በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለእስራኤላውያን የተሰጠው ሕግ ፍትሐዊ ነበር?

ለእስራኤላውያን የተሰጠው ሕግ ፍትሐዊ ነበር?

ከተወሰኑ ዓመታት በፊት በአንድ ምዕራባዊ አገር ያሉ ፍርድ ቤቶች፣ በነፍስ ግድያ በተከሰሱ ሁለት ሰዎች ላይ የቀረበውን የተሳሳተ ማስረጃ ተቀብለው በሰዎቹ ላይ ሞት ፈረዱ። የቀረበው ማስረጃ ስህተት መሆኑ ሲታወቅ፣ ጠበቆች ከፍተኛ ጥረት በማድረግ አንደኛውን ተከሳሽ ነፃ አወጡት። ይሁን እንጂ አንቱ የተባሉት ጠበቆች እንኳ ሌላኛውን ተከሳሽ ለመርዳት ምንም ማድረግ አልቻሉም፤ ምክንያቱም ማስረጃው ስህተት እንደሆነ ከመታወቁ በፊት ግለሰቡ የሞት ፍርዱ ተፈጽሞበት ነበር።

በማንኛውም የሕግ ሥርዓት ውስጥ እንዲህ ዓይነት የፍትሕ መዛባት ሊያጋጥም ይችላል፤ በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “ቅን ፍርድን ብቻ ተከተል” በማለት አጥብቆ ይመክራል። (ዘዳግም 16:20) ዳኞች እንዲህ ያለውን መመሪያ የሚከተሉ ከሆነ ዜጎች ይጠቀማሉ። ለጥንቶቹ እስራኤላውያን የተሰጠው የአምላክ ሕግ አድልዎ የሌለበትና ፍትሐዊ ፍርድ ለማግኘት የሚያስችል የፍትሕ ሥርዓት እንዲኖር አድርጎ ነበር። ‘የአምላክ መንገድ ሁሉ ትክክል’ ወይም ፍትሐዊ እንደሆነ ለመመልከት እስቲ አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠውን ሕግ እንመርምር።—ዘዳግም 32:4

‘ጥበበኛ፣ አስተዋይና የተከበሩ’ ዳኞች

ዳኞች ብቃት ያላቸው፣ የማያዳሉና ከሙስና የጸዱ ሲሆኑ ሕዝቡ ፍትሐዊ ፍርድ ያገኛል። አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ፣ ዳኞች የላቁ መሥፈርቶች እንዲያሟሉ ይጠይቅ ነበር። እስራኤላውያን በምድረ በዳ እየተጓዙ ሳሉ ሙሴ “ችሎታ ያላቸው . . . እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ ታማኞችና በማታለል የሚገኘውን ጥቅም የሚጸየፉ” ሰዎችን መርጦ ዳኞች አድርጎ እንዲሾማቸው ተነግሮት ነበር። (ዘፀአት 18:21, 22) ከአርባ ዓመታት በኋላም ሙሴ ‘ጥበበኛ፣ አስተዋይና የተከበሩ’ ዳኞችን መምረጥ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጿል።—ዘዳግም 1:13-17

ይህ ከሆነ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ * ዳኞችን እንዲህ ሲል አዟቸው ነበር፦ “እናንተ የምትፈርዱት ለሰው ሳይሆን፣ ፍርድ በምትሰጡበት ጊዜ ሁሉ ከእናንተ ጋር ለሆነው ለእግዚአብሔር ስለሆነ፣ በምትሰጡት ውሳኔ ሁሉ ብርቱ ጥንቃቄ አድርጉ፤ አሁንም እግዚአብሔርን መፍራት በእናንተ ላይ ይሁን፤ በአምላካችን በእግዚአብሔር ዘንድ ፍርድ ማጣመም፣ አድልዎ ማድረግና መማለጃ መቀበል ስለሌለ ተጠንቅቃችሁ ፍረዱ።” (2 ዜና መዋዕል 19:6, 7) ንጉሡ ይህንን የተናገረው ዳኞቹ አድልዎ ወይም ስግብግብነት በውሳኔያቸው ላይ ተጽዕኖ እንዲያደርግ የሚፈቅዱ ከሆነ በዚህ ምክንያት ለሚደርሰው ጉዳት አምላክ ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው ለማሳሰብ ነበር።

የእስራኤል ዳኞች እነዚህን ላቅ ያሉ መሥፈርቶች ሲጠብቁ ብሔሩ ጥበቃና ደኅንነት ያገኝ ነበር። ይሁን እንጂ የአምላክ ሕግ፣ ዳኞቹ በጣም አስቸጋሪ የሆኑ የፍርድ ጉዳዮች በሚያጋጥሟቸው ጊዜም እንኳ ፍትሐዊ ፍርድ እንዲያስተላልፉ የሚረዱ መመሪያዎችንም ይዟል። ከእነዚህ መመሪያዎች አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?

