በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክን ስም ማወቅ ምን ነገሮችን ይጨምራል?

የአምላክን ስም ማወቅ ምን ነገሮችን ይጨምራል?

ስምህ ትርጉም አለው? በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ለአንድ ሕፃን ትርጉም ያለው ስም ማውጣት የተለመደ ነው። የሚመረጠው ስም የወላጆቹን እምነት፣ ትልቅ ቦታ የሚሰጡትን ነገር ወይም ለልጃቸው የወደፊት ሕይወት ያላቸውን ተስፋና ሕልም የሚያንጸባርቅ ሊሆን ይችላል።

ያለው ስም ማውጣት አዲስ ነገር አይደለም። በጥንት ዘመን አብዛኛውን ጊዜ ለአንድ ሰው ስም የሚወጣለት ስሙ በሚያስተላልፈው ትርጉም መሠረት ነው። ለአንድ ሰው የሚወጣለት ስም በሕይወቱ እንዲያሳይ የሚጠበቅበትን ባሕርይ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ፣ ይሖዋ ለዳዊት ልጁ ሰሎሞን ስለሚኖረው የወደፊት ሚና በነገረው ጊዜ “ስሙም ሰሎሞን [“ሰላም” የሚል ትርጉም ካለው ቃል የመጣ ነው] ይባላል። በዘመኑም ለእስራኤል ሰላምንና ጸጥታን እሰጣለሁ” ብሎታል።—1 ዜና መዋዕል 22:9

አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ አዲስ የሥራ ድርሻ ወይም ሚና ለሚኖረው ሰው አዲስ ስም ያወጣ ነበር። መካን ለነበረችው የአብርሃም ሚስት “ልዕልት” የሚል ትርጉም ያለው ሣራ የሚል ስም ወጥቶላታል። ለምን? ይሖዋ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ እባርካታለሁ ከእርሷም ወንድ ልጅ እሰጥሃለሁ፤ የብዙም ሕዝቦች እናት ትሆን ዘንድ እባርካታለሁ፤ የሕዝቦችም ነገሥታት ከእርሷ ይወጣሉ።” (ዘፍጥረት 17:16) ሣራ ይህ አዲስ ስም ለምን እንደወጣላት ለመረዳት የተሰጣትን አዲስ ሚና ማወቅ አስፈላጊ እንደሚሆን ግልጽ ነው።

ከስሞች ሁሉ ስለሚበልጠው ይሖዋ ስለተባለው ስምስ ምን ማለት ይቻላል? ይሖዋ የሚለው ስም ትርጉም ምንድን ነው? ሙሴ አምላክን ስለ ስሙ በጠየቀው ጊዜ ይሖዋ “ያለሁና የምኖር ነኝ” ሲል መልሶለታል። (ዘፀአት 3:14) በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይሖዋ የሰጠውን መልስ በዚህ መንገድ ተርጉመውታል። ይሁን እንጂ የሮዘርሃም ትርጉም “መሆን የምሻውን ሁሉ እሆናለሁ” ሲል ተርጉሞታል። የይሖዋ ስም፣ እሱ በርካታ ተግባሮች የሚያከናውን አምላክ መሆኑን ይገልጻል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንዲት እናት ለልጆቿ በቀን ውስጥ አስታማሚ፣ የወጥ ቤት ሠራተኛ፣ አስተማሪ እንዲሁም ልጆቿ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ በመሆን ድርሻዋን መወጣት ሊያስፈልጋት ይችላል። ከይሖዋ ጋር በተያያዘም ደረጃው ከፍ ያለ ይሁን እንጂ ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅራዊ ዓላማ ከግቡ ለማድረስ ሲል መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ መሆን ይችላል። ስለዚህ አምላክን በስም ማወቅ እሱ የሚያከናውናቸውን በርካታ ተግባሮች መረዳትና ማድነቅ ይጠይቃል።

የሚያሳዝነው ግን የአምላክ ማንነትና ባሕርይ ስሙን ከማያውቁ ሰዎች ተሰውሯል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ይሖዋ ጥበበኛ መካሪ፣ ኃያል አዳኝ፣ ለጋስ ሰጪና የመሳሰሉትን በመሆን የሚጫወተውን ሚና መገንዘብ ትችላለህ። በእርግጥም የይሖዋ ስም ያለው ትርጉም በጣም አስገራሚ ነው።

ይሁን እንጂ አምላክን በስም ማወቅ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። የሚቀጥለው ርዕስ ምክንያቱን ያብራራልናል።