በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ ዘጠኝ

በነጠላ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች የተሳካ ሕይወት መምራት ይችላሉ!

በነጠላ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች የተሳካ ሕይወት መምራት ይችላሉ!

1-3. በነጠላ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች ቁጥር እንዲጨምር አስተዋጽኦ ያደረገው ነገር ምንድን ነው? ይህስ ሁኔታ በእንዲህ ዓይነቶቹ ቤተሰቦች ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?

በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በነጠላ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች ከየትኛውም ዓይነት ቤተሰብ ይበልጥ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመሩ እንዳሉ ይነገራል። በሌሎች ብዙ አገሮችም ውስጥ ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። የሚፋቱ፣ የትዳር ጓደኞቻቸውን የሚከዱና ከትዳር ጓደኞቻቸው የሚለያዩ ሰዎች እንዲሁም ከጋብቻ ውጪ የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ከምንጊዜውም በበለጠ ሁኔታ መጨመሩ በሚልዮን በሚቆጠሩ ወላጆችና ልጆች ላይ መጠነ ሰፊ ችግር አስከትሏል።

2 “በ28 ዓመት ዕድሜ ላይ የምገኝ ባሌ የሞተብኝ የሁለት ልጆች እናት ነኝ” ስትል አንዲት ነጠላ ወላጅ ጽፋለች። “ልጆቼን ያለ አባት ማሳደግ ስለማልፈልግ ከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት ውስጥ ወድቄያለሁ። ስለ እኔ የሚያስብ ሰው ያለ እንኳ መስሎ አይታየኝም። ልጆቼ ብዙ ጊዜ ሳለቅስ ይመለከቱኛል፤ ይህ ደግሞ በእነሱ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።” አብዛኞቹ ነጠላ ወላጆች ከብስጭት እንዲሁም ከጥፋተኝነትና ከብቸኝነት ስሜት ጋር የሚታገሉ ከመሆኑም በላይ ከቤት ውጪ ሥራ የመያዝና በቤት ውስጥ ያሉትን ሥራዎች የማከናወን ፈታኝ የሆነ ኃላፊነት በጫንቃቸው ላይ ይወድቃል። አንዲት ነጠላ ወላጅ እንዲህ ብላለች:- “ነጠላ ወላጅ መሆን በርካታ ኳሶችን በአንድ ጊዜ ከማቀላለብ ተለይቶ አይታይም። ለስድስት ወራት ስትለማመዱ ከቆያችሁ በኋላ አራት ኳሶችን በአንድ ጊዜ ማቀላለብ ትለምዳላችሁ። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ወዲያውኑ ሌላ አምስተኛ ኳስ ይወረውርላችኋል!”

3 በነጠላ ወላጅ በሚተዳደሩ ቤተሰቦች ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ብዙውን ጊዜ የራሳቸው ችግሮች ይኖሯቸዋል። አንድ ወላጅ ድንገት ጥሏቸው ሲሄድ ወይም ሲሞት በጣም ሊሰማቸው ይችላል። ብዙ ወጣቶች ወላጃቸውን ማጣታቸው በጣም መጥፎ የሆነ ተጽዕኖ ያሳድርባቸዋል።

4. ይሖዋ በነጠላ ወላጅ ለሚተዳደሩ ቤተሰቦች እንደሚያስብ እንዴት እናውቃለን?

4 በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በነጠላ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች ነበሩ። ቅዱሳን ጽሑፎች ‘አባት ስለሌለው ልጅና’ ስለ “መበለት” በተደጋጋሚ ጊዜያት ይናገራሉ። (ዘጸአት 22:​22፤ ዘዳግም 24:​19-21፤ ኢዮብ 31:​16-22) ይሖዋ አምላክ መከራቸውን በግድየለሽነት የሚመለከት አልነበረም። አምላክ ‘የድሀ አደጎች አባት፣ የባልቴቶችም ዳኛ’ እንደሆነ መዝሙራዊው ገልጿል። (መዝሙር 68:​5) ይሖዋ ዛሬም በነጠላ ወላጅ ለሚተዳደሩ ቤተሰቦች እንደሚያስብ የተረጋገጠ ነው! እንዲያውም ቃሉ እነዚህ ቤተሰቦች የተሳካ ሕይወት መምራት እንዲችሉ የሚረዷቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ያቀፈ ነው።

የዕለት ተዕለት የቤት ውስጥ ሥራዎችን በሚገባ ማከናወን መቻል

5. ነጠላ ወላጆች መጀመሪያ የሚጋረጥባቸው ችግር ምንድን ነው?

