በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከችግሮች ለመራቅ የሚረዳ ምክር

ከችግሮች ለመራቅ የሚረዳ ምክር

መጽሐፍ ቅዱስ፣ በውስጡ የያዘው ምክር በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ እንደሆነ እንዲሁም “ለማስተማር፣ ለመውቀስ፣ ነገሮችን ለማቅናት” እንደሚጠቅም ይገልጻል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ታዲያ ይህ እውነት ነው? በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ጥበብ ያዘለ ምክር፣ ከባድ ችግሮችን ሥር ከመስደዳቸው በፊት ለማስወገድ ይረዳል፤ በዚህ ረገድ እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

አልኮል ከመጠን በላይ መጠጣት

ባለፈው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው ዴልፊን በጭንቀት ስትዋጥ አልኮል ከመጠን በላይ መጠጣት ጀመረች። እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ በመጠኑ መጠጣትን አይከለክልም፤ ሆኖም “ብዙ የወይን ጠጅ እንደሚጠጡ ሰዎች . . . አትሁን” ይላል። (ምሳሌ 23:20) ከመጠን በላይ መጠጣት ለከባድ የጤና ችግሮች ሊዳርግ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ያለን ግንኙነት እንዲሻክር ወይም እንዲበላሽ ሊያደርግ ይችላል፤ በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ያለዕድሜያቸው የሚቀጩትም በዚህ ምክንያት ነው። ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ጥበብ ያዘለ ምክር ቢከተሉ ኖሮ ከእነዚህ ችግሮች አብዛኞቹን ማስወገድ ይቻል ነበር።

ዴልፊን ያደረገችው ይህንን ነው። እንዲህ ብላለች፦ “አልኮል መጠጣቴ ለጭንቀቴ መፍትሔ እንዳላመጣ ተገነዘብኩ። በፊልጵስዩስ 4:6, 7 ላይ የሚገኘውን ‘ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ . . . ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ’ የሚለውን ጥበብ ያዘለ ምክር በሥራ ላይ አዋልኩ። አእምሮዬን የሚረብሹ ሐሳቦች ሲመጡብኝና በጭንቀት ስዋጥ በየምሽቱ ወደ ይሖዋ ምልጃ አቀርባለሁ። የሚያበሳጩኝን፣ የሚያሳዝኑኝንና ተስፋ የሚያስቆርጡኝን ነገሮችን ጨምሮ የሚሰማኝን ሁሉ ግልጽልጽ አድርጌ እነግረዋለሁ፤ እንዲሁም አዎንታዊ አመለካከት ለማዳበር እንዲረዳኝ እማጸነዋለሁ። በማግስቱም አዎንታዊ ነገሮች ላይ ለማተኮር የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ። እንዲህ ዓይነት ጸሎት ማቅረቤ በሌሉኝ ነገሮች ላይ ሳይሆን ባገኘኋቸው ነገሮች ላይ እንዳተኩር የረዳኝ ይመስለኛል። የአልኮል መጠጥ ዳግመኛ ላለመጠጣት ወስኛለሁ። አሁን ያለኝን ሰላም በጣም ከፍ አድርጌ ስለምመለከተው ሰላሜን የሚያሳጣኝ ነገር ፈጽሞ ማድረግ አልፈልግም።”

የፆታ ብልግና

ብዙዎች ስሜታቸው እንዲጎዳ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ የፆታ ብልግና ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ግን እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ውስጥ እንዳንገባ ይጠብቁናል፤ የአምላክ ቃል የፆታ ብልግና ወደ መፈጸም ከሚመሩ ነገሮች ለምሳሌ ከማሽኮርመምና የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን ከመመልከት እንድንርቅ ያሳስበናል። ሳሙኤል የሚባል አንድ ወጣት “ማሽኮርመም ለእኔ በጣም ቀላል ነበር” በማለት ይናገራል። “አንዲት ልጅ ያን ያህል ባትማርከኝም እሷ በእኔ እንደተማረከች ማወቅ አይከብደኝም፤ እንዲህ ዓይነቷን ልጅ ማሽኮርመም ደስ ይለኝ ነበር።” ሳሙኤል ለማሽኮርመም ባላሰበበት ጊዜም ጭምር በዚህ ጉዳይ ስሙ ብዙ ጊዜ እንደሚነሳ ሲያውቅ ደግሞ ሆን ብሎ ሴቶችን ማሽኮርመም ጀመረ። ይሁን እንጂ ድርጊቱ ይረብሸው ነበር። “የማደርገው ነገር በጣም ጎጂ ነበር፤ ምክንያቱም የራስ ወዳድነት ዝንባሌ እንዲያድርብኝ ያደርጋል” በማለት ተናግሯል።

