በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓለምን እየገዛ ያለው ማን ነው?

ዓለምን እየገዛ ያለው ማን ነው?

 ዓለምን እየገዛ ያለው ማን ነው?

የወንጀለኞች ቡድን መሪ ከሆነ ከአንድም ሰው ጋር ፈጽሞ ተገናኝተህ አታውቅ ይሆናል። እንዲህ ሲባል ግን እነዚህ መሪዎች የሉም ማለት ነው? የወንጀል ቡድን መሪዎች ማንነታቸውን በመደበቅ ረገድ የተዋጣላቸው ከመሆናቸውም ሌላ እስር ቤት ውስጥ ሆነውም እንኳ አመራር መስጠት ይችላሉ። ይሁንና ከዕፅ ጋር በተያያዘ የሚካሄዱ ጦርነቶችን፣ በዝሙት አዳሪነት ዙሪያ የተቋቋሙ መዋቅሮችንና ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን የመሳሰሉ ጉዳዮችን የሚያትቱ የጋዜጣ ርዕሰ አንቀጾች እነዚህ ተግባሮች መጥፎ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩና አስከፊ መዘዝ እንደሚያስከትሉ እንዲሁም እነዚህን ወንጀሎች የሚያቀነባብር አካል እንዳለ ይጠቁማሉ። ደግሞም በሰብዓዊው ኅብረተሰብ ላይ ጥለው ከሚያልፉት አሻራ በመነሳት የወንጀል ድርጊቶችን የሚያደራጁ መሪዎች እንዳሉ ማወቅ እንችላለን።

የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰይጣን በእውን ያለ አካል እንደሆነና ልክ እንደ አንድ ኃይለኛ የወንጀለኞች መሪ ዓላማውን ለመፈጸም “በሐሰተኛ ምልክቶችና” ‘በማንኛውም ዓይነት የክፋት ዘዴ’ እንደሚጠቀም ይገልጻል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን “የብርሃን መልአክ ለመምሰል ዘወትር ራሱን ይለዋውጣል” በማለት ይናገራል። (2 ተሰሎንቄ 2:9, 10፤ 2 ቆሮንቶስ 11:14) በተመሳሳይም ዲያብሎስ የተዋቸው አሻራዎች የእሱን መኖር ያረጋግጣሉ። ያም ሆኖ ብዙ ሰዎች በዓይን የማይታይ ክፉ መንፈሳዊ አካል አለ ብሎ ማመን ይከብዳቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዲያብሎስ የሚናገረውን ነገር በጥልቀት ከመመርመራችን በፊት በርካታ ሰዎች ዲያብሎስ በእውን ያለ አካል ነው የሚለውን ሐሳብ እንዳይቀበሉ የሚያደርጓቸውን አንዳንድ የተለመዱ አመለካከቶችና የተሳሳቱ እምነቶች እንመልከት።

“አፍቃሪ የሆነ አምላክ ዲያብሎስን እንዴት ሊፈጥር ይችላል?” መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፈጣሪ ጥሩና ፍጹም አምላክ እንደሆነ ስለሚናገር ክፉና መሠሪ ብሎም ጨካኝ የሆነን አካል ይፈጥራል ብሎ ማሰብ አያስኬድም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ እንዲህ ያለውን አካል እንደፈጠረ አይናገርም። እንዲያውም አምላክን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “እርሱ ዐለት፣ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ ትክክል ነው፤ የማይሳሳት ታማኝ አምላክ፣ ቀጥተኛና ጻድቅ አምላክም እርሱ ነው።”​—ዘዳግም 32:4፤ መዝሙር 5:4

እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ ‘አምላክ የፈጠረው ፍጹም የሆነ አካል ትክክል ከሆነው ነገር ውጭ ማድረግ ይችላል ወይስ አይችልም?’ የሚለው ነው። አምላክ ፍጡራኖቹን እንደ ሮቦት አድርጎ አልፈጠራቸውም፤ ከዚህ ይልቅ የመምረጥ ነፃነት ይኸውም የራሳቸውን ምርጫ የማድረግ ችሎታ ሰጥቷቸዋል። በመሆኑም የማሰብ ችሎታ ያለው ፍጹም የሆነ አንድ ፍጡር ጥሩ ወይም መጥፎ የሆነውን ነገር ለማድረግ መምረጥ ይችላል። የማሰብ ችሎታ ያላቸው ሥጋዊም ሆኑ መንፈሳዊ ፍጡራን የሚፈጽሙት ድርጊት ትክክል ወይም ስህተት ሊባል የሚችለው እነዚህ ፍጡራን የመምረጥ ነፃነት ካላቸው ብቻ ነው።

አምላክ ለፍጡራኑ በአንድ በኩል የሥነ ምግባር ነፃነት ሰጥቶ በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ ነፃነታቸው ተጠቅመው መጥፎ ነገር ለመሥራት ቢመርጡ ይህን እንዳያደርጉ ይከለክላቸዋል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይሆንም። ኢየሱስ ዲያብሎስን በተመለከተ “በእውነት ውስጥ ጸንቶ አልቆመም” ብሎ በተናገረ ጊዜ በመምረጥ ነፃነት አላግባብ መጠቀም እንደሚቻል ጠቁሟል። (ዮሐንስ 8:44) ይህ ጥቅስ፣ ከጊዜ በኋላ ዲያብሎስ የሆነው አካል በተፈጠረበት ጊዜ ፍጹም መንፈሳዊ ፍጡር እንደነበርና በአንድ ወቅት “በእውነት ውስጥ ጸንቶ” ይመላለስ እንደነበር በግልጽ ያሳያል። * ይሖዋ አምላክ፣ ፍጥረታቱን ስለሚወዳቸውና ስለሚያምናቸው የመምረጥ ነፃነት እንዲኖራቸው አድርጎ ፈጥሯቸዋል።​—በገጽ 6 ላይ የሚገኘውን   “ፍጹም የሆነ ፍጡር ፍጽምናውን ሊያጣ ይችላል?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

“ዲያብሎስ የአምላክ አገልጋይ ነው” አንዳንዶች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የኢዮብ መጽሐፍ ይህን ሐሳብ እንደሚያስተላልፍ ይሰማቸዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ትንታኔ የሚሰጥ አንድ ጽሑፍ ዲያብሎስ “በምድር ሁሉ ዞርሁ” በማለት የተናገረው ሐሳብ በጥንት ጊዜ የነበሩት የፋርስ ሰላዮች የንጉሣቸው መልእክተኞች ሆነው ወደተለያዩ ቦታዎች በመጓዝ እንዲሁም የሰበሰቧቸውን መረጃዎች ሪፖርት በማድረግ ረገድ የነበራቸውን ሚና የሚያመለክት እንደሆነ ገልጿል። (ኢዮብ 1:7) ይሁንና ዲያብሎስ በእርግጥ አምላክን የሚያገለግል ሰላይ ከሆነ “በምድር ሁሉ ዞርሁ” ብሎ ለአምላክ መልስ መስጠት ለምን አስፈለገው? የኢዮብ መጽሐፍ ዲያብሎስን ከአምላክ ጎን የቆመ እንደሆነ አድርጎ ከመግለጽ ይልቅ ሰይጣን ብሎ የሚጠራው ሲሆን ትርጉሙም “ተቃዋሚ” ማለት ነው፤ ይህም የአምላክ ቀንደኛ ጠላት እንደሆነ ይጠቁማል። (ኢዮብ 1:6) ታዲያ ዲያብሎስ የአምላክ አገልጋይ ነው የሚለው ሐሳብ የመጣው ከየት ነው?

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. የተጻፉትን “የኢዮቤልዩ መጽሐፍ” እና በኩምራን የነበረው የሃይማኖት ቡድን የሚጠቀምበትን “የጋራ ሕግ” ተብሎ የሚጠራውን መጽሐፍ የመሳሰሉ የአዋልድ መጻሕፍት ዲያብሎስን በአንድ በኩል ከአምላክ ጋር እንደሚከራከር በሌላ በኩል ደግሞ ለእሱ ፈቃድ እንደሚገዛ አድርገው ይገልጹታል። ታሪክ ጸሐፊው ጄፍሪ በርተን ራስል ሜፊስቶፈሊዝ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ የፕሮቴስታንት ተሃድሶ አራማጅ የነበረው ማርቲን ሉተር፣ ዲያብሎስን የአምላክ መሣሪያ ይኸውም “አምላክ የአትክልት ስፍራውን ለማሳመር እንደሚጠቀምበት መከርከሚያ ወይም መኮትኮቻ” አድርጎ ይመለከተው እንደነበር ተናግረዋል። ራስል ይህን ሐሳብ እንዲህ በማለት አብራርተውታል፦  “መኮትኮቻው አረሞቹን በማጥፋት ይደሰታል”፤ ያም ሆኖ መኮትኮቻው ኃያል ከሆነው የአምላክ እጅ ሳይወጣ የአምላክን ፈቃድ ይፈጽማል። ከጊዜ በኋላ፣ ጆን ካልቪን በተባለው ፈረንሳዊ የሃይማኖት ምሑር ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው ይህ የሉተር ትምህርት በብዙ አማኞች አመለካከት ከፍትሕ አንጻር ምክንያታዊነት የጎደለው ነበር። አፍቃሪ የሆነ አምላክ ክፋት እንዲኖር መፍቀዱ ሳያንስ መጥፎ ነገሮች እንዲደርሱ የሚፈልገው ለምንድን ነው? (ያዕቆብ 1:13) ከዚህ መሠረተ ትምህርት በተጨማሪ በ20ኛው መቶ ዘመን የተፈጸሙት ዘግናኝ ድርጊቶች በርካታ ሰዎች በአምላክም ሆነ በዲያብሎስ መኖር እንዳያምኑ አድርጓቸዋል።

“ዲያብሎስ የክፋት ሐሳብ ነው” ዲያብሎስ እንዲያው የክፋት ሐሳብ ነው ብለን የምናምን ከሆነ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን መረዳት ፈጽሞ የማይቻል ነገር ይሆንብናል። ለምሳሌ ያህል፣ በኢዮብ 2:3-6 ላይ በተገለጸው መሠረት አምላክ እየተነጋገረ የነበረው ከማን ጋር ነው? አምላክ እየተነጋገረ የነበረው በኢዮብ ውስጥ ካለ ክፉ ሐሳብ ጋር ነበር? ወይስ ከራሱ ጋር ነበር? ከዚህም በተጨማሪ፣ አምላክ መጀመሪያ ላይ የኢዮብን መልካም ጎኖች ሲያደንቅ ቆይቶ በኋላ ደግሞ ኢዮብ በክፉ ሐሳብ እንዲፈተን እየፈቀደ ነበር ማለት ነው? አምላክ እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ይኖረዋል ብሎ ማሰብ እሱ ክፉ ነው የማለት ያህል ነው፤ ደግሞም “በእርሱ ዘንድ እንከን የለም” ብሎ መናገር አይቻልም። (መዝሙር 92:15) ከዚህ በተቃራኒ አምላክ ‘እጁን ዘርግቶ’ ኢዮብን ለመጉዳት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ዲያብሎስ የክፋት ሐሳብ ወይም የአምላክ ማንነት መጥፎ ገጽታ አይደለም፤ ይልቁንም ራሱን የአምላክ ተቃዋሚ ያደረገ መንፈሳዊ አካል ነው።

በእርግጥ ዓለምን እየገዛ ያለው ማን ነው?

በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች በዲያብሎስ መኖር ማመን ጊዜ ያለፈበት ነገር እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሆኖም ዲያብሎስ የለም ካልን ዛሬ ለምናየው ዘግናኝ የሆነ የክፋት ድርጊት መንስኤው ማን እንደሆነ ማወቅ አንችልም። እንዲያውም የዲያብሎስን ሕልውና ላለመቀበል የሚደረገው ጥረት በርካታ ሰዎች በአምላክ መኖር እንዳያምኑ እንዲሁም ማንኛውንም ዓይነት የሥነ ምግባር መሥፈርቶች እንዲጥሱ አድርጓቸዋል።

የ19ኛው መቶ ዘመን ገጣሚ የሆኑት ሻርል ፕዬር ቡድሌር “የሰይጣን ዋነኛ ማታለያ እኛን እሱ እንደሌለ አድርጎ ማሳመን ነው” በማለት ጽፈዋል። ዲያብሎስ ማንነቱን በመሰወር በአምላክ ሕልውና ላይ ጥርጣሬ አስነስቷል። ዲያብሎስ ከሌለ ለክፋት ድርጊቶች ሁሉ ተጠያቂው አምላክ ይሆን ነበር። የዲያብሎስ ፍላጎትስ ቢሆን ሰዎች እንዲህ ብለው እንዲያምኑ ማድረግ አይደለም?

ዲያብሎስ ልክ እንደ አንድ የወንጀል ቡድን መሪ ዓላማውን ለመፈጸም ሲል ማንነቱን ይደብቃል። ለመሆኑ ዓላማው ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጠናል፦ “የአምላክ አምሳል ስለሆነው ስለ ክርስቶስ የሚገልጸው ክብራማ ምሥራች ብርሃን በእነሱ ላይ እንዳያበራ የዚህ ሥርዓት አምላክ የማያምኑትን ሰዎች አእምሮ አሳውሯል።”​—2 ቆሮንቶስ 4:4

አሁንም መልስ የሚያሻው አንድ አንገብጋቢ ጥያቄ አለ። አምላክ፣ ለክፋትና ለመከራ ሁሉ ዋነኛ ተጠያቂ የሆነውን ብሎም ማንነቱን ሰውሮ የሚንቀሳቀሰውን ይህን አካል ምን ያደርገዋል? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይህን ጥያቄ እንመረምራለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 አምላክ ዲያብሎስ ባመፀበት ጊዜ ወዲያውኑ እርምጃ ያልወሰደው ለምን እንደሆነ ለማወቅ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 11 ተመልከት።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ዲያብሎስ የአምላክ አገልጋይ ነው ወይስ የአምላክ ተቃዋሚ?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

 ፍጹም የሆነ ፍጡር ፍጽምናውን ሊያጣ ይችላል?

አምላክ የማሰብ ችሎታ ላላቸው ፍጡራኑ የሰጣቸው ፍጽምና አንጻራዊ ነው። አዳም ፍጹም ሆኖ የተፈጠረ ቢሆንም እንኳ አምላክ ያስቀመጠለትን ከተፈጥሮው ጋር የተያያዙ ገደቦች አክብሮ መኖር ነበረበት። ለምሳሌ አፈር፣ ድንጋይ አሊያም እንጨት ቢበላ ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች እንደሚያጋጥሙት የታወቀ ነው። የስበት ሕግን ችላ ብሎ ከተራራ አፋፍ ላይ ቢዘል ለከፋ ጉዳት ወይም ለሞት ሊዳረግ ይችላል።

በተመሳሳይም ፍጹም የሆነ ሰው ወይም መልአክ አምላክ የደነገገውን የሥነ ምግባር ደንብ ጥሶ ከሚደርስበት ጎጂ ውጤት ማምለጥ አይችልም። በመሆኑም የማሰብ ችሎታ ያለው አንድ ፍጡር የመምረጥ ነፃነቱን አላግባብ ከተጠቀመበት በቀላሉ ስህተት መፈጸሙና ኃጢአት ውስጥ መውደቁ አይቀርም።​—ዘፍጥረት 1:29፤ ማቴዎስ 4:4