በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዘመን የማይሽራቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች

ዘመን የማይሽራቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች

የሚከተለውን ሁኔታ ለማሰብ ሞክር፦ ጥንታዊ ቅርሳ ቅርሶች የሞሉበትን አንድ ሙዚየም እየጎበኘህ ነው። በሙዚየሙ ውስጥ ካሉት ቅርሶች አብዛኞቹ ተሸራርፈዋል፣ ዝናብና ፀሐይ ስለተፈራረቀባቸው ተበላሽተዋል እንዲሁም ጉዳት ደርሶባቸዋል። በዚያ ላይ የአንዳንዶቹ ቅርሶች የተወሰኑ ክፍሎች ጎድለዋል። ከመካከላቸው አንዱ ግን ምንም የጎደለው ነገር የለም ማለት ይቻላል፤ በቅርጹ ላይ ያለው በአስደናቂ ሁኔታ የተሠራ ንድፍ እንኳ ጥርት ብሎ ይታያል። በመሆኑም አስጎብኚህን “ይኼኛው ከሌሎቹ ይልቅ አዲስ ነው?” ብለህ ጠየቅከው። እሱም “አይደለም፤ እንዲያውም ከአብዛኞቹ የበለጠ ዕድሜ ያለው ሲሆን እድሳትም ተደርጎለት አያውቅም” በማለት መለሰልህ። “ፀሐይና ዝናብ እንዳያበላሸው ተከልሎ ተቀምጦ ነበር?” ብለህ ጠየቅከው። አሁንም አስጎብኚህ “ኧረ በጭራሽ፤ እንዲያውም ከሌሎቹ ይበልጥ ለነፋስና ለዝናብ ተጋልጦ የቆየው ይሄኛው ቅርስ ነው። ብዙዎችም ሊያበላሹት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል” አለህ። በዚህ ጊዜ በመገረም ‘እንዴ፣ ይህ ቅርስ የተሠራው ከምንድን ነው?’ ብለህ አሰብክ።

መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ አስደናቂ ቅርስ ጋር ይመሳሰላል ማለት ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስ ከአብዛኞቹ መጻሕፍት ይበልጥ ዕድሜ ያለው እጅግ ጥንታዊ መጽሐፍ ነው። እርግጥ ነው፣ ጥንታዊ የሆኑ ሌሎች መጻሕፍትም አሉ። ይሁን እንጂ ረጅም ዕድሜ በማስቆጠራቸው ምክንያት እንደተሸራረፉ ቅርሶች ሁሉ፣ አብዛኞቹ ጥንታዊ ጽሑፎችም ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ዋጋማነታቸውን አጥተዋል ወይም ጉዳት ደርሶባቸዋል። ለአብነት ያህል፣ ጽሑፎቹ የያዙት ሳይንስ ነክ ሐሳብ ከአዳዲስ እውቀትና ከተረጋገጡ እውነታዎች ጋር ይቃረናል። ስለ ሕክምና የሚሰጡት ምክርም ብዙውን ጊዜ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን ይመስላል። በዚያ ላይ ደግሞ ብዙዎቹ ጥንታዊ ጽሑፎች እንዳሉ ተጠብቀው መቆየት ስላልቻሉ አሁን ማግኘት የሚቻለው የተወሰኑ ቁርጥራጮችን ብቻ ነው፤ ከፊሎቹ ጠፍተዋል አሊያም ክፉኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከእነዚህ ሁሉ የተለየ ነው። የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የተጻፉት ከ3,500 ዓመታት በፊት ቢሆንም ከመጽሐፉ ውስጥ አንድም የጎደለ ነገር የለም። እንዲሁም ባለፉት በርካታ ዘመናት ውስጥ በተደጋጋሚ ጥቃት የተሰነዘረበት (ለምሳሌ እንዲቃጠል የተደረገ፣ እገዳ የተጣለበት ብሎም ከፍተኛ ትችት የተሰነዘረበት) ቢሆንም በውስጡ የሚገኘው ሐሳብ እንዳለ ተጠብቆ ቆይቷል። አዳዲስ እውቀት መገኘቱ መጽሐፍ ቅዱስን ዘመን ያለፈበት እንዲሆን አላደረገውም፤ እንዲያውም ከዘመኑ የቀደመ ጥበብ የያዘ መጽሐፍ መሆኑ ተረጋግጧል።—“ዘመን ያለፈበት ወይስ ከዘመኑ የቀደመ?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