ትክክለኛ ፍርድ ለመስጠት የሚረዱ መመሪያዎች

የሚመረጡት ዳኞች ጥበበኞችና ችሎታ ያላቸው ቢሆኑም እንኳ በራሳቸው ችሎታ ወይም ጥበብ ላይ ተመርኩዘው እንዲፈርዱ አልተፈቀደላቸውም። ይሖዋ አምላክ ትክክለኛ ውሳኔ ላይ መድረስ የሚያስችሏቸውን መመሪያዎች ሰጥቷቸው ነበር። ለእስራኤላውያን ዳኞች ከተሰጡት መመሪያዎች መካከል አንዳንዶቹን እስቲ እንመልከት።

ጉዳዩን በጥንቃቄ መመርመር። አምላክ ‘በወንድሞቻችሁ መካከል ክርክር ሲነሳ በትክክል ፍረዱ’ የሚል ትእዛዝ በሙሴ በኩል ለእስራኤላውያን ዳኞች ሰጥቶ ነበር። (ዘዳግም  1:16) ዳኞች በትክክል መፍረድ የሚችሉት ከክሱ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ማስረጃዎች በሙሉ በጥንቃቄ ከመረመሩ ብቻ ነው። በዚህም ምክንያት አምላክ የፍርድ ጉዳዮችን ለሚመለከቱ ሰዎች “ጕዳዩን አጣራ፤ መርምር፤ በሚገባም ተከታተል” የሚል መመሪያ ሰጥቷቸዋል። ዳኞች የፍርድ ሂደቱን ከመጀመራቸው በፊት የቀረበው ክስ “እውነት” መሆኑን ‘ማረጋገጥ’ ነበረባቸው።—ዘዳግም 13:14፤ 17:4

የምሥክሮችን ቃል መስማት። ጉዳዩ በሚመረመርበት ወቅት ምሥክሮች የሚሰጡት ቃል በጣም አስፈላጊ ነው። የአምላክ ሕግ እንዲህ ይላል፦ “በማንኛውም ወንጀል ወይም ሕግ በመተላለፍ ሰውን ጥፋተኛ ለማድረግ፣ አንድ ምስክር አይበቃም፤ ጕዳዩ በሁለት ወይም በሦስት ሰዎች ምስክርነት መረጋገጥ አለበት።” (ዘዳግም 19:15) የአምላክ ሕግ ለምሥክሮችም “የሐሰት ወሬ አትንዛ፤ ተንኰል ያለበትን ምስክርነት በመስጠት ክፉውን ሰው አታግዝ” የሚል ትእዛዝ ይሰጣል።—ዘፀአት 23:1

በፍርድ ሂደቱ ላይ ሐቀኝነት እንዲኖር ማድረግ። ችሎት ፊት ቀርቦ በሚዋሽ ሰው ላይ የሚወሰደው እርምጃ፣ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ሁሉ ‘እኔን ያየ ይቀጣ’ የሚያስብል ነበር፤ ሕጉ እንዲህ ይላል፦ “ፈራጆችም ጕዳዩን በጥልቅ ይመርምሩት፤ ያም ምስክሩ በወንድሙ ላይ በሐሰት የመሰከረ መሆኑ ከተረጋገጠ፣ በወንድሙ ላይ ለማድረግ ያሰበውን በእርሱ ላይ አድርጉበት፤ ክፉውን ከመካከልህ አስወግድ።” (ዘዳግም 19:18, 19) በመሆኑም አንድ ሰው የሌላውን ሰው ንብረት ለመውሰድ ብሎ በችሎቱ ፊት ከዋሸ እኩል መጠን ያለው ንብረት ከራሱ ይወሰድበታል። ወይም አንድ ሰው የሞት ፍርድ እንዲፈረድበት ለማድረግ ሲል በሐሰት የሚመሠክር ከሆነ የራሱን ሕይወት ያጣል። ይህ መመሪያ፣ በፍርድ ሂደቱ ላይ ያሉት ሁሉ እውነትን እንዲናገሩ የሚያነሳሳ ነበር።

ያለ አድልዎ መፍረድ። ዳኞቹ አስፈላጊውን ማስረጃ በሙሉ ከተመለከቱ በኋላ ብይን ለመስጠት ይመካከራሉ። “ለድኻው አታድላለት፤ ለትልቁም ሰው ልዩ አክብሮት አትስጥ፤ ለብርቱው አታዳላ፤ ነገር ግን ለባ[ል]ንጀራህ በትክክል ፍረድ” የሚለውን በአምላክ ሕግ ውስጥ የሚገኝ ላቅ ያለ መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ያለባቸው በዚህ ወቅት ነው። (ዘሌዋውያን  19:15) ዳኞች የባለጉዳዮቹን ውጫዊ ገጽታ ወይም በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ቦታ በመመልከት ሳይሆን ምንጊዜም ተገቢውን ፍርድ መስጠት ነበረባቸው።

ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ለእስራኤላውያን በተሰጠው የአምላክ ሕግ ውስጥ በግልጽ የተቀመጡት እነዚህ መመሪያዎች በዛሬው ጊዜም ፍርድ ለመስጠት የሚረዱ ጠቃሚ መመሪያ ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ። እነዚህ መመሪያዎች ሥራ ላይ መዋላቸው የፍትሕ መዛባት እንዳይኖር ያደርጋል።

በአምላክ ሕግ ውስጥ ያሉት መመሪያዎች ሥራ ላይ መዋላቸው የፍትሕ መዛባት እንዳይኖር ያደርጋል

እውነተኛ ፍትሕ ያገኘ ሕዝብ

ሙሴ ለእስራኤላውያን እንዲህ የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር፦ “ዛሬ እኔ በፊታችሁ እንዳስቀመጥሁት ሕግ ያለ፣ ጽድቅ የሆነ ሥርዐትና ሕግ ያሉት ሌላ ታላቅ ሕዝብስ ማነው?” (ዘዳግም 4:8) በእርግጥም እንዲህ ዓይነት አጋጣሚ የነበረው ሌላ ሕዝብ አልነበረም። በወጣትነቱ የይሖዋን ሕጎች በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት ባደረገው በንጉሥ ሰሎሞን የግዛት ዘመን ሕዝቡ “በሰላም ለመኖር” በቅቷል፤ በወቅቱ የነበሩት እስራኤላውያን በብልጽግናና ያለ ስጋት ይኖሩ የነበረ ከመሆኑም ሌላ “ይበሉ፣ ይጠጡና ይደሰቱም ነበር።”—1 ነገሥት 4:20, 25

የሚያሳዝነው ግን እስራኤላውያን የኋላ ኋላ በአምላክ ላይ ዓመፁ። አምላክ በነቢዩ ኤርምያስ በኩል “የእግዚአብሔርን ቃል ተቃውመው፣ ምን ዐይነት ጥበብ ይኖራቸዋል?” ብሎ ነበር። (ኤርምያስ 8:9) በዚህም ምክንያት ኢየሩሳሌም ‘ጸያፍ ተግባር የሞላባት ደም የምታፈስስ ከተማ’ ሆና ነበር። በመጨረሻም ለጥፋት የተዳረገች ሲሆን ለ70 ዓመታት ሰው የማይኖርባት ባድማ ሆነች።—ሕዝቅኤል 22:2፤ ኤርምያስ 25:11

ነቢዩ ኢሳይያስ የኖረው በእስራኤል ታሪክ ውስጥ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ወቅት ላይ ነበር። ኢሳይያስ፣ የቀድሞውን ዘመን መለስ ብሎ በማሰብ ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ሕጉ የሚከተለውን እውነት ለመናገር ተገፋፍቷል፦ “ፍርድህ ወደ ምድር በመጣ ጊዜ፣ የዓለም ሕዝቦች ጽድቅን ይማራሉ።”—ኢሳይያስ 26:9

ኢሳይያስ፣ መሲሐዊ ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሚገዛበት ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የሚከተለውን ትንቢት መጻፉ ሳያስደስተው አልቀረም፦ “[ኢየሱስ] ዐይኑ እንዳየ አይፈርድም፤ ጆሮውም እንደ ሰማ አይበይንም። ነገር ግን ለድኾች በጽድቅ ይፈርዳል፤ ለምድር ምስኪኖችም ፍትሕን ይበይናል።” (ኢሳይያስ 11:3, 4) በአምላክ መንግሥት ሥር የመሲሐዊው ንጉሥ ተገዢዎች የሚሆኑት ሁሉ እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ይጠብቃቸዋል!—ማቴዎስ 6:10

^ አን.6 ኢዮሣፍጥ የሚለው ስም “ይሖዋ ፈራጅ ነው” የሚል ትርጉም አለው።