ሳሙኤል jw.org በተባለው ድረ ገጽ ላይ የወጣ ለወጣቶች የተዘጋጀ አንድ ርዕስ አነበበ። ይህም በምሳሌ 20:11 ላይ እንዲያሰላስል አነሳሳው፤ ጥቅሱ “ሕፃን እንኳ ባሕርይው ንጹሕና ትክክል መሆኑ በአድራጎቱ ይታወቃል” ይላል። ታዲያ ይህ ጥቅስ የረዳው እንዴት ነው? ሳሙኤል ማሽኮርመም፣ ንጹሕም ሆነ ትክክል እንዳልሆነ ተገነዘበ። አሁን እንዲህ ይላል፦ “የሚያሽኮረምም ወጣት፣ ወደፊት ቢያገባ እንኳ ጥሩ የትዳር ጓደኛ እንዳይሆን የሚያደርጉትን ባሕርያት እያዳበረ እንደሆነ አስተዋልኩ። የወደፊቷ የትዳር ጓደኛዬ ሌላ ሴት ሳሽኮረምም ብታየኝ ምን እንደሚሰማት ማሰብ ጀመርኩ። ይህም ማሽኮርመም፣ ጉዳት የሌለው ልማድ አለመሆኑን እንዳስተውል አደረገኝ። ማሽኮርመም ቀላል ስለሆነ ብቻ ትክክል ነው ማለት አይደለም።” በመሆኑም ሳሙኤል ለውጥ አደረገ። ከማሽኮርመም መቆጠቡ ከፆታ ብልግናም ለመራቅ ረድቶታል።

አንቶንዮ ደግሞ በፆታ ብልግና እንዲሸነፍ ሊያደርገው የሚችል አደገኛ ልማድ ተጠናውቶት ነበር፤ አንቶንዮ የብልግና ምስሎችን ማየትና ጽሑፎችን ማንበብ ሱስ ሆኖበት ነበር። በጣም የሚወዳት የትዳር ጓደኛ ያለችው ቢሆንም ይህ ልማድ በተደጋጋሚ ያሸንፈው ነበር። አንቶንዮ በ1 ጴጥሮስ 5:8 ላይ ማሰላሰሉ በእጅጉ እንደጠቀመው ይሰማዋል። ጥቅሱ “የማስተዋል ስሜታችሁን ጠብቁ፤ ንቁ ሆናችሁ ኑሩ! ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይንጎራደዳል” ይላል። አንቶንዮ እንዲህ ብሏል፦ “የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች ዓለም ላይ ተስፋፍተዋል፤ ደግሞም እነዚህ ምስሎች በቀላሉ ከአእምሮ አይወጡም። በ1 ጴጥሮስ ላይ የሚገኘው ጥቅስ የእነዚህ ፈተናዎች ምንጭ ማን መሆኑን እንድገነዘብ ረድቶኛል። የእነዚያ አስጸያፊ ምስሎች ምንጭ ዲያብሎስ መሆኑ ቶሎ ወደ አእምሮዬ እንዲመጣ ራሴን ማሠልጠን ነበረብኝ። ‘የማስተዋል ስሜቴን ለመጠበቅና ንቁ ሆኜ ለመኖር’ ሊረዳኝ የሚችለው ይሖዋ ብቻ እንደሆነ አሁን ተገንዝቤያለሁ፤ ከእሱ የማገኘው እርዳታ አእምሮዬንና ልቤን ለመቆጣጠር ብሎም ትዳሬን ለማናጋት የሚሰነዘርብኝን ጥቃት ለመመከት አስችሎኛል።” አንቶንዮ የሚያስፈልገውን እርዳታ ያገኘ ሲሆን በመጨረሻም ከመጥፎ ሱሱ መላቀቅ ችሏል። ይህም ከዚያ የባሰ ጣጣ ውስጥ እንዳይገባ ረድቶታል።

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ ከችግሮች ለመራቅ ሊረዳን የሚችል ጠቃሚ ምክር ይዟል። ይሁንና ሥር የሰደዱና በቀላሉ የማይወገዱ ችግሮችን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? የአምላክ ቃል እንደዚህ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት እንዴት እንደሚረዳን እስቲ እንመልከት።

መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ጠቃሚ ምክር ከአንዳንድ ችግሮች ለመራቅ ይረዳናል