5 አንድን ቤተሰብ ማስተዳደር ምን ዓይነት ሥራ ማከናወን እንደሚጠይቅ ተመልከቱ። “ምነው አጠገቤ ወንድ ቢኖር የምትሉባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ፤ ለምሳሌ ያህል መኪናችሁ ያልተለመደ ድምፅ ማሰማት ሲጀምርና ችግሩ ምኑ ላይ እንደሆነ ማወቅ ተስኗችሁ ግራ ስትጋቡ እንዲህ ዓይነት ስሜት ይሰማችኋል” ስትል አንዲት ባልዋን የፈታች ሴት በግልጽ ተናግራለች። ልክ እንደዚሁም ወንዶች ከሚስቶታቸው ሲፋቱ ወይም ሚስቶቻቸው በሞት ሲለዩአቸው ከፊታቸው የሚደቀነው ሥፍር ቁጥር የሌለው የቤት ውስጥ ሥራ መጀመሪያ ላይ በጣም ግራ ሊያጋባቸው ይችላል። ልጆች በቤት ውስጥ እንዲህ ያለ የተመሰቃቀለ ነገር ሲመለከቱ ስሜታቸው ይበልጥ ሊረበሽና ሊጨነቁ ይችላሉ።

ልጆች፣ ከነጠላ ወላጃችሁ ጋር ተባብራችሁ ሥሩ

6, 7. (ሀ) በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጸችው “ባለሙያ ሚስት” ምን ግሩም ምሳሌ ትታለች? (ለ) በነጠላ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች የቤት ውስጥ ኃላፊነቶችን በትጋት መወጣታቸው ሊረዳቸው የሚችለው እንዴት ነው?

6 እንዲህ ዓይነቱን ችግር ለመቋቋም ምን ነገር ሊረዳ ይችላል? በ⁠ምሳሌ 31:​10-31 ላይ የተጠቀሰችው ‘ባለሙያ ሚስት’ የተወችውን ምሳሌ ተመልከቱ። የምታከናውነው ነገር ብዛቱ በጣም ያስደንቃል፤ ትገዛለች፣ ትሸጣለች፣ ትሰፋለች፣ ታበስላለች፣ ርስት ትገዛለች፣ የግብርና ሥራ ታከናውናለች፣ እንዲሁም ትነግዳለች። ይህን ሁሉ ማድረግ የቻለችው እንዴት ነው? ማታ እያመሸችና ጠዋት ማልዳ እየተነሳች በትጋት የምትሠራ ሴት ነበረች። በተጨማሪም አንዳንድ ሥራዎችን ለሌሎች በማከፋፈልም ሆነ ለቤተሰቧ የሚያስፈልገውን ሠርታ በማቅረብ ረገድ በሚገባ የተደራጀች ነበረች። በመሆኑም መመስገኗ ምንም አያስደንቅም!

7 ነጠላ ወላጅ ከሆናችሁ የቤት ውስጥ ኃላፊነቶቻችሁን በሚገባ ለመወጣት ጥረት አድርጉ። ይህ ልጆቻችሁን በጣም የሚያስደስት በመሆኑ በእንዲህ ዓይነቱ ሥራ እርካታ ማግኘት ይኖርባችኋል። ይሁን እንጂ ትክክለኛ ዕቅድ ማውጣትና የተደራጁ መሆን በጣም አስፈላጊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “በጥንቃቄ ዕቅድ አውጥተህ ብትሠራ፣ ብዙ ሀብት ታገኛለህ” ይላል። (ምሳሌ 21:​5 የ1980 ትርጉም) ነጠላ ወላጅ የሆነ አንድ አባት “እስካልራበኝ ድረስ ስለ ምግብ አላስብም ነበር” ሲል በግልጽ ተናግሯል። ይሁን እንጂ ታስቦባቸው በዕቅድ የሚሰሩ ምግቦች በጥድፊያ ከሚሠሩ ምግቦች ይበልጥ ገንቢና ጣፋጭ ናቸው። በተጨማሪም አዳዲስ የቤት ውስጥ ሙያዎችን መማር ሊያስፈልጋችሁ ይችላል። ነጠላ ወላጅ የሆኑ አንዳንድ እናቶች ዐዋቂ የሆኑ ጓደኞችን በማማከር፣ ራስ አገዝ መጽሐፎችን በማንበብና ባለሙያዎችን በመጠየቅ ቀለም መቀባት፣ አንዳንድ የቧንቧ ሥራዎችን ማከናወንና ቀላል የመኪና ጥገና ማድረግ ችለዋል።

8. ነጠላ ወላጅ ያሏቸው ልጆች በቤት ውስጥ የበኩላቸውን እርዳታ ማበርከት የሚችሉት እንዴት ነው?

8 ልጆች እንዲረዷችሁ መጠየቅ ተገቢ ነውን? ነጠላ ወላጅ የሆነች አንዲት እናት እንዲህ ብላለች:- “ልጆቻችሁ እንዲሠሩት በማድረግ ሌላው ወላጅ አለመኖሩ ያጎደለውን ነገር ለመሸፈን ትፈልጋላችሁ።” እንዲህ የምታደርጉበት በቂ ምክንያት ይኖራችሁ ይሆናል፤ ሆኖም ይህ ልጁን ሁልጊዜ ላያስደስተው ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው ወጣቶች አግባብነት ያላቸው ሥራዎች ተሰጥተዋቸው ነበር። (ዘፍጥረት 37:​2፤ መኃልየ መኃልይ 1:​6) ስለዚህ ምንም እንኳ ልጆቻችሁን ከአቅማቸው በላይ ሥራ እንዳታበዙባቸው መጠንቀቅ ያለባችሁ ቢሆንም የምግብ ዕቃዎችን እንዲያጥቡና ክፍላቸውን እንዲያጸዱ ብታደርጓቸው ጥሩ ነው። አንዳንድ ሥራዎችን ለምን አብራችሁ አትሠሩም? ይህ በጣም አስደሳች ሊሆንላችሁ ይችላል።

መተዳደሪያ የማግኘት ችግር

9. ነጠላ ወላጅ የሆኑ እናቶች ብዙውን ጊዜ ገንዘብ ነክ ችግሮች የሚያጋጥሟቸው ለምንድን ነው?

9 አብዛኞቹ ነጠላ ወላጆች የሚያስፈልጓቸውን ገንዘብ ነክ ነገሮች ማሟላት ያስቸግራቸዋል፤ በተለይ ከጋብቻ ውጪ የወለዱ ወጣት እናቶች ብዙውን ጊዜ ይህን ማሟላቱ በጣም ይከብዳቸዋል። * መንግሥት ለሕዝቡ የገንዘብ ድጎማ በሚያደርግባቸው አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ነጠላ ወላጆች ቢያንስ ሥራ እስኪያገኙ ድረስ ይህን እርዳታ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ክርስቲያኖች በእንዲህ ዓይነቶቹ ዝግጅቶች እንዲጠቀሙ ይፈቅዳል። (ሮሜ 13:​1, 6) መበለቶችና ከባሎቻቸው የተፋቱ ሴቶችም ተመሳሳይ የሆኑ ፈታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። ለበርካታ ዓመታት የቤት እመቤት ሆነው የቆዩ ብዙ ሴቶች ወደ ሥራው ዓለም ለመግባት በሚገደዱበት ጊዜ በአብዛኛው የሚያገኙት ሥራ አነስተኛ ክፍያ ያለው ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች የሙያ ሥልጠና በመውሰድ ወይም ደግሞ የአጭር ጊዜ ኮርስ በመከታተል ኑሯቸውን ማሻሻል ችለዋል።

10. ነጠላ ወላጅ የሆነች አንዲት እናት ሰብዓዊ ሥራ መያዝ እንዳለባት ለልጆቿ መግለጽ የምትችለው እንዴት ነው?

10 ሥራ ለመያዝ ጥረት በምታደርጉበት ጊዜ ልጆቻችሁ ቅር ቢሰኙ ልትገረሙም ሆነ የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማችሁ አይገባም። ከዚህ ይልቅ ሥራ መያዝ ያለባችሁ ለምን እንደሆነ ግለጹላቸው፤ በተጨማሪም ይሖዋ ለእነርሱ የሚያስፈልገውን ነገር እንድታሟሉ የሚፈልግ መሆኑን እንዲገነዘቡ እርዷቸው። (1 ጢሞቴዎስ 5:​8) ከጊዜ በኋላ አብዛኞቹ ልጆች ይስተካከላሉ። ይሁን እንጂ በሥራ የተጣበበው ፕሮግራማችሁ የሚፈቅድላችሁን ያህል ከልጆቻችሁ ጋር ብዙ ጊዜ ለማሳለፍ ጥረት አድርጉ። እንዲህ ያለው ፍቅራዊ አሳቢነት ቤተሰቡ ሊያጋጥመው የሚችለው ማንኛውም ዓይነት ገንዘብ ነክ ገደብ የሚፈጥረውን ተጽዕኖ ለመቀነስም ሊረዳ ይችላል።​—⁠ምሳሌ 15:​16, 17

ማን ማንን ነው የሚንከባከበው?

ጉባኤው “መበለቶችን” እና “አባት የሌላቸውን ልጆች” ችላ አይልም

11, 12. ነጠላ ወላጆች የትኞቹን ገደቦች መጠበቅ አለባቸው? ይህን ማድረግ የሚችሉትስ እንዴት ነው?

