መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አምላክ ቃል በቃል ልጆች የምትወልድለት ሚስት የለውም። ይሁን እንጂ፣ እሱ ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ ፈጣሪ ነው። (ራእይ 4:11) በመሆኑም አምላክ የፈጠረው የመጀመሪያው ሰው ማለትም አዳም “የአምላክ ልጅ” ተብሎ ተጠርቷል። (ሉቃስ 3:38) በተመሳሳይም ኢየሱስ የተፈጠረው በአምላክ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። በመሆኑም ኢየሱስም “የአምላክ ልጅ” ተብሏል።—ዮሐንስ 1:49

አምላክ ኢየሱስን የፈጠረው አዳምን ከመፍጠሩ በፊት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስን አስመልክቶ “እሱ የማይታየው አምላክ አምሳልና የፍጥረት ሁሉ በኩር ነው” በማለት ጽፏል። (ቆላስይስ 1:15) ኢየሱስ ሕልውና ያገኘው በቤተልሔም በግርግም ውስጥ ከመወለዱ ከረጅም ጊዜ በፊት ነው። እንዲያውም ኢየሱስ “አመጣጡ ከጥንት፣ ከቀድሞ ዘመን” እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ሚክያስ 5:2) ኢየሱስ የአምላክ የበኩር ልጅ እንደመሆኑ መጠን ሰው ሆኖ በምድር ላይ ከመወለዱ በፊት በሰማይ መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ ይኖር ነበር። ኢየሱስ ራሱ ‘ከሰማይ እንደመጣ’ ተናግሯል።—ዮሐንስ 6:38፤ 8:23