በዓይነቱ ልዩ የሆነ መጽሐፍ
“በታሪክ ውስጥ በሰፊው የተሰራጨ መጽሐፍ ቢኖር መጽሐፍ ቅዱስ ነው።”—ዘ ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ
ከ550 ዓመታት በፊት ጀርመናዊው ዮሐንስ ጉተንበርግ እሱ ራሱ በፈለሰፈው ተንቀሳቃሽ የሕትመት መሣሪያ አማካኝነት አንዳንድ ነገሮችን ማተም ጀመረ። በማሽኑ ያተመው የመጀመሪያው መጽሐፍ ትልቅ ግምት የሚሰጠው መጽሐፍ ቅዱስ ነበር። * ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ለቁጥር የሚያታክቱ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳስሱ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠሩ መጻሕፍት ታትመዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከእነዚህም ሁሉ በላቀ መጠን ተሰራጭቷል።
እስካሁን ድረስ ከ4.7 ቢሊዮን የሚበልጡ መጽሐፍ ቅዱሶች (በሙሉም ሆነ በከፊል) እንደታተሙ ይገመታል። ይህ አኃዝ በሰፊው በመሰራጨት ረገድ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ኮቴሽንስ ፍሮም ቼርማን ማኦ ከተሰኘው ጽሑፍ ከአምስት እጥፍ በላይ ይበልጣል።
በቅርቡ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ወይም የተወሰነው ክፍል ከ50 ሚሊዮን በላይ በሚሆኑ ቅጂዎች ተሰራጭቷል። ዘ ኒው ዮርከር በተሰኘ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ዘገባ “መጽሐፍ ቅዱስ በየዓመቱ በብዛት በመሸጥ ረገድ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል” በማለት ይናገራል።
መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉም ይሁን በከፊል ከ2,400 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች ተተርጉሟል። ቢያንስ የተወሰኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ በሚናገራቸው ቋንቋዎች ይገኛሉ።
ግማሽ የሚሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ጽሑፎቻቸውን ያጠናቀቁት ታዋቂው ቻይናዊ ፈላስፋ ኮንፊሽየስም ሆነ የቡድሂዝም እምነት መሥራች የሆነው ሲድሃርታ ጋውታማ ከመወለዳቸው በፊት ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ኪነ ጥበብ ላይ፣ ለምሳሌ ያህል ታዋቂ በሆኑ የሥነ ሥዕል፣ የሙዚቃና የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል።
መጽሐፍ ቅዱስ መንግሥታት የጣሏቸውን እገዳዎች፣ ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎች ያካሄዱትን የማቃጠል ዘመቻና ተቺዎች የሰነዘሩትን ጥቃት ተቋቁሞ አልፏል። በታሪክ ውስጥ እንዲህ ያለ ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶበት ከጥፋት የዳነ ሌላ መጽሐፍ የለም።
ከላይ የተጠቀሱት ሐቆች ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ናቸው ቢባል አትስማማም? እርግጥ ነው፣ አስደናቂ የሆኑ ዝርዝር ሐሳቦችና አኃዛዊ መረጃዎች ብቻቸውን መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበት መጽሐፍ መሆኑን አያረጋግጡም። ቀጥለን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እምነት ሊጣልበት የሚገባ መጽሐፍ ነው ብለው እንዲያምኑ ያደረጓቸውን አምስት ምክንያቶች እንመረምራለን።
^ አን.3 የጉተንበርግ መጽሐፍ ቅዱስ በላቲንኛ የተተረጎመ ሲሆን ተተርጉሞ የተጠናቀቀው በ1455 ነበር።