በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመልካሚቱ ምድር ‘ሰባት ምርቶች’

የመልካሚቱ ምድር ‘ሰባት ምርቶች’

የመልካሚቱ ምድር ‘ሰባት ምርቶች’

የእስራኤል ምድር ኮረብቶችና ሸለቆዎች፣ የባሕር ዳርቻዎችና አምባዎች እንዲሁም ወንዞችና የውኃ ምንጮች እንዳሏት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። በስተደቡብ የሚገኘውን ጭው ያለ በረሃና በስተሰሜን የሚገኙትን በበረዶ የተሸፈኑ ተራራዎች ጨምሮ ልዩ ልዩ የአፈር ዓይነቶችና የአየር ንብረቶች ያሏት ይህች ምድር ብዙ ዓይነት ምርቶችን ትሰጣለች። ሙሴ፣ እስራኤላውያን ከፊታቸው የምትጠብቃቸውን ‘መልካሚቱን ምድር’ በጉጉት እንዲጠባበቁ ለማድረግ ሲል በተናገረው ሐሳብ ላይ ምድሪቱ “ስንዴና ገብስ፣ ወይንና የበለስ ዛፎች፣ ሮማን፣ የወይራ ዘይትና ማር የሚገኝባት ምድር” መሆኗን በመናገር ሰባት የግብርና ምርቶችን ለይቶ ጠቅሷል።​—ዘዳግም 8:7, 8

ሰዎች ምድሪቱ የምታስገኛቸውን የግብርና ውጤቶች ለማመልከት “ሰባቱ ምርቶች” የሚለውን አገላለጽ ዛሬም ድረስ ይጠቀማሉ። የምድሪቱን ለምነት ለማሳየት፣ እነዚህ የግብርና ውጤቶች በአገሪቱ በሚሠራባቸው ሳንቲሞችና ቴምብሮች ላይ በተለያዩ ጊዜያት ሲወጡ ቆይተዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን እነዚህ የግብርና ውጤቶች ይመረቱ የነበረው በምን መንገድ ነው? በዚያን ጊዜ የነበሩ ሰዎች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ይጠቀሙባቸው የነበረውስ እንዴት ነው? እስቲ እንመልከት።

“ስንዴና ገብስ” ምንም እንኳ ስንዴና ገብስ የሚዘሩት በመጸው ወቅት ቢሆንም ገብስ ከስንዴ አንድ ወር ቀድሞ ይደርሳል። በመጋቢት ወይም በሚያዝያ ወር በሚከበረው ያልቦካ ቂጣ በዓል ላይ ከገብስ አዝመራ መጀመሪያ የደረሰው ነዶ ለይሖዋ መባ ሆኖ በቤተ መቅደሱ ይቀርብ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ በግንቦት ወር በሚከበረው የሳምንታት በዓል ወይም የጴንጤቆስጤ በዓል ላይ ከስንዴ የተዘጋጁ ዳቦዎች መባ ሆነው ይቀርባሉ።​—ዘሌዋውያን 23:10, 11, 15-17

ለበርካታ መቶ ዓመታት እንዲያውም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ማለት ይቻላል በእስራኤል የሚገኙ ገበሬዎች እህል የሚዘሩት በመደረቢያቸው እጥፋት ውስጥ የያዙትን ዘር በእጃቸው እየዘገኑ በመበተን ነበር። ገብስ ለመዝራት ዘሩን መበተን በራሱ በቂ ነበር። የስንዴ ዘር ግን አፈር መልበስ ይኖርበታል። መሬቱን ከብት እንዲሄድበት በማድረግ ወይም በድጋሚ በማረስ ዘሩ አፈር ውስጥ ዘልቆ እንዲገባ ይደረጋል።

መጽሐፍ ቅዱስ እህል ስለ መዝራት፣ ስለ ማጨድ፣ ስለ መውቃት፣ ስለ ማዝራትና ስለ መፍጨት በተደጋጋሚ ይናገራል። እነዚህ ሁሉ ከፍተኛ ጉልበት የሚጠይቁ ሥራዎች ናቸው። የተሰበሰበው እህል ቤት ውስጥ ከተፈጨ በኋላ ቤተሰቡ የሚመገበው ዳቦ የሚዘጋጅ ሲሆን ይህ በየቀኑ የሚከናወን ሥራ ነበር። ይህ ሁኔታ ኢየሱስ ‘የዕለቱን ምግባችንን ስጠን’ ብለን እንድንጸልይ ሲናገር ምን ማለቱ እንደሆነ እንዲገባን ያደርጋል። (ማቴዎስ 6:11) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ ሰዎች ዋና ምግባቸው ከስንዴ ወይም ከገብስ ዱቄት የተዘጋጀ ዳቦ ነበር።​—ኢሳይያስ 55:10

‘ወይን፣ በለስና ሮማን’ ሙሴ ሕዝቡን ለ40 ዓመት ሲመራ ከቆየ በኋላ ተስፋይቱ ምድር የምታፈራቸውን ነገሮች መመገብ እንደሚጀምሩ በመንገር የሚያጓጓ ተስፋ ከፊታቸው አስቀምጦላቸው ነበር። ከ40 ዓመት በፊት አሥሩ ሰላዮች ተስፋይቱ ምድር ምን ያህል ፍሬያማ መሆኗን ለማሳየት በምድረ በዳ ሰፍረው ወደነበሩት እስራኤላውያን ያመጡት ምን ነበር? “የወይን ዘለላ ያንዠረገገ አንድ ቅርንጫፍ” ሲሆን ወይኑ በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ “በመሎጊያ አድርገው ለሁለት” መሸከም አስፈልጓቸዋል። በተጨማሪም በለስና ሮማን አምጥተው ነበር። በበረሃ ይንከራተቱ የነበሩት እስራኤላውያን ይህን ማየታቸው ምራቃቸውን እንዲውጡ አድርጓቸው መሆን አለበት! ይህ ወደፊት ለሚያገኙት መልካም ነገር እንደ ቅምሻ ነበር!​—ዘኍልቍ 13:20, 23

የወይን እርሻዎች ምርታማነታቸው እንዳይቀንስ ተክሎቹን በመግረዝ፣ በመስኖ ውኃ በማጠጣትና ፍሬውን በመሰብሰብ የማያቋርጥ ክትትል ማግኘት ያስፈልጋቸው ነበር። ኮረብታ ላይ የሚገኝ በጥሩ ሁኔታ የተያዘ የወይን እርሻ የድንጋይ ካብ፣ በጥንቃቄ የተሠሩ እርከኖችና ጠባቂው የሚቀመጥበት ዳስ ይኖረዋል። እስራኤላውያን ከወይን እርሻ ጋር በተያያዘ ስለሚከናወነው ሥራ ያላቸው ግንዛቤ በጊዜ ሂደት እያደገ የመጣ ከመሆኑም ሌላ እርሻው ቸል ከተባለ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ተረድተው ነበር።​—ኢሳይያስ 5:1-7

የወይን ፍሬው የሚሰበሰብበት ወቅት ሲደርስ ወይን የመጥመቅ ሥራም ይጀምራል። የወይን ዘለላዎች በገንዳ ውስጥ ይረገጣሉ ወይም በወይን መጭመቂያ ውስጥ ይጨመቃሉ። የወይን ጭማቂው ውስጥ የሚገኘውን ስኳር ለማውጣት ጭማቂውን ያንተከትኩታል ወይም ደግሞ ጭማቂው ፈልቶ ወደ ወይን ጠጅነት እንዲቀየር ከፈለጉ እንዳለ ይተዉታል። እስራኤል፣ ወይን ለማልማትና የወይን ጠጅ ለመጥመቅ የሚያመች የተፈጥሮ ጸጋ የታደለች ምድር ነች። *

በለስ በማይበቅልባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች አይተው የሚያውቁት የደረቀ የበለስ ጥፍጥፍ ብቻ ሊሆን ይችላል። በአንጻሩ ደግሞ ከበለስ ዛፍ ላይ ወዲያውኑ ተቆርጦ የመጣ ፍሬ ጣዕሙም ሆነ በውስጡ የያዘው ፈሳሽ ሌላ ፍሬ ሊያስመስለው ይችላል። የበለስ ፍሬ የሚሰበሰብበት ወቅት የሚቆየው ለአጭር ጊዜ ሲሆን ፍሬው ሳይበላሽ እንዲቆይ ከተፈለገ ፀሐይ ላይ ተሰጥቶ መድረቅና መታሸግ ይኖርበታል። “ጥፍጥፍ የበለስ ፍሬ” መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዙ ቦታዎች ላይ ተጠቅሶ ይገኛል።​—1 ሳሙኤል 25:18

ጠንካራ ሽፋን ያለውን የበሰለ ሮማን ከፍተን ስንመለከተው ጥቅጥቅ ያሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትናንሽ ፍሬዎችን እናገኛለን፤ ይህን ፍሬ እንዳለ መብላትም ሆነ በጭማቂ መልክ መጠጣት የሚያረካና ለጤና ተስማሚ ከመሆኑም ሌላ ገንቢ ነው። በሮማን ፍሬ ምስል የተሠራ ጌጥ በሊቀ ካህናቱ ቀሚስ ጠርዝ ላይና በሰለሞን ቤተ መቅደስ በሚገኙት ዓምዶች ላይ ይደረግ የነበረ መሆኑ ይህ ፍሬ ትልቅ ቦታ ይሰጠው እንደነበር ያሳያል።​—ዘፀአት 39:24፤ 1 ነገሥት 7:20

‘ወይራና ማር’ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወይራ ዛፍ 60 ጊዜ ያህል የሚጠቅስ ሲሆን ወይራ ለምግብነትም ሆነ ዘይት ለማምረት የሚውል ጠቃሚ ፍሬ ነበር። የወይራ ዛፍ እርሻዎች፣ በአሁኑ ጊዜም በእስራኤል ምድር በብዙ አካባቢዎች ይገኛሉ። (ዘዳግም 28:40) ዛሬም ጭምር በጥቅምት ወር የወይራ ፍሬ ሲለቀም በበርካታ ማኅበረሰቦች ውስጥ መላው ቤተሰብ በዚህ ሥራ ይሳተፋል። የወይራ ፍሬ የሚለቅሙት ሰዎች ፍሬዎቹ እንዲወድቁ ለማድረግ የዛፉን ቅርንጫፎች ይመታሉ፤ ከዚያም የወደቁትን ፍሬዎች ይሰበስባሉ። ፍሬው ሳይበላሽ ለቤተሰቡ የዓመት ቀለብ እንዲሆን ይቀመጣል፤ አሊያም ዘይት ማዘጋጀት ከፈለጉ ወደሚጨመቅበት ቦታ ይወስዱታል። እንዲያውም የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች በተለያየ መንገድ የተሠሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዘይት መጭመቂያዎችን በቁፋሮ አግኝተዋል። ለቤተሰቡ የዓመት ቀለብ የሚሆነውን ወይም ለሽያጭ የሚዘጋጀውን ፈዛዛ አረንጓዴ ቀለም ያለው ዘይት፣ በማስቀመጫ ውስጥ ሲንቆረቆር ማየት ይማርካል። የወይራ ዘይት ለምግብነት የሚውል ከመሆኑም ባሻገር ለመዋቢያነት እንዲሁም ኩራዝ ለማብራት ነዳጅ ሆኖ ያገለግላል።

ሙሴ የጠቀሰው ማር ከንቦች የሚገኝ አሊያም ከተምርና ከወይን ተጨምቆ የሚዘጋጅ ማር ሊሆን ይችላል። ከእነዚህ ፍሬዎች የሚዘጋጀውን ማር በዛሬው ጊዜም ለማጣፈጫነት መጠቀም የተለመደ ነው። ሆኖም ስለ ሳምሶንና ስለ ዮናታን በሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ላይ የተጠቀሰው ማር ከንብ ቀፎ የተገኘ የተፈጥሮ ማር እንደነበር ግልጽ ነው። (መሳፍንት 14:8, 9፤ 1 ሳሙኤል 14:27) በሰሜን እስራኤል፣ በቴል ረሆቭ ከተማ በቅርቡ የተገኘው ከ30 በላይ የንብ ቀፎዎች ያሉት አንድ የንብ ማርቢያ ቦታ በሰለሞን ዘመንም እንኳ በምድሪቱ ንብ ማርባት የተለመደ ሥራ እንደነበር ያሳያል።

በዛሬው ጊዜ አንድ ሰው ዳቦ መጋገሪያዎችንና በቂ አቅርቦት ያላቸውን የፍራፍሬና የአትክልት መሸጫዎች አካትቶ በያዘ በእስራኤል ውስጥ በሚገኝ አንድ የገበያ ቦታ ሲዘዋወር ‘ከሰባቱ ምርቶች’ ውስጥ በተለያየ መልክ ተዘጋጅተው ለገበያ የቀረቡ በርካታ ነገሮችን ማግኘት ይችላል። እርግጥ ነው፣ እነዚህ ሰባት ምርቶች ምድሪቱ ከምታፈራቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው የምግብ ዓይነቶች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። ዘመናዊ የግብርና ዘዴዎች በሌሎች አገሮች ብቻ ይገኙ የነበሩ ተክሎችን በእስራኤልም ለማሳደግ አስችለዋል። በእርግጥም ይህች ትንሽ ምድር ይህ ሁሉ የተትረፈረፈ ምርት የሚገኝባት ከመሆኗ አንጻር ‘መልካሚቱ ምድር’ ተብላ መጠራቷ የተገባ ነው።​—ዘኍልቍ 14:7

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.9 በተጨማሪም ሰዎች የወይን ፍሬን በማድረቅ ዘቢብ ያዘጋጁ ነበር።​—2 ሳሙኤል 6:19

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስንዴ

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ገብስ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወይን

[በገጽ 12 እና 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በለስ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሮማን

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወይራ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማር