ዘዳግም 13:1-18

  • ከሃዲዎችን በተመለከተ መደረግ ያለበት ነገር (1-18)

13  “አንድ ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ከመካከልህ ተነስቶ ተአምራዊ ምልክት ወይም ድንቅ ነገር እንደሚያሳይ ቢነግርህና  የነገረህ ተአምራዊ ምልክት ወይም ድንቅ ነገር ቢፈጸም፣ እሱም ‘ሌሎች አማልክትን እንከተል’ ይኸውም አንተ የማታውቃቸውን አማልክት እንከተል፤ ‘እናገልግላቸውም’ ቢልህ፣  የዚያን ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ቃል እንዳትሰማ፤+ ምክንያቱም አምላካችሁ ይሖዋ በሙሉ ልባችሁና በሙሉ ነፍሳችሁ* አምላካችሁን ይሖዋን ትወዱት+ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ እየፈተናችሁ ነው።+  እናንተ አምላካችሁን ይሖዋን ተከተሉ፤ እሱን ፍሩ፤ ትእዛዛቱን ጠብቁ፤ ቃሉን ስሙ፤ እሱን አገልግሉ፤ እንዲሁም እሱን አጥብቃችሁ ያዙ።+  ያ ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ግን ይገደል፤+ ምክንያቱም አምላካችሁ ይሖዋ እንድትሄዱበት ካዘዛችሁ መንገድ ዞር እንድትሉ፣ ከግብፅ ምድር ባወጣችሁና ከባርነት ቤት በታደጋችሁ በአምላካችሁ በይሖዋ ላይ እንድታምፁ አበረታቷችኋል። አንተም ክፉውን ከመካከልህ አስወግድ።+  “የእናትህ ልጅ ወንድምህ ወይም ወንድ ልጅህ ወይም ሴት ልጅህ አሊያም የምትወዳት ሚስትህ ወይም የቅርብ ጓደኛህ* ‘ሌሎች አማልክትን እናምልክ’+ በማለት በሚስጥር ሊያባብልህ ቢሞክርና እነዚህ አማልክት ደግሞ አንተም ሆንክ አባቶችህ የማታውቋቸው  እንዲሁም በቅርብም ሆነ በሩቅ፣ ከአንዱ የምድር ጫፍ እስከ ሌላኛው የምድር ጫፍ የሚገኙ በዙሪያህ ያሉ ሕዝቦች የሚያመልኳቸው አማልክት ቢሆኑ  እሺ አትበለው ወይም አትስማው+ አሊያም አትዘንለት ወይም ደግሞ አትራራለት፤ ከለላም አትሁነው፤  ከዚህ ይልቅ ያለማመንታት ግደለው።+ እሱን ለመግደል መጀመሪያ እጅህን መሰንዘር ያለብህ አንተ ነህ፤ ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ እጁን ይሰንዝርበት።+ 10  ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ካወጣህ ከአምላክህ ከይሖዋ ዞር እንድትል ሊያደርግህ ስለሞከረ እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ውገረው።+ 11  ከዚያም እስራኤላውያን ሁሉ ሰምተው ይፈራሉ፤ በመካከልህም እንዲህ ያለ መጥፎ ነገር ዳግመኛ አያደርጉም።+ 12  “አምላክህ ይሖዋ እንድትኖርባቸው ከሚሰጥህ ከተሞች በአንዱ ውስጥ እንዲህ ሲባል ትሰማ ይሆናል፦ 13  ‘እናንተ የማታውቋቸውን “ሌሎች አማልክት ሄደን እናምልክ” እያሉ የከተማቸውን ነዋሪዎች ለማሳት የሚሞክሩ የማይረቡ ሰዎች ከመካከልህ ተነስተዋል’፤ 14  በዚህ ጊዜ ጉዳዩን በጥልቀት በመመርመርና በማጣራት ስለ ሁኔታው ማወቅ ይኖርብሃል፤+ ይህ አስጸያፊ ነገር በመካከልህ ተፈጽሞ ከሆነና ነገሩ እውነት መሆኑ ከተረጋገጠ 15  የከተማዋን ነዋሪዎች በሰይፍ ግደላቸው።+ እንስሶቿን ጨምሮ ከተማዋንና በውስጧ ያለውን ነገር ሁሉ በሰይፍ ሙሉ በሙሉ አጥፋ።+ 16  ከዚያም በከተማዋ ውስጥ የተገኘውን ምርኮ በሙሉ በአደባባይዋ ላይ ሰብስብ፤ ከተማዋን በእሳት አቃጥል፤ በውስጧ የተገኘው ምርኮ ደግሞ ለአምላክህ ለይሖዋ ሙሉ በሙሉ የሚቀርብ መባ ይሆናል። እሷም ለዘላለም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች። ፈጽሞ ተመልሳ አትገነባም። 17  ይሖዋ ከሚነድ ቁጣው እንዲመለስ፣ ለአባቶችህ በማለላቸው መሠረት+ ምሕረት እንዲያደርግልህና እንዲራራልህ እንዲሁም እንዲያበዛህ ከፈለግክ፣ እንዲጠፉ ከተለዩት ነገሮች መካከል እጅህ ምንም አይውሰድ።+ 18  እኔ ዛሬ የምሰጥህን የእሱን ትእዛዛት በሙሉ በመጠበቅ አምላክህን ይሖዋን ታዘዝ፤* በዚህ መንገድ በአምላክህ በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር ታደርጋለህ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “እንደ ገዛ ነፍስህ የሆነው ጓደኛህ።”
ወይም “ድምፁን ስማ።”