የተሳሳተውን አመለካከት ከሐቁ መለየት
የተሳሳተውን አመለካከት ከሐቁ መለየት
ክርስቲያን ሽማግሌ ሆኖ ያገለግል የነበረው ጢሞቴዎስ እውነተኛውን አምላክ የማምለክ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ‘ለሐሰት ትምህርት’ እና ‘ለተረት’ ቦታ እንዳይሰጡ አዟቸው ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 1:3, 4) ይህ ዓይነቱ ምክር በዛሬው ጊዜም አስፈላጊ ነው? አዎን፣ ምክንያቱም ስለ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ስለሚያስተምራቸው ትምህርቶች የሚነገሩት የተሳሳቱ ሐሳቦች ሰዎችን ከእውነተኛው አምልኮ እያራቁ ነው። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነገሩ አንዳንድ የተለመዱ ሐሳቦች ከዚህ በታች ሰፍረዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብም እዚህ ላይ ተገልጿል። እነዚህን ሁለት ሐሳቦች ማወዳደርህ የተሳሳተውን አመለካከት ከሐቁ መለየት እንድትችል ይረዳሃል።
▪ የተሳሳተው አመለካከት:- በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹት ተአምራት ሊፈጸሙ የማይችሉ ናቸው።
ሐቁ:- ሰዎች ስለ አምላክ የፍጥረት ሥራዎች ብዙ የሚማሯቸው ነገሮች አሉ። የትኛውም ሳይንቲስት ቢሆን ስለ ስበት ሕግ የተሟላ ማብራሪያ መስጠት፣ በአንድ አቶም ውስጥ የሚገኙትን ነገሮች በሙሉ በትክክል መግለጽ አሊያም የጊዜን ምንነት በዝርዝር ማስረዳት አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔርን ጥልቅ ምስጢር ልትለካ ትችላለህን? ወይስ ሁሉን የሚችለውን አምላክ መርምረህ ትደርስበታለህን?” ይላል። (ኢዮብ 11:7) ፍጥረት ከመረዳት ችሎታችን በላይ ስለሆነ አንዳንድ ታዋቂ ሳይንቲስቶች አንድ ነገር ሊፈጸም አይችልም ብለው ላለመናገር በጣም ይጠነቀቃሉ።
▪ የተሳሳተው አመለካከት:- ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ አምላክ ያደርሳሉ።
ሐቁ:- ኢየሱስ “በትምህርቴ ብትጸኑ እናንተ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነጻ ያወጣችኋል” ብሏል። (ዮሐንስ 8:31, 32) ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ አምላክ የሚያደርሱ ከሆነ አባላቶቻቸው ነጻ የሚወጡት ከምንድን ነው? እንዲያውም ኢየሱስ ‘ወደ ሕይወት በሚያደርሰው መንገድ’ ላይ የሚጓዙት ሰዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ጥቂት እንደሆኑ ተናግሯል።—ማቴዎስ 7:13, 14
▪ የተሳሳተው አመለካከት:- ጥሩ ሰዎች በሙሉ ሲሞቱ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ።
ሐቁ:- “ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ። ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ። እግዚአብሔርን ደጅ ጥና፤ መንገዱንም ጠብቅ፤ ምድሪቱን ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል።” (መዝሙር 37:11, 29, 34) ወደ ሰማይ የሚሄዱት ታማኝ የሆኑ 144,000 ሰዎች ብቻ ናቸው። ወደዚያ የሚሄዱትም አምላክ የሰጣቸውን ሥራ ለማከናወን ማለትም ‘በምድር ላይ ለመንገሥ’ ነው።—ራእይ 5:9, 10፤ 14:1, 4
▪ የተሳሳተው አመለካከት:- “ብሉይ ኪዳን” ለክርስቲያኖች አይጠቅምም።
ሐቁ:- ‘ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ የአምላክ መንፈስ ያለባቸውና ጠቃሚ ናቸው።’ (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) “በጽናትና ቅዱሳት መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ እንዲኖረን፣ ቀደም ብሎ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና።” (ሮሜ 15:4) “ብሉይ ኪዳን” ማለትም የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን የያዘው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መንፈሳዊ መመሪያ የምናገኝበት አንዱ ምንጭ ከመሆኑም ሌላ “አዲስ ኪዳንን” ማለትም የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ይበልጥ ለመረዳት መሠረት ይሆንልናል።
▪ የተሳሳተው አመለካከት:- ስለ አዳምና ሔዋን የሚናገረውን ታሪክ ጨምሮ የዘፍጥረት መጽሐፍ አብዛኛው ክፍል ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ የተጻፈ ነው።
ሐቁ:- ወንጌል ጸሐፊው ሉቃስ እስከ አዳም ድረስ ያለውን የኢየሱስን የዘር ሐረግ ዘርዝሯል። (ሉቃስ 3:23-38) የዘፍጥረት ዘገባ እውነተኛ ታሪክ ካልሆነ፣ በዘር ሐረጉ ዝርዝር ውስጥ ከሰፈሩት ስሞች መካከል እውነተኞቹ የሚያበቁትና ምሳሌያዊዎቹ የሚጀምሩት የት ላይ ነው? ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ ይኖር የነበረው ኢየሱስ ስለ አዳምና ሔዋን የሚናገረውን ታሪክ ጨምሮ በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ የሰፈሩት ዘገባዎች እውነት መሆናቸውን ያምን ነበር። (ማቴዎስ 19:4-6) በመሆኑም የዘፍጥረትን ዘገባ መጠራጠር በኢየሱስም ሆነ በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ተአማኒነት ላይ ጥያቄ ከማንሳት ተለይቶ አይታይም።—1 ዜና መዋዕል 1:1፤ 1 ቆሮንቶስ 15:22፤ ይሁዳ 14