11 ነጠላ ወላጆች ይበልጥ ከልጆቻቸው ጋር የቀረበ ግንኙነት እንዳላቸው ግልጽ ነው፤ ሆኖም አምላክ በወላጆችና በልጆች መካከል ያስቀመጣቸው ገደቦች እንዳይጣሱ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያህል ነጠላ ወላጅ የሆነች እናት ወንድ ልጅዋ የቤቱን ራስ ኃላፊነቶች እንዲወስድ የምትጠብቅበት ከሆነ ወይም ደግሞ የግል ችግሮቿን ለሴት ልጅዋ በማማከር የምስጢር ጓደኛዋ ልታደርጋት የምትሞክር ከሆነ ከባድ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ። እንዲህ ማድረጉ ተገቢ ያልሆነና ጭንቀት የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ ልጁን ወይም ልጅቷን ግራ ሊያጋባቸው ይችላል።

12 ወላጆች እንደ መሆናችሁ መጠን ልጆቻችሁ እናንተን ሳይሆን፣ እናንተ ልጆቻችሁን እንደምትንከባከቧቸው እንዲገነዘቡ አድርጓቸው። (ከ⁠2 ቆሮንቶስ 12:​14 ጋር አወዳድሩ።) አንዳንድ ጊዜ ምክር ወይም እርዳታ ሊያስፈልጋችሁ ይችላል። ሆኖም ምክር ወይም እርዳታ ማግኘት ያለባችሁ ከክርስቲያን ሽማግሌዎች ወይም ደግሞ ከጎለመሱ ክርስቲያን ሴቶች እንጂ ለአካለ መጠን ካልደረሱት ልጆቻችሁ አይደለም።​—⁠ቲቶ 2:​3

ተግሣጽ መስጠት

13. ነጠላ ወላጅ የሆነች አንዲት እናት ተግሣጽ በመስጠት ረገድ ምን ችግር ሊያጋጥማት ይችላል?

13 ብዙውን ጊዜ ልጆች አባት የሚሰጣቸውን ተግሣጽ አክብደው ይመለከቱታል፤ እናት የምትሰጠውን ተግሣጽ ግን አክብደው ላይመለከቱት ይችላሉ። ነጠላ ወላጅ የሆነች አንዲት እናት እንዲህ ብላለች:- “ወንዶች ልጆቼ ቁመናቸውና ድምፃቸው የትልቅ ሰው ነው። አንዳንድ ጊዜ ከእነሱ ሁኔታ አንፃር ሲታይ የምትናገሩት ነገር ኃይል ላይኖረው ይችላል።” ከዚህም በተጨማሪ የትዳር ጓደኛችሁ በሞት በመለየቱ ከደረሰባችሁ መሪር ሐዘን ገና አላገገማችሁ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ በትዳራችሁ መፍረስ የተነሳ የጥፋተኝነት ወይም የብስጭት ስሜት ይሰማችሁ ይሆናል። ልጆቹን የማሳደግ ሕጋዊ መብት ለሁለታችሁም ከተሰጠ ልጃችሁ ከቀድሞ የትዳር ጓደኛችሁ ጋር ለመሆን ይመርጥ ይሆናል የሚል ፍርሃት ሊያድርባችሁ ይችላል። እንዲህ ዓይነቶቹ ሁኔታዎች ሚዛናዊ ተግሣጽ እንዳትሰጡ እንቅፋት ሊፈጥሩባችሁ ይችላሉ።

14. ነጠላ ወላጆች ተግሣጽን በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ የሚችሉት እንዴት ነው?

14 መጽሐፍ ቅዱስ “ያልተቀጣ ብላቴና ግን እናቱን ያሳፍራል” ሲል ይናገራል። (ምሳሌ 29:​15) የቤተሰብ መመሪያዎችን በማውጣትና በማስፈጸም ረገድ የይሖዋ አምላክ ድጋፍ ያላችሁ በመሆኑ የጥፋተኝነት ስሜት፣ ጸጸት ወይም ደግሞ ፍርሃት ሊሰማችሁ አይገባም። (ምሳሌ 1:​8) ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ያላችሁን አቋም አታላሉ። (ምሳሌ 13:​24) ምክንያታዊና በአቋማችሁ የምትጸኑ ሁኑ። ውሎ አድሮ አብዛኞቹ ልጆች አዎንታዊ ምላሽ መስጠታቸው አይቀርም። ያም ሆኖ ግን የልጆቻችሁን ስሜት ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባችኋል። ነጠላ ወላጅ የሆነ አንድ አባት እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ልጆቼ እናታቸውን በማጣታቸው ስሜታቸው በጣም ተጎድቷል፤ ስለዚህ ተግሣጽ ስሰጣቸው ችግራቸውን ግምት ውስጥ አስገባለሁ። ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ከልጆቼ ጋር የሐሳብ ልውውጥ አደርጋለሁ። እራት በምንሠራበት ጊዜ ምሥጢራዊ የሆነ ውይይት ለማድረግ አጋጣሚ እናገኛለን። የልባቸውን ሁሉ ግልጥልጥ አድርገው የሚያጫውቱኝ በዚህ ጊዜ ነው።”

15. አንድ የተፋታ ወላጅ ስለ ቀድሞ የትዳር ጓደኛው በሚናገርበት ጊዜ ምን ከማድረግ መቆጠብ ይኖርበታል?

15 ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ተፋትታችሁ ከሆነ እሱን ወይም እሷን በመተቸት የምታገኙት ምንም ጥቅም አይኖርም። የወላጆች መናቆር ልጆችን በጣም የሚያበሳጫቸው ከመሆኑም በላይ ውሎ አድሮ ለሁለታችሁም ያላቸው አክብሮት እንዲቀንስ ያደርጋል። ስለዚህ “አንተ ድሮም እንደ አባትህ ነህ!” እንደሚሉት ዓይነት ጎጂ የሆኑ ቃላት ከመሰንዘር መቆጠብ ይኖርባችኋል። የቀድሞ የትዳር ጓደኛችሁ ምንም ያህል ቢበድላችሁ አሁንም የልጃችሁ ወላጅ መሆኑን አትዘንጉ፤ ልጃችሁ ደግሞ የሁለታችሁም ፍቅር፣ ትኩረትና ተግሣጽ ያስፈልገዋል። *

16. በነጠላ ወላጅ የሚተዳደር ቤተሰብ ተግሣጽ ለመስጠት በየትኞቹ መንፈሳዊ ዝግጅቶች መጠቀም ይኖርበታል?

16 ቀደም ባሉት ምዕራፎች ውስጥ እንደተገለጸው ተግሣጽ ቅጣት ብቻ ሳይሆን ማሠልጠኛንና ትምህርትንም የሚጨምር ነው። ጥሩ የሆነ የመንፈሳዊ ማሠልጠኛ ፕሮግራም በመጠቀም ብዙ ችግሮችን ማስወገድ ይቻላል። (ፊልጵስዩስ 3:​16) በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘት በጣም አስፈላጊ ነው። (ዕብራውያን 10:​24, 25) ሳምንታዊ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረግም በጣም ወሳኝ ነው። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ዓይነቱን ፕሮግራም በቋሚነት ማካሄድ ቀላል ላይሆን ይችላል። “ሙሉ ቀን ስትሠሩ ከዋላችሁ በኋላ ማረፍ ትፈልጋላችሁ” ስትል አንዲት ታታሪ እናት ገልጻለች። “ሆኖም ማድረግ ያለብኝ ነገር እንደሆነ ስለማውቅ ከልጄ ጋር ለማጥናት መንፈሴን አዘጋጃለሁ። ልጄ የቤተሰብ ጥናታችን በጣም ያስደስታታል!”

17. የጳውሎስ ጓደኛ ከሆነው ከጢሞቴዎስ ግሩም አስተዳደግ ምን ልንማር እንችላለን?

17 የሐዋርያው ጳውሎስ ጓደኛ የሆነው ጢሞቴዎስ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ማሠልጠኛ የተሰጠው በእናቱና በአያቱ እንጂ በአባቱ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ሆኖም ጢሞቴዎስ እንዴት ያለ ግሩም ክርስቲያን እንደወጣው አስቡ! (ሥራ 16:​1, 2፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:​5፤ 3:​14, 15) እናንተም ልጆቻችሁን “በጌታ ምክርና በተግሣጽ” ለማሳደግ በምትጥሩበት ጊዜ ጥሩ ውጤት እናገኛለን ብላችሁ መጠበቅ ትችላላችሁ።​—⁠ኤፌሶን 6:​4

የብቸኝነትን ስሜት ማሸነፍ

18, 19. (ሀ) ነጠላ ወላጅ የብቸኝነት ስሜት ሊሰማው የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ሥጋዊ ፍላጎቶችን መቆጣጠር እንድንችል ለመርዳት ምን ምክር ተሰጥቷል?

18 ነጠላ ወላጅ የሆነች አንዲት እናት እንዲህ ስትል የሚሰማትን ሐዘን ገልጻለች:- “ከሥራ ከተመለስኩ በኋላ በተለይ ልጆቹ ሲተኙና ቤቱ ጭር ሲል የብቸኝነት ስሜት ይከበኛል።” አዎ፣ ነጠላ ወላጅ ብዙውን ጊዜ የሚያጋጥመው ትልቁ ችግር የብቸኝነት ስሜት ነው። ትዳር የሚፈጥረውን የሞቀ ወዳጅነትና የተቀራረበ ግንኙነት ለማግኘት መጓጓት ያለ ነገር ነው። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ይህን ችግር ለመፍታት ማንኛውንም ዓይነት መሥዋዕትነት ለመክፈል መነሳሳት ይኖርበታልን? በሐዋርያው ጳውሎስ ዘመን አንዳንድ ወጣት መበለቶች “ጾታዊ ፍላጎታቸው ለክርስቶስ ካላቸው ፍቅር እንዲያይል” ፈቅደዋል። (1 ጢሞቴዎስ 5:​11, 12 NW) ሥጋዊ ፍላጎት መንፈሳዊ ጉዳዮችን አቅልለን እንድንመለከት እንዲያደርገን የምንፈቅድ ከሆነ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትልብናል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 5:​6

19 አንድ ክርስቲያን እንዲህ ብሏል:- “የፍትወት ስሜት በጣም ከፍተኛ ኃይል አለው፤ ሆኖም ልትቆጣጠሩት ትችላላችሁ። እንዲህ ዓይነቱ ሐሳብ ወደ አእምሯችሁ ሲመጣ ልታስተናግዱት አይገባም። ወዲያውኑ ከአእምሯችሁ ማውጣት አለባችሁ። ስለ ልጃችሁ ማሰባችሁም ይህን ማድረግ እንድትችሉ ይረዳችኋል።” የአምላክ ቃል ‘በምድር ያሉትን ብልቶቻችሁን ማለትም የፍትወት ስሜታችሁን ግደሉ’ ሲል ምክር ይሰጣል። (ቆላስይስ 3:​5) የምግብ ፍላጎታችሁን ለመግደል በምትሞክሩበት ጊዜ የሚያጓጉ ምግቦችን የሚያሳዩ መጽሔቶችን ታነባላችሁ? ወይም ደግሞ ሁልጊዜ ስለ ምግብ ከሚያወሩ ሰዎች ጋር ትውላላችሁ? እንደዚያ እንደማታደርጉ የታወቀ ነው! የጾታ ፍላጎትንም በተመለከተ ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።

20. (ሀ) አማኝ ካልሆኑ ሰዎች ጋር መጠናናት የጀመሩ ምን አደጋ ያጠላባቸዋል? (ለ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩም ሆኑ በዛሬው ጊዜ ያሉ ነጠላ ሰዎች የብቸኝነት ስሜትን የተዋጉት እንዴት ነው?

20 አንዳንድ ክርስቲያኖች አማኝ ካልሆኑ ሰዎች ጋር መጠናናት ጀምረዋል። (1 ቆሮንቶስ 7:​39) ይህ ችግራቸውን ይፈታላቸዋልን? አይፈታላቸውም። አንዲት ከባልዋ የተፋታች ክርስቲያን “ከነጠላነት እጅግ የከፋ አንድ ነገር አለ። እርሱም ከማይሆን ሰው ጋር መጋባት ነው!” ስትል አስጠንቅቃለች። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያን መበለቶች በብቸኝነት ስሜት የተሠቃዩባቸው ጊዜያት እንደነበሩ ግልጽ ነው፤ ሆኖም ጥበበኞቹ መበለቶች ጊዜያቸው ‘እንግዶችን በመቀበል፣ የቅዱሳንን እግር በማጠብና የተጨነቁትን በመርዳት’ እንዲያዝ አድርገዋል። (1 ጢሞቴዎስ 5:​10) በዛሬው ጊዜም ፈሪሃ አምላክ ያለው የትዳር ጓደኛ ለማግኘት ለብዙ ዓመታት የቆዩ ታማኝ ክርስቲያኖች ጊዜያቸው እነዚህን በመሳሰሉ ነገሮች እንዲያዝ አድርገዋል። አንዲት የ68 ዓመት ክርስቲያን መበለት የብቸኝነት ስሜት ሲሰማት ሌሎች መበለቶችን እየሄደች ትጠይቃለች። “ሌሎች መበለቶችን መጠየቄ፣ የቤት ውስጥ ሥራዬን ዘወትር አሟልቼ መሥራቴና መንፈሳዊነቴን መጠበቄ ለብቸኝነት ስሜት የሚያጋልጥ ጊዜ እንዳይኖረኝ ረድቶኛል” ብላለች። ሌሎችን ስለ አምላክ መንግሥት ማስተማር ይበልጥ ጠቃሚ የሆነ መልካም ሥራ ነው።​—⁠ማቴዎስ 28:​19, 20

21. ጸሎትና ጥሩ ወዳጅነት መመሥረት የብቸኝነት ስሜትን ለመቋቋም ሊረዱ የሚችሉት በምን መንገድ ነው?

21 የብቸኝነት ስሜት ተአምራዊ የሆነ ፈውስ እንደሌለው እሙን ነው። ሆኖም ይህን ችግር ከይሖዋ በሚገኝ ኃይል መቋቋም ይቻላል። አንድ ክርስቲያን “ሌትና ቀንም በልመና በጸሎትም” በመጽናት ይህን ኃይል ማግኘት ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 5:​5) ልመና ከልብ መማፀንን ያመለክታል፤ እርዳታ ለማግኘት በብርቱ ጩኸትና በእንባ መለመን ማለትም ሊሆን ይችላል። (ከ⁠ዕብራውያን 5:​7 ጋር አወዳድሩ።) ልባችሁን ለይሖዋ “ሌትና ቀን” ማፍሰሳችሁ በእርግጥም ሊረዳችሁ ይችላል። በተጨማሪም ጤናማ የሆነ ወዳጅነት መመሥረት የብቸኝነት ስሜት የሚፈጥረውን ክፍተት ለመድፈን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል። አንድ ሰው ጥሩ ወዳጅነት በመመሥረት በምሳሌ 12:​25 ላይ የተገለጸውን የማበረታቻ “መልካም ቃል” ማግኘት ይችላል።

22. አልፎ አልፎ የብቸኝነት ስሜት በሚሰማን ጊዜ የትኞቹን ነገሮች ግምት ውስጥ ማስገባቱ ሊረዳን ይችላል?

22 አልፎ አልፎ የብቸኝነት ስሜት የሚሰማችሁ ከሆነ፣ ደግሞም ሊሰማችሁ እንደሚችል የታወቀ ነው፣ ከችግር ነፃ የሆነ ሕይወት የሚመራ ሰው እንደሌለ አስታውሱ። እንዲያውም “በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ” በሙሉ በዚህም ሆነ በዚያ መከራ ይደርስባቸዋል። (1 ጴጥሮስ 5:​9) ስላለፈው ነገር ብዙ ማሰብ የለባችሁም። (መክብብ 7:​10) ያሏችሁን ከሌሎች የተሻሉ ነገሮች ለማሰብ ሞክሩ። ከሁሉም በላይ ደግሞ በአቋማችሁ በመጽናት የይሖዋን ልብ ለማስደሰት ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ።​—⁠ምሳሌ 27:​11

ሌሎች እርዳታ ማድረግ የሚችሉበት መንገድ

23. መሰል ክርስቲያኖች በጉባኤ ውስጥ ላሉ ነጠላ ወላጆች ምን የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው?

23 መሰል ክርስቲያኖች የሚሰጡት ድጋፍና እርዳታ ከፍተኛ ጥቅም አለው። ያዕቆብ 1:​27 “ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ” ይላል። አዎ፣ ክርስቲያኖች በነጠላ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦችን የመርዳት ግዴታ አለባቸው። ይህን ማድረግ የሚቻልባቸው አንዳንድ ተግባራዊ መንገዶች ምንድን ናቸው?

24. ችግር ያለባቸውን በነጠላ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች በየትኞቹ መንገዶች መርዳት ይቻላል?

24 ቁሳዊ እርዳታ መስጠት ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “የዚህ ዓለም ገንዘብ ያለው፣ ወንድሙም የሚያስፈልገውን ሲያጣ አይቶ ያልራራለት ማንም ቢሆን፣ የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ እንዴት ይኖራል?” (1 ዮሐንስ 3:​17) “ማየት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል እንዲሁ እንደ ነገሩ መመልከት ማለት ብቻ ሳይሆን ሆን ብሎ በትኩረት መመልከት ማለት ነው። ይህም አንድ ደግ ክርስቲያን በመጀመሪያ አንድ ቤተሰብ ያለበትን ሁኔታና የሚያስፈልጉትን ነገሮች ማወቅ እንደሚችል ያመለክታል። ምናልባት የገንዘብ ችግር ይኖርባቸው ይሆናል። አንዳንድ ቤተሰቦች ደግሞ ቤታቸው ውስጥ ጥገና የሚያስፈልጋቸው ነገሮች ይኖሯቸው ይሆናል። አለዚያም ደግሞ እራት ቢጋበዙ ወይም ለመጫወት ሲባል በሚደረግ ዝግጅት ላይ ቢጠሩ ሊያስደስታቸው ይችላል።

25. መሰል ክርስቲያኖች ለነጠላ ወላጆች ርኅራኄ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

25 በተጨማሪም 1 ጴጥሮስ 3:​8 “ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ፣ የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ፣ እንደ ወንድሞች ተዋደዱ፣ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ” ይላል። ነጠላ ወላጅ የሆነች አንዲት የስድስት ልጆች እናት እንዲህ ብላለች:- “ሁኔታውን መቋቋም ከብዶኝ ነበር፤ አንዳንድ ጊዜ በጭንቀት እዋጣለሁ። ይሁን እንጂ አልፎ አልፎ ወንድሞችና እህቶች ‘ጆአን፣ በጣም የሚደነቅ ሥራ ነው እየሠራሽ ያለሽው። ወደፊት እንደምትካሺ አትጠራጠሪ’ ይሉኛል። ሌሎች እንደሚያስቡላችሁና እንደሚጨነቁላችሁ ማወቁ ብቻ እንኳ በጣም ያጽናናል።” ነጠላ ወላጅ የሆኑ ወጣት ሴቶች ወንዶችን ለማማከር የሚያሳፍር ዓይነት ችግር በሚገጥማቸው ጊዜ በዕድሜ የገፉ ክርስቲያን ሴቶች ጆሯቸውን በመስጠት ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ሊረዷቸው ይችላሉ።

26. የጎለመሱ ክርስቲያን ወንዶች አባት የሌላቸውን ልጆች ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት ነው?

26 ክርስቲያን ወንዶች በሌሎች መንገዶች ሊረዱ ይችላሉ። ጻድቅ ሰው የነበረው ኢዮብ “ድሀ አደጉንና ረጂ የሌለውን አድኜ ነበርሁ” ሲል ተናግሯል። (ኢዮብ 29:​12) በዛሬው ጊዜም አንዳንድ ክርስቲያን ወንዶች ምንም ዓይነት ስውር ዓላማ ሳይኖራቸው አባት ለሌላቸው ልጆች ጤናማ የሆነ አሳቢነትና “ከንጹሕ ልብ . . . የሚወጣ ፍቅር” ያሳያሉ። (1 ጢሞቴዎስ 1:​5) የራሳቸውን ቤተሰብ ችላ ሳይሉ ከእንዲህ ዓይነቶቹ ልጆች ጋር በክርስቲያናዊ አገልግሎት ለመሳተፍ ፕሮግራም ሊያወጡና በቤተሰብ ጥናታቸው ወይም ደግሞ በአንድ የመዝናኛ ዝግጅት ላይ እንዲገኙ ሊጋብዟቸው ይችላሉ። እንዲህ ዓይነቱ ደግነት አባት የሌለውን ልጅ ከመጥፎ ጎዳና ሊታደገው ይችላል።

27. ነጠላ ወላጆች ምን ዓይነት እርዳታ እንደሚያገኙ እርግጠኞች መሆን ይችላሉ?

27 በመሠረቱ፣ ነጠላ ወላጆች ‘የራሳቸውን የኃላፊነት ሸክም መሸከም’ አለባቸው። (ገላትያ 6:​5) ሆኖም የክርስቲያን ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን እንዲሁም የራሱን የይሖዋ አምላክን ፍቅር ማግኘት ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ሲናገር “ድሀ አደጎችንና ባልቴቶችን ይቀበላል” ይላል። (መዝሙር 146:​9) በነጠላ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች በይሖዋ ፍቅራዊ እርዳታ በመታገዝ የተሳካ ሕይወት መምራት ይችላሉ!

^ አን.9 አንዲት ወጣት ክርስቲያን የጾታ ብልግና ፈጽማ ብትጸንስ ክርስቲያን ጉባኤው የፈጸመችውን ድርጊት በቸልታ አያልፈውም። ይሁን እንጂ ንስሐ ከገባች የጉባኤው ሽማግሌዎችና ሌሎች የጉባኤው አባላት ሊረዷት ይችላሉ።

^ አን.15 ልጁን ስለሚበድል ወላጅ መናገራችን አይደለም፤ ልጃችሁን ከእንዲህ ዓይነት ወላጅ መጠበቅ ሊያስፈልጋችሁ ይችላል። በተጨማሪም የቀድሞ የትዳር ጓደኛችሁ ልጆቻችሁ እናንተን ጥለው ከእሱ ጋር እንዲኖሩ ለማሳመን በመጣር ሥልጣናችሁን ለማዳከም የሚሞክር ከሆነ ከክርስቲያን ጉባኤ ሽማግሌዎችና እነሱን ከመሰሉ ተሞክሮ ካላቸው ወዳጆቻችሁ ጋር በመነጋገር ይህን ችግር እንዴት መቋቋም እንደምትችሉ ብትማከሩ ጥሩ ሊሆን ይችላል።