈስ አነሳሽነት የጻፉት ሰዎች ባሕርይና ዝንባሌ በጻፏቸው መጻሕፍት ላይ የተንጸባረቀው እንዴት ነው? —ማቴዎስ 27:3፤ ሉቃስ 4:38