በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ መጀመሪያ አለው?

አምላክ መጀመሪያ አለው?

 አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

አምላክ መጀመሪያ አለው?

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ መጀመሪያ እንደሌለው ይናገራል። አምላክ ያልነበረበት ጊዜ የለም። የአምላክን ዘላለማዊነት መረዳት ከባድ እንደሆነ እሙን ቢሆንም ሐሳቡን ሙሉ በሙሉ መረዳት ስላልቻልን ብቻ ዘላለማዊነቱን ለመቀበል አሻፈረን ማለት የለብንም።

የአምላክን መንገዶች በሙሉ መረዳት እንዳለብን ማሰብ ምክንያታዊ ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “የአምላክ ብልጽግናና ጥበብ እንዲሁም እውቀት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱም ፈጽሞ የማይመረመር ነው! መንገዱም የማይደረስበት ነው!” (ሮም 11:33) አንድ ሕፃን ስለ ወላጁ ሁሉንም ነገር ማወቅ እንደማይችል ሁሉ እኛም የአምላክ ጥበብና እውቀት ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ መረዳት ከአቅማችን በላይ ነው። ጳውሎስ በመንፈስ ተመርቶ የጻፈው ይህ ሐሳብ በዋነኝነት የሚያጎላው የአምላክ ጥበብና ምሕረት ወደር የማይገኝለት መሆኑን ቢሆንም ይሖዋ አምላክንና እሱ ነገሮችን የሚያከናውንባቸውን መንገዶች በተመለከተ ልንረዳቸው የማንችላቸው ጥልቅ ነገሮች እንዳሉም ይጠቁማል። ከእነዚህም መካከል አምላክ መጀመሪያ የለውም የሚለው ትምህርት ይገኝበታል። ያም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን በተመለከተ በሚያስተምራቸው ነገሮች ላይ ሙሉ እምነት ልንጥል እንችላለን። ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን መጻሕፍትን በተመለከተ “ቃልህ እውነት ነው” ብሏል።—ዮሐንስ 17:17

ሙሴ “ለዘላለም አምላክ ነህ፤ ከእንግዲህ ወዲህም የዘላለም አምላክ ሆነህ ትኖራለህ” በማለት ወደ ይሖዋ ጸልዮ ነበር። (መዝሙር 90:2 የ1980 ትርጉም) እዚህ ላይ ሙሴ የአምላክን ሕልውና የገለጸው ማቆሚያ ከሌላቸው ሁለት ተቃራኒ አቅጣጫዎች አንጻር ነው። አንደኛው የወደፊቱን ጊዜ የሚያመለክት ነው። ይሖዋ “ከዘላለም እስከ ዘላለም [የሚኖር]” አምላክ ነው። (ራእይ 4:10) በመሆኑም የአምላክ ሕልውና ወደፊት ማብቂያ ለሌለው ጊዜ ይቀጥላል። ሌላኛው አቅጣጫ ደግሞ ያለፈውን ጊዜ የሚያመለክት ነው። በሌላ አባባል አምላክ አልተፈጠረም፤ አሊያም በዚህ ጊዜ ወደ ሕልውና መጣ ሊባል አይችልም። እንዲያውም ዝንተ ዓለም ወደኋላ ቢኬድ የአምላክ ሕልውና የጀመረበትን ጊዜ ማግኘት አይቻልም።

ረቂቅ ሐሳቦችን መረዳት ለብዙዎቻችን አዳጋች መሆኑ ግልጽ ነው። ያም ሆኖ አንዳንድ ጊዜ ለመገንዘብ አስቸጋሪ የሆኑ ጽንሰ ሐሳቦችን ለመቀበል እንገደዳለን። ለምሳሌ ከዜሮ በፊትና በኋላ ስላሉት ቁጥሮች የሚገልጸውን የሒሳብ ትምህርት እንመልከት። ከዜሮ ጀምረን ወደፊትም ሆነ ወደኋላ ብንቆጥር ምንም ማቆሚያ አይኖረንም። ታዲያ ይህን ምሳሌ ፈጣሪ የኖረበትን ዘመን ለማስረዳት ልንጠቀምበት አንችልም?

በመሆኑም ‘የዘላለም ንጉሥ’ የሚለው ልዩ ማዕረግ የተሰጠው ለአምላክ ብቻ መሆኑ ተገቢ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:17) እስቲ አስበው፦ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በሰማይ ላይ የሚኖሩት እልፍ አእላፍ መላእክት እንዲሁም በምድር ላይ የሚኖሩት የሰው ልጆች በሙሉ የተፈጠሩ በመሆናቸው መጀመሪያ አላቸው። (ቆላስይስ 1:15, 16) የአምላክ ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነው። አምላክ መጀመሪያ ሊኖረው ይገባል የሚል ግትር አቋም መያዝ ‘ፈጣሪን ማን ፈጠረው?’ የሚል ትርጉም የለሽና መቼም ቢሆን መቋጫ የማይኖረው ጥያቄ ያስነሳል። ነጥቡ ግን አንድ ነው፦ “ከዘላለም እስከ ዘላለም” ሕያው የሆነው ይሖዋ ብቻ ነው። (መዝሙር 90:2) በሌላ አባባል ይሖዋ “ከዘመናት ሁሉ በፊት” ሕያው ነበር።—ይሁዳ 25

ይሁን እንጂ ስለ አምላክ ዘላለማዊ ሕልውና የሚናገረው ትምህርት ለእኛ ምንም ትርጉም የሌለው ተራ እውነታ አለመሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል። የሙሴን ጸሎት መመርመራችን የአምላክ ዘላለማዊነት፣ በፍቅር ተነሳስቶ ለሰጠን የዘላለም ሕይወት ተስፋ አስተማማኝ ዋስትና እንደሆነ እንድንገነዘብ ያደርገናል። እንደ ጤዛ ዛሬ ታይቶ ነገ ከሚጠፋው ከአሁኑ ሕይወታችን በተቃራኒ አምላክ “ከትውልድ እስከ ትውልድ መጠጊያችን” እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል። ይሖዋ አፍቃሪ አባት በመሆኑ ባለፉት ዘመናትም ሆነ ዛሬ እንዲሁም ወደፊት ለሕዝቡ መጠጊያ ነው። ግሩም የሆነውን ይህን እውነት በማወቅህ እንደምትደሰት ተስፋ እናደርጋለን!—መዝሙር 90:1