ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
▪ በአሁኑ ጊዜ ሙሉው የአዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም በ43 ቋንቋዎች የተተረጎመ ሲሆን በሦስት ቋንቋዎች ደግሞ በብሬል ተዘጋጅቷል፤ የአዲስ ዓለም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ደግሞ በሌሎች 18 ቋንቋዎች ተተርጉመዋል፤ እንዲሁም በአንድ ቋንቋ በብሬል ተዘጋጅቷል። እስከ ሐምሌ 2007 ድረስ ባለው ጊዜ በጠቅላላው 143,458,577 ቅጂዎች ታትመዋል።
▪ እስካሁን ሳይጠፋ የቆየው እጅግ ጥንታዊው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የካህን ቡራኬ ተብሎ የሚጠራው ዘኍልቍ 6:24-26 ነው። እንደ ብራና ጥቅልል የተጠቀለሉ በሚመስሉ ሁለት የብር ክታቦች ላይ ተቀርጾ የተገኘው ይህ ጥቅስ የተጻፈው ከክርስቶስ ልደት በፊት በሰባተኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ወይም በስድስተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው።—ቢብሊካል አርኪኦሎጂ ሪቪው፣ ዩ ኤስ ኤ
▪ እስከ ታኅሣሥ 31, 2006 ድረስ ቢያንስ ከአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ላይ የተወሰደ ጥቅስ የተጠቀሰበት ጽሑፍ የታተመባቸው ቋንቋዎችና ቀበሌኛዎች ብዛት 2,426 እንደሆነ ታውቋል። ይህ አኃዝ ከዚያ በፊት ከነበረው ዓመት በ23 ይበልጣል።—የተባበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት፣ ብሪታንያ
▪ ከአሜሪካውያን መካከል 28 በመቶ የሚሆኑት መጽሐፍ ቅዱስን “ቃል በቃል ልንረዳው የሚገባን . . . ትክክለኛው የአምላክ ቃል” እንደሆነ አድርገው የሚመለከቱት ሲሆን 49 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ “በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ የአምላክ ቃል ቢሆንም ሁሉንም ነገር ቃል በቃል መረዳት አይገባንም” የሚል እምነት አላቸው፤ የተቀሩት 19 በመቶ የሚያህሉ ሰዎች ደግሞ “አፈ ታሪኮችን የያዘ መጽሐፍ” እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል።—ጋልአፕ የዜና አገልግሎት፣ ዩ ኤስ ኤ
እጅግ ጥንታዊ የሆነው የቻይንኛ መጽሐፍ ቅዱስ
“ወደ ቻይንኛ ስለተተረጎመ የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገር እጅግ ጥንታዊ የሆነ ጽሑፍ በ781 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በተሠራ የድንጋይ ሐውልት [በስተግራ] ላይ” እንደተገኘ የፔኪንግ ዩኒቨርሲቲ ምሑር የሆኑት ይይ ቼን ይናገራሉ። ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው የሚል እምነት ባላቸው ኔስቶሪያን ተብለው በሚጠሩ ክርስቲያኖች የተገነባው ይህ ሐውልት በ1625 የተገኘው ሼዓን በተባለች ከተማ ነበር። ቼን እንዲህ ብለዋል:- “ቻይናውያን ለሐውልቱ የሰጡት ስም ‘ከዳቺን መጥቶ ቻይና ውስጥ ለተስፋፋ አንጸባራቂ ሃይማኖት የቆመ መታሰቢያ’ የሚል ትርጉም አለው፤ (. . . ዳቺን የሚለው አጠራር በቻይንኛ የሮማን ግዛት ያመለክታል።)” አክለውም “በሐውልቱ ላይ ካገኘናቸው ጽሑፎች መካከል ‘እውነተኛ ቀኖና’ እና ‘መጽሐፍ ቅዱስን መተርጎም’ የሚል ትርጉም ያላቸው የቻይንኛ አገላለጾች ይገኙበታል” ብለዋል።
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
© Réunion des Musées Nationaux/Art Resource
ረግረግ ውስጥ የተገኘ ቅርስ
በ2006 አየርላንድ ውስጥ በአንድ ረግረጋማ ቦታ ለማዳበሪያ የሚሆን ብስባሽ ቆፍረው የሚያወጡ ሠራተኞች በስምንተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ እንደተዘጋጀ የሚገመት የመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ ግልባጭ አገኙ። በአሁኑ ጊዜ ከሚገኙት ጥቂት የዚያ ዘመን የላቲን ቅጂዎች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ጽሑፍ ውድ ሀብት ወይም ታላቅ ቅርስ እንደሆነ ተገልጿል። መጀመሪያ በተጠረዙበት ሁኔታ የሚገኙት የዚህ መጽሐፍ 100 ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ የብራና ገጾች ከፍተኛ ጥራት እንዳላቸው ታውቋል። “ከመጽሐፉ ጋር በስብሰው የተገኙት መጠቅለያና ከቆዳ የተሠራ ቦርሳ መጽሐፉ ሆን ተብሎ እንደተደበቀ ይጠቁማሉ፤ ይህም የተደረገው ከ1,200 ዓመታት በፊት የነበሩት የስካንዲኔቪያ ወራሪዎች እንዳያገኙት ታስቦ ሊሆን ይችላል” በማለት የለንደኑ ዘ ታይምስ ዘግቧል። የመጽሐፉ ገጾች እርስ በርስ የተጣበቁና በከፊል የበሰበሱ ቢሆኑም በመስኩ የተሰማሩ ባለሙያዎች ገጾቹን መነጣጠልና ለመጪው ትውልድ ጠብቀው ማቆየት እንደሚችሉ በእርግጠኝነት ይናገራሉ።
ከጭነት መኪናዎች ላይ የተገኘ ታሪክ
አርኪኦሎጂስቶች የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ከነበረበት ሥፍራ በጭነት መኪና ተወስዶ ከተገለበጠ አፈር ውስጥ እስራኤላውያን በቦታው ከመስፈራቸው በፊት ጀምሮ እስከ ዘመናችን ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በነበሩ ሰዎች የተሠሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ዕቃዎችን አግኝተዋል። ከእነዚህ ዕቃዎች ውስጥ በዚያ ቦታ የነበረውን የመጀመሪያውን የአይሁድ ቤተ መቅደስ ያጠፋው የናቡከደነፆር ሠራዊት ይጠቀምበት ከነበረው ጋር የሚመሳሰል ቀስት ይገኝበታል። ከግኝቶቹ መካከል በጣም አስደናቂ የሚባለው በሰባተኛው ወይም በስድስተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት የተሠራውና ገዳልያሁ ቤን ኢሜር ሀ ኮሄን የሚል የዕብራይስጥ ስም እንደያዘ የሚነገርለት የሸክላ ማኅተም ነው። ጋብሪኤል ባርካይ የተባሉ አርኪኦሎጂስት እንደሚሉት ከሆነ የዚህ ማኅተም ባለቤት “መጽሐፍ ቅዱስ [ኤርምያስ 20:1] ካህንና የቤተ መቅደስ አለቃ እንደሆነ የሚናገርለት የጳስኮር ኢሜር ወንድም ሳይሆን አይቀርም።”