በዛሬው ጊዜ የሚያስፈልጉን የሥነ ምግባር መመሪያዎች

‘መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምራቸው ነገሮች በእርግጥ ለዘመናችን ጠቃሚ ናቸው?’ የሚል ጥያቄ ታነሳ ይሆናል። መልሱን ለማግኘት ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘በዛሬው ጊዜ የሰው ልጆች ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች ሁሉ አስከፊ የሆኑት የትኞቹ ናቸው? ከሁሉ ይበልጥ አስፈሪ የሆኑትስ የትኞቹ ናቸው?’ ምናልባት ጦርነት፣ የአካባቢ ብክለት፣ ወንጀል ወይም ሙስና ወደ አእምሮህ ይመጡ ይሆናል። እስቲ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን እንመርምር። መመሪያዎቹን ስታነብ ‘ሰዎች እነዚህን የሥነ ምግባር መመሪያዎች አክብረው ቢኖሩ በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ የተሻለ አይሆንም ነበር?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ።

ሰላምን መውደድ

“ሰላም ፈጣሪዎች ደስተኞች ናቸው፤ የአምላክ ልጆች ይባላሉና።” (ማቴዎስ 5:9) “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ።”—ሮም 12:18

ምሕረትና ይቅር ባይነት

“መሐሪዎች ደስተኞች ናቸው፤ ምሕረት ይደረግላቸዋልና።” (ማቴዎስ 5:7) “አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እንኳ እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ። ይሖዋ * በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ።”—ቆላስይስ 3:13

ዘረኝነትን ማስወገድ

አምላክ “በምድር ሁሉ ላይ [እንዲኖሩ] የሰውን ወገኖች በሙሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ።” (የሐዋርያት ሥራ 17:26) “አምላክ [አያዳላም]፤ ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።”—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35

ምድርን በአግባቡ መያዝ

“ይሖዋ አምላክ ሰውየውን ወስዶ እንዲያለማውና እንዲንከባከበው በኤደን የአትክልት ስፍራ አስቀመጠው።” (ዘፍጥረት 2:15) አምላክ “ምድርን እያጠፉ ያሉትን [ያጠፋቸዋል]።”—ራእይ 11:18

ስግብግብነትንና የሥነ ምግባር ብልግናን መጥላት

“አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ንብረቱ ሕይወት ሊያስገኝለት አይችልም፤ ስለዚህ ተጠንቀቁ፤ ከስግብግብነትም ሁሉ ተጠበቁ።” (ሉቃስ 12:15) “ለቅዱሳን የማይገባ ስለሆነ የፆታ ብልግናና ማንኛውም ዓይነት ርኩሰት ወይም ስግብግብነት በመካከላችሁ ከቶ አይነሳ።”—ኤፌሶን 5:3

ሐቀኝነትና በትጋት መሥራት

“በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር እንፈልጋለን።” (ዕብራውያን 13:18) “የሚሰርቅ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፤ ከዚህ ይልቅ . . . በትጋት ይሥራ።”—ኤፌሶን 4:28

የተቸገሩ ሰዎችን መርዳት

“የተጨነቁትን አጽናኗቸው፤ ደካሞችን ደግፏቸው፤ ሁሉንም በትዕግሥት ያዙ።” (1 ተሰሎንቄ 5:14) “ወላጅ አልባ የሆኑ ልጆችንና መበለቶችን በመከራቸው [እርዱ]።”—ያዕቆብ 1:27

መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን መመሪያዎች ከመስጠት ባለፈ መመሪያዎቹን ከፍ አድርገን እንድንመለከታቸው ያሳስበናል፤ በተጨማሪም በዕለት ተዕለት ሕይወታችን እንዴት ተግባራዊ ልናደርጋቸው እንደምንችል ያስተምረናል። ቀደም ሲል የተመለከትናቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ብዙዎች በተግባር ቢያውሏቸው ኖሮ የሰው ልጆች የሚያጋጥሟቸው ችግሮች በእጅጉ አይቀንሱም ነበር? ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጠቃሚና ወቅታዊ ናቸው! ይሁንና የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች በአሁኑ ወቅት ሊጠቅሙህ የሚችሉት እንዴት ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች በአሁኑ ወቅት የሚጠቅሙህ እንዴት ነው?

ከማንም በላይ ጠቢብ የሆነው ሰው “ጥበብ ትክክል መሆኗ በውጤቷ ተረጋግጧል” በማለት በአንድ ወቅት ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 11:19 የግርጌ ማስታወሻዎች) አንተስ በዚህ አባባል አትስማማም? አንድ ምክር፣ ጥበብ ያዘለ መሆኑን መፈተን የሚቻለው በተግባር ላይ አውለኸው የምታገኘውን ውጤት በማየት ነው። ከዚህ አንጻር ‘መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው ምክር በእርግጥ ጠቃሚ ከሆነ በእኔም ሕይወት ላይ ለውጥ ማምጣት የለበትም? ደግሞስ በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥሙኝን ችግሮች ለመፍታት የሚረዳኝ እንዴት ነው?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት።

ዴልፊን * ሕይወቷ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች የተሞላ ከመሆኑም ሌላ አርኪ እንደሆነ ይሰማት ነበር። ይሁንና አሳዛኝ የሆኑ ነገሮች በድንገት ደረሱባት። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ልጇ ሞተችባት። ትዳሯ ፈረሰ። እንዲሁም የገንዘብ ችግር አጋጠማት። እንዲህ በማለት ታስታውሳለች፦ “ልጄን፣ ባሌንና ቤቴን አጥቼ ባዶ እጄን ቀረሁ፤ ሁሉ ነገር ግራ ገባኝ። በባዶነት ስሜት ተዋጥኩ፤ ኃይሌ እንደተሟጠጠና ሕይወቴም ትርጉም የለሽ እንደሆነ ተሰማኝ።”

የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል፦ “የዕድሜያችን ርዝማኔ 70 ዓመት ነው፤ ለየት ያለ ጥንካሬ ካለን ደግሞ 80 ዓመት ቢሆን ነው። ይህም በችግርና በሐዘን የተሞላ ነው፤ ፈጥኖ ይነጉዳል፤ እኛም እናልፋለን።” ዴልፊን ይህ ጥቅስ ምን ያህል እውነት እንደሆነ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የተገነዘበችው በዚህ ወቅት ነበር።—መዝሙር 90:10

ዴልፊን በዚህ አስቸጋሪ ወቅት መጽናኛ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ጀመረች። ይህን በማድረጓም ብዙ ተጠቅማለች። በቀጣዮቹ ሦስት ርዕሶች ላይ እንደተገለጸው፣ ሌሎች ብዙ ሰዎችም የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በሥራ ላይ ማዋላቸው በሕይወታቸው ውስጥ የገጠሟቸውን ችግሮች ለመፍታት አስችሏቸዋል። እነዚህ ሰዎች፣ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ እንደተገለጸው ቅርስ እንደሆነ ይሰማቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አርጅተው ከጥቅም ውጭ ከሆኑትና ጊዜ ካለፈባቸው በርካታ መጻሕፍት በጣም የተለየ ነው። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የሰውን ሳይሆን የአምላክን ሐሳብ ስለያዘ ይሆን?—1 ተሰሎንቄ 2:13

ምናልባት አንተም ሕይወት አጭርና በችግር የተሞላ እንደሆነ አስተውለህ ይሆናል። ታዲያ ችግሮች ተደራርበው ከአቅምህ በላይ እንደሆኑ ሲሰማህ መጽናኛ፣ ድጋፍና አስተማማኝ ምክር ለማግኘት ፊትህን የምታዞረው ወዴት ነው?

ከመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ጥቅም ማግኘት የምትችልባቸውን ሦስት አቅጣጫዎች እስቲ እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ

  1. በተቻለ መጠን ከችግሮች ለመራቅ፣

  2. ችግሮች ሲከሰቱ ለመፍታት እንዲሁም

  3. ልንለውጠው የማንችለውን ሁኔታ ለመቋቋም የሚረዳንን ምክር ይዟል።

ቀጣዮቹ ርዕሶች እነዚህን ሦስት ነገሮች ያብራራሉ።

^ አን.10 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ የግል ስም ይሖዋ ነው።—መዝሙር 83:18

^ አን.24 በዚህና በቀጣዮቹ ሦስት ርዕሶች ላይ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።