ሕዝቅኤል 22:1-31

  • ኢየሩሳሌም፣ የደም ዕዳ ያለባት ከተማ (1-16)

  • እስራኤል ከላይ እንደሚሰፍ የማይረባ ቆሻሻ ናት (17-22)

  • የእስራኤል ሕዝብና መሪዎች ተወገዙ (23-31)

22  የይሖዋም ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦  “የሰው ልጅ ሆይ፣ አንተስ የደም ዕዳ ባለባት ከተማ ላይ ፍርድ ለማወጅና+ አስጸያፊ ነገሮቿን ሁሉ+ ለማሳወቅ ተዘጋጅተሃል?  እንዲህ በል፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “በመካከልሽ ደም የምታፈሺ፣+ ፍርድ የምትቀበዪበት ጊዜ የደረሰብሽ፣+ ትረክሺም ዘንድ አስጸያፊ የሆኑ ጣዖቶች* የምትሠሪ ከተማ ሆይ፣+  ያፈሰስሽው ደም በደለኛ አድርጎሻል፤+ ደግሞም አስጸያፊ ጣዖቶችሽ አርክሰውሻል።+ የቀኖችሽን መጨረሻ አፋጥነሻል፤ የዘመኖችሽም መጨረሻ ደርሷል። ስለዚህ ብሔራት ነቀፋ እንዲሰነዝሩብሽ፣ አገሩም ሁሉ እንዲሳለቅብሽ አደርጋለሁ።+  አንቺ ስምሽ ርኩስ የሆነና ሽብር የሞላብሽ ከተማ ሆይ፣ በቅርብም ሆነ በሩቅ ያሉት አገሮች ይሳለቁብሻል።+  እነሆ፣ በመካከልሽ ያለ እያንዳንዱ የእስራኤል አለቃ ሥልጣኑን ደም ለማፍሰስ ይጠቀምበታል።+  በአንቺ ውስጥ ያሉት ሰዎች አባቶቻቸውንና እናቶቻቸውን ያቃልላሉ።+ ከባዕድ አገር የመጣውን ሰው ያጭበረብራሉ፤ ደግሞም አባት የሌለውን ልጅና* መበለቲቱን ይበድላሉ።”’”+  “‘ቅዱስ ስፍራዎቼን ታቃልያለሽ፤ ሰንበቶቼንም ታረክሻለሽ።+  በአንቺ ውስጥ ደም የማፍሰስ ዓላማ ያላቸው ስም አጥፊዎች አሉ።+ በአንቺ ውስጥ በተራሮች ላይ መሥዋዕቶችን ይበላሉ፤ በመካከልሽም ጸያፍ ምግባር ይፈጽማሉ።+ 10  በአንቺ ውስጥ የአባታቸውን መኝታ ያረክሳሉ፤*+ ደግሞም በወር አበባዋ የረከሰችን ሴት አስገድደው ይደፍራሉ።+ 11  በአንቺ ውስጥ አንዱ ከባልንጀራው ሚስት ጋር አስጸያፊ ነገር ይሠራል፤+ ሌላው ጸያፍ ምግባር በመፈጸም የገዛ ምራቱን ያረክሳታል፤+ ሌላው ደግሞ የገዛ አባቱ ልጅ የሆነችውን እህቱን አስገድዶ ይደፍራል።+ 12  በአንቺ ውስጥ ያሉ ሰዎች ደም ለማፍሰስ ጉቦ ይቀበላሉ።+ ወለድና ትርፍ ለማግኘት* ታበድሪያለሽ፤+ የባልንጀሮችሽንም ገንዘብ ትቀሚያለሽ።+ አዎ፣ እኔን ጨርሶ ረስተሻል’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ። 13  “‘እነሆ፣ ያገኘሽውን አግባብ ያልሆነ ጥቅምና በመካከልሽ ያፈሰስሽውን ደም በመጸየፍ አጨበጭባለሁ። 14  በአንቺ ላይ እርምጃ በምወስድበት ጊዜ ልብሽ ሊጸና፣ እጆችሽስ ብርቱ ሆነው ሊቀጥሉ ይችላሉ?+ እኔ ይሖዋ ራሴ ተናግሬአለሁ፤ ደግሞም አደርገዋለሁ። 15  በብሔራት መካከል እበትንሻለሁ፤ በየአገሩም እዘራሻለሁ፤+ ርኩሰትሽንም አስወግዳለሁ።+ 16  አንቺም በብሔራት ፊት ትዋረጃለሽ፤ እኔም ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቂያለሽ።’”+ 17  የይሖዋም ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ 18  “የሰው ልጅ ሆይ፣ የእስራኤል ቤት ሰዎች ከላይ እንደሚሰፍ የማይረባ ቆሻሻ ሆነውብኛል። ሁሉም ምድጃ ውስጥ ያለ መዳብ፣ ቆርቆሮ፣ ብረትና እርሳስ ናቸው። ብር ሲቀልጥ ከላይ እንደሚሰፍ ቆሻሻ ሆነዋል።+ 19  “ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ሁላችሁም ከላይ እንደሚሰፍ የማይረባ ቆሻሻ+ ስለሆናችሁ በኢየሩሳሌም ውስጥ እሰበስባችኋለሁ። 20  እሳት በላያቸው ላይ እንዲነድባቸውና እንዲቀልጡ ብር፣ መዳብ፣ ብረት፣ እርሳስና ቆርቆሮ በምድጃ ውስጥ እንደሚሰበሰቡ ሁሉ እኔም እናንተን በንዴትና በታላቅ ቁጣ እሰበስባችኋለሁ፤ በእናንተም ላይ እሳት በማንደድ አቀልጣችኋለሁ።+ 21  አንድ ላይ እሰበስባችኋለሁ፤ በላያችሁም ላይ የቁጣዬን እሳት አነዳለሁ፤+ እናንተም በውስጧ ትቀልጣላችሁ።+ 22  ብር በምድጃ ውስጥ እንደሚቀልጥ ሁሉ እናንተም በውስጧ ትቀልጣላችሁ፤ በእናንተ ላይ ቁጣዬን ያፈሰስኩት እኔ ይሖዋ ራሴ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ።’” 23  የይሖዋም ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ 24  “የሰው ልጅ ሆይ፣ እንዲህ በላት፦ ‘አንቺ በቁጣ ቀን የማትጸጂ ወይም ዝናብ የማይዘንብብሽ ምድር ነሽ። 25  ነቢያቷ ያደነውን እንስሳ እንደሚቦጫጭቅ የሚያገሳ አንበሳ+ በውስጧ ሴራ ጠንስሰዋል።+ ሰዎችን* ይውጣሉ። ውድ ሀብትንና የከበሩ ነገሮችን ይነጥቃሉ። በውስጧ ያሉትን ብዙ ሴቶች መበለት አድርገዋል። 26  ካህናቷ ሕጌን ጥሰዋል፤+ ቅዱስ ስፍራዎቼንም ያረክሳሉ።+ ቅዱስ በሆነውና ተራ በሆነው ነገር መካከል ምንም ልዩነት አያደርጉም፤+ ደግሞም ንጹሕ ባልሆነውና ንጹሕ በሆነው ነገር መካከል ያለውን ልዩነት አያስታውቁም፤+ ሰንበቶቼንም ለማክበር አሻፈረኝ ይላሉ፤ እኔም በመካከላቸው ረከስኩ። 27  በመካከሏ ያሉት አለቆቿ ያደኑትን እንስሳ እንደሚቦጫጭቁ ተኩላዎች ናቸው፤ አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ደም ያፈሳሉ፤ የሰዎችንም ሕይወት* ያጠፋሉ።+ 28  ነቢያቷ ግን እነሱ የሚያደርጉትን ነገር በኖራ ይለስናሉ። የሐሰት ራእዮች ያያሉ፤ የውሸት ሟርትም ያሟርታሉ፤+ ደግሞም ይሖዋ ራሱ ምንም ሳይናገር “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል” ይላሉ። 29  የምድሪቱ ሰዎች የማጭበርበር ድርጊት ፈጽመዋል፤ ሌሎችን ዘርፈዋል፤+ ችግረኛውንና ድሃውን በድለዋል፤ ደግሞም ከባዕድ አገር የመጣውን ሰው አጭበርብረዋል፤ ፍትሕንም ነፍገውታል።’ 30  “‘ከመካከላቸው የድንጋይ ቅጥሩን የሚጠግን ወይም ምድሪቱ እንዳትጠፋ በፈረሰው ቦታ ላይ በፊቴ የሚቆምላት ሰው ይኖር እንደሆነ ተመለከትኩ፤+ ሆኖም አንድም ሰው አላገኘሁም። 31  ስለዚህ ቁጣዬን በእነሱ ላይ አወርዳለሁ፤ በታላቅ ቁጣዬም እሳት ፈጽሜ አጠፋቸዋለሁ። የመረጡት መንገድ የሚያስከትለውን መዘዝ በራሳቸው ላይ አመጣባቸዋለሁ’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል “ፋንድያ” ከሚለው ቃል ጋር ዝምድና ሊኖረው የሚችል ሲሆን ንቀትን ለማመልከት ተሠርቶበታል።
ወይም “ወላጅ አልባ የሆነውን ልጅና።”
ቃል በቃል “የአባታቸውን እርቃን ይገልጣሉ።”
ወይም “በወለድና በአራጣ።”
ወይም “ነፍሳትን።”
ወይም “ነፍሳትንም።”