በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓለምን በስውር የሚገዛው መሪ ተጋለጠ

ዓለምን በስውር የሚገዛው መሪ ተጋለጠ

 ዓለምን በስውር የሚገዛው መሪ ተጋለጠ

ኢየሱስ በአንድ ወቅት ለአድማጮቹ “የዚህ ዓለም ገዥ . . . ወደ ውጭ ይጣላል” ብሏቸው ነበር። በሌላ ጊዜ ደግሞ ‘የዚህ ዓለም ገዥ በእሱ ላይ ምንም ኃይል እንደሌለው’ እንዲሁም ‘የዚህ ዓለም ገዥ እንደተፈረደበት’ ተናግሯል። (ዮሐንስ 12:31፤ 14:30፤ 16:11) ኢየሱስ እዚህ ላይ እየተናገረ የነበረው ስለ ማን ነው?

ኢየሱስ ‘የዚህን ዓለም ገዥ’ አስመልክቶ ከተናገረው ነገር በመነሳት ስለ አባቱ ስለ ይሖዋ አምላክ እየተናገረ እንዳልነበር በግልጽ መረዳት ይቻላል። ታዲያ “የዚህ ዓለም ገዥ” ማን ነው? ይህ ገዥ ‘ወደ ውጭ የሚጣለው’ እንዲሁም ‘የተፈረደበት’ እንዴት ነው?

“የዚህ ዓለም ገዥ” ማንነቱን ገለጠ

የወንጀለኞች ቡድን መሪ የሆነ አንድ ሰው በሥልጣኑ እንደሚኩራራ ሁሉ ዲያብሎስም የአምላክ ልጅ የሆነውን ኢየሱስን በፈተነው ጊዜ ተመሳሳይ ነገር አድርጓል። ሰይጣን ለኢየሱስ “የዓለምን መንግሥታት ሁሉ” ካሳየው በኋላ እንዲህ የሚል ግብዣ አቅርቦለት ነበር፦ “ይህን ሁሉ ሥልጣንና የእነዚህን መንግሥታት ክብር ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ይህ ሁሉ ለእኔ ስለተሰጠ እኔ ደግሞ ለፈለግሁት እሰጠዋለሁ። ስለዚህ አንድ ጊዜ በፊቴ ተደፍተህ ብታመልከኝ ይህ ሁሉ የአንተ ይሆናል።”​—ሉቃስ 4:5-7

አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት ዲያብሎስ የክፋት ሐሳብ ከሆነ ኢየሱስ የቀረበለት ይህ ፈተና ምን ትርጉም ይኖረዋል? ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ በአንድ ዓይነት የክፋት ሐሳብ ወይም በውስጡ በተከሰተ የመረበሽ ስሜት እየተፈተነ ነበር ማለት ነው? ሁኔታው እንዲህ ከሆነ ኢየሱስ “ኃጢአት የለበትም” እንዴት ሊባል ይችላል? (1 ዮሐንስ 3:5) ኢየሱስ፣ ዲያብሎስ በሰዎች ላይ ያለውን ሥልጣን ከመካድ ይልቅ ዲያብሎስ “ነፍሰ ገዳይ” እንዲሁም “ውሸታም” መሆኑን በመግለጽ “የዚህ ዓለም ገዥ” እንደሆነ አረጋግጧል።​—ዮሐንስ 8:44፤ 14:30

ዲያብሎስ ክርስቶስን ከፈተነው ወደ 70 የሚጠጉ ዓመታት ካለፉ በኋላ ሐዋርያው ዮሐንስ “መላው ዓለም . . . በክፉው ኃይል ሥር ነው” በማለት ዲያብሎስ ስለሚያሳድረው ከባድ ተጽዕኖ ክርስቲያኖችን አስጠንቅቋቸዋል። በተጨማሪም ዮሐንስ፣ ዲያብሎስ “መላውን ዓለም እያሳሳተ” እንዳለ ተናግሯል። (1 ዮሐንስ 5:19፤ ራእይ 12:9) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ “የዚህ ዓለም ገዥ” በዓይን የማይታይ መንፈሳዊ አካል እንደሆነ ይናገራል። ይሁንና ይህ አካል በሰው ዘር ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ ያሳድራል?

የዓለም ገዥ ለተባባሪዎቹ ሥልጣን ያካፍላል

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች ለእምነታቸው ሲሉ ስለሚያደርጉት ተጋድሎ በጻፈ ጊዜ ቀንደኛ ጠላቶቻቸው እነማን እንደሆኑ ተናግሯል። እንዲህ በማለት በግልጽ ጽፏል፦ “ትግል የምንገጥመው ከደምና ከሥጋ ጋር ሳይሆን ከመንግሥታት፣ ከሥልጣናት፣ ይህን ጨለማ ከሚቆጣጠሩ የዓለም ገዢዎች እንዲሁም በሰማያዊ ስፍራዎች ካሉ ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር ነው።” (ኤፌሶን 6:12) ይህ ትግል የሚደረገው “ከደምና ከሥጋ ጋር ሳይሆን . . . ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች” ጋር ስለሆነ ውጊያው በሰዎች መካከል የሚካሄድ አይደለም።

አብዛኞቹ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “ክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች” የሚለው ሐረግ የማይጨበጥ የክፋት ሐሳብን ሳይሆን ኃይለኛ የሆኑ ክፉ መንፈሳዊ አካላትን እንደሚያመለክት ያሳያሉ። አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች ይህን ሐረግ “በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት” (የ1954 ትርጉም)፣ “በሰማያዊ ስፍራ ካሉ ከርኩሳን መናፍስት ሰራዊት” (አዲሱ መደበኛ ትርጉም) እንዲሁም “በሰማያት ያሉ ከሰው በላይ የሆኑ የክፋት ኃይሎች” (ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) በማለት ተርጉመውታል። በመሆኑም ዲያብሎስ፣ በሰማይ የሚገኘውን “ትክክለኛ መኖሪያቸውን የተዉትን” ሌሎች ዓመፀኛ መላእክት በመጠቀም ተጽዕኖ ያሳድራል።​—ይሁዳ 6

የትንቢት መጽሐፍ የሆነው የዳንኤል መጽሐፍ እነዚህ “የዓለም ገዢዎች” ከጥንት ዘመን አንስቶ ዓለምን ሲቆጣጠሩ እንደቆዩ ይገልጻል። ነቢዩ ዳንኤል በ537 ዓ.ዓ.  ከባቢሎን ግዞት ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት የአይሁዳውያን ወገኖቹ ሁኔታ በጥልቅ ስላሳሰበው ለሦስት ሳምንታት ስለ እነሱ ጸልዮ ነበር። አምላክ ዳንኤልን ለማጽናናት የላከው መልአክ ነቢዩ ጋር የደረሰው ዘግይቶ ነበር። መልአኩ የዘገየበትን ምክንያት ለነቢዩ ሲነግረው “የፋርስ መንግሥት አለቃ ሃያ አንድ ቀን ተቋቋመኝ” ብሎታል።​—ዳንኤል 10:2, 13

‘የፋርስ አለቃ’ የተባለው ማን ነው? መልአኩ እየተናገረ የነበረው ለዳንኤልና ለወገኖቹ በጎ አመለካከት ስለነበረው ስለ ፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ እንዳልነበረ ግልጽ ነው። ደግሞስ አንድ መልአክ በአንድ ሌሊት ብቻ 185,000 ኃያል ተዋጊዎችን መግደል ከቻለ አንድ ሰብዓዊ ንጉሥ አንድን መንፈሳዊ ፍጡር ለሦስት ሳምንት እንዴት ሊቋቋም ይችላል? (ኢሳይያስ 37:36) የጠላትነት መንፈስ ያንጸባረቀው ይህ ‘የፋርስ አለቃ’ የዲያብሎስ ወኪል ይኸውም በፋርስ መንግሥት ላይ የመግዛት ሥልጣን የተሰጠው ጋኔን እንጂ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። ዘገባው በመቀጠል የአምላክ መልአክ እንደገና ‘ከፋርስ አለቃ’ ጋር እንዲሁም የአለቅነት ሥልጣን ካለው ሌላ ጋኔን ይኸውም ‘ከግሪክ አለቃ’ ጋር እንደሚዋጋ ተናግሯል።​—ዳንኤል 10:20

ከዚህ ዘገባ ተነስተን ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን? የማይታዩ የዚህ “ዓለም ገዢዎች” እንዳሉ ይኸውም አለቃቸው በሆነው በሰይጣን ዲያብሎስ ሥልጣን ሥር ሆነው ዓለምን ተከፋፍለው የሚገዙ የአለቅነት ሥልጣን የተሰጣቸው አጋንንት መኖራቸውን እንረዳለን። ይሁንና ጥንትም ሆነ ዛሬ ዓላማቸው ምንድን ነው?

የዚህ ዓለም ገዥ ትክክለኛ ፍላጎት ታወቀ

የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን የራእይን መጽሐፍ የጻፈው ሐዋርያው ዮሐንስ፣ የመላእክት አለቃ ሚካኤል የተባለው ኢየሱስ ዲያብሎስንና አጋንንቱን እንዴት ድል እንዳደረጋቸው ከመናገሩም በተጨማሪ የእነሱ ከሰማይ መባረር ያስከተለውን አስከፊ መዘዝ ይገልጻል። እንዲህ ይላል፦ “ምድርና ባሕር . . . ወዮላችሁ! ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ስላወቀ በታላቅ ቁጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዷል።”​—ራእይ 12:9, 12

ዲያብሎስ በታላቅ ቁጣ እንደተሞላ ያሳየው እንዴት ነው? ተስፋ የቆረጡ በርካታ ወንጀለኞች ‘ግዛ ወይም አጥፋ’ የሚለውን መርህ እንደሚከተሉ ሁሉ ዲያብሎስና አጋንንቱም ምድርና ነዋሪዎቿ አብረዋቸው እንዲጠፉ ለማድረግ ቆርጠው ተነስተዋል። ዲያብሎስ የቀረው ጊዜ ጥቂት መሆኑን ስለሚያውቅ በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለውንና ሰብዓዊው ኅብረተሰብ ከተመሠረተባቸው መዋቅሮች መካከል አንዱ የሆነውን የንግዱን ሥርዓት በመጠቀም ሰዎች ቅጥ ያጣ ሸቀጥ የመሸመት አባዜ እንዲጠናወታቸው አድርጓል። ይህ ደግሞ የተፈጥሮ ሀብቶች እየተመናመኑ እንዲሄዱና ምድር እንድትበላሽ በማድረግ የሰው ልጆችን ሕልውና አደጋ ላይ ጥሏል።​—ራእይ 11:18፤ 18:11-17

ዲያብሎስ ለሥልጣን ያለው ጥማት የሰው ልጅ ታሪክ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የታየ ሲሆን ይህ ፍላጎቱ የፖለቲካውና የሃይማኖቱ ሥርዓት በተዋቀረበት መንገድ ላይም ተንጸባርቋል። የራእይ መጽሐፍ፣ የፖለቲካ ኃይሎችን በአራዊት የሚመስላቸው ከመሆኑም ሌላ ዲያብሎስ “ታላቅ ሥልጣን” እንደሰጣቸው ይገልጻል። በተጨማሪም በፖለቲካና በሃይማኖት መካከል ያለው አሳፋሪ ጥምረት አስጸያፊ መንፈሳዊ ምንዝር እንደሆነ ይገልጻል። (ራእይ 13:2፤ 17:1, 2) ባለፉት መቶ ዓመታት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ስለሆኑት ጭቆና፣ ባርነት፣ ጦርነቶችና የጎሳ ግጭቶች አስብ። በሰው ዘር ታሪክ ላይ ጥቁር ነጥብ ጥለው ያለፉት አስደንጋጭና ዘግናኝ ክስተቶች፣ የተለመዱ ሰብዓዊ እንቅስቃሴዎች ናቸው ብሎ መናገር የሚችል ሰው ይኖራል? ወይስ በዓይን በማይታዩ ክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ተጽዕኖ የተከናወኑ ነገሮች ናቸው?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰብዓዊ መሪዎችንና ኃያላን መንግሥታትን እንደፈለገው እያሽከረከረ ያለውን አካል በትክክል የሚያሳውቅ ከመሆኑም ሌላ ማንነቱን ያጋልጣል። ሰብዓዊው ኅብረተሰብ አውቆትም ሆነ ሳያውቀው የገዥውን ባሕርይ ያንጸባርቃል፤ እንዲሁም ‘ግዛ ወይም አጥፋ’ የሚለውን የእሱን መርህ ይከተላል። ይሁንና የሰው ልጅ በዲያብሎስ አገዛዝ ሥር ሆኖ የሚማቅቀው እስከ መቼ ነው?

የዲያብሎስ መጥፊያ ተቃርቧል

ክርስቶስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በምድር ላይ ያደረገው እንቅስቃሴ ዲያብሎስና አጋንንቱ ጥፋት እንደሚጠብቃቸው የሚያመላክት ነበር። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በዓይን የማይታዩትን አጋንንት እንዴት እንዳስወጡ ለኢየሱስ በነገሩት ጊዜ ኢየሱስ “ሰይጣን እንደ መብረቅ ከሰማይ  ሲወድቅ አየሁ” ብሏቸው ነበር። (ሉቃስ 10:18) ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ሲናገር ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ሆኖ በዓለም ገዥ ላይ ወደፊት የሚቀዳጀውን ድል በማሰብ የተሰማውን ደስታ መግለጹ ነበር። (ራእይ 12:7-9) በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ላይ የተደረገ ጥልቀት ያለው ጥናት እንደሚያሳየው በሰማይ ይህ ድል የተገኘው በ1914 ወይም ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ነበር። *

ከዚያን ጊዜ አንስቶ ዲያብሎስ የቀረው ጊዜ ጥቂት እንደሆነ ያውቃል። ‘መላው ዓለም በእሱ ኃይል ሥር’ ቢሆንም በዛሬው ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ዲያብሎስ እነሱን ለመቆጣጠር በሚያደርገው የሞት ሽረት ትግል አልተሸነፉም። ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ የዲያብሎስን እውነተኛ ማንነትና የእሱን ዕቅዶች ማወቅ እንዲችሉ ዓይናቸውን ከፍቶላቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 2:11) እነዚህ ሰዎች፣ ጳውሎስ ለክርስቲያን ባልንጀሮቹ “ሰላም የሚሰጠው አምላክ . . . በቅርብ ጊዜ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ይጨፈልቀዋል” ሲል በጻፈው ሐሳብ ይጽናናሉ። *​—ሮም 16:20

ዲያብሎስ የሚጠፋበት ጊዜ ተቃርቧል! ጻድቅ የሆኑ ሰዎች በክርስቶስ ፍቅራዊ አገዛዝ ሥር ሆነው በምሳሌያዊ ሁኔታ የአምላክ የእግር ማረፊያ የሆነችውን ምድር ወደ ገነትነት ይለውጣሉ። ግፍ፣ ጥላቻና ስግብግብነት ለዘላለም ይወገዳሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ያለፉት ነገሮች አይታሰቡም” ይላል። (ኢሳይያስ 65:17) ይህን ዓለም በስውር እየገዛ ካለው መሪና ከእሱ አገዛዝ ነፃ የወጡ ሰዎች ሁሉ እንዴት ያለ ታላቅ እፎይታ ያገኛሉ!

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.20 ስለዚህ ቀን ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት ከፈለግህ በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ ላይ ከሚገኘው ተጨማሪ ክፍል ላይ ከገጽ 215 እስከ 218 ተመልከት።

^ አን.21 ጳውሎስ የጻፈው ይህ ሐሳብ በ⁠ዘፍጥረት 3:15 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ከጊዜ በኋላ ዲያብሎስ እንደሚጠፋ የሚጠቁመውን የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ያስታውሰናል። ጳውሎስ፣ ዲያብሎስ የሚደርስበትን ጥፋት ለማመልከት የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል “አንድን ነገር በመጨፍለቅ ማድቀቅ፣ መሰባበር፣ ድምጥማጡን ማጥፋት” የሚል ትርጉም ያስተላልፋል።​—ቫይንስ ኮምፕሊት ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ወርድስ

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ጻድቅ የሆኑ ሰዎች በክርስቶስ ፍቅራዊ አገዛዝ ሥር ሆነው ምድርን ወደ ገነትነት ይለውጣሉ