በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የክርስቶስ መምጣት ሲባል ምን ማለት ነው?

የክርስቶስ መምጣት ሲባል ምን ማለት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ክርስቶስ በምድር ሕዝቦች ላይ ለመፍረድ ወደፊት ስለሚመጣበት ጊዜ በብዙ ቦታዎች ላይ ይናገራል። a ለምሳሌ ያህል ማቴዎስ 25:31-33 እንዲህ ይላል፦

 “የሰው ልጅ [ኢየሱስ ክርስቶስ] ከመላእክቱ ሁሉ ጋር በክብሩ ሲመጣ በክብራማ ዙፋኑ ላይ ይቀመጣል። ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛ በጎቹን ከፍየሎቹ እንደሚለይ ሁሉ እሱም ሰዎችን አንዱን ከሌላው ይለያል። በጎቹን በቀኙ፣ ፍየሎቹን ግን በግራው ያደርጋቸዋል።”

 ይህ የፍርድ ቀን ‘የታላቁ መከራ’ አካል ሲሆን ይህ ወቅት በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ እጅግ የተለየ ቀን ነው። ይህ ታላቅ መከራ በአርማጌዶን ጦርነት ይደመደማል። (ማቴዎስ 24:21፤ ራእይ 16:16) በምሳሌው ላይ በፍየል የተመሰሉት የክርስቶስ ጠላቶች ‘ዘላለማዊ ጥፋት ተፈርዶባቸው ይወገዳሉ።’ (2 ተሰሎንቄ 1:9፤ ራእይ 19:11, 15) በተቃራኒው ግን በበግ የተመሰሉት ታማኝ አገልጋዮቹ ‘የዘላለም ሕይወት’ ተስፋ ይኖራቸዋል።—ማቴዎስ 25:46

ክርስቶስ የሚመጣው መቼ ነው?

 ኢየሱስ “ስለዚያ ቀንና ሰዓት . . . ማንም አያውቅም” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:36, 42፤ 25:13) ይሁን እንጂ እሱ ሊመጣ ሲል ስለሚከሰተው የተለያዩ ገጽታዎች ያሉት የሚታይ “ምልክት” ገልጿል።—ማቴዎስ 24:3, 7-14፤ ሉቃስ 21:10, 11

ክርስቶስ የሚመጣው መንፈሳዊ አካል ይዞ ነው ወይስ ሥጋዊ አካል?

 ኢየሱስ ከሞት የተነሳው መንፈሳዊ አካል ይዞ ስለሆነ የሚመጣውም መንፈሳዊ አካል ሆኖ እንጂ ሥጋዊ አካል ይዞ አይደለም። (1 ቆሮንቶስ 15:45፤ 1 ጴጥሮስ 3:18) በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ከመሞቱ ከአንድ ቀን በፊት ለደቀ መዛሙርቱ “ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዓለም ከቶ አያየኝም” ብሏቸዋል።—ዮሐንስ 14:19

ሰዎች ስለ ክርስቶስ መምጣት ያሏቸው የተሳሳቱ አመለካከቶች፦

 የተሳሳተ አመለካከት፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ኢየሱስ ‘በደመና ሲመጣ’ ሰዎች ያዩታል የሚለው አገላለጽ ኢየሱስ በሚታይ ሁኔታ እንደሚመጣ ይጠቁማል።—ማቴዎስ 24:30

 እውነታው፦ ብዙውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ደመናን የሚጠቀመው ከእይታ የተሰወረ ነገርን ለማመልከት ነው። (ዘሌዋውያን 16:2፤ ዘኁልቁ 11:25፤ ዘዳግም 33:26) ለምሳሌ ያህል አምላክ “በጥቁር ደመና ወደ አንተ እመጣለሁ” ብሎ ለሙሴ ነግሮት ነበር። (ዘፀአት 19:9) ሙሴ አምላክን ቃል በቃል አላየውም። በተመሳሳይም ክርስቶስ ‘በደመና ሲመጣ’ ሰዎች ቃል በቃል ባያዩትም መምጣቱን ግን ይገነዘባሉ።

 የተሳሳተ አመለካከት፦ ስለ ክርስቶስ መምጣት የሚናገረው በራእይ 1:7 ላይ የሚገኘው “ዓይኖች ሁሉ . . . ያዩታል” የሚለው አገላለጽ ቃል በቃል ሊወሰድ ይገባዋል።

 እውነታው፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ዓይን’ እና ‘ማየት’ ተብለው የተተረጎሙት የግሪክኛ ቃላት አንዳንድ ጊዜ ቃል በቃል ማየትን ሳይሆን ማስተዋልን ወይም መገንዘብን ለማመልከት ይሠራባቸዋል። b (ማቴዎስ 13:15፤ ሉቃስ 19:42፤ ሮም 15:21፤ ኤፌሶን 1:18) መጽሐፍ ቅዱስ ከሞት ስለ ተነሳው ኢየሱስ ሲናገር “ሊቀረብ በማይችል ብርሃን ውስጥ ይኖራል፤ . . . ሊያየው የሚችል አንድም ሰው የለም” ይላል። (1 ጢሞቴዎስ 6:16) በመሆኑም የአምላክን ፍርድ የሚያስፈጽመው ኢየሱስ እንደሆነ ሰዎች ሁሉ ስለሚገነዘቡ “ዓይኖች ሁሉ . . . ያዩታል” ሊባል ይችላል።—ማቴዎስ 24:30

 የተሳሳተ አመለካከት፦ በ2 ዮሐንስ 7 ላይ የሚገኘው ጥቅስ ኢየሱስ የሚመጣው በሥጋ እንደሆነ ይናገራል።

 እውነታው፦ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ መምጣቱን አምነው የማይቀበሉ ብዙ አሳቾች ወደ ዓለም ወጥተዋል።”

 በሐዋርያው ዮሐንስ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው በሥጋ እንደሆነ አይቀበሉም ነበር። እነዚህ ሰዎች ግኖስቲኮች ተብለው ይጠሩ ነበር። ሁለተኛ ዮሐንስ 7 የተጻፈው የእነዚህ ሰዎች ትምህርት ውሸት መሆኑን ለማሳየት ነበር።

a ብዙ ሰዎች የክርስቶስን መምጣት ለማመልከት “ዳግም ምጽዓት” የሚለውን ሐረግ ቢጠቀሙም ይህ ሐረግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም።

b ዘ ኒው ቴየርስ ግሪክ-ኢንግሊሽ ሌክሲከን ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት (1981) ገጽ 451ን እና 470ን ተመልከት።