በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለይሖዋ እንደ ልቡ የሆነለት ሰው

ለይሖዋ እንደ ልቡ የሆነለት ሰው

 ለይሖዋ እንደ ልቡ የሆነለት ሰው

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተገለጸው ስለ ዳዊት ስታስብ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? ግዙፍ ሰው በነበረው በፍልስጥኤማዊው ጎልያድ ላይ የተቀዳጀው ድል? ንጉሥ ሳኦል ለእሱ ከነበረው ጥላቻ የተነሳ ወደ ምድረ በዳ መሸሹ? ከቤርሳቤህ ጋር የፈጸመው ኃጢአትና በዚያ ሳቢያ የደረሰበት መከራ? ወይስ በመዝሙር መጽሐፍ ላይ ተመዝግበው የሚገኙት በመንፈስ መሪነት ያቀናበራቸው መዝሙሮች?

ዳዊት በሕይወት ዘመኑ ለብዙ መብቶች የበቃና በርካታ ድሎች የተጎናጸፈ ከመሆኑም ሌላ አሳዛኝ የሆኑ ክስተቶችም አጋጥመውት ነበር። ሆኖም ከሁሉም በላይ ትኩረታችንን የሚስበው ነገር ነቢዩ ሳሙኤል ‘ለእግዚአብሔር እንደ ልቡ የሚሆንለት ሰው’ በማለት ስለ ዳዊት የተናገረው ሐሳብ ነው።​—1 ሳሙኤል 13:14

ሳሙኤል የተናገረው ትንቢት ተፈጻሚነቱን ያገኘው ዳዊት ገና ትንሽ ልጅ ሳለ ነበር። ለይሖዋ እንደ ልቡ የሚሆንለት ሰው ተብሎ ቢነገርልህ ደስ አይልህም? ከሆነ እንዲህ ዓይነት ሰው ለመሆን ከዳዊት ሕይወት በተለይም ከልጅነት ሕይወቱ ምን ትምህርት ማግኘት እንደምትችል እስቲ እንመልከት።

ቤተሰቡና ሥራው

የሩትና የቦዔዝ የልጅ ልጅ የነበረው የዳዊት አባት እሴይ ለአምላክ ያደረ ሰው እንደነበር ከሁኔታው መረዳት እንችላለን። እሴይ ዳዊትን፣ ሰባት ወንድሞቹንና ሁለት እህቶቹን ገና ከልጅነታቸው አንስቶ የሙሴን ሕግ አስተምሯቸዋል። ዳዊት ከመዝሙሮቹ መካከል በአንዱ ላይ የይሖዋ ‘ሴት ባሪያ’ ልጅ እንደሆነ ገልጿል። (መዝሙር 86:16) ከዚህም የተነሳ አንዳንዶች የዳዊት እናት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በስም ባትጠቀስም በዳዊት መንፈሳዊነት  ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድራ እንደነበር ይስማማሉ። አንድ ምሁር፣ ዳዊት “አምላክ ሕዝቡን ስለያዘበት አስደናቂ መንገድ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማው ከእሷ አንደበት መሆን አለበት” ካሉ በኋላ ይህ ደግሞ የሩትንና የቦዔዝን ታሪክ እንደሚጨምር ተናግረዋል።

ስለ ዳዊት የምናነበው የመጀመሪያው ነገር የአባቱን በጎች የሚንከባከብ ወጣት እረኛ እንደሆነ የተጠቀሰውን ሐሳብ ነው። ይህ ሥራ ደግሞ ዳዊት ቀንና ሌሊት በመስክ ላይ ረጅም ሰዓት ብቻውን ማሳለፍ ይጠይቅበት እንደነበር መገመት አያዳግትም። እስቲ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር።

ዳዊትና ቤተሰቡ በተራራማው የይሁዳ ኮረብታ አናትና ተረተር ላይ በምትገኘው ቤተልሔም በተባለች ትንሽ ከተማ ውስጥ ይኖሩ ነበር። በቤተልሔም ዙሪያ ያለው ድንጋያማ የሆነ የእርሻ መሬት ጥሩ የእህል ምርት ያስገኛል። ተረተሮቹና ሸለቆዎቹ ደግሞ በፍራፍሬ፣ በወይራ ዛፎች እንዲሁም በወይን ተክሎች ተሸፍነዋል። በዳዊት ዘመን፣ ከፍ ብለው የሚገኙ ያልታረሱ መሬቶች ለግጦሽ ይውሉ ነበር። ከዚያ ባሻገር ደግሞ የይሁዳ ምድረ በዳ ይገኝ ነበር።

የዳዊት ሥራ ለአደጋ የሚያጋልጥ ነበር። ከእነዚህ ኮረብቶች በአንዱ ላይ ከመንጋው መካከል በግ ነጥቆ ሊሄድ የሞከረ አንበሳና ድብ አጋጥሞት ያውቃል። * ይህ ደፋር ልጅ አውሬዎቹን አሳድዶ በመግደል በጎቹን ከአፋቸው አስጥሏል። (1 ሳሙኤል 17:34-36) ምናልባትም ዳዊት ወንጭፍ የመጠቀም ችሎታውን ያዳበረው በዚህ ወቅት ሊሆን ይችላል። ከመኖሪያ ከተማው ብዙም ሳይርቅ የብንያም ክልል ይገኛል። የብንያም ሰዎች ደግሞ “ድንጋይ ወንጭፈው ጠጕር እንኳ የማይስቱ” ተዋጊዎች ነበሩ። ዳዊትም ቢሆን ወንጭፍ ሲጠቀም እንደ እነሱ ዒላማውን አይስትም ነበር።​—መሳፍንት 20:14-16፤ 1 ሳሙኤል 17:49

ጊዜውን በአግባቡ ተጠቅሞበታል

እረኝነት በአብዛኛው አንድ ሰው ብዙ እንቅስቃሴ ማድረግ ሳያስፈልገው ብቻውን ሊያከናውነው የሚችል ሥራ ነው።  ዳዊት ግን ይህ ሁኔታ አሰልቺ አልሆነበትም። እንዲያውም ፀጥታ የሰፈነበት ሰላማዊ ሁኔታ ለማሰላሰል የሚችልበት ብዙ አጋጣሚ ፈጥሮለታል። በመዝሙሮቹ ውስጥ የሚገኙት አንዳንዶቹ ሐሳቦች ዳዊት በልጅነቱ ዘመን ያጋጠሙት ነገሮች ሳይሆኑ አይቀሩም። እንደ ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ባሉት በሰማያት የሚገኙ ድንቅ የሆኑ የይሖዋ ‘ጣት ሥራዎች’ ላይ በማሰላሰል የሰው ልጅ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ስላለው ቦታ ያስብ የነበረው ብቻውን በሚሆንበት ጊዜ ይሆን? ፍሬያማ ስለሆነው መሬት፣ ስለ ከብቶችና በሬዎች፣ ስለ ወፎች እንዲሁም ‘ስለ ዱር አራዊት’ ያወጣ ያወርድ የነበረው በቤተልሔም አካባቢ ባሉ መስኮች ላይ ይሆን?​—መዝሙር 8:3-9፤ 19:1-6

ዳዊት እረኛ ሆኖ ያሳለፈው ሕይወት፣ ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ የሚያሳየውን ጥልቅ አሳቢነት በሚገባ ለመረዳት አጋጣሚ እንደከፈተለት ምንም ጥርጥር የለውም። በመሆኑም ዳዊት እንዲህ ሲል ዘምሯል፦ “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፤ አንዳች አይጐድልብኝም። በለመለመ መስክ ያሳርፈኛል፤ በዕረፍት ውሃ ዘንድ ይመራኛል፤ በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ፤ ብሄድ እንኳ፣ አንተ ከእኔ ጋር ስለ ሆንህ፣ ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኵዝህ፣ እነርሱ ያጽናኑኛል።”​—መዝሙር 23:1, 2, 4

‘ታዲያ ይህ ሁሉ ነገር ከእኔ ጋር ምን ግንኙነት አለው?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። ዳዊት ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ሊመሠርትና ለአምላክ ‘እንደ ልቡ የሚሆንለት ሰው’ ሊባል የቻለበት አንዱ ምክንያት በይሖዋ የእጅ ሥራዎችና ከአምላክ ጋር ባለው ዝምድና ላይ በጥልቀት እንዲሁም በቁም ነገር ያሰላስል ስለነበር ነው። ስለ አንተስ ተመሳሳይ ነገር ማለት ይቻላል?

አምላክ በፈጠረው ነገር ላይ በጥልቅ ካሰብክ በኋላ ፈጣሪህን ለማወደስ ወይም ከፍ ከፍ ለማድረግ ተነሳስተህ ታውቃለህ? ይሖዋ ከሰው ልጆች ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ የሚያንጸባርቃቸውን ባሕርያቱን ተመልክተህ ለእሱ ባለህ ፍቅር ልብህ ተሞልቶ ያውቃል? እርግጥ ነው፣ ለይሖዋ እንደዚህ ዓይነት የአድናቆት ስሜት እንዲያድርብህ ከፈለግክ በአምላክ ቃልና በፍጥረት ሥራው ላይ ጸጥታ በሰፈነበት ሁኔታ በጸሎት ለማሰላሰል ጊዜ መመደብ ይኖርብሃል። በዚህ መልኩ ማሰላሰልህ ይሖዋን በሚገባ እንድታውቀው ያስችልሃል፤ ይህ ደግሞ እሱን እንድትወደው ያደርግሃል። ወጣት አረጋዊ ሳይል ሁሉም ሰው ይህን መብት ማግኘት ይችላል። ዳዊት ከልጅነቱ ጀምሮ ወደ ይሖዋ ቀርቦ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው። ይህን እንዴት ማወቅ እንችላለን?

ዳዊት ተቀባ

ንጉሥ ሳኦል የአምላክን ሕዝብ ለመምራት ብቁ ሳይሆን በቀረበት ጊዜ ይሖዋ ነቢዩ ሳሙኤልን እንዲህ ብሎታል፦ “በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው? ወደ ቤተ ልሔሙ ሰው ወደ እሴይ ስለምልክህ፣ ዘይት በቀንድ ሞልተህ ሂድ፤ ከልጆቹ አንዱ ንጉሥ ይሆን ዘንድ መርጬዋለሁ።”​—1 ሳሙኤል 16:1

የአምላክ ነቢይ ቤተልሔም በደረሰ ጊዜ እሴይ ወንዶች ልጆቹን እንዲጠራቸው አዘዘው። ሳሙኤል ንጉሥ እንዲሆን የሚቀባው የትኛውን ልጅ ይሆን? የሁሉም ታላቅና መልከ መልካም የነበረውን ኤልያብን ባየ ጊዜ ሳሙኤል ‘ይሄ መቼም እሱ መሆን አለበት’ ብሎ አሰበ። ይሖዋ ግን “መልኩን ወይም ቁመቱን አትይ፤ እኔ ንቄዋለሁና። እግዚአብሔር የሚያየው፣ ሰው እንደሚያየው  አይደለም። ሰው የውጭውን ገጽታ ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” አለው። በተመሳሳይም ይሖዋ አሚናዳብን፣ ሣማን እንዲሁም ሌሎች አራት ወንድሞቻቸውን አልመረጠም። ዘገባው በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ “[ሳሙኤል] እሴይን፣ ‘ልጆችህ እነዚሁ ብቻ ናቸውን?’ ሲል ጠየቀው። እሴይም፣ ‘የሁሉም ታናሽ ገና አልመጣም፤ ነገር ግን በጎች እየጠበቀ ነው’ ብሎ መለሰ።”​—1 ሳሙኤል 16:7, 11

የእሴይ መልስ ‘መቼም የምትመርጠው ዳዊትን እንደማይሆን እርግጠኛ ነኝ’ የሚል አንድምታ ያለው ይመስላል። ዳዊት በቤተሰቡ ውስጥ ትንሹና እምብዛም ትኩረት የማይሰጠው ልጅ እንደመሆኑ መጠን በጎች የመጠበቅ ሥራ ተሰጥቶታል። ሆኖም አምላክ የመረጠው እሱን ነበር። ይሖዋ ልብን ይመለከታል፤ ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው በዳዊት ውስጥ በጣም ልዩ የሆነ ባሕርይ ተመልክቷል። እሴይ ሰው ልኮ ዳዊትን ካስጠራው በኋላ ይሖዋ ሳሙኤልን “‘የመረጥሁት ይህ ነውና ተነሥተህ ቅባው’ አለው። ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ ፊት ቀባው። ከዚያ ቀን ጀምሮ የእግዚአብሔር መንፈስ በዳዊት ላይ በኀይል መጣ።”​—1 ሳሙኤል 16:12, 13

በዚህ ወቅት ዳዊት ዕድሜው ስንት እንደነበር አልተገለጸም። ይሁንና ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሦስቱ ትላልቅ ወንድሞቹ ማለትም ኤልያብ፣ አሚናዳብና ሣማ በሳኦል ሠራዊት ውስጥ ያገለግሉ ነበር። ምናልባትም የቀሩት አምስት ልጆች ከእነሱ ጋር የሠራዊቱ ክፍል ለመሆን ዕድሜያቸው አልደረሰ ይሆናል። አንድ ሰው በእስራኤል ሠራዊት ውስጥ ገብቶ ለማገልገል 20 ዓመት ሊሆነው ስለሚገባ አምስቱ ልጆች እዚህ ዕድሜ ላይ አልደረሱ ይሆናል። (ዘኍልቍ 1:3፤ 1 ሳሙኤል 17:13) ያም ሆነ ይህ ዳዊት ይሖዋ በመረጠው ጊዜ በጣም ልጅ ነበር። በዚያ ዕድሜውም እንኳ መንፈሳዊ አመለካከት ነበረው። ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው ስለ አምላክ በሚያውቀው ነገር ላይ በማሰላሰል ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና ማዳበር ችሏል።

ዛሬ ያሉ ወጣቶችም ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ ማበረታቻ ሊሰጣቸው ይገባል። ታዲያ ወላጆች ልጆቻችሁ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንዲያሰላስሉ፣ የአምላክን የፍጥረት ሥራ እንዲያደንቁ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፈጣሪ የሚናገረውን ነገር እንዲያጠኑ እያበረታታችኋቸው ነው? (ዘዳግም 6:4-9) እናንተ ወጣቶችስ ይህን በራሳችሁ ተነሳሽነት እያደረጋችሁ ነው? እንደ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች * ያሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች እናንተን ለመርዳት የተዘጋጁ ናቸው።

በገና በመጫወት የተካነ

ዳዊት ባቀናበራቸው በርካታ መዝሙሮች ውስጥ ከተካተቱት የግጥም ስንኞች በተጨማሪ ሙዚቃውም እረኛ ስለነበረበት ጊዜ የሚጠቁመን ነገር አለ። እርግጥ ነው፣ እነዚህን ቅዱስ መዝሙሮች ከሚያጅቡ ሙዚቃዎች መካከል ዛሬ አንዱም አይታወቅም። ሆኖም የሙዚቃዎቹ አቀናባሪ የተዋጣለት ሙዚቀኛ እንደነበር እናውቃለን። እንዲያውም ዳዊት የእረኝነት ሥራውን አቁሞ ንጉሥ ሳኦልን እንዲያገለግል የተጠራው በገና የመጫወት ጥሩ ችሎታ ስለነበረው ነው።​—1 ሳሙኤል 16:18-23 *

ዳዊት የሙዚቃ ችሎታውን ያዳበረው መቼ እና የት ሆኖ ነበር? መስክ ላይ በጎችን እየጠበቀ በሚውልበት ጊዜ ሊሆን ይችላል። ዳዊት በልጅነቱም እንኳ ለአምላኩ ከልብ በመነጨ ስሜት ይዘምር እንደነበር ምንም አያጠራጥርም። ደግሞስ ይሖዋ የመረጠውና ኃላፊነት የሰጠው ለአምላክ ያደረ በመሆኑና በመንፈሳዊነቱ የተነሳ አይደለም?

ዳዊት ትልቅ ሰው ከሆነ በኋላ በሕይወቱ ውስጥ ያጋጠመው ነገር ራሱን የቻለ ሌላ ታሪክ ነው። ሆኖም በመላው ሕይወቱ ያሳየው መንፈስ ልጅ ሳለ በቤተልሔም በጎችን ሲጠብቅ ከብዙ ዓመታት በፊት ያጋጠሙትን ነገሮች ያስታውሰናል። እስቲ ዳዊት የሚከተለውን መዝሙር ለይሖዋ ሲዘምር በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ፦ “የቀድሞውን ዘመን አስታወስሁ፤ ሥራህንም ሁሉ አሰላሰልሁ፤ የእጅህንም ሥራ አውጠነጠንሁ።” (መዝሙር 143:5) በዚህና በሌሎቹ የዳዊት መዝሙሮች ላይ የሚንጸባረቀው የአድናቆት ስሜት የይሖዋን ልብ የማስደሰት ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች መንፈስ ያነሳሳል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.9 ቀድሞ በፓለስቲና ይገኝ የነበረው ቡናማ ቀለም ያለው የሶርያ ድብ፣ በአማካይ 140 ኪሎ ግራም የሚመዝን ሲሆን ትልቅ በሆነው መዳፉ በመምታት ብቻ አንድን ሰው ወይም እንስሳ መግደል ይችላል። በወቅቱ በዚህ አካባቢ በርካታ አንበሶች ይኖሩ ነበር። ኢሳይያስ 31:4 “ብዙ እረኞች” እንኳ አንድ “የአንበሳ ደቦል” የያዘውን እንስሳ ማስጣል እንደማይችሉ ይናገራል።

^ አን.20 በይሖዋ ምሥክሮች የሚዘጋጁ።

^ አን.22 ዳዊት እንዲጠራ ሐሳብ ያቀረበው የንጉሡ አማካሪ “በአነጋገሩ አስተዋይና የደስ ደስ ያለው ነው፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው” በማለት ስለ ዳዊት ተጨማሪ ሐሳብ ሰጥቷል።​—1 ሳሙኤል